እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን – ራዕ. 2.10

በዲ. ኤፍሬም ውበት

 
 
ክርስትና በእምነት እያደጉ እና እየጠነከሩ ዘወትር የሚጎለብቱበት ሕይወት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ከትናንት ዛሬ ከአምና ዘንድሮ አድጎና ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ «ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ጎልምሱ ጠንክሩ» እንደተባለ በጊዜውም /በተመቸ ጊዜ/ ያለጊዜውም/ባልተመቸ ጊዜም/ በእምነት ጸንቶ ለመገኘትና እስከ ሞት ድረስ ለመታመን የግድ በእምነት አድጎና ጠንክሮ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ /1ቆሮ.6.13ጠ14/፡፡ እምነትን በምግባርና በትሩፋት ለመግለጽም ራስን በመካድ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡ ለዚህም መከራን እየታገሱ ራስን ከዓለም መለየት ይገባል፡፡ በዚህ ዓይነት ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ በማስገዛት በእምነቱ የጠነከረ ሰው ከማናቸውም ነገር ይልቅ መንግሥቱንና ጽድቁን ያስቀድማል፡፡ /ማቴ.6.13/፡፡ ይህም ማለት ሃይማኖትን ከምግባር አዋሕዶ ልጅነቱን አጽንቶ ጽድቅ የሚገኝበትን ሀገር መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ አድርጎ ይኖራል ማለት ነው፡፡ በዚህም የመንፈስን ፍሬ የሚያፈራ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን የተተከለ የሃይማኖት ተክል ይሆናል፡፡ /ገላ.5:22/፡፡ ተክልነቱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱም ሰው በክፋዎች ምክር አይሄድም፡፡ በኃጢአተኞችም መንገድ አይቆምም፡፡ በዋዘኞችም ወንበር አይቀመጥም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፡፡ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡ /መዝ.1.3/፡፡

 

ቅዱስ ጳዉሎስ የተሰሎንቄ ምእመናን በእምነት አድገውና ጠንክረው በማየቱ «በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናስብ የእምነታችሁን ሥራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፡፡» በማለት ስለእነርሱ እግዚአብሔርን አመስግኗል፡፡ /1ተሰ.1.2ጠ3/፡፡ ከጥንት ጀምሮ በእምነታቸው ጠንካሮች የነበሩ ሰዎች በጉዟቸው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተዋል፡፡ እግዚአብሔርም ደስ የተሰኘባቸው በእምነታቸው ጸንተው በጎ ሥራ በመሥራታቸውና ዓለምን ድል በማድረጋቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ በዕብራውያን መልእክቱ እንደዘረዘረው፡

 

•    አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ያቀረበው፣
•    አብርሃም ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ የወጣው፤ አንድ ልጁን ይስሐቅንም ለመሠዋት ፈቀደኛ የሆነው፣
•    ሙሴ የግብጽን ብዙ ገንዘብ የናቀውና ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን የመረጠው፤ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል እምቢ ያለው፣
•    የኢያሪኮ ግንብ በእስራኤላውያን ጩኸት የፈረሰው፣
•    ጌዴዎንና ባርቅ፣ሶምሶንና ዮፍታሔ ጠላቶቻቸውን ድል ያደረጉት፣
•    ብላቴናው ዳዊት ኃይለኛውን ጎልያድን ያሸነፈው፣
•    ሠለስቱ ደቂቅ ወደ እቶነ እሳት ቢጣሉም ከመቃጠል የዳኑት በእምነት ነው፡፡ /ዕብ.11.1ጠ4/፡፡

 

በአዲስ ኪዳንም ቅዱሳን ሐዋርያት ሁሉን ትተው እስከ መጨረሻው የተከተሉት በእምነት ነው፡፡ /ማቴ.19.27/ ከእነርሱም ሌላ በሰው ዘንድ ያልተጠበቁ፣ በእርሱ ዘንድ ግን የታወቁ ጥቂት ሰዎች የእምነታቸው ጽኑነት ተመስክሮላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከነናዊቷ ሴት «አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ» ተብላለች፡፡ /ማቴ. 15.28/፡፡ በእምነት የጸኑ ሰዎች የቤተክርስቲያንን ሥርዓት፣ ትውፊት ለመጠበቅ መልካሙን ገድል ይጋደላሉ፡፡ /2ጢሞ.4.7/፡፡

አንድ ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት እስከ ሞት ድረስ ታምኖ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ሊያከናውናቸው ከሚገቡ መንፈሳዊ ተግባራት ጥቂቶችን እንመለከታለን፡፡

 

1. የእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ ለበጎ መሆናቸውን ማመን

 

በማናቸውም ጊዜ እግዚአብሔር ሁሉን የሚሰጥ አምላከ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእኛ ክፉ የሚመስሉን ነገሮችን እንኳን ለበጎ መሆናቸው ማመን አለብን፡፡ /ሮሜ.8.28/፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉውን ወደ በጎ ሊለውጥ የሚችል ኃያል አምላክ ነውና፡፡ ብላቴናው ዮሴፍ ባሪያ አድርገው የሸጡትን ወንድሞቹን «እናንተ ክፉ ነገር አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው፡፡» ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ /ዘፍ.50.20/፡፡ አበ ብዙኃን አብርሃም እግዚአብሔር «ልጅህን ሠዋልኝ» ያለው ለበጎ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡ ማወቅም ብቻ ሳይሆን እንደተባለው ልጁን ቢሠዋ እንኳን ከሞት አስነሥቶ በእርሱ በኩል ዘሩን እንደሚያበዛለት ያምን ነበር፡፡ /ዕብ.11.17/፡፡ ኢዮብም ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ አውቆ «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን» ብሏል፡፡ /ኢዮ.1.21/፡፡

 

2. የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳኖች ማመን

 

ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸው ተስፋ ደርሶ ቃሉ የሚፈፀም አይመስላቸውም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ያለጥርጥር ይፈጸማል፡፡ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው ተስፋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ተፈጽሟል፡፡ /ዘፍ.3.15/፡፡ ለኤልያስ የተሰጠው ተስፋ ምንድን ነው) የተሰጠው ተስፋ በሰራፕታዊቷ ሴት መጋቢነት ሲፈጸም ታይቷል፡፡ እንዲሁም በነቢዩ በኢዩኤል አንደበት የተነገረው ተስፋ የበዓለ ሃምሣ ዕለት ለቅዱሳን ሐዋርያት በመሰጠቱ ተፈጽሟል፡፡ /ኢዩ.2.28፤ ሐዋ.2.16/፡፡ በዚህ ዓይነት እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባውን ቃል ኪዳን እንደማይሽርና ከአፉ የወጣውን ቃል እንደማይለውጥ ማመን ይገባል፡፡/መዝ.88.34/፡፡ በቤተ ክርስቲያን በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁ ባለው መሠረት በመካከላችን እንደሚገኝ የታመነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከውስጥም ሆነ ከውጭ መከራ በሚበዛባት ጊዜ መከራ የሚያስነሣባትና የሚያጸናባት ዲያብሎስ መሆኑን አውቀን «የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም» በሚለው ቃል ኪዳን መጽናት ይገባል፡፡ /ማቴ.16.18/፡፡ መናፍቃን ከእውነት መንገድ ለማውጣት በሚከራከሩን ጊዜም «ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁ»የሚለውን ቃል ኪዳን በማሰብ መታመን ያስፈልጋል /ሉቃ.21.15/፡፡

 

3. በችግር ጊዜ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ፈቃድ ተስፋ ማድረግ

 

በመንፈሳዊ ጎዳና ስንጓዝ በየአቅጣጫው የሚከበንን መከራ አይተን ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ተመልክተን አዳኝነቱን ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወገኖቹ እስራኤል ቀይ ባሕርን ከኋላ ደግሞ የፈርኦንን ሠራዊት ተመልክተው ተስፋ በቆረጡ ጊዜ «ቁሙ፣ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፡፡» ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ /ዘዳ.14.13ጠ14/፡፡

ብላቴናው ዳዊት የተመለከተው በአካሉ ግዙፍ ወደሆነው ወደ ጎልያድ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር አዳኝነት ነው፡፡ /1ሳሙ.17.46/፡፡በአጠቃላይ ዓለም ድብልቅልቅ ቢል ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ ምክንያቱም «እግዚአብሔር በወጀብና በዓውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለውና»/ናሆ.1.3/፡፡

 

4. የቅዱሳንን ገድል ማሰብ

 

ቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጣቸው ሃይማኖት እሰከ መጨረሻው ተጋድለዋል፡፡ /2ጢሞ.4.7/፡፡ በሰይፍ ተመትተዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ ለአናብስት ተሰጥተዋል፣ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለዋል፣ ይህም የሚያሳየን የእምነታቸውን ጥንካሬ ነው፡፡ በመሆኑም የቅዱሳንን ገድል በምናስብበት ጊዜ ከእነርሱ የምንማረው እምነታቸውን፣ ሥርዓታቸውንና ትውፊታቸውን ለመጠበቅ መጽናታቸውን ነው፡፡ መማርም ብቻ ሳይሆን በተሰጣቸው ቃል ኪዳንም እንጠቀማለን፡፡ እስራኤል ዘሥጋ «እናንተ ጽድቅን የምተከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ ስሙኝጠ ከእርሱ የተቆረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቆፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ፣ ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፡፡ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፣ ባረኩትም፣ አበዛሁትም፡፡» የተባለለት ለዚህ ነው፡፡ /ኢሳ.51.1/፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም «የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው» ብሏል /ዕብ.13.7/፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑንና ሥራችንን ሁሉ እንደሚከናውንልን፣ ከሁሉም በላይ እንደሚወደን ማመን ያስፈልጋል፡፡ /ዘፍ.15.21፤1.22፤ መሳ.16.3/፡፡ ምክንያቱም አንድ ልጁን እንኳን አልከለከለንምና /ዮሐ.3.16/፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱም በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡ /1ዮሐ.4.9/፡፡ እርሱም በትምህርቱ «ከእንግዲሀ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ወደጆች ግን ብያችኋለሁ» ብሎናልና፡፡ /ዮሐ.15.15/፡፡ በመጨረሻም ስለማናቸውም ነገር እንደምንጸልይ ሁሉ ስለ እምነታችንም ጽናት ልንጸልይ ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ እምነታችን ዕለት ዕለት እያደገ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እስከ ሞት ድረስ እንዳንታመን በእምነትና በምግባር እንዳንጸና የሚያደርጉን ፈተናዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ፡

 

1. የራስን ክብር መሻት

 

ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር ትተው የራሳቸውን ምድራዊ ክብር ሲፈልጉ እምነታቸው ደክሞባቸዋል፡፡ ዲያብሎስ ከክብሩ የተዋረደው፣ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያሳደደው፣ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ «እነሆ ዓለሙ ሁሉ በኋላው ተከትሎት ሄዷል፡፡» በማለት ይቃወሙት የነበረው የራስን ክብር በመሻት ነው፡፡ /ማቴ.2.17፤ ዮሐ.12.19/፡፡ ይሁን እንጂ ምድራዊ ክብር ፈጥኖ እንደ ሣር ይጠወልጋል፣ እንደ አበባም ይረግፋል፡፡ /ኢሳ.40.6፤1ጴጥ.1.24/፡፡ ስለሆነም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «ነፍሴን/ሰውነቴን/ በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ» ማለት ይገባል፡፡

 

2. እምነትንና ዕውቀትን መደባለቅ

 

የሰው ልጅ አእምሮው ውሱን፣ ዕውቀቱም የተገደበ ስለሆነ ነገረ ሃይማኖትን ከአቅሙ በላይ ለመተንተን ይከብደዋል፡፡ ስለሆነም የረቀቀውን የእግዚአብሔርን አሠራር ስፋቱንና ጥልቀቱን በሥጋዊ ዕውቀቱ እመረምራለሁ ሲል ከተሳሳተ ሀሳብ ላይ ደርሶ ይሰናከላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደምናየው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ግኖስቲኮች ከሃይማኖት ተሳስተው የወደቁት፣ ሃይማኖትንና ዕውቀትን በመደባለቅ ለመጓዝ ባደረጉት ሙከራ ነው፡፡ ሥጋዊውን ዓለም ልንመረምር እንችላለን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ልንመረምር አንችልም፡፡ በመሆኑም ሊቃውንት በእምነት ተራቅቀው ብዙ የሃይማኖትን ምሥጢር ባወቁ ቁጥር የሚያውቁት ገና አለማወቃቸውን ነው፡፡ ስለሆነም ውሱን የሆነ ዕውቀታችንን በትህትናና በትዕግሥት እግዚአብሔርን ከማገልገል ጋር ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

 

3. ክፉ ባልንጀርነት

 

ከመናፍቃን ጋር በመወዳጀት የእነርሱን ስብከትና መዝሙር መስማት እምነትን ያደክማል፡፡ ምክንያቱም የመዝሙሩ መሣሪያና ስሜት ለሥጋዊ ሀሳብና ፈቃድ መጥፎ ጎን መነሣሣት ይፈጥራልና፡፡ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ስሜታዊ ያደርጋል፡፡ የዜማው ስልተ አልባ መሆንና ከዘፈን ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ዓለማዊነት ጠባይ የለበትም መንፈሳዊ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ ለዚህም ነው «ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋዋል» የተባለው /1ቆሮ.15.33/፡፡ በሃይማኖት በሥርዓት ከማይመስል ጋር ለመመሳሰል መሞከር፣ አብሮ ማደርም ሆነ መዋል መልካሙን እምነት ያጠፋዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ «በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት ሰላምም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና፡፡» ብሏል፡፡ /2ዮሐ.1.10 – 12/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም «ከማያምን ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፡፡» ብሏል፡፡ ስለሆነም ብርሃን ከጨለማ ጋር ምንም አንድነት ስለሌለው መለየት ያስፈልጋል፡፡ /2ቆሮ. 6.14-16/፡፡

 

4. ክፉ ወሬ

 

ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው መስማት የሚገባቸው ቤተ ክርስቲያናቸው የምትነግራቸውን መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» እንዲሉ በወሬ የተፈቱ ብዙዎች ናቸውና፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስትን ከመውረስ የደከሙትና በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውም ተስፋ የጠወለገው፣ ዐሥሩ ሰላዮች ያወሩትን እምነት የጎደለው ወሬ እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው ነበር፡፡ /ዘኁ.13. 28/፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ አይሁድ «ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ከመቃብር ሰርቀው ወሰዱት» ብለው አስወርተው ነበር፡፡ ይህም ወሬ መግደላዊት ማርያምን አሳምኗት ስለነበረ ከአንዴም ሦስት ጊዜ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል እስከ ማለት ደርሳለች፡፡ /ዮሐ. 20.2-13፤15/፡፡ ጥንትም አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር የተጣሉት የሰይጣንን ወሬ እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው ነበር፡፡ /ዘፍ.3.4/፡፡ ምክንያቱም የሐሰት ወሬ ከዲያብሎስ ነው፤ የሐሰት አባት እርሱ ነውና፡፡ /ዮሐ.8.44/፡፡ በእምነት መድከም በመጀመሪያ ሥርዓትን ትውፊትን ያስንቀናል፡፡ በሃይማኖት ለሚኖር ሰው ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም፡፡ እንግዲህ ይህንን ሁሉ አውቀን በጊዜውም አለጊዜውም በሃይማኖት በምግባር ጸንተን ልንገኝ ይገባል፡፡ በእምነታችን እንድንጸና ምክንያት ሳናበዛ እምነታችንን ከሚያዳክሙ እኩይ ተግባራት በመራቅ እምነትን የሚያጠናክሩትን በጎ ተግባራት ሁሉ መያዝ አለብን፡፡ «በዓመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ» እንደተባለ በማንም ሳንወሰድ የቅዱሳን አባቶቻችንን ሃይማኖት ከምግባር አስተባብረን ልንይዝ ይገባናል፡፡ /2ጴጥ.3.17/፡፡

 

5. ሥጋዊ መከራን መፍራት

 

ሥጋዊ መከራን መፍራት እምነትን ያደክማል፡፡ ይህም ለዘለዓለም ሞት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ /ራዕ.21.7/፡፡ እግዚአብሔር ግን የፍርሃትን መንፈስ አላሳደረብንም /2ጢሞ.1.7/፡፡ ለሥጋ ፍላጎት መገዛት ማለትም ለዝሙት፣ ለገንዘብና ለሥልጣን ወዘተ መገዛትም እምነትን ያዳክማል፡፡ /1ነገ.11.1፤ ማቴ.19.22፤ ዮሐ.5.4-9፤ ዕብ.4.4፤ 2ጴጥ.2.15፤3ዮሐ.10፤ ራዕ.2.14/፡፡ ምድራዊ ችግርም ሲያዩት የሚያልፍ ስለማይመስል እምነትን ያዳክማል፡፡ ጌዴዎን «ጌታዬ ሆይጠ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን)» ያለው በምድራዊ ችግር ብዛት እምነቱ ደክሞ ስለነበር ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የማዕበሉን ኃይል አይተው «ጌታ ሆይ ስንጠፋ አይገድህምን)» ያሉ ለዚህ ነው፡፡ /ማር.4.35/፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ልንጠነቀቅ የሚገባው ሰይጣን እንዳያታልለን ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው የብርሃን መልአክ እስከሚመስል ድረስ ራሱን ይለውጣልና፡፡ /2ቆሮ.11.14/፡፡ እንዳለ፡፡ ምትሐታዊ የሆኑ ድንቅ ምልክቶችንም ያደርጋልና፡፡ /2ተሰ.2.3-9/፡፡ ሌላው ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ካለው ነገር የምንጠራጠርበት ምንም ዓይነት ነገር መኖር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በዓይነ ሥጋ ብቻ በመመልከት ጥቃቅን መስለው በሚታዩን ነገሮች መጠራጠር ከጀመርን ነገ ደግሞ የእግዚአብሔርን አዳኝነት እስከ መጠራጠር እንደርሳለንና ነው፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ የተሰደዱትን በማሰብ ይሁን

ለክርስቲያን ዓመታት፣ ወራትና ቀናት በሙሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቀን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳን መልካም ምግባር ተቀድሷል፡፡ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚገኙ 365 ቀናት በቅዱሳን ስም ተሰይመው የሚዘከሩት፡፡
ምእመናን ቤተክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት በፍቅር በደስታ ከሚዘከሩት ዕለታት ደግሞ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ቀን የሚዘከረው የእመቤታትን ቅድስት ድንግል ማርያምና የልጇ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስደት አንዱ ነው፡፡

የእመቤታችን ስደት የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ስደት ነው፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደሚለው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? እያሉ በመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ምድረ እስራኤልን ይገዛ የነበረው ሄሮድስ የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ የሚለውን ቃል ሰምቶ፤ ከኔ ሌላ ንጉሥ ማን አለ? በማለት በአማካሪዎቹ ግፊት ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት የሚሆን ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት እንዲገደሉ አደረገ፡፡
 
በዚያን ጊዜ «እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ እናቱንና ሕፃኑን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው»፤ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሔደ፡፡ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያ ኖረ፡፡ /ማቴ 2-13-15/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ፤ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ፣ ዮሴፍና ሰሎሜን አስከትላ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብጽ አውራጃዎች ስደተኛ በመሆን ኖራለች፡፡

ነቢያት ስለጌታ ትንቢት በመናገራቸው፣ እመቤታችን የጌታ እናት በመሆኗ፣ ሐዋርያት ስለጌታ በማስተማራቸው ተሰደዋል፡፡

የጌታ አገልጋይም እናትም የሆነችው የእመቤታችን ስደት ግን. . . ከሁሉ የሚለይ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት ልዩ የሚያደርገው: –

1.    ሕግን በመተላፉ ከገነት ተሰዶ የነበረውን አዳምን ለመካስ የተደረገ በመሆኑ
2.    በግብጽ ነግሦ የነበረውን አምልኮት ጣኦት ለማሳደድ የተደረገ ስለሆነ የጌታችንና የእናቱ ስደት ልዩ ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ግብጽ ስትሰደድ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር አግኝቷታል፡፡ እሾህ እየወጋት እንቀፋት እየመታት ተጉዛለች /ተሰዳለች/፤ በስደቷም ረሃብና ጥም፣ ችግርና መከራ ደርሶባታል፡፡ በበረሃው ወንበዴዎችን ባየች ጊዜም በስደት ከሄሮድስ ጭካኔ ከሀገር ያወጣሁትን ልጄን ይገድልብኛል ብላ መሪር እንባ አልቅሳለች፡፡

በስደቷ ወቅት በደረሰባት ረሐብና ጥም የተነሣ ወደ መንደር ገብታ ብትለምን በችግር ምክንያት የሰው ፊት ማየት ከእሳት የበለጠ ወላፈኑ ስለሚያቃጥል የሰው ፊት ገርፏታል፡፡ የትእማን ቤተሰቦች ዘብተውባታል፡፡

«ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሸክማችንን ሊሸከም ነውና ውኃውን ለፍጥረታት የሚሰጥ እርሱ እየጠማው፤ እንስሳትን የሚመግብ እየራበው ምድርን በልምላሜ የሚያለብስ፣ ተራቁቶ የኛን ከገነት መሰደድ የመጣብንን ዕዳ ሊክስልን ከእናቱ ጋር ተሰደደ፤ ድንግል ማርያምም የአምላክ እናት ሆና መከራን ቀመሰች፡፡ ጌታን አዝላ በረሐብ አለንጋ ተገረፈች፡፡

በመጨረሻ ግን ያ ሁሉ የመከራና የስቃይ ስደት ሲያበቃ «አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ» ሲል በመኃልየ ማኀልይ ዘሰሎሞን ተነግሮ የነበረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከዚያ ሁሉ መከራና ስደት ልጇን ይዛ ወደ ናዝሬት ተመልሳለች፡፡

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ «ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲነግሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» /ማቴ 5-11/ የሚለውን የስደት ዋጋ ጭምር እያሰብን መሆን ይገባል፡፡

ይህንንም የእመቤታችንን ስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ በማኅሌትና በመዝሙር ትዘክራለች፡፡ ካህናቱም በዕለተ ሰንበት ከምሽት ጀምረው በማኅሌትና በመዝሙር ምስለ ፍቁር ወልዳን /የልጇ እና የእርሷ/ ሥዕል ይዘው ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡

ይህም የእመቤታችንን ስደት ለማጠየቅ ነው፡፡ ሌሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰባቸውን መከራ ለማስታወስ የፍቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በቅድስት ቤተክርስቲያን ተገኝተን በመንፈስ የሩቁን አቅርበን የእመቤታችንን ስደት በእምነት እያየን በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታችን በዜማ «መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ንጹሕ፣ ፀአዳ ፣ቀይህና ብሩህ የሚሆን ልጅሽን ታቅፈሽ ርኅሩኅ የሆነ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትለሽ ከሐዘናችንና ከችግራችን ታረጋጊን ዘንድ ፈጥነሽ ድረሽልን» ልንላት ያስፈልጋል፡፡

በቅዳሴያችንም «ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ እንላለን፡፡

በዚህ መታሰቢያ ወቅት እመቤታችን ከልጇ ጋር መሰደዷን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን እኛም በመንፈስ አብረን ከእመቤታችን ጋር መሰደድ ይገባናል፡፡ የመሰደድ ዋጋው ብፅእና ነውና፡፡ ነገር ግን ወዴት እንደምንሰደድ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ብዙዎች ከጽድቅ ወደ ኃጢአት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ፣ ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከፍቅር ወደ ጸብ ተሰደዋል፡፡ የኛ ስደት ግን መሆን ያለበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞተ ወደ ሕይወት፣ ከሐሰት ወደ እውነት፣ ከጥላቻና ክስ ወደ ፍቅርና መተሳሰብ፣ ከክህደት ወደ እምነት መሰደድ ያስፈልጋል፡፡ ከማሳደድ ይልቅ መሰደድ ይሻላልና፡፡

ዛሬ ብዙዎች ለሥጋ ተድላ በኃጢአት እየተሰደዱ ነው፡፡ እነዚህን ወገኖቻችን ከኃጢአት ስደት እንዲመለሱ በማስተ ማር፣ በመምከርና በመገሰጽ ጭምር ልንመልሳቸው ያስፈለጋል፡፡ መምህራንም ለኃጢአት የተሰደዱትን ወገኖች የንስሐ ፍሬ እንዲያፈሩ ሕይወት የሆነውን ወንጌል ሊያስተምሯቸው ይገባል፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍላት በችግርና በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የተሰደዱትን በጸሎት ማሰብ በሚያስፈልጉ ድጋፎች ሁሉ መርዳት የክርስቲያን የዘወትር ምግባሩ ቢሆንም በተለይ በዚህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት መታሰቢያ ጊዜ በልዩ ሁኔታ በችግር የተሰደዱትን ልናስባቸው ያስፈልጋል፡፡

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ በኃጢአትና በመከራ የተሰደዱትን በማሰብ ይሁን፡፡

 
ወስብሐት ለእግዚአብሔ

ኢይብቁል ብክሙ መሪር ሥርው

/መራራ ሥር አይብቀልባችሁ/ /ዕብ.12፡15/  
ዘገብርኤሏ

የአብርሃም ልጆች ነን የሚሉ ነገር ግን የአብርሃምን ሥራ የማይሠሩና የነቢዩ ዳዊት ልጆች ነን የሚሉ የእርሱን ፈለግ የማይከተሉ ዕብራውያንን ቅዱሱ ጳዉሎስ «መራራ ሥር አይብቀልባችሁ» ሲል መከራቸው፡፡ ዕብራውያን በእግዚአብሔር እናምናለን፤ የእሱ ልጆች ነን እያሉ ይመጻደቁ ስለነበሩ መልካም ሥራ በመሥራት ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ የከለከላቸውን መራራውን ሥር እንዲያስወግዱ አሳሰባቸው፡፡ ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ አምላከ ሰማይ ወምድር ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ውጫቸውን ያሳመሩ ነገር ግን ውስጣቸውን በኃጢአት ያሳደፉትንና በመራራ ሥር የተመሰለው ኃጢአት በውስጣቸው የበቀለባቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን ሲገስጽ «እናንተ ግብዞች ጻፎች፤ ፈሪሳዉያን በውስጡ ቅድሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ ወዮላችሁ፡፡» ብሏቸውል፡፡ /ማቴ.23፡25/

ኃጢአትን በሐልዮ ጸንሶ በነቢብ መውለድ፣ በነቢብ ወልዶም በገቢር ማሳደግ መራራ ሥር ነው፡፡ /ማቴ.24፡16/ ይህም ማለት ኃጢአትን ማሰብ አስቦም ሥራ ላይ ማዋል በአጠቃላይ በኃጢአት መውደቅ በሰው ልቡና ውስጥ የሚበቅል መራራ ሥር ነው፡፡ በዚህም «ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ» /ዘዳ.18፡19/ የተባለውም የሰው ልጅ በመራራ ሥር፣ በሐሞትና በእሬት የተመሰለውን ኃጢአት ከሕይወቱ ካላራቀ መራራ ገሀነመ ዕሳት እጣ ፈንታው ይሆናል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሐሳቦች በሙሉ መራራ ሥር የተባለው ኃጢአት መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም እስኪ በሕይወታችን ውስጥ ሊነቀሉ የሚገባቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለዩንን መራራ ሥሮች በዝርዝር እንመልከት፡፡

1.ዝሙት

ዝሙት አእምሮን የሚያጐድል፣ ሰላምን የሚነሣ፣ ጤንነትን የሚያሳጣ፣ ሕይወትን የሚያበላሽ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የሚያሳጣ /የሚገፍፍ/ በሰው ልቦና ውስጥ የሚበቅልና መነቀል ያለበት መራራ ሥር ነው፡፡ ብዙ ታላላቅ አባቶች ክብራቸውን ያጡት በዝሙት እንደሆነ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ፡- እስራኤላዊያን ከሞአብ ልጆች ጋር በማመንዘራቸው ብኤልፌጐር የሚባል ጣዖት እንዲያመልኩ አደረጓቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔርን በማስቆጣታቸው 24 ሺሕ ሕዝብ በአንድ ቀን ተቀስፏል፡፡ /ዘፍ.22፡37፣ ዘኁ.27፡1/ «ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል» እንደተባለው፡፡ /ምሳ.22፡1ዐ/
ዝሙት፣ ሴሰኝነትና አመንዝራነት ቅድስናን ከሚያሳጡ ታላላቅ ኃጢአቶች ውስጥ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
የሰው ልጅ በእነዚህ ኃጢአቶች እንዳይወድቅ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን አዋቂ ነውና አንድ ለአንድ በመወሰን ጸንቶ እንዲኖር ጋብቻን ባርኮ ቀድሶ ሰጥቶታል፡፡ «መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፣ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡» እንዲል፡፡ /ዕብ.13፡4፣ 1ቆሮ.7፡1/ ዝሙት ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለይ መራራ ሥር ነው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሶምሶንም ጸጋውን እንዲገፈፍ ያደረገው ይህው በውስጡ የበቀለው መራራ ሥር ነው፡፡ /መሳ.17፡1/ ይህ ታላቅ ሰው ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ቢሆንም አንድ ናዝራዊ ማድረግ የሌለበትን የዝሙትን ተግባር ፈጽሞ በመገኘቱ ከክብሩ ተዋርዷል ኀይሉ ተነፍጎታል፡፡ /ዘኁ.6፡1/ ዛሬም ትእዛዛተ እግዚአብሔርን በመጣስና ዝሙት በመሥራት ከክብር እየተዋረድን ያለን ሰዎች ራሳችንን ልንመረምርና መራራውን ሥር በንስሐ በጣጥሰን በመጣል ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ ይገባል፡፡ ለሶምሶን እግዚአብሔር አምላክ ታላላቅ ውለታዎችን ቢውልለትም፤ እሱን ያስጨነቀው አምላክ ያደረገለት ውለታ ሳይሆን ከደሊላ በዝሙት የመውደቅ መንፈስ አእምሮውን አሳጥቶት ነበር፡፡ /መሳ.16፡17/ ይህች ሴት ቃሏን አጣፍጣ የዚህን የተመረጠ ሰው ሕይወት እንዳጠመደችው ዛሬም የብዙዎቹን ሕይወት በዝሙት የሚያጠምዱ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው መራራ ሥር የበቀለባቸው እንዳሉ ማስተዋል ይገባል፡፡
ከክብራችን እንዳንዋረድ የቅዱሳን አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል ሥጋችንን ለነፍሳችን አስገዝተን መኖር ያስፈልጋል፡፡ ዓይኖቻችን ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ቅዱስ ደሙ የሚመለከቱ መሆን አለባቸው፡፡ «ልጄ ሆይ ወደ ጋለሞታ ሴት ልብህ አይባዝን በጐዳናዋ አትሳት፡፡ ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፡፡» /ምሳ.7፡24/ በዝሙት ተወግተው ከወደቁት ወገኖች እንዳንደመር በየትኛውም ቦታ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡

2.ትዕቢት

 ሳጥናኤልን ያህል ታላቅ መልአክ ከክብሩ ያዋረደው ሌላው መራራ ሥር ትዕቢት ነው፡፡ ትዕቢት በመራራ ሥር የተመሰለውም ከኔ በላይ ማን አለ በማለት የማይገባውን ይገባኛል እያሰኘ ሌላውን የመናቅ፤ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መራራ መንፈስ ስለሚያበቅል ነው፡፡ «አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ አንተ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ አልህ፡፡ ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓድም ጥልቅ ትወርዳለህ፡፡» /ኢሳ.14፡12-16/ ብሎ የተናገረለት ሳጥናኤል በትዕቢቱ ምክንያት ነው፡፡ «ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም፡፡» /መዝ.3፡5/ ተብለ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልናስብ ይገባል፡፡
ይሁን እንጂ ትናንት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ቅዱስ ሥጋውንና ቅዱስ ደሙን እየበላና እየጠጣ አድጎ በትዕቢት ምክንያት የበላበትን ወጭት ሰባሪ የሆነ ብዙ ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ በሀብቱ በጉልበቱ በእውቀቱ፣ በወገኑ የሚኩራራና የሚታበይም አለ፡፡ ይሁን እንጂ ሀብታሙ በደሃው ላይ፣ የተማረው ባልተማረውላይ አሠሪ በሠራተኛው ላይ የሚታበይ ከሆነ ክርስቲያን ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ፤ ያለው የሌለውን መርዳት፣ የተማረውም ላልተማረው ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ማለት፣ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲባል ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የማገልገል ጸጋ ቢሰጠንም በቸርነቱ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናገለግል ሁሉ የምናቀርበው የአገልግሎት መስዋዕት በእግዚአብሔር ቸርነት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ልክ «… የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ፡፡» እንደተባለ፡፡ /ሉቃ.17፡1ዐ/
ስለዚህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሊኖረን እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ «እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡፡» /ምሳ.22፡4/ እንዳለ ጠቢቡ በምሳሌው፡፡

 3. ማስመሰል

መመሳሰልና መስሎ መታየት፣ ለመመሳሰል መጣር የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳች ፍሬ ባገኝባት ብሎ ወደ አንዲት ዛፍ ሲጠጋ ፍሬ ያፈራች መስላ እንጂ አፍርታ ባለመገኘቷ ምክንያት ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ ወዲያውም ደረቀች፡፡ /ማቴ.21፡18/
ከዚህ ኀይለ ቃልም የምንረዳው በመስሎ መኖርና ሆኖ አለመገኘት የሚያመጣውን ርግማን ነው፡፡ ማስመሰል መራራ ሥር ነውና ሊነቀል ይገባዋል፡፡ ዛሬም ብዙ ሰው በአፉ የሃይማኖት ሰው ይመስላል፣ እውነታው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱ ጾም የሚጾሙ፣ ነገር ግን ከኃጢያት ያልተለዩ፣ በንስሐ መመለስን ችላ የሚሉ፣ ታቦት ሲነግሥ እልል ስለተባለ ብቻ እልል የሚሉ ከዚያ ሲወጡ ግን ኃጢአት ለመሥራት የሚጣደፉና በልባቸው የሸፈቱ ሰዎች የማስመሰሉን መራራ ሥር ከውስጣቸው በንስሐ ነቅለው መጣል አለባቸው፡፡ ሆኖ መገኘት እንጂ መስሎ መታየት አያድንምና፡፡ «ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከኔ በጣም የራቀ ነው፡፡ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል፡፡» /ኢሳ.29፡13፣ ማቴ.5፡8/ እንደተባለው ዛሬም የብዙ ሰው አምልኮ የዚህ ትንቢት መፈጸሚያ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ጥዋት ቤተ ክርስቲያን፤ ከሰዓት ቤተ ጣኦት በመሔድ ጊዜን በከንቱ ከማሳለፍ መቆጠብ ያሻል፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ ጨሌውን፣ የዐውደ ነገሥቱን ጥንቆላ ማመን፣ መናፍስትን መጥራትና የመሳሰሉትን እየፈጸሙ መገኘት በልብ መሸፈት ነውና ልንመለስ ይገባል፡፡ «በሰማያት ያለው የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ የሚሉኝ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ አይደሉም፡፡» /ማቴ.7፡21/ ተብሏልና፡፡
 መስለው ለመኖር የሞከሩ ብዙ ሰዎች ሲጎዱ እንጂ ሲጠቀሙ አላይንም፡፡ ግያዝ ከኤልሳዕ ጋር መስሎ ሲኖር ልቡ ግን ወደ ገንዘብ ሸፍቶ ስለነበር በለምጽ ተመታ፡፡ /2ኛ ነገ.5፡2ዐ/ የይሁዳንም ታሪክ ስንመለከት ከሐዋርያት ጋር ተመሳስሎ እየኖረ ልቡናው በፍቅረ ንዋይ ተነድፎ እንደነበር ነው፡፡ እናም እነዚህንና የመሳሰሉትን የፍቅረ ንዋይ፣ የስስት፣ የእምነት ጎደሎነት ወዘተ መራራ ሥሮች በቶሎ በንስሐ መነቃቀል ያስፈልጋል፡፡
 ካህኑም፣ ዲያቆኑም፣ ሰባኪውም፣ ዘማሪውም በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ የሚል ሁሉም አገልግሎቱ ዋጋ የሚያገኘው ከእግዚአብሔር መሆኑን ከልብ በማጤንና ራሱን በመመርመር የጐደለውን ሊያስተካክል ይገባል፡፡ እያንዳንዷ ሥራችን የምትበጠርበት ጊዜ ይመጣልና፡፡ «መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፡፡ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደሥራቸው መጠን ተከፈሉ፡፡ … እያንዳንዱ እንደሥራው መጠን ተከፈለ፡፡» እንዲል፡፡ /ራእ.2ዐ፡12/
 ስለዚህ መልካም ዋጋ ለማግኘት መልካም ሥራ ለመሥራት መጣር ይገባል፡፡ «አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ እርሱንም ፍሩ ትእዛዙንም ጠብቁ ቃሉንም ስሙ እርሱንም አምልኩ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ» /ዘዳ.13፡4/ ስለተባልን ለመልካም ሥራ እሺ እንድንል ያስፈልጋል፡፡ «እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯል» ተብሏልና፡፡ /ኢሳ.1፡19/

4. ዓላማ ቢስነት

ዓላማ የሌለው ሰው ከየት ተነሥቶ ወዴት መሔድ እንዳለበት የማያውቅ፣ ካሰበበት የማይደርስ ነው፡፡ ማንም ወደነዳው የሚነዳ፣ በጭፍን የሚጓዝ ሰው ዓላማ ቢስ ሊባል ይችላል፡፡ ዓላማ የሌለው ሰው በጀመረውና በተሠማራበት ተግባር ላይ ጸንቶ አይቆይም፡፡ በተለይ ክርስቲያን ዓላማ ከሌለው በትንሽ ነገር የሚፈተን፣ ሥጋዊ ፍላጐቱ ካልተሟላለት የማያገለግል፣ የሚያማርር፣ በሆነ ባልሆነው የሚያኰርፍ፣ መንፈሳዊነትን ያዝ፣ ለቀቅ የሚያደርግ የጸሎቱ፣ የጾሙ ዋጋ ዛሬውኑ እንዲከፈለው የሚፈልግ ይሆናል፡፡ የሚያገለግልበትንም ዓላማ ያልተገነዘበ ሰው በየደቂቃው እንዲመሰገን ይፈልጋል፡፡ ሰዎች ዓላማቸውን እንዲስቱ በልባቸው ውስጥ የማዘናጋትን ተግባር የሚፈጽም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ቅዱሳን አባቶች በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፉም ዓላማን የመሳት መራራ ሥር በውስጣቸው አልበቀለም፡፡ በሁሉም ጸንተው በመቆማቸው ለክብር አክሊል በቅተዋል፡፡
 ሙሴ እስራኤልን በምድረ በዳ ይመራ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ከዓላማው አልተዘናጋም፡፡ ይልቁንም ያህዌህ ንሲ /እግዚአብሔር ዓላማዬ ነው አለ እንጂ፡፡ /ዘዳ. 12፡15/
 ዮሴፍ ጽኑ ዓላማ ስለነበረው የተዘጋጀለትን የዝሙት ግብዣ እምቢ አለ፡፡ /ዘፍ. 39/
 ሶስና ልትሸከመው የማትችል የሚመስል ፈተና ቢያጋጥማት ንጽሕናዋን ክብሯን ጠብቃ፣ ለአምላኳ ታምና መኖርን ዓላማዋ ስላደረገች የመጣባትን ፈተና በጽናት፣ በታማኝነት፣ በንጽሕና በቅድስና ልታልፍ ችላለች፡፡ /መጽሐፈ ሶስና/
 ኢዮብ ዓላማው እግዚአብሔር ስለነበር ይፈራረቅበት የነበረውን መከራ፣ ሥቃይና ችግር ሊያልፍ ችሏል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ ተፈትኖ፣ ነጥሮ ታላቅነቱን አስመስክሯል፡፡ /ኢዮ.2፡10/ በአንጻሩ ደግሞ ዓላማቸውን የሚያስት መራራ ሥር በውስጣቸው በመብቀሉ ምክንያት የተጐዱ ከክብራቸው ያነሡ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
 ለምሳሌ ሳኦልን ብንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ከሕዝበ እስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ቢሾመውም የቅንዓት መንፈስ በውስጡ ስለበቀለ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር ሲሠራ እናያለን፡፡ /1ኛሳሙ. 11፡9፣15፡35/
ዛሬም ትናንት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የነበርን፣ እግዚአብሔር ከፍ ስላደረገን፣ ስለሾመን ዓላማችንን የዘነጋን አንታጣምና ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ ከዓላማችን እንድንስት የሚያዘናጉ ነገሮች በርካቶች ናቸው፡፡ ሰው ለገንዘብ፣ ለሥልጣን፣ ለሓላፊ ጠፊ ሀብት ብሎ ዓላማውን ይስታል፡፡ ይሁዳ ምንም እንኳን ከሐዋርያት አንዱ ሆኖ ቢቆጠርም ዓላማው መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ሳይሆን ገንዘብን ማሳደድ ስለነበረ አምላኩን እስከ መሸጥ ደረሰ፡፡ «እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ፡፡» ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመበት፡፡ /መዝ.4ዐ፡9/ ይሄው ዛሬ የነፍሰ ገዳዮችና የክፉዎች ተምሳሌት ሆኖ ይነገራል፡፡ ስለዚህ «ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ይሻላል፡፡» እንደተባለ ስማችን በክፉ እንዳይጠራ በዓላማችን እንጽና፡፡ /መክ. 7፡1/ ዓላማችን መንግሥቱን ለመውረስ፣ ስሙን ለመቀደስ ይሁን፡፡ እንደ ዴማስ ወደ ዓለም የሚመለስ መራራ ሐሳብ በውስጣችን እንዳይበቅል ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ /2ኛጢሞ. 4፡9/

5. የጥርጥር መንፈስ

«የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህርን ማዕበል ይመስላል፡፡ ሁለት ሐሳብ ላለው፣ በመንገድም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች የሚያገኝ አይምስለው፡፡» /ያዕ. 1፡6/ በማለት እንደተነገረው ተጠራጣሪ ሰው ከጌታ አንዳች ነገር አያገኝም፡፡
 በአሁኑ ወቅት ከጽናታችን እንድንናወጥ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የተጠራበትን ዓላማ ጠንቅቆ የማያውቅ ክርስቲያን በጥርጥር ነፋስ ተነቅሎ ይገነደሳል፡፡ ስለዚህ ጊዜው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻው በመሆኑ በማስተዋል መራመድ ያስፈልጋል፡፡
 ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ይመጣ ዘንድ ስላለው ክህደትና ሐሳዊ መሲህ «… የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየተሳቡ የሚያጠፉ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤ … በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል፡፡» /2ጴጥ.2፡1/ በማለት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠርና የሚያጠራጥር፣ በቅዱሳን ላይ አፉን የሚከፍት ሐሳዊ መሲህ ቢነሣ የሚያስደንቅ መሆን የለበትም፡፡ ለምን ቢሉ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና፡፡ ዮሐንስም ስለዚህ ነገር «አውሬው ታላቅ ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው … እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡» ብሎ ጽፏል፡፡ /ራእ.13/
ስለዚህ በልባችን የሚበቅለውን የጥርጥር መንፈስ ከውስጣችን ነቅለን ልንጥል ያስፈልጋል፡፡ «ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፡፡ /2ጴጥ.3፡17/ እንደተባልነው ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ መራራ ሥር ኃጢአትና ክርስቲያናዊ ምግባር በአንድ ሰውነት ላይ ሊበቅሉ የማይገባቸው እንክርዳድና ፍሬ ናቸው፡፡ በመሆኑም በንስሐ መከር መለየት ይኖርብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የመራራ ሥራ ፍሬዎችን የሥጋ ሥራ በማለት ገልጿቸዋል፡፡ «አስቀድሜ እንዳልኩ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሏል፡፡ ገላ. 5፡21» ስለዚህ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲያብብ የክፋት ሥራ የሆኑ ኃጢአቶችን በንስሐ እና በተጋድሎ በተለይም ዝሙት፣ ትዕቢት፣ ማስመሰል፣ ዓላማ ቢስነትና የጥርጥር መንፈስ የመሰሉ መራራ ስሮች በጥንቃቄ መንቀልና ማራቅ ያስፈልገናል፡፡ መራራ ሥሮችን ነቅለን የመንፈስ ፍሬያትን በሰውነታችን እናበቅል ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

                                                    

                                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘመነ ጽጌ

 
 
ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡
ጌታ ሲወለድ ሰብአ ሰገል «የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናል» እያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡» ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡
 
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡

ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡

«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13  14/

ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስድታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥው ሀገራችንን ባርከዋል።

ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን «.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..» የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡

በኋላ በዚህች ቦታ ላይ የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን  ከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፈሎስ /384-412 ዓ.ም/ ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል፡፡

በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡

በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። እነዚህን ለየሳምንቱ በሚዘጋጁት ትምህርቶች እናቀርባቸዋለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማገኘት በርካታ ክርስቲያኖች ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው /Homilies on the Gospel of Saint Mathew/ ይህንን ስደት አስመልክቶ ያስተማረውን ትምህርት ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል፡፡

ሰብአ ሰገልም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በህልም ለዮሴፍ ተገልጾ፡- ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳና ሕፃኑን ከእናቱ ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚህ ተቀመጥ አለው እርሱም  ተነስቶ  ሕፃኑና እናቱን ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን  ከግብፅ ጠራሁት የተባለው ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሄደ። ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ / ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. 1.13-18/

እዚህ ላይ ሕፃኑን በተመለከተና ሰብአ ሰገልን በተመለከተ ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምን ሰብአ ሰገልም፣ ሕፃኑም /ጌታም/ በዚያው አልቆዩም? ለምን እነርሱ እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ በድብቅ ወደ ፋርስ፣ እርሱም ከእናቱ ጋር ወደ ግብፅ ሄዱ?

ከዚህ ሌላ ምን መደረግ ነበረበት? ጌታ በሄሮድስ እጅ መውደቅና ከዚያ አለመገደል ነበረበት? እንዲህ ቢያደርግም ኖሮ ሥጋን መዋሃዱ ግልጽ አይሆንም ነበር፡፡ የክርስቶስ የማዳን ሥራም አይታመንም ነበር፡፡

ሥጋን መዋሃዱን የሚያሳዩ ይህን የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች ተደርገው፣ ሥጋን ለበሰ /ተዋሃደ/ መባሉ ተረት /ውሸት/ ነው የሚሉ ካሉ ሁሉን ነገር እንደ አምላክነቱ ብቻ ቢያደርገውማ ከእነዚህ የሚበልጡ ብዙዎች በተሳሳቱ ነበር፡፡

ሰብአ ሰገልንም በፍጥነት የላካቸው አንደኛ ለፋርስ ሰዎች መምሀራን እንዲሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታን ለማስገደል ላሰበው ሄሮድስ እየሞከረ ያለው የማይቻል ነገርን መሆኑን አስረድቶ የሄሮድስን እብደት ለማቆምና ንዴቱን አስታግሶ ከከንቱ ድካሙ እንዲያርፍ ለማድረግ ነበር፡፡

ምክንያቱም አምላካችን ጠላቶቹን በግልጽ እና በኃይል ማስገዛት ብቻ ሳይሆን በቀላል እና ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች ማሳመንም፣ ያውቅበታል፡፡

ለምሳሌ ግብጻውያንን በግልጽ /በኃይል/ ንብረታቸውን ለእስራኤል እንዲያስረክቡ ማድረግ ሲችል እርሱ ግን በጥበብ ያለ ጦርነት ይህንን እንዲያደርጉ አድርጎአቸል፡፡ ይህም አድራጎቱ ከሌሎቹ ተአምራት ባልተናነሰ ሁኔታ በጠላቶቹ ዘንድ የሚፈራ አድርጎታል፡፡

ለምሳሌ ፍልስጤማውያን ታቦተ ጽዮንን ማርከው በመውሰዳቸው በተቀጠቀጡ ጊዜ የሀገራቸውን ጠቢባን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት እንዳይሞክሩ በነገሯቸው ጊዜ ከሌሎች ተአምራት ጋር ይህንን እግዚአብሔር በሥውር የሠራውንም ሥራ አንስተውታል፡፡ በግልጽ ከተደረጉት የተለየ አድርገው አላዩትም፡፡ 1ኛ ሳሙ. 6-6

በዚህ ጊዜም የተደረገው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ደም የጠማውን ነፍሰ ገዳይ ሊያስደንቅ የሚችል ነገር ነበር፡፡ ሄሮድስ ሊያስብ የሚገባው እንዲህ ነበር፡፡ ሰብአ ሰገል እንደካዱት፣ እንደተናቀና መሳቂያ መሳለቂያ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ መደንገጥ ትንፋሹ መቆም ነበረበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ካላሻሉት /ካላስተካከሉት/ ግን እርሱን ከጥፋቱ ለመመለስ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረገ እግዚአብሔር በእርሱ ጥፋት ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ሄሮድስ ከዚህ በኋላ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያደረገው የእብደቱ ብዛት እነዚህ ሁሉ እውነተኛ ግልጽ ነገሮች እንዲያሳምኑት ስላላደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከጥፋቱ መመለስ አልቻለም፡፡ በክፋቱ ስለ ቀጠለበትም ስለ ሞኝነቱ የከፋ ቅጣት ተቀብሏል፡፡

ሕፃኑ ለምን ወደ ግብጽ ሄደ? የመጀመሪያውን ምክንያት ወንጌላዊው ራሱ በግልጽ ይነግረናል፤ «ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ» /ማቴ. 1-15/

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድርጊት ለዓለም መልካም ተስፋ ተሰብኳል፡፡ በዚያን ጊዜ በዓለም ካለው ቦታ ሁሉ በከፋ ሁኔታ ባቢሎን /ፋርስ/ እና ግብጽ በእምነተ ቢስነት /በአምላክ አልባነት/ ነበልባል ተቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ሁለቱንም እንደሚያስተካክል ምልክት ሰጥቶ ሰዎችን ማዳኑ /ስጦታዎቹ/ ለዓለሙ በሙሉ እንደሆኑ አውቀው በተስፋ እንዲጠብቁ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ወደ አንዱ /ባቢሎን፣ ፋርስ/ ሰብአ ሰገልን ላከ፣ ሌላውን /ግብጽን/ ራሱ ከእናቱ ጋር ጎበኘ፡፡

ከዚህም ሌላ በዚህ የምንማረው ሌላ ትምህርት አለ፤ ከፍ ያለ ጽናት ሊኖረን እንደሚገባ፡፡ ይህ ምን ዓይነት ነው? ክፉ ሃሳብ /ተንኮል/ እና ክፉ ድርጊት ገና በመጠቅለያ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ላይ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በልደቱ ጊዜ መጀመሪያ ክፉ ነፍሰ ገዳይ፣ ተነሳበት ከዚያም ስደት እና ሀገርን ትቶ መሄድ ተከተለ፡፡ ያለ ምንም ጥፋትና በደል ከቤቷ እንኳን ርቃ ተጉዛ የማታውቀው እናቱ ወደ አረመኔዎች /barbarians/ ሃገር ተሰደደች፡፡ አስጨናቂና አስቸጋሪ የሆነ ረጅም ጉዞ እንድታደርግ ታዘዘች፡፡ ይህንን የሰማ ሰው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽም አስጨናቂ ችግሮችና ህመሞች ቢደርሱበትና ህመሞች ቢያጋጥሙት መሸበር የለበትም፡፡

«የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለፈጸምኩ መሸለም መከበርና ታዋቂ መሆን ሲገባኝ ለምን ይህ ሆነ?» ማለትም የለበትም፤ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን እንደ ምሳሌ ወስደን ሁሉን ነገር በደስታ መቀበል አለብን፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ባሉበት ሁሉ ተቃዋሚ እንደማይጠፋ እና የመንፈሳዊ ነገሮች ሂደትም ይህ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡

ቢያንስ ይህ ነገር የሆነው በሕፃኑና በእናቱ ብቻ ላይ ሳይሆን በሰብአ ሰገልም ላይ መሆኑን እናስተውል፡፡ እነርሱም እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ ሆነው በምስጢር እንዲሸሹ ሆነዋል፡፡

ሌላም አስደናቂ ነገር ተመልከቱ፡፡ የእግዚአብሔር ሐገር፣ የተስፋ ምድር የተባለችው ፍልስጤም በጌታ ላይ የተንኮል መረብ /ሤራ/ ስትዘረጋ የኀጢአትና የጣኦት አምልኮ ሀገር የሆነችው ግብጽ ደግሞ ተቀብላ አዳነችው፡፡

ጌታችን በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው አብዛኞቹ  ነገሮች ወደፊት ሊመጡ ላላቸው ነገሮች ትንቢት ናቸው፡፡

ዮሴፍ ጌታንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ እንዲሄድ በመልአክ ታዘዘ፡፡ ግብጽ በሥፋት ጣኦት የሚመለክባት ሀገር ነበረች፡፡ ይህም በኋላ ክርስትና በአምልኮት ባዕድ ወደ ነበሩ ህዝቦች /አሕዛብ/ ዘንድ ለመውሰዷ ትንቢት /ምልክት/ነው፡፡ እመቤታችን ጌታን ይዛ ወደማታውቀው ሀገር ስትሰደድ ቤተልሄም /ይሁዳ/ ሄሮድስ ባስገደላቸው ሕፃናት በሰማዕታት ደም ተጥለቅልቃለች፤ የሄሮድስ ጭፍጨፋና ሕፃናቱን መግደሉ ወደፊት ክርስቲያኖች በአይሁድ እጅ ለሚቀበሉት ሰማዕትነት ምሳሌ ነው፡፡

መልአኩ ተገልጦ የተነጋገረው ከእመቤታችን ጋር ሳይሆን ከዮሴፍ ጋር ነበር፡፡ ምን አለው? «ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ..» የእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽነስ ሲነግረው ያለው «እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ» ነበር፡፡ አሁን ግን እጮኛህን አላለውም «የሕፃኑን እናት» አለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም እመቤታችን ጌታችንን ከወለደች እና በጌታ ልደት ጊዜ የሆኑትን ነገሮች /ኮከቡን፣ ሰብአ ሰገልን/ ካየ በኋላ ሁሉን ነገር ተረድቶ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በቂ ነገር ዓይቶ፣ ባየው ነገር ተረጋግቶ ነበር፡፡ ስለዚህ መልአኩ አሁን በግልጽ ይናገራል «ልጅህን» ወይም «እጮኛህን» አላለም፡፡ «ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ አለው» እንጂ፡፡ የስደቱንም ምክንያት አብሮ ይነግረዋል፤ «ሄርድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋልና፡፡»

ዮሴፍ ይህንን ሲሰማ ቅር አልተሰኘም፤ «ይህን ነገር ለመረዳት ይከብዳል፤ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል አላለከኝም ነበር? አሁን ደግሞ ራሱን እንኳን ማዳን አይችልምን? እኛም ከቤታችን ወጥተን ርቀን ለብዙ ጊዜ መሰደድ አለብን አሁን ያለት ነገሮች ከተሰጠው ተስፋ /ቃል/ ጋር ተቃራኒ ናቸው፡፡» አላለም ጻድቅ እና እውነተኛ አማኝ ነበርና፡፡

ምንም እንኳን መልአኩ መመለሻውን ግልጽ ሳያደርግ እስከምነግርህ ድረስ በዚያው ተቀመጥ ቢለውም ስለሚመለሱበት ጊዜ አልተጨነቀም፤ አልጠየቀምም፡፡ ዮሴፍ ፍርሃትም እንኳን አላሳየም፡፡ ሁሉንም ነገር በደሰታ ተቀበለ እንጂ፡፡

ሰውን ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር መከራንና ደስታን በሰዎች ሕይወት ላይ ያመጣል፡፡ በችግር ወይም በደስታ ብቻ አያኖርም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ችግርን /ሀዘንን/ እና ደስታን /ሃሴትን/ እያፈራረቀ ያመጣል፡፡ አሁንም ያደረገው ይህንኑ ነገር ነው፡፡ ዮሴፍ ድንግልን ጸንሳ ባያት ጊዜ ተጨነቀ፤ ተረበሸ፤ ታወከ፡፡ በዚህ መሃል ግን መልአኩ ተገልጦ ፍርሃቱን አስወገደለት፡፡ ሕፃኑን ተወልዶ ባየ ጊዜም ከፍ ያለ ደስታ ተደሰተ፡፡ ደስታው ብዙም ሳይቆይ አደጋ መጣ፤ በሰብአ ሰገል መምጣት ከተማው ተረበሸ ንጉሡም ከእብደቱና ከክፋቱ የተነሳ የተወለደውን ሕፃን ሊገድል ተነሳ፡፡ ይህ ጭንቀት ደግሞ በደስታ ተተካ ኮከቡና የሰብአ ሰገል ለጌታ መስገድ እጅግ አስደሳች ነበሩ፡፡ ከዚህ ደስታ በኋላም ጭንቀትና ፍርሃት መጣ፡፡ መልአኩ «ንጉሥ ሄሮድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋል፡፡» ብሎ ነገረው፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን በሕዝብ ፊት ተዓምራት ለማድረግ ጊዜው ገና ነውና መሰደድ አስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ገና በልጅነቱ ተአምራትን በአደባባይ /በሕዝብ ፊት/ ቢያደረግ፣ ሥጋን እንደተወሃደ አይታመንም ነበር፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉን ማድረግ ሲችል ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅጸን ያደረው፣ እንደ ሕፃናት ጡትን እየጠባ፣ በጥቂት በጥቂቱ ያደገው፣ ሥራውን እስኪጀምርም ሠላውን ዘመን በዝምታ /በስውር ተዓምራት/ ያሳለፈው፡- የተዋህዶን ነገር እንረዳ ዘንድ ነው፡፡

አይሁድ ትንቢቱን በተመለከተ ጥያቄ ቢያነሱ እና ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ስለ እኛ ነው ቢሉን ይህ የትንቢት አካሄድ /መንገድ/ ነው እንላቸዋለን፡፡ ብዙ ጊዜ ስለተወሰኑ ሰዎች የተናገረው የሚፈጸመው በሌሎች ነው፡፡ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ልጆችን ሰብስቦ በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባቸው ሲነገራቸው እንዲህ ብሎ ነበር፡-

ስምኦንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤

ሰይፎቻቸው የአመጽ መሣሪያ ናቸው፡፡

ከምክራቸው ነፍሴ አትግባ፡፡

ከጉባኤያቸውም ጋር ክብሬ አትተባበር

በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና

በገዛ ፈቃዳቸው በሬን አስነክሰዋልና፡፡

በያዕቆብ እከፍላቸዋለሁ፡፡ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ፡፡ ዘፍ. 49-7

ይህ ግን በእነርሱ አልተደረገም በልጆቻቸው እንጂ፡፡ በዘፍ. 9-25 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘውም ኖህ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «ከነአን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን» ይህ የተፈጸመው በከንአን ሳይሆን በእርሱ ዘሮች ነው፡፡

ይህ መቼ እና እንዴት እንደሆነ በመጽሐፈ ኢያሱ እና በመጽሐፈ ዜና መዋዕል፤ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንዲህም ሆነ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቆላውም በታላቁ ባሕር ዳርና ሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ኬጢያዊ፣ አሞራዊም፣ ከነአናዊም፣ ኢያቡሳዊም፣ ይህን በሰሙ ጊዜ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ ወጡ፡፡

በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠው ሥፍራ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው፡፡ /ኢያ. 9-1-27/

1ኛ ዜና.8-7 ሰሎሞንም ኬጤያውያንንም፣ አምራውያንንም፣ ፌርዜያውያንንም ኢያቡሳውያንንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ… ገባሮች አድርጎ መለመላቸው፡፡

ይስሐቅ «ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፡፡ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ»፡፡ ብሎ ያዕቆብን የመረቀው ምርቃት የተፈፀመው በእርሱ ሳይሆን በልጆቹ ነው፡፡ ዘፍ. 27-19

ስለዚህ እርሱ ባይወለድ ኖሮ፣ ትንቢቱ ፍጻሜውን አያገኝም ነበር፡፡ ወንጌላዊውም ያለውን አስተውሉ፡- «ይፈፀም ዘንድ፡፡» ይህም እርሱ ባይመጣ አይፈፀምም ነበር ማለት ነው፡፡

በዚህኛውም ጊዜ የተደረገው /የሆነው/ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ ለእስራኤል የተነገረው ነገር በኋላ በጌታ ተፈጽሟል፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔር እውነተኛ ልጅ ሊባል የሚችለው የትኛው ነው? ጥጃን ያመለከና ለቤልሆር ልጆቹን የሰዋ? ወይስ በባሕሪው ልጅ የሆነና የወለደው አባቱ «የምወደው ልጄ» ብሎ የሚያመሰግነው?

ከዚህም ሌላ /ግብጽ መሄዳቸው/ እመቤታችን ከፍ ያለ ክብር ያላት እንደሆነች እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ህዝቡ የሚመኩበትን ከእግዚአብሔር ያገኙትን ስጦታ እርሷም ለራሷ አግኝታለችና፡፡ ማለትም፣ እነርሱ ከግብጽ በመውጣታቸው /ከስደት በመመለሳቸው/ ይመኩና ይኮሩ ነበር፡፡ ይህንኑ የሚመኩበትን ነገር ለእመቤታችንም ስጣት፡፡

ያዕቆብና ህዝበ እስራኤል ወደ ግብጽ በመሄዳቸውና ከዚያም በመመለሳቸው የእርሱን ግብጽ ሄዶ መመለስ ምሳሌ እየፈጸሙ ነበር፡፡ እነርሱ ግብጽ የሄዱት በረሃብ /በድርቅ/ የመጣ መሞትን ለማምለጥ ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በተንኮል መሞትን ለማምለጥ ነው፡፡

እነሱ /ህዝበ እስራኤል/ ግብጽ መሄዳቸው ከረሃቡ /ከድርቁ/ ተርፈዋል፡፡ እርሱ ግን እዚያ በመሄዱ በኪዳተ እግሩ /በእግሩ በመርገጥ/ ምድሪቱን ቀድሷታል፡፡

በዚህ ራሱን ዝቅ በማድረጉ መሀልም ግን የአምላክነቱ ማሳያዎች /ምልክቶች/ ተገልጸዋል፡፡ ሰብአ ሰገልና እርሱን ለማምለክ በኮከብ እየተመሩ መጡ፤ አውግስጦስ ቄሳርም የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ በማወጅ ልደቱ ቤተልሔም እንዲሆን አገለገለ፤ በግብጽም በርካታ ተዓምራት ተደርገዋል፡፡

አሁን ወደ ግብጽ ብንሄድ በረሃው ከማንኛውም የአትክልት ስፍራ የተሻለ ሥፍራ ያማረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላእክት አምሳል ያመሰግኑበታል የሰማእታት ብሔር፣ የደናግል በአት፣ የሰይጣን አገዛዝ ድል የተመታበትና የክርስቶስ መንግስት ደምቆ የሚያበራበት ቦታ ነው፡፡

በትምህርተ ሃይማኖታቸው /doctrine/ ካላቸው ትክክለኛነት በተጨማሪ፣ በህይወታቸውም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡ ያላቸውን ሁሉ ትተው ራሳቸውን ከዓለም ካገለሉና ለዓለሙ በሙሉ ከተሰቀሉ በኋላ በድጋሚ የተቸገሩትን ይረዱ ዘንድ የጉልበት ሥራ ይሠራሉ፡፡

ስለሚጾሙና ብዙ ጊዜ በተመስጦ ስለሚያሳልፉ፤ ቀናቱን /ጊዜን/ ሥራ በመፍታት /ቦዝነው/ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለው አያስቡም፡፡ ስለዚህም ቀኑን በጸሎት ሌሊቱንም በዝማሬና በትጋት ያሳልፉታል፡፡ ከዚህም የሐዋርያውን አሰር ይከተላሉ፡፡

«ከማንም ብር ወይም ወርቅ አላስፈለገኝም እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲህ እየደከማችሁ ድውያንን ልትረዱና፣ «እርሱ ራሱ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጽዕ ነው» የሚለው የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ አሳየኋችሁ፤» ሐዋ. 10-34 ይህንን የሐዋርያውን ቃል ሲሰሙ በበረሃ ያሉት የግብጽ መነኮሳት እንዲህ ይላሉ፡- «እርሱ /ሐዋርያው/ በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግባቸው ብዙዎች እየጠበቁት የእጅ ሥራ ይሠራ ከነበረ፣ መኖሪያችንን በገዳም፣ በዱር፣ በበረሃ ያደረግን፣ የከተማ ጾር /ፈተና/ የቀረልን እኛማ ከጸሎታችንና ከተመስጦአችን የተረፈንን ጊዜ ለተመሳሳይ ሥራ ልናውለው ምን ያህል ይገባናል)!»

እኛም ራሳችንን እንመርምር ሀብታምም ድሃም የሆንን እነዚህ መነኮሳት ከሰውነት /እጅና፣ እግር/ በስተቀር ምንም የሌላቸው ሲሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት እንዲህ ከወጡና ከወረዱ የተረፈንን እንኳን ለእነዚህ ሰዎች /ችግረኞች፣ ድውያን/ የማንሰጥ እኛ ለዚህ አድራጎታችን ምን ምክንያት፣ ምን ማስተባበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡

ታላቁን አባት ቅዱስ እንጦንስን እናስታውስ፡፡ ይህ ሰው የተወለደው ፈርኦን በተወለደበት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት እነርሱን አልመሰለም፡፡ የነበረው ሰማያዊ ራእይ ስለጠበቀው እግዚአብሔር በሚወደው መልኩ ህይወቱን አሳልፏል፡፡ ከጽድቁ የተነሳ ከእርሱ በኋላ የሚመጡ መነኮሳት ምን ዓይነት እንደሚሆኑ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡

ጻድቁ እንጦንስን ታሪክ ማንበብና ማድነቅ ብቻ ሳይሆን በሕይወት መተርጎምም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አለመበርታት ቦታን፣ አለመማርን፣ የአባቶችን መርገም… ምክንያት አናድርግ፡፡

ነገሮችን በማስተዋል ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለእኛ መሰናክል መሆን አይችሉም፡፡ አብርሃም ጣኦት አምላኪ አባት ነበረው /ኢያ. 24-2/ ነገር ግን የአባቱን ክፋት አልወረሰም፣ የሕዝቅኤልም አባት አካዝ ኀጢአተኛ ሰው ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ ነበር፡፡

ዮሴፍም በግብጽ ሆኖ ራሱን በትምህርት አስጊጧል፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም በባቢሎን ቤተመንግስት ሆነው ታላቅ ራስን መግዛት አሳይተውናል፡፡ ሙሴም በግብጽ ነበር፣ ቅዱስ ጳውሎስም በዓለም ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ያሉበት ቦታና ሁኔታ ከጽድቅ ጉዞአቸው አላደናቀፋቸውም፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ክፍል ሦስት

በልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት

ይህ ዘርፍ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖ ሚያዊ ሥራዎች የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም ለቅዱሳት መካናት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ተማሪዎች፣ ለምእመናን ብሎም ለጠቅላላው ኅብረተሰብ አቅም በፈቀደ መጠን ዘላቂ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ረገድ በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በዕውቀት እንዲሁም በጉልበት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ተማሪዎች ድጎማ፣ ለገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ጊዜያዊ ርዳታ፣ የዘላቂ ገቢ ቋሚ የልማት ፕሮጀክት ቀረፃና ትግበራ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የማድረግ፣ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በቀጣይም የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ዙርያ ለመሥራት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በትምህርት መስክ በአዲስ አበባ ሦስት ቦታዎች ላይ፣ በአዋሳ፣ በደብረ ብርሃንና፣ በባሕርዳር፣ ሃገረ ማርያም ወዘተ የራሱን መደበኛ ት/ቤት በመክፈት ሕፃናት በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀታቸው ዳብረው እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሀ. አብነት ት/ቤቶችን ከመደገፍ አንጻር

አብነት ትምህርት ቤት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ታሪክና ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ የሚቻልበት ብቸኛ መድረክ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን፣ ትውፊቷንና ትምህርቷን በየዘመኑ የሚቀበል ትውልድ እንዳታጣ የአብነት ት/ቤቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የአብነት ት/ቤቶች በተለያየ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት የከፋ አደጋ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ጥንታውያን የሆኑት የአብነት ት/ቤቶች እና ሊቃውንቶቻቸው ቀደም ሲል የነበረው የመሬት ባለቤትነታቸውን በማጣታቸው እና የአካባቢው ምእመንም ቀደም ሲል ያደርግላቸው የነበረውን ድጋፍ በኑሮው ጫና ምክንያት በማቆሙ፣ መምህራኑ ወንበራቸውን አጥፈው ለመሰደድ፤ ተማሪዎቻቸውም ለመበታተን ተዳርገዋል፡፡ የነዚህ ለመላው አብያተ ክርስቲያናት የአገልጋይ ምንጭ የሆኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ምክንያት፤ በደቡብ በምሥራቅ እና በምዕራቡ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የካህናት እጦት መንስኤ በመሆን አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ ማኅበሩ ይህንን ችግር በመረዳት፤ የአብነት ት/ቤቶች መምህራንን እና ተማሪዎችን በመደጎም፣ ጥንታውያን የሆኑት የቀድሞ ይዞታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እና በደቡብ፣ በምሥራቅ እና በምዕ ራቡ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ የአካባቢውን ልጆች በማስተማር አገልጋይ ካህናትን በማፍራት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ድጎማው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር በወር ከአንድ መቶ እስከ ሦስት መቶ ሃምሳ ብር፣ ለስልሳ ሦስት መምህራን ድጎማ እንዲሁም አራት መቶ ሃያ ስምንት ለሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ በወር በሁለት መንገድ የሚፈጸም ነው፡፡ የመጀመሪያው ለመምህራኑና ለተማሪዎቹ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጻሕፍትና ከሠላሳ እስከ መቶ ሃያ ብር ይደጉማል፡፡ በዚህም ለአብነት ደመወዝ /ለመምህራኑ/ ድጎማ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአብነት ት/ቤቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን መቅረፅና ተግባራዊ ማድረግና ለመምህራን እና ተማሪዎች ድጎማ ያደርጋል፡፡ በዓመት እስከ ዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር፣ እንዲሁም የገንዘብ ድጎማ ለማይደረግላቸው አንዳንድ የአብነት ት/ቤቶች በጊዜያዊነት ለልብስ፣ ለምግብ፣ ለመጻሕፍት እና ሌሎች ወጪዎች እስከ ስልሳ ሺሕ ብር በዓመት ያወጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተመረጡ የአብ ነት ት/ቤቶች ተማሪዎቹ ከአብነት ትምህርቱ ጎን ለጎን ትምህርተ ሃይማኖት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የስ ብከት ዘዴ እንዲማሩ በማድረግ ለተሻለ አገልግሎት አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ለ. ገዳማትና አድባራትን ከመደገፍ አንጻር

ማኅበሩ ከአብነት ት/ቤቶች በተጨማሪ ችግር ላለባቸው አድባራትና ገዳማት ጊዜያዊ ርዳታ በማድረግ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን በማመቻቸት የገዳማቱንና አድባራቱን ችግር በመጠኑም ቢሆን እየፈታ ይገኛል፡፡ በጊዜያዊ ርዳታ የተለያዩ የመባዕ /ጧፍ፣ ነዕጣን፣ ዘቢብና ሻማ/፣ የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት /ልብሰ ተክህኖ፣ መጎናጸፊያ ወዘተ/፣ የዘወትር ልብስ፣ የምግብ እህልና ሌሎችን ርዳታዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዓመት በአማካይ ለሠላሳ ቅዱሳት መካናት የልብሰ ተክህኖ ድጋፍ፣ ለሁለት መቶ ቅዱሳት መካናት የመባዕ፣  እንዲሁም የምግብ፣ የአልባሳት እና ለሌሎች ድጋፎች በዓመት እስከ ዘጠና ሺሕ ብር ወጪ ያደርግላቸውል፡፡ በ1995 ዓ.ም በሁለት የአብነት መምህራን የተጀ መረው ድጎማ ዛሬ ቁጥሩን ከፍ በማድረግ ስልሳ ለሚሆኑ ለተመረጡ አብነት ት/ቤቶች ድጎማ ያደርጋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ገዳማትና አድባራት ያሉባቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ማኅበሩ የተለያዩ የልማትና ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችን አጥንቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ቅዱሳት መካናቱ ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል መሠረት በማድረግ የአነስተኛ መስኖና አትክልት ልማት፣ የወተት ላም ርባታ፣ ዘመናዊ ንብ ርባታ፣ የከብት ማድለብ፣ ወፍጮ ቤት፣ ሽመና፣ የጥበበ ዕድ ፕሮጀክቶች የሚከራይ ቤት ግንባታ፣ የአብነት ተማሪዎች መኖሪያ ቤት እና የመሳሰሉትን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ቅዱሳት መካናቱን ወደ ቀደመው የልማት አውታርነታቸው ለመመለስ፣ የአካባቢውን ኅብረተሰብ የምርቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማ ድረግ በተጨማሪ ለአካባቢው አርሶ አደሮችም ሠርቶ ማሳያ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡

እስከ 2000 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ከአንድ መቶ ሃያ በላይ የተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል እስከ 2000 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በጠቅላላው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የፈጁ ሃያ ሦስት የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ገዳማቱ ተረክበዋቸው ሥራ ጀምረዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጁ ሃያ ስድስት ከአለፈው የቀጠሉ ፕሮጀክቶች እና ሰባት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር በጎ አድራጊዎች የገንዘብ እርዳታ ማሰባሰብ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡  የእነዚህ ፕሮጀክቶች የእያንዳንዳቸው ጠቅላላ ወጪ ከ35,000 እስከ 350,000 ብር የሚደርስ ሲሆን እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነት ሊለያይ ይችላል፡፡ በዚህም የአምስት ዓመት ጉዞ በአብነት ትምህርቱ፣ በገዳማትና አድባ ራት ድጋፍ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ በዘላቂና ጊዜያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ወጪ ተደርጓል፡፡

ሐ. ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ

ማኅበሩ በተለያዩ ሰው ሠራሽም ሆኑ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ችግር ከደረሰባቸው ገዳማትና አድባራት ባሻገር በችግር ውስጥ ያሉ ምእመናንንም በመታደግ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ በመስከረምና ጥቅምት 1999 ዓ.ም በአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ ጉዳት ለደረሰባቸው የጅማ፣ ኢሉባቦር እና የምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ምእመናንን እና አባላትን በማስተባበር የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሠርቷል፡፡ በዚህም ለተፈናቀሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ርዳታ ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ በጠቅላላው ለዘጠኝ መቶ ሃያ ስድስት አባወራ አምስት መቶ አሥራ አንድ ኩንታል ገዝቶ አከፋፍሏል፡፡ በኢሊባቦር ለተቃጠሉ ቤቶችም መልሶ ግንባታ ለሃምሳ አንድ አባወራ ለእያንዳንዳቸው አርባ ቆርቆሮና ሚስማር ሰጥቷል፡፡ በኢሊባቡር እና በምዕራብ ወለጋ ለተቃጠሉ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ማሠሪያ ሁለት መቶ ሃምሳ ቆርቆሮ፣ ሦስት መቶ ኩንታል ሲሚንቶ እና አንድ መቶ ሺሕ ብር አስረክቧል፡፡ በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር ለአሥር አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ አልባሳትና አንድ መቶ ዘጠና ሁለት መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቶ ያከፋፈለ ሲሆን ለአምስት መምህራንና ለሁለት አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ዲያቆናት የአንድ ዓመት ደመወዝ መድቧል፡፡ የሁለት መምህራንን ቅጥርም አካሒዷል፡፡ በጅማ አካባቢ ያሉትን አብያተ ክርስ ቲያናትና ምእመናን በደረሰው ጉዳት ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ለመርዳት ሁለት የኤሌክትሪክ እና ሁለት በናፍጣ የሚሠሩ ወፍጮዎችን ገዝቶ ያስተከለ ሲሆን እንዲሁም ስድስት ክፍል ያለው መጸዳጃ ቤት በማሠራት ለገዳሙ አስረክቧል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ላሉ ሠላሳ ሁለት ካህናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በ2000 ዓ.ም ደብረ ወገግ አሰቦት ገዳም ላይ ለደረሰው የቃጠሎ አደጋ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለገዳሙ መናንያንም በየወሩ ለቀለብ የሚሆን ስምንት ሺሕ ብር ድጎማ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ሌላም በገዳሙ የበቀሉ አላስፈላጊ እፅዋትን ለማስወገጃ ከስልሳ ሺሕ ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ በያዝነው በ2001 ዓ.ም «አንድ መጽሐፍ ይለግሱ» የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከአባላትና ከምእመናን ከሶስት ሺሕ አምስት መቶ በላይ መጻሕፍትን በማሰባሰብ ለተለያዩ የአብነት ት/ቤቶችና ሰንበት ት/ቤቶች የማሠራጨት ሥራ ተሠርቷል፡፡

መ. ኤች አይ ቪ/ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ

ማኅበሩ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድም ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እያስጨበጠ ይገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲ ያን ትምህርትን መሠረት ያደረጉ የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከስዊድን የሕፃናት አድን ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአክሽን ኤይድ እና ቪ.ኤስ.ኦ. ከተባሉ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችንም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከተሠሩትም ሥራዎች መካከል ተከታታይ ጽሑፎች በ«ስምዐ ጽድቅ» ጋዜጣ እና «ሐመር» መጽሔት በማውጣት፣ አርባ የሚሆኑ ፀረ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ክበባትን ማቋቋም፣ ለዘጠኝ መቶ ዘጠና ሦስት ካህናትና ካውንስለሮች ሥልጠና በመስጠት፣ ለስድስት መቶ አምስት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የአቻ ለአቻ የምክር አገልግሎት በመስጠት፣ ውይይቶችና በሃያ አምስት አህጉረ ስብከት ላይ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናቶች ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በ2001 ዓ.ም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከብሔራዊ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽ/ቤት በተገኘ ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ በሆነ ገንዘብ ጠበልን ከፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ጋር አስማምቶ መጠቀም ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በዚህ ዘርፍ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን ብሎም ለጠቅላላው ኅብረተሰብ አቅም በፈቀደ መጠን በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በዕውቀት እንዲሁም በጉልበት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሠ. የሙያ አገልግሎት

የማኅበሩ አባላት በገቡት ቃል መሠረት የተለያየ ሙያ ያላቸው አባላት ማኅበሩንና ቤተ ክርስቲያንን በሙያቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በገንዘቸው፣ በጉልበታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በምህንድስና እና ጥበበ ዕድ ክፍል ባለሙያዎች ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የዲዛይን፣ የቅየሳ፣ የሱፐርቪዥን ወዘተ ሥራ በመሥራት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለቤተ ክርስቲያን እያዳኑ እና የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ከ1995 ዓ.ም ወዲህ ከተሠሩትና በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ለስምንት የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ዲዛይንና የዋጋ ዝርዝር፣ ለሰባ አምስት አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ዲዛይን፣ ከሠላሳ በላይ ለሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ዲዛይን፤ እንዲሁም ከሠላሳ በላይ ለተለያዩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ዲዛይኖችን ሠርተው አስረክበዋል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ልታወጣ የነበረውን ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ እንዳታወጣና ወጭ እንድትቆጥብ አድርጓታል፡፡ የሕግ ባለሙያዎቹም የሕግ ምክር አገልግሎት ለሚፈልጉ የቤተ ክርስቲያን አካላት የምክር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንዲ ሁም የተለያዩ የሒሳብና የአስተዳደር ማንዋሎች ተሠርተዋል፡፡ ለቱሪዝም ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ የሚረዳ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አስረክቧል፡፡ «ቅርስና ቱሪዝም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን» በሚል ርዕስ ከቅርስና ቱሪዝም ጋር ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት ባሉበት አቅርቦ ውይይቶች እንዲካሔዱ አድርጓል፡፡ በማኅበራዊና ምጣኔ ሀብት ክፍል ለአብነት ትምህርት ተማሪዎችና ገዳማዊያን ያሉባቸውን የጤና ችግሮች ላይ መፍትሔና ቅድመ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የመገምገምና የማበልጸግ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ማኅበሩ አገልግሎቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥር በየቦታው በተበታተነ ሁኔታ የሚከራያቸው ቤቶች ለቢሮ አገልግ ሎት አስቸጋሪ በመሆናቸው ቀደም ሲል በጽሕፈት ቤትነት ተከራይቶ ይጠቀምበት የነበረውነ ቦታ በአባላት ልዩ መዋጮና በበጎ አድራጊዎች ርዳታ በ1.3 ሚሊዮን ብር በመግዛት የሕንፃ ግንባታው ሥራ ተጀምሯል፡፡ እስከ ሚያዝያ 2001 ዓ.ም መጨረሻም የመሠረቱንና እስከ አራተኛው ፎቅ ወለል ያለውን ሥራ አጠናቆአል፡፡

ረ. አቡነ ጎርጎርዮስ አፀደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት

ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ማንነት የሚያውቁና በግብረ ገብ ትምህርት የታነፁ ሕፃናት ቁጥር  ትንሽ መሆኑን በመገንዘብ ትምህርት ቤት ከፍቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ ሰባት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ ሦስቱ በአዲስ አበባ፣ አንድ በአዋሳ፣ አንድ በባሕርዳር፣ አንድ በሀገረ ማርያም እና አንድ በደብረ ብርሃን ይገኛሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ2001 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሰባቱ ቅርንጫፎች ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ተማሪዎች በላይ ተቀብሎ ከአፀደ ሕፃናት እስከ አምስተኛ ክፍል እያስተማረ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከሃያ ለሚበልጡ ሕፃናትም የነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል፡፡

ሰ. የልማት ተቋማት

ማኅበሩ «ሐመር» መጽሔት፤ «ስምዐ ጽድቅ» ጋዜጣ፤ መጻሕፍት እና ሌሎችም የኅትመት ውጤቶቹን አሳትሞ በማሠራጨት እንዲሁም ሌሎች የማኅበሩን አገልግሎት ለመደገፍ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን የሚያከናውን በልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ የሚመሩ የራሱ የልማት ተቋማት አሉት፡፡ የልማት ተቋማቱ በ18 ማዕከላት /አዲስ አበባን ጨምሮ/ የሚገኙ የማኅበሩን የኅትመት ውጤቶችና ንዋያተ ቅድሳት ማቅረቢያዎች ሲኖሩት በዓይነታቸውም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ የካህናት አልባሳት፣ የሞካሽ ሥራ፣ የቆብ እና ጃንጥላ ሥራ ኢንዱስትሪ፣ ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች /በቁጥር ሦስት/፣ ምግብ ቤት /በቁጥር ሁለት/፣ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ማከፋፈያዎች /በቁጥር ዐሥራ ዘጠኝ/፣ የመብዐ /የተቀመመ ዕጣን፣ የተለቀመ ነዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ ሻማ/ ማምረቻ ኢንዱስትሪን እንዲሁም የትምህርት ማዕከል በሥሩ ያቅፋል፡፡ ከእነዚህ ገቢ ማስገኛ ተቋማት የሚገኘው ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለስብከተ ወንጌል ማጠናከሪያ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡

 ማኅበረ ቅዱሳን ሥርዐተ ቤተክርስቲያን ከማስጠበቅና ቤተክርስቲያንን ከአሕዛብና ከመናፍቃን ከመከላከል አንጻር ምን ሥራ ሠራ?

ማኅበረ ቅዱሳን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው የሥራ መመሪያ መሠረት ካከናወናቸው ሥራዎች በተጨማሪ የቅሰጣ ዓላማቸውን በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን በውስጥም በውጪም ከሚንቀሳቀሱ የመናፍቃንና ቤተክርስቲያንን እናድሳለን ብለው እስከተነሱት እኩዮች ሥራቸውን እየተከታተለ በቅዱስ ሲኖዶስና በምእመናን በመረጃ ላይ የተደገፈ ሪፖርት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አሁንም እያቀረበ ነው፡፡ ወደፊትም ያቀርባል፡፡ ከዚህም ሌላ በእስልምና ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አክራሪዎች በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሱ ያሉትን የጥፋት ዘመቻ ለማስታገስና ምእመናን እንዲረጋጉ ለማድረግ አክራሪዎቹ በቤተክርስቲያን ላይ ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ያለው መልስ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን እስልምናን በተመ ለከተ የሠራቸው ሥራዎችን በሚከተ ለው መንገድ ማጠቃለል ይቻላል፡፡

1. ከመጀመሪያው ጀምሮ ምእመናን አክራሪውንና ነባሩን ሰላማዊውን እስልምና ነጥለው እንዲመለከቱ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡

2.. ለሚያነሷቸው ታሪካዊና ዶግማዊ ጥያቄዎች በተጻፉት ጽሑፎች መጠንና ቁጥር ጋር ሊነጻጸር ቀርቶ እዚህ ግባ   የሚባል ባይሆንም መጠነኛ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡

3. ተቻችሎና ተከባብሮ ስለመኖር ከየትኛውም አካል በፊት እና በከፍተኛ ሽፋን ሠርቷል፡፡

4. ስለ አክራሪ እስልምና እና ስለ ትንኮሳው እጅግ አነሥተኛ እና ክስተት ተኰር የሆኑ መረጃዎችን በመስጠት ችግሩ ሲያጋጥም ለመንግሥት ማመልከት እንደሚገባ አቅጣጫ ለማሳየት ሞክሯል፡፡

 የፕሮቴስታንትና የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ በማጋለጥ ረገድ

ከላይ ለመግለጽ እንደሞርነው ማኅበረ ቅዱሳን የፕሮቴስታንትና የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ በማጋለጥ ረገድ ቤተክርስቲያንንና ምእመናን እንዲጠነቀቁ እንዲሁም የመናፍቃኑን ማንነት እንዲያውቁ በማድረጉ ረገድ በጣም ብዙ ሥራዎች ሠርቷል፤ እየሠራም ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ «የዘመቻ ፊሊጶስን» የመናፍቃን ባለብዙ በጀት ሰፊ እንቅስቃሴ ቀድሞ መረጃ ለቤተክርስቲያንና ለምእመናን በመስጠት ሴራው እንዲከሽፍ ምእመናንም እንዲጠበቁ አድርጓል፡፡ በዚህም የመናፍቃኑ ሴራ በታሰበበት ሁኔታ ሳይሔድ ተኮላሽቷል፡፡

ሌላው እግራቸውን በቤተክርስቲያን ታዛ ልባቸውን በመናፍቃኑ አዳራሽ አድርገው በቤተክርስቲያን ውስጥ በመሽሎክሎክ የሚሠሩ ተሐድሶ መናፍቃንን ማንነት መረጃ በማቅረብና በማጋለጥ ከድብቅ ዓላማቸው እንዲገቱና እንዲወገዙ አድርጓል፡፡ በዚህ መረጃም ምእመናን ማንነታቸውን እንዲለዩና እንዲጠነቀቁም ተደርጓል፡፡ /በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በገሃድ በቤተክርስቲያኒቱ ሰርገው በመግባትና ለተልዕኮ ባስቀመጧቸው የውስጥ ሰዎች አማካኝነት ተጠናክረው እየሠሩ ነው፡፡ የነዚህንም ማንነት መረጃዎቻችንን አጠናክረን ስንጨርስ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለምእመናን የምናሳውቅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡/

በተጨማሪም ላይችሉት የተቀበሉትን የምንኩስና ሕይወት ትተው በመናፍቃኑ አዳራሽ በድብቅ ጉባኤ ያደረጉትን ግለሰቦች ማንነት በማጋለጥ ለምእመናንና ለቤተክርስቲያን አባቶች ለማቅረብ የተደረገውና መናፍቃኑ የቤተክርስቲያንን የዋሀንን ለማሳሳት አስመስለው ከሚያሳትሟቸው የሕትመት ውጤቶችና የድምፅ መልእክቶች ምንነትና ማንነት በማጋለጥ ማኅበረ ቅዱሳን መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል፤ አሁንም ወደፊትም ይሰጣል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በዐለት ላይ የተመሠረተ ማኅበር ነውና ቤተክርስቲያን የሰጠችውን ሓላፊነት በብቃት ይወጣል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆ በሰጠው መመሪያና ደንብ መሠረት ማኅበሩ በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ለውጥ ያመጣ ሥራ ሠርቶ አሳይቷል፡፡ በማሳየት ላይም ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊትም ያሳያል፡፡ ነገር ግን በውስጥ ያሉ ሥራቸው ያልታወቀባቸው የመሰላቸው የመናፍቃኑ ዐርበኞች ማኅበሩን ሳያውቁት አልያም ለማወቅ ባለመፈለግ ጥቅመኛ አድረገው የሚያስወሩት አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ሐቅ መሆኑን ሊረዱት ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ እኩያን የቤተክርስቲያን ጠላቶች ማኅበረ ቅዱሳን ባሉት አባላትና በበጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ በጉልበት በዕውቀትና በገንዘብ ቤተ ክርስቲያን ያለባትን ክፍተት እያጠና ይሞላል እንጂ ከቤተክርስቲያን ዜሮ አምስት ሣንቲም በጀት እንደ ማይመደብለት እያወቁ አለማወቃቸው ነው፡፡ በጀት ከመምሪያቸው በመመደብ ማኅበሩን ያንቀሳቀሱት ይመስል ቤተክርስቲያን ይሠሩልኛል ብላ ያስቀመጠቻቸው አንዳንድ በሓላፊነት ቦታ ላይ ያሉ የመናፍቃኑ ተላላኪዎች ግን ማኅበሩ ሒሳቡን ኦዲት እንደማያደርግና እንደማያስደርግ ጊዜያዊ ትርፍ የሚያገኙ መስሏቸው አሉባልታ በመንዛት ማኅበሩን ያልሆነ ስም ለማሰጠት ሲጣጣሩ እየተሰማና እየታየን ነው፡፡ እውነቱ ግን ይኼ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ሲኖዶሱ ባጸደቀለት ግልጽ መመሪያን መሠረት በሚያገለግሉ ባለሙያ አባላቶቹ በየጊዜው ሒሳቡን እያሰላና እያስመረመረ ነው ሥራውን በጥራት እየሠራ የሚገኘው፡፡ ይኼንን አሠራር ለማወቅ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል ሁሉ ማኅበሩን ቀርቦ ማየት፤ በማኅበሩም በተለያዩ አህጉረ ስብከት የተሠሩትን ሥራዎች መመርመር ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አሠራሩ ግልጽ አገልግሎቱም የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ የማኅበሩን አገልግሎት ለማሳጣት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚለፍፉት አንዳንድ የመምሪያ ሓላፊዎች ባልሆነ ነገር ላይ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ከሚያባክኑ ይልቅ ቤተክርስቲያኒቱ የመደበችላቸውን በጀት በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ምክንያት በየጊዜው በየጠቅላላ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ላይ በሪፖርት ላይ ከመወቀስ ቢድኑ መልካም ይሆን ነበር፡፡

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ስለ ማኅበሩ አሠራር ብዙ ማለት ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ምእመናን ከአሳሳቾች ትጠበቁ ዘንድ ስለማኅበሩ አገልግሎት ከብዙ በጥቂቱ ይኽን እውነታ እንድታውቁ እንወዳለን፡፡

                                                           ወስብሐት ለእግዚአብሔር