መፃጉዕ

                                           
                                                                                                                                                                                                                  በእመቤት ፈለገ
ልጆች በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም አረተኛ እሑድ መጻጉዕ
 ይባላል፡፡ ታሪኩም እንደዚህ ነው፡፡ በኢየሩሳሌም በር አጠገብ ቤተሳይዳ የምትባል የመጠመቂያ ቦታ ነበረች በዚያም ማየት የተሳናቸው፣ መራመድ የማይችሉ ብዙ በሽተኞች በመጠመቂያው ቦታ ተኝተው የውሃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ÷ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ /ይድን/ ነበር፡፡ በዚያ ቦታም ከታመመ ሰላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ስሙም መጻጉዕ ይባላል፡፡ ልጆች መጻጉዕ እንዴት በሕመም እንደተሰቃየ አያችሁ?

ታዲያ ልጆች ጌታችን ኢየሱስ ያሰው በአልጋው ተኝቶ ባየ ጊዜ በበሽታ ብዙ ዘመን እንደቆየ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ መጻጉዕም “አዎን ጌታዬ ሆይ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑ ያሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፡፡ ልጆች ታሪኩን በደንብ አነበባችሁ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጻጉዕን ከበሽታው እንደፈወሰው አነበባችሁ አይደል? ጎበዞች! እኛም በታመምን ጊዜ እንደመጻዕጉም የሚረዳን ሰው ባጣን ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን ይረዳናል፡፡
ደህና ሰንብቱ!

የመፃጉዕ ወንጌል(ዮሐ. 5÷1-24)

ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡

አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡

አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡

የመፃጉዕ ምንባብ3(የሐዋ.3÷1-11)

ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፤ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም÷ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ÷ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ አጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭምቱ ጸና፡፡ ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እግዝአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፡፡ እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው፡፡

የመፃጉዕ ምንባብ2(ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.)

ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡

የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች፡፡ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም፡፡ ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር÷ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር÷ ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ÷ ብዙ ኀጢአቱንም እንደ አስትሰረየ ይወቅ፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

የመፃጉዕ ምንባብ1(ገላ. 5÷1-ፍጻሜ ምዕ.)

እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም አንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡ በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል፡፡ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ÷ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ አናደርጋለን፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡ ቀድሞስ በመልካም ተፋጠናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ÷ እኔ ግዝረትን ገና የምስብክ ከሆነ÷ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል፡፡ የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል፡፡

ወንድሞቼ ሆይ÷ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ፡፡ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡ እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትንካከሱ ከሆነ ግን÷ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ፡፡

እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ፡፡ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና÷ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ÷ ከኦሪት ወጥታችኋል፡፡ የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት÷ ርኲሰት÷ መዳራት÷ ጣዖት ማምለክ÷ ሥራይ ማድረግ÷ መጣላት÷ ኲራት÷ የምንዝር ጌጥ÷ ቅናት÷ቊጣ÷ ጥርጥር÷ ፉክክር ÷ምቀኝነት መጋደል÷ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡

አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር÷ ደስታ ÷ሰላም÷ ትዕግሥት÷ ምጽዋት÷ ቸርነት÷ እምነት÷ ገርነት÷ ንጽሕና ነው፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና፡፡

ዐሥራ አምስተኛው ዙር ሐዋርያዊ የጉዞ መርሐ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡

በደረጀ ትዕዛዙ
ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ትክክለኛ አስተ ምህሮ ለምእመናን ለማዳረስ ከሚጠቀምባቸው መርሐ ግብሮች አንዱ የሆነውና በደቡብ ኢትዮ ጵያ ቦረና ጉጂ ሊበን ዞኖች ሃገረ ስብከት የተካሔደው  የአሥራ አምስተኛው ዙር ሐዋርያዊ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡ እንዲህ ያለ መርሐ ግብር በተከታታይ ሊካሔድ እንደሚገባ የአካባቢው ምእመናን ቿይቀዋል፡፡
በማኅበሩ ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ከየካቲት 11- 20 2003 ዓ.ም ድረስ የተካሔደው ይኸው መርሐ ግብር ቦረና ጉጂ ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት የሚገኙ አምስት ከተሞችን የሸፈነ መሆኑን የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ዲ/ን ምትኩ አበራ ተናግረዋል፡፡

አራት መምህራንና አሥራ ሰባት ዘማሪያንን እንዲሁም ሌሎች አባላትን ያካተተው ይኸው የልኡካን ቡድን ይዞት ከተነሣው ተልእኮ አንጻር የተሻለ አገልግሎት ሰጥቶ መመለሱን የገለጡት አስተባባሪው በዚህም ምእመናኑ እጅግ ተደስተዋል ብለዋል፡፡

በሐዋርያዊ ጉዞው ትክክለኛውን የቤተክ ርስቲያን ትምህርት እና ዝማሬ ወደ ምእመናኑ ማድረስ ዋና ዓላማው አድርጎ የተንቀሳቀሰው ይኸው የልኡካን ቡድን፤ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ክብረ መንግሥት፣ ሻኪሶ፣ ዋደራ፣ ቦሬ እና ነገሌ ቦረና ከተሞች በሚገኙ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በምእምናን ጥያቄ መሠረት ከዕቅድ በላይ በሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንም አገልግሎቱን ሰጥቷል ብለዋል፡፡ በዚህም የሐዋርያዊ ጉዞው ቡድን ከሕዝቡ ተቀባይነትን፣ ከበሬታንና ፍቅርን አግኝቶ መመለሱን አስረድተዋል፡፡

ትምህርተ ወንጌሉ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች መሰጠቱ ምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን በአግባቡ እንዲረዱ ያስቻለ ከመሆኑም በተጨማሪ የልኡካን ቡድኑ አባላት የሆኑ ካህናት በቅዳሴ እና በዓመታዊ ክብረ በዓል ወቅት የቤተ መቅደስ አገልግሎት መስጠታቸው አገልግሎቱን ይበልጥ የተሳካ እንዲሆን አግዟል ብለዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ ከቤተክርስቲያኒቱ የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ፈቃድ ይዞ በሕጋዊነት ተንቀሳቅሷል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ከተሞች በዓላማቸው የተሐድሶ እንቅ ስቃሴውን ለማራመድ በሚጥሩ ግለሰቦች መርሐ ግብሩን የማደናቀፍ አዝማሚያ አጋጥሞት አንደነበር ዲያቆን ምትኩ አበራ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በቤተክርስቲያኒቷ ሥርዓትና መመሪያ መሠረት የሚካሔድ ሕጋዊ አገልግሎት ስለሆነ የፈቃድ ወረቀቱን ለሕጋዊ አካላት በማሳየት እና ከየደብሩ ሓላፊዎች እና ከምእመናኑ ጋር በመነጋገር መርሐ ግብሩ ሳይስተጓጎል ከተጠበቀው በላይ የተሳካ ሆኖ መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በተካሔደባቸው አካባቢዎች ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና መመሪያ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሰባክያንና ዘማሪያን ስፍራውን ደጋግመው በመጎብኘታቸው ትክክለኛውን የቤተክር ስቲያኒቱን አስተምህሮ ሳያገኙ መቆየታቸውን የአካባቢው ምእመናን ለልኡካን ቡድኑ አባላት ሲገልጡ እንደነበር የተናገሩት ዲ/ን ምትኩ፤ መርሐ ግብሩ በተከታታይ ሊካሔድ እንደሚገባ መጠየቃቸውንም አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ በእነዚህ አካባቢዎች መዋቅሩን በማጠናከር የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና መመሪያ አክብረው ከሚንቀሳቀሱ መምህራነ ወንጌል እና ዘማሪያን ጋር በመተባበር ደጋግሞ ወደ ስፍራው ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህ አካባቢ ትኩረት ሰጥቶ በተከታታይ የተጠናከረ አገልግሎት መስጠትና ትምህርተ ወንጌል የተጠማውን ሕዝብ በማስተማር የቅድስት ቤተክርስቲያንን ተልዕኮዋን ይበልጥ ውጤታማ ለማደረግ መነሣሣት እንደሚያስፈልግ ዲ/ን ምትኩ ተናግረዋል፡፡

 
 /ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ከመጋቢት 1-15 ቀን 2003 ዓ.ም/
kidusuraeal.jpg

የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወጣቶች መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ዓመታዊ በዓሉን አከበረ፡፡

በኅሩይ ባየ
በአዲስ አበባ ሃገረ ሰkidusuraeal.jpgብከት በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አጥቢያ ዐሥራኹለት ቀበሌዎች የሚኖሩ ወጣት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የካቲት 20 ቀን 2003 ዓ. ም በደብረ ፅጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የሰንበቴ አዳራሽ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበራቸው የተመሠረተበትን አንደኛ ዓመት አከበሩ፡፡ 
ቁጥራቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሆኑት እነዚህ ወጣቶች በአንድ ዓመት ቆይታቸው በየወሩ በተለያዩ አዳራሾች እየተሰበሰቡ ኦርቶዶክሳዊ የሃይ ማኖት ትምህርት ሲማሩ መቆየታቸውን የማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ተስፋዬ አዳነ ገልጧል፡፡
 
«የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በጠበቀና በተደራጀ መልኩ፤ ትምህርተ ሃይማኖትን ለመማርና በመልካም ሥነ ምግባር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል መዋቅርና አሠራሯን ጠብቆ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ መሰባሰብ የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመ ንበታል፡፡ ስለዚሀ በአጥቢያችን በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስ ቲያን እየተገኘን መሰብሰብ ጀምረናል፡፡» ሲል የገለጠው ወጣት ተስፋዬ አዳነ፤ ወጣቶቹ በየሳምንቱ በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ ስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን እንደሚከታተሉና በወር አንድ ጊዜ ደግሞ በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ጉባኤያቸውን በማካሔድ የመዝሙር ጥናት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሚማሩ ተናግሯል፡፡

ማኅበሩ በ2002 ዓ. ም ተመሥርቶ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በርካታ መንፈሳዊ ተግባ ራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ በእስር ቤት ያሉ ወገኖቻችን በዓል ጥምቀትን አስበው እንዲውሉ የምሣ ግብዣ ማዘጋጀት፤ የቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ በዓላት ኦርቶዶክሳዊ ትውፊቶችን ሳይለቁ እንዲከበሩ የግንዛቤ ማስጨ በጪያ ትምህርት ማካሔድ፤ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መሠረት ታቦተ ሕጉን አጅበው የንግሥ በዓላትን እንዲያከብሩና የሚጠበቅባቸውን አገል ግሎት እንዲያበረክቱ በማድረግ ካከናወኗቸው ተግባራት ጥቂቶች እንደሆኑ በዕለቱ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ማኅበሩ በቀጣዩ የሥራ ጊዜ ካቀዳቸው ተግባራት ዋናዋናዎቹ፤ በቤተ ክርስቲያናችን የተቀጣጠለውን ውጫ ዊና ውስጣዊ ፈተና ለመቋቋም ዋናው መሣሪያ ጸሎት ስለሆነ በሳምንት አንድ ቀን የማኅበር ጸሎት ማድረስ፤ በተጀመረው የዐቢይ ጾም ወራት እያንዳንዱ የማኅበሩ አባል ቁርሱን ለነዳያን እንዲሰጥ ማድረግ፤ በምግብና በልብስ እጦት ምክንያት ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ወደ ሌላ የእምነት ተቋም እንዳይፈልሱ አሳዳጊ አልባ የሆኑ ሕፃናትን እና ጧሪ ያጡ አረጋውያንን በግልና በቡድን መርዳት፤ በትምህርተ ሃይማኖት እውቀት ማነስ ምክንያት ወጣቶች በነጣቂ ተኩላ እንዳይወሰዱ ከአጥቢያቸው የሰበካ ጉባኤ እና ከሰንበት ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዐት፣ ታሪክና ትውፊት ትምህርቶች እንዲከታተሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ደጋግ አባቶችን በዓለ ልደታቸውን እና ዕረፍታቸውን ማክበር በሁለት ወር አንድ ጊዜ የሚታተም መንፈሳዊ መጽሔት ማዘጋጀት ዋና ዕቅዳቸው መሆኑን ወጣት ተስፋየ አዳነ ገልጧል፡፡

 
/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ከመጋቢት 1-15 ቀን 2003 ዓ.ም/

በጎቹና ፍየሎቹ

የ”እናስተውል” 1ኛና መለሰተኛ 2ኛ ደረጃ የሕዝብ ትምህርት ቤት ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የአማርኛ ትምህርት ፈተና
በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
 

ለፈተናው የተሰጠ ሰዓት ፡- 0፡05    
የተማሪው ሙሉ ስም:_________________ ቁጥር:______                            

   

የሚከተለውን ምንባብ በጥንቃቄ አንብቡ
በጎቹና ፍየሎቹ
 
ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንድ ሀገር ትልቅ የበጎች በረት ነበረ፡፡ በዚህ የበጎች በረት ውስጥ ብዙ በጎች ይኖሩ ነበር፡፡ ይህ የበጎች በረት ለረዥም ዓመት የቆየ እና ብዙ ታሪክ ያለው በረት ሲሆን በጎቹ ሁሉ ግን የሚኖሩበትን በረት ጥንታዊነት እና ታሪክ በሚገባ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ በቅርብ ጊዜ ከሚወለዱት በጎች መካከል ለመስማት ፈቃደኞች ያልሆኑ አሉ እንጂ በረቱን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቆ ለማቆየት ብዙ በጎች ከሚያገሳ አንበሳ ጋር ጭምር ተታግለው ብዙ ድል አድርገዋል፡፡ ብዙ በጎችም ለዚሁ በረት መቆየት ሲሉ አንገታቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ ከአሁኑ በጎች ውስጥ ግን አንዳንዶቹ እንኳን ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው ሊሰጡ የቀድሞዎቹ በጎች የፈጸሙትን ገድል እንኳን ለማመን ይከብዳቸዋል ፤ ለመስማትም ይሰለቻሉ፡፡
   
በዚህ በረት ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አንድ ችግር ተፈጥሯል፡፡ የችግሩ መነሻ አንዳንድ ፍየሎች በጎች መስለው ከመንጋው መቀላቀላቸው ነው፡፡ እነዚህ ፍየሎች ምንም እንኳን ሥራቸው ፣ ድምፃቸው ፣ አኗኗራቸው ሁሉ ፍየል መሆናቸውን የሚመሰክር ቢሆንም ከበጎቹ በረት ረዥም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው ብዙ በጎችን ግራ ያጋባ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አስተዋይና የበግን ጠባይ ከፍየል ለይተው የሚያውቁ በጎች ‹‹ኸረ እነዚህ ፍየሎች ናቸው ፣ ድምፃቸው ፣ አነጋገራቸውና አኗኗራቸው ያስታውቃል!›› እያሉ ሲሟገቱ ከጥቂቶች በቀር የሚሰማቸው አላገኙም፡፡
 
አንዳንዶቹ በጎች ‹‹ምን ችግር አለው ፤ አነጋገራቸው እንደ በግ ባይሆንስ? እስከ መቼ እንደ በግ ብቻ እንናገራለን!›› እያሉ ከመቃወማቸውም በላይ በግ የመሰሉትን ፍየሎች ለመምሰል እነርሱም የፍየሎችን አኗኗር ለመኮረጅ ሞከሩ፡፡ የሚያሳዝነው ግን እውነተኛዎቹ በጎች በግ በመሆናቸው ፍየሎቹን ለመምሰል ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም፡፡ ሌሎቹ የዋሃን በጎች ደግሞ ምን ችግር አለው? ‹‹የምንመገበው አንድ ዓይነት ምግብ እስከሆነ ድረስ አንድ እኮ ነን!›› ብለው መከራከር ጀመሩ፡፡ ‹‹ኸረ ከመቼ ወዲህ ነው ፍየሎች አንድ የሆንነው?›› ብለው የተቃወሙ በጎች ደግሞ በእነዚህ በፍየሎች በተታለሉ በጎች ጥርስ ውስጥ ገቡ ‹‹አክራሪ ፣ ጽንፈኛና ወግ አጥባቂ በጎች››  የሚል ስያሜም ወጣላቸው፡፡
 
ይህንን ትርምስ አስቀድሞም ይፈልጉት የነበሩት በግ መሳይ ፍየሎችም ጉዳዩን ማራገብ ጀመሩ፡፡ ‹‹እኛ ለበረታችን ያልሆነው ነገር የለም ፤ እኛ ታማኝ በጎች ነን ፤ ይህቺ በረት ድሮ እንዲህ እንዲህ ነበረች›› ብለው የበረቲቱ መብት ተቆርቋሪዎች ሆኑ፡፡ ይባስ ብለው ድሮ በረቷ የፍየሎች መንጋ እንደነበረች ፣ የምትተዳደረውም በፍየሎች ሕግ እንደነበረ ፤ ከጥቂት ምዕተ ዓመታት ወዲህ በተነሡ በጎች በረቲቱ እንደተበላሸች መወትወት ጀመሩ፡፡ ምንም የማያውቁት በጎች ደነገጡ፡፡ ‹‹ወይኔ በረታችን! ለካ በችግር ላይ ነሽ?›› ብለው በረቲቱን የፍየል በረት ለማድረግ ቆርጠው ተነሡ፡፡ ስለበግነት የሚያነሣን በግ ባገኙት መንገድ ማንቋሸሽም ጀመሩ፡፡
በዚህ መካከል ሌላ ክስተት ተፈጠረ ፤ አንዳንድ ከበጎች ጋር ተቀላቅለው የነበሩ ፍየሎች በይፋ በረቱን ለቅቀው እንደወጡ ተሰማ፡፡ ከወጡ በኋላ ‹‹እውነቱን ተረድተን በግ ከመሆን ፍየል መሆን ይሻላል ብለን ተፀፅተናል ፤ ይህንን እውነት ካወቅን ትንሽ ቆይተናል›› ብለው በአደባባይ ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡ ሁሉን አይተነዋል ፤ ከእኛ ወዲያ በግነት ለኀሣር አሉ፡፡ በረቱ ውስጥም እያሉ ወሳኝ በጎች እንደነበሩና የበረቱን ጓዳ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሊቃውንት እንደሆኑም በዘዴ ጠቆሙ፡፡ አንዳንዶቹም ‹‹የበረቱ ጓዳ›› የሚል መጽሐፍ አዘጋጅተው በተኑ፡፡ ተረባርበው የገዙት በጎቹ ሲሆኑ መልስ ከመስጠት ይልቅ ብዙዎቹ በጎች ተሸማቅቀው ‹‹ጉድ ፣ ጉድ ለካ ይሄ ሁሉ ጉድ አለ?›› ብለው ተንሾካሾኩ፡፡
በዚህ ጊዜ በጎች አሁንም ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አስቀድመው ሲቃወሙአቸው የነበሩት በጎች ብዙም ሳይደነቁ ‹‹ከመጀመሪያውስ መች በጎች ነበሩና ነው ፍየል ሆንን የሚሉት ፤ በጎች አለመሆናቸው ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ዘንድ ወጡ ፤ በጎች ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ዘንድ ጸንተው በኖሩ ነበር፡፡›› ብለው አስረዱ፡፡ አንዳንድ የዋሃን በጎች ግን ‹‹በግ እገሌ ፍየል ከሆነማ ምን ተረፈን? እንደርሱ ያለ በግ ከየት ይገኛል? ፍየሎችን ያሳፈራቸው እርሱ አልነበረም እንዴ! አይ ይህቺ በረት ምን ቀራት ከእንግዲህ…›› እያሉ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ ‹‹ከእንግዲህ ትልቅ ነው ብዬ በግ አልከተልም!›› የሚሉም አልጠፉም ይህን ሲሰሙ አስተዋዮቹ በጎች ‹‹አስቀድሞስ በግ በእረኛ እንጂ በግ በበግ ሲመራ የት አይታችኋል ፤ በሉ ይኼ ትምህርት ይሁናችሁ›› አሏቸው፡፡ከዚህ በተጨማሪ “በግ መስለው የሚኖሩ ፍየሎች አሉ” የሚለው የበጎች አቤቱታ አዝማሚያው ያሰጋቸው አንዳንድ በግ መሰል ፍየሎች የበጎችን ልቅሶ ቀምተው ‘ኧረ ፍየሎች በዙ!’ እያሉ ማስመሰል ጀመሩ።
 
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ ትክክለኛው የበጎች በረት የት እንደሆነ ባለማወቅ በጎች ሆነው ሳለ ከፍየሎች መንጋ ጋር የሚንከራተቱ በጎች ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው በረት እንዳይመጡ በበጎቹ በረት አካባቢ የሚታየው ትርምስ የበጎች በረት መሆኑን ስለሸፈነባቸው ተቸገሩ ፣ የብዙዎቹ በጎች ሕይወት ደግሞ የበግ ስለማይመስል የበረቱን በጎ ምስል እንዳይታይ አድርጎታል፡፡ ከፍየል ሌላ የጅብ ፣ የዕባብ ፣ የውሻ ወዘተ ጠባይ የሚያሳዩ በጎች ቁጥር መብዛቱም እነዚህሰ የጠፉ በጎች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆነባቸው፡፡ እረኛው ደግሞ ‹‹ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች ብዙ በጎች አሉኝ›› ብሏል፡፡ ከዚህ በረት ውስጥ ያሉ ፍየሎች እንዳሉ ሁሉ ከበረቱ ውጪ ያሉ በጎችም ብዙዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ የጠፉ በጎች በፍየሎች መካከል ቢሆኑም የበጎች በረት ነገር ሲነሣ ግን በቀላሉ የሚነኩ ፣ልባቸው በቶሎ የሚሰበር ፣ ዕንባ የሚቀድማቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ በጎች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆነ፡፡ ‹‹ኸረ ብዙ በጎች እየወጡ ነው!›› እያሉ የሚጮኹም አልታጡም፡፡ አንዳንድ በጎች ደግሞ ለበረቱ የተቆረቆሩ መስሎአቸው ‹‹ይውጡ ፤ ኖረውም አይጠቅሙም! ይላሉ›› እረኛው ግን በጎቹን በበረቱ ለመሰብሰብ ብዙ እንደተሰቃየ ታላላቅ በጎች ታሪክ ጠቅሰው ይናገራሉ፡፡
 
በዚህ ሁሉ መካከል በረቱ እየፈረሰ ነው፡፡ በጎችም እየኮበለሉ ነው፡፡ ፍየሎችም ሌት ተቀን በረቱን የፍየል መንጋ መስፈሪያ ለማድረግ እየተጉ ነው፡፡ ተስፋ የሚጣልባቸው በጎችም ግማሾቹ ወጣ ብለው ሣር ሲግጡ ውኃ ሲጠጡ ፣ ግማሾቹም በዋዛ በተራ እሰጥ አገባ ተጠምደው ፣ ግማሾቹ በፍየሎች ላለመጠመድ ሲሉ የበረቱን ነገር ወደ ጎን ተዉት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንኳን በረቱን ገብተው ሊታደጉ ሌሎች ትንሽ ሲፍጨረጨሩ ሲያዩ ‹‹አዬ የዚህ በረት ነገር በቀላሉ የሚፈታ እንዳይመስላችሁ… ለማንኛውም መፍጨርጨር ጥሩ ነው!›› ‹‹ይኼን ሠራን ብላችሁ ነው? ወይ አለመብሰል!›› ይሏቸው ጀመር፡፡ ነገር ግን በጎቹ ምንም ባያውቁ በበረቱ ማደጋቸው በራሱ ከመብሰል አልፎ ካልተጠቀሙበት ለማረርም የሚበቃ ጊዜ ነበር፡፡ ይሁንና የጥቂቶቹ በጎች ጥረት ውጤቱ ቶሎ እንዳይታይ ደግሞ ምንም እንኳን ፍየሎች ባይሆኑም እንደ በግ ግን መኖር ያቃታቸው ደካሞች በመሆናቸው አቅም አጠራቸው፡፡ በጎችም ሆነው ፍየሎችን እንዴት እናጥቃ በሚለው ጉዳይ መስማማት አቅቷቸው ሥራውን ሳይጀምሩ የጨረሱ ታካቾችም አሉ፡፡ አንዳንድ በጎች መፍትሔ ለማግኘት “ወደ አንበሳ ሔደን አቤት እንበል” ይላሉ። ሌሎች ብጎች ደግሞ ‘አንበሳ ብዙ አንበሳዊ ጉዳዮች አሉበት ደግሞም አንበሳ የሚፈርደው በጎችንና ፍየሎችን በእኩል ዓይን ተመልክቶ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
 
የበረቱ ችግር እየከፋ ፣ የፍየሎቹ አካሔድም እየተስፋፋ ቢመጣም አሁንም ግን ዝምታው ሰፍኗል፡፡ ስለ ፍየሎች ጉዳይ እንዲነሣባቸው የማይፈልጉ በጎችም ተፈጥረዋል፡፡ ‹‹ኸረ ፍየሎች እንዲህ እያደረጉ ነው›› የሚል በግ ሲገኝም ‹‹መዓት አታውራ!›› ተብሎ ይገሠፅ ጀመር፡፡ በዕድሜ የገፉ በጎች ደግሞ ‹‹ይህንን ሳላይ በሞትኩ!›› ብለው ያዝኑ ጀመር፡፡ በእርግጥም በዕድሜ የገፉት በጎች ከመቼውም በላይ የተናቁት አሁን ነው፡፡
 
ፍየሎችን ‹ፍየሎች ናቸው› ብሎ መጥራትም በበጎች ዘንድ ጥላቻን የሚያተርፍ ሆነ፡፡ አንዳንድ በጎች ደግሞ መፍትሔ ያመጡ መስሎአቸው ቢንቀሳቀሱም ፍየልን ፍየል ከማለት ውጪ የበግነትንና የፍየልነትን ልዩነት በሚገባ ማስረዳት ተሳናቸው፡፡ በረቱ የፍየል እንጂ የበግ አልመስል አለ፡፡ አንዳንድ በጎች ጆሮአቸውን ማመን እስኪያቅታቸው የፍየሎች ድምፅ ከበረቱ መሰማቱ እየተለመደ እየተለመደ መጣ፡፡ የሚያስፈራው አዲስ የሚወለዱ ግልገሎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሰሙ የሚያድጉት የፍየሎችን ድምፅ በመሆኑ ስለ በግነት እና የበግ ድምፅ ምንም ሳያውቁ የሚያድጉ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳንድ በበረቱ ያደጉ በጎች ጭንቀቱን አልቻሉትም፡፡ ‹‹ጆሮዬ ነው ወይስ … እውነት የበረታችን አኗኗር እንደዚህ ነበረ ፤ እውነት ይህቺ በረት ከፍየሎች ጋር አንድ ነበረች? የተሳሳትኩት እኔ ነኝ ወይስ ሌላው?››የሚሉም ነበሩ፡፡ ለማን አቤት እንደሚሉ ጨነቃቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለእረኛው አመለከቱ፡፡ በጎ ስላደረጉ በጎች መነገሩ ነውር ሆነ፡፡ ፍየሎቹ ስለ እረኛው ብቻ ነው መነገር ያለበት ባዮች ሆኑ፡፡ ስለ እረኛም ግን ስሙን እየጠሩ ከመፎከር በቀር ፍሬ ያለው ነገር አይወጣቸውም፡፡ በዚህ ከቀጠለ ቀስ በቀስ በግ የመሆንና ፍየል የመሆን ልዩነት ጠፍቶ በረቱ መፍረሱ እንደማይቀር አንዳንድ በጎች ይናገራሉ፡፡ 
 

በምንባቡ መሠረት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሱ

1.    ለበረቱ መበጥበጥ ምክንያት የሆኑት እነማን ነበሩ?
2.    በግ መስለው የተቀላቀሉት ፍየሎች በምን ይታወቃሉ? (መለያ ጠባያቸው)
3.    አንዳንድ የዋሃን በጎች የተሳሳቱት በምን በምን ነበር?
4.    በግ ነበርን ብለው የወጡት ፍየሎች መውጣት የማያስደንቀው ለምንድን ነው?
5.    ጥሩ ጥሩ በጎች ለምን የበረቱን ችግር ለመፍታት አልቻሉም?
6.    ፍየሎችን ‹ፍየሎች› ብሎ መጥራት ለምን ነውር ሆነ?
7.    ለበረቱ መልካም ነገርን የሚመኙ በጎች ለምን ተባብረው መሥራት አልቻሉም?
8.    ከበረቱ ውጪ ያሉት በጎች ለምን ወደ በረቱ ለመመለስ አልቻሉም?
9.    በጎች መመራት ያለባቸው በሌላ በጎች ነው ወይስ በእረኛ?
10.     የበረቱን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት (ከጓደኞቻችሁ ጋር ተወያዩበት)

ማሳሰቢያ ፡- ተማሪዎች ይህን ፈተና ከተፈተናችሁ በኋላ የበጎቹንና የፍየሎቹን ገጸባሕርያት እያነሣችሁ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ስም እየሰጣችሁ እርስ በእርስ እንድትነቃቀፉ አልተፈቀደላችሁም! የጎበዝ ተማሪ መለያ በረቱ ሰላም የሚሆንበትን መፍትሔ መጠቆም ነው፡፡
                                             መልካም ፈተና
ምንጭ፡ሐመር የካቲት 2003 ዓ.ም. 

ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (ለህጻናት)

በአዜብ ገብሩ

 

በአንድ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በቤተ መቅደስ ውስጥም በሬዎችና በጎችን፣ ርግቦችንም ሲሸጡ አገኘ፡፡ በዚህን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አዘነ፡፡ የገመድ ጅራፍም አበጀ፡፡ በጎችንና በሬዎችን፣ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ ቤት አይደለችም” አላቸው፡፡

ልጆች ጌታ እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደስ የማይሠራ ሥራ ስለሠሩ እንዴት እንዳዘነ አያችሁ? ቤተ ክርስቲያንን ስናከብር ጌታችን በእኛ ደስ ይለዋል፤ የምንፈልገውንም ነገር ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ልጆች እኛም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ እግዚአብሔርን እንዳናሳዝነው ሥርዓትን መጠበቅ አለብን፡፡

1.ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ተሳልመን መግባት፣
2.የተቀደሰ ቦታ ስለሆነ ጫማችንን ማውለቅ፣
3.በጸጥታ ሆነን ሥርዓቱን መከታተል
4.መጸለይና እግዚብሔርን ማመስገን አለብን፡፡

 

ልጆች በቤተ ክርስቲያን ስትሆኑ ይህን ማክበር አለባችሁ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ልጆችም ሲያጠፉ ስታዩ ምከሯቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያወሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲመገቡ ብታዩ፣ በቅደሴ ጊዜ ያለ አግባብ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ተው ልትሏቸው ይገባል፡፡
እንግዲህ ልጆች የአግዚአብሔር ቤት ስለሆነች ቤተ ክርስቲያንን ልትወዷት ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውንም ሥርዓት ሁሉ ልትፈጽሙ ይገባል፡፡ ይህን ካደረጋችሁ አግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ እናንተንም ይወዳችኋል፡፡

 

ደህና ሰንብቱ እሺ ልጆች!

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቀ ጉባኤ በወሊሶ ተካሄደ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

መጋቢት 1፣ 2003 ዓ.ም

በምዕራብ ሸዋ ሃገረ ስብከት በወሊሶ ከተማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ሥርዓትና ቀኖና ውጪ የሆነ ጉባኤ ተካሄደ።

ከየካቲት 25 እስከ 27፣ 2003 ዓ.ም ባሉት ቀናት የተካሄደው ጉባኤ ምእመናንን ለመጠበቅና ለማጽናት በ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጥሪ የተዘጋጀ ቢሆንም በጉባኤው ማለቂያ ቀን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በዐቢይ ፆም መዝሙር በከበሮና በጭብጨባ ሊቀ ጳጳሱ በተገኙበት ሲዘመር እንደነበር ታውቋል።
ከማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ “በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በዐቢይ ፆም ማኅሌት አይቆምም፣ ከበሮ አይመታም፣ ጸናጽል አይንሿሿም፣ እልልታም የለም። ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርሰውም በዘንግ /በመቋሚያ/ ብቻ ነው፤ በዝማሜ። የሚቆመውም ፆመ ድጓና የፆም ምዕራፍ ነው።” በማለት ሥርዓቱን ያብራራሉ።
እሑድም ቢሆን የመወድስ አደራረስ እንዳለና ቅኔም በየምዕራፉ እንደሚደረግ፥ ማኅሌት ግን እንደማይቆም፣ ከበሮም እንደማይመታ ጨምረው ያስረዳሉ።
በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት በዐቢይ ፆም መሐል ከሚውሉ ክብረ በዓላት ውጭ ማኅሌት መቆም፣ ከበሮ መምታትና ማጨብጨብ እና ሌሎች ደስታን የሚፈጥሩ ነገሮችን ማድረግ ክልክል ነው።
ይህንንም ብያኔ ለማሻሻል የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑን የሚገልጹት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አንድ ሀገረ ስብከት በተናጠል ሥርዓት መለወጥ እንደማይችልም አስረግጠው ይናገራሉ።
በጉባኤው የነበሩ በርካታ ምእመናን በነበረው የሥርዓት መፋለስ ማዘናቸውንና በጉባኤው ላይ የተሰጡ ትምህርቶችም ብቁ ያልነበሩና የታለመውን ግብ ይመታሉ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።