«ማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም ግልጽ አሠራር አለው» ክፍል ሁለት

ስምዐ ጽድቅ፦ አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳን የተወሰነ ብሔር ስብስብ ነው የሚል አስተያየት አላቸው፤ ማኅበሩ ለዚህ ዓይነት አስተያየት የሚሰጠው መልስ ምንድነው?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡-  በመሠረቱ ማኅበረ ቅዱሳን የክርስቲያኖች የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ የክርስቲያኖች አገልግሎት ደግሞ «ሑሩ ወመሐሩ፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሒዱና አስተምሩ» ማር.16÷15 በሚለው የክርስቶስ ቃል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አገልግሎቱ ለሀገርም፣ ለአህጉርም ብቻ አይደለም ለዓለም ሁሉ ነው፡፡ ስለዚህ ለማገልገልም ለመገልገልም በቋንቋ ወይም በቀለም ወይም በጾታ… ላይ የተመሠረተ የወገንተኛነት አካሔድ ከሃይማኖታችን መሠረታዊ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበራችን ማገልገልም መገልገልም የሚፈልጉ የትኞቹንም  ወገኖች ከልብና በእውነት የማገልገል ፍላጎት አለው፡፡ ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገሮች የመጡ ወንድሞቻችንን ለጥ ምቀት እንዳበቃን ሁሉ ከአውሮ­ ከአሜሪካ  የመጡና በዚያውም ያሉ በቋንቋና በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎችን ሁሉ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና መድኃኒትነት አምነው ለጥምቀት  በቅተዋል፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ እጅግ ሊታሰብ በማይችል ጠባብነት ታጥሮ የአንድ የተወሰነ ወገን ስብስብ ሆኖ የሚሠራ ነው የሚለው ሐሜት ካለማወቅ ወይም ደግሞ ሌላ ዓላማ ካለው ወገን የሚመጣ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ማኅበሩ ከተለያዩ ብሔረሰብ ለተውጣጡ ምእመናን ሥልጠና በመስጠት በተለያዩ ቋንቋዎች ወንጌል ለሁሉም እንዲደረስ በትምህርትና ሐዋርያ ዋና ክፍሉ አማካኝነት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ አባላቱም ዕድሉን አግኝተው ወደ ከፍተኛ ተቋማት በመግባት በማኅበሩ አገልግሎት የታቀፉ ሁሉ ወይም የማኅበሩን አገልግሎት ተረድተው አባል ለመሆን ፈቃደኛ ሆነው የቀረቡ ሁሉ ናቸው፡፡ የአባልነት መመዘኛም የቤተክርስቲያን ልጅ በመሆን የሰበካ ጉባኤ ወይም ሰንበት ት/ቤት አባል መሆን ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የ­ለቲካ አቋምን በተመለከተስ?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእኛ ማኅበር ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ እንደ ተቋም የሚሰጠውም አገልግሎት ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ለየትኛውም የፖለቲካ ዓይነትና አደረጃጀት የሚያግዝ /የሚሠራ/ እንዲሆን መቼም ቢሆን ፍላጐቱ የለንም፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አምስት እንደተቀመጠው «ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አይኖረውም»  ይላል፡፡ የዚህን አንቀጽ ይዘት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በማኅበሩ ያሉ የተወሰኑ አካላት በሓላፊነት ላይ እያሉ የማንኛውም የፖለቲካ አባል እንዳይሆኑ በ1998 ዓ.ም የሥራ አመራር ጉባኤያችን ወስኗል፡፡ በውሳኔውም መሠረት የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የማኅበሩ መደበኛ መምህራን፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ጽ/ቤት አባላት፣ የኦዲትና ኤንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የማዕከላት ሰብሳቢዎች በሓላፊነት ላይ ያሉ መደበኛ አገልጋዮች የማንኛውም የፖለቲካ ­ፓርቲ አባል አይሆኑም፡፡

ይህ ማለት ግን ­ለፖለቲከኞች በማኅበሩ የማገልገል ዕድል አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ዓላማቸው ማኅበሩን መጠቀም ግን አይችሉም፡፡ ስለዚህ የትኛውንም የማኅበሩን አባል በግሉ የ«ሀ» ወይም የ«ለ» ­ፓርቲ ደጋፊ፣ አባል ወይም አመራር እንዲሆን ወይም እዳይሆን ምንም ዓይነት ተቋማዊ ተጽዕኖ በማኅበሩ የሚፈጠርበት ዕድል የለም፡፡ ይህ ግን ሀገርን በመገንባት ረገድ ለአጠቃላዩ ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው ልማታዊ ተግባራትን የማከናውን ዓላማና እንቅስቃሴ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ያላት የሀገራዊ ልማት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ክርስቲያን ምሁራንና ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ ይሳተፋሉ፡፡ የልማት ተሳትፎአቸው ለሀገርና ለትውልድ እንዲጠቅም፣ ቤተክርስቲያንም ያላትን ድርሻ እድትወጣ በማሰብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ልማታዊ ተግባሮቻችን ደግሞ በቀጥታ የቤተክርስቲያናችንን ጥቅም የሚያስጠብቁ በመሆናቸው እንቅስቃሴያችን ለሌላ ትርጉም በሚጋለጥ መልኩ የሚደረግ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡  

በእርግጥ እንደተባለው በሀገር ውስጥም በውጪም በ­ፖለቲካ ወገንተኝነት ማኅበሩን ለማማት የሚፈለጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የሚሰጡት አስተያየቶች የተዘበራረቁ መሆናቸው በራሳቸው መሠረት የሌላቸው አስተያየቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ማኅበሩ የ«ሀ» ፖርቲ ደጋፊ ነው ሲል በውጪ ሀገር ያሉ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የ«ለ» ፖርቲ ደጋፊ ነው እያሉ ተጨባጭነት የሌለውና ምናልባትም የማኅበራችን አባላት በሆኑ የአንዳንድ ግለሰቦች ተሳትፎን መነሻ አድርጐ የሚሰጥ ሚዛናዊ ያልሆነ ድምዳሜ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ማኅበራችን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተመርኩዞ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ከሚቋቋመው መንግሥት ጋር መሥራት ሃይማኖታዊም ሕገ መንግሥታዊም ግዴታው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ማኅበሩ እንደተቋም የትኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ /Ideology/ በመደገፍ ወይም በመቃውም ከፖርቲዎች ጋር ግንኙነት ስለሌለው /ስለማይኖረው/ ለማንም ስጋት ወይም ዕድል ልንሆን አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ፈርጆን የሚነሣ አካል ካለ ግን ለመፈረጅ ያበቁትን የመረጃ ምንጮች እንዲመረምር በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበሩ አክራሪ ነው ስለሚባለውስ?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- እኛ «አክራሪ» የሚለውን ቃል በጥንቃቄ ነው የምንመረምረው?  አክራሪ ማለት የሃይማኖቱን ሕግ አክብሮ የሚኖር ተግቶ የሚጾም፣ የሚጸልይ በሃይማኖቱ ላይ ለሚነሡ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ፣ ታሪኩን፣ ቤተክርስቲያኑን የሚወድ፣ ለሃይማኖቱ የሚቀና የማይዋሽ ወይም ወደ ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራሱንም የሃይማኖት ወገኑን ሁሉ ለማድረስ የሚተጋ ከሆነ የማኅበራችንን አባላት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሰዎች ምናልባት በልማድ በዚህ ብያኔ ለመጥራት ፈልገው ከሆነ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ የሚመላለሱትን ክርስቲያኖች «አክራሪ» ተብ ለው ከሚጠሩ አጥባቂ፣ ዐቃቤ ሃይማኖት ቢባሉ የተሻለ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን «አክራሪ» የሚለው የሚያሰቃይ፣ የሚገድል፣ የሚያስገድድ፣ የሚሳደብ፣ የሌላውን ሳይነኩ የራሳቸውን አምልኮ እየፈጸሙ ያሉትን የሚረብሸ፣.. ወዘተ ለማለት የተቀመጠ ብያኔ ከሆነ በወንጌል የሚያምኑ፤ አምነውም የሚያስተምሩ ክርስቲያኖች ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከላዩ የተጠቀሱት ተግባራት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ጋር ተጣጥመው አይሔዱም፡፡ ማኅበራችንም ስብከተ ወጌልን በመላው ሀገሪቱ  እና ዓለማት የማስፋፋት ዓላማ ይዞ የሚሠራ በመሆኑ ለፍቅርና ለመከባበር ትልቅ ቦታ አለው፡፡

ምናልባት በማስጨነቅ ወይም በማስገደድ ሃይማኖታችንን ለማስጣል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችንና በሃይማኖታችን ላይ በኅትመት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አማካኝነት የሚሰጡ አስተያየትና ጥያቄዎች ሲኖሩ መልስና የአጸፋ አስተያየቶችን መስጠታችን በዚህ ደረጃ አስ ፈርጆን ከሆነ ሚዛናዊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እነዚህን የምናደርገው በሃይማኖታችን ላይ ጥያቄ ያነሣውን ወይም አስተያየት የሰጠውን አካል ለመተቸት ወይም ለመሳደብ ተፈልጐ ሳይሆን እነዚህ አካላት ካሠራጯቸው መልእክቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ሐሳብ እንዳይበረዝ፣ ሃይማኖታችን መልስና አስተያየት የሌለው መስሎ ለምእመናን እንዳይታሰብ ለመጠበቅ የሚደረጉና ለጠየቁን መልስ እንድንሰጥ በሃይማኖታችንም የታዘዘውን መንፈሳዊ ተግባር ለመፈጸም ነው፡፡

መከራ የደረሰባቸውና የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ሲኖሩ ቅሬታችንን መግለጻችን ተገቢ ይመስ ለኛል፡፡ ምክንያቱም ለሀገር ሰላምም የሚበጀው ችግሮች መኖራቸውን ጠቁሞ ሕዝብም መንግሥትም መፍትሔ እየሰጣቸው ሲሔዱ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስሜታዊ በሆነ መልክና ከጀርባው ሌላ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴን በክርስቲያኖች ስም ማካሔድን በጽኑ የምንቃወመው ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያን ያለውን ተቆርቋሪነት ከግምት አስገብቶ የተለያዩ አካላት በስሜት የሚያካሒዷቸው ግልጽና ሥውር እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አካላት እንደሚኖሩ እናምናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓውደ ምሕረት ቆሞ ያለ ሕግና ሥርዓት የሚያስተ ምሩ መምህራንን ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን መምህራን ናቸው የሚሉም እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን በጭፍን የሚሰጡ እነዚህን የሚመስሉ አስተያየቶች ተገቢ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት ማኅበሩ ያሰማራቸው መሆን አለመሆኑን ማጣራትም ወይም ሆኖም ከተገኘ ማኅበሩ ባለው አሠራር ርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ የተሻለ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት አቋም ላይ ያለን ማኅበር አክራሪ የሚሉት አካላት ካሉ ያን ለማለት መነሻ ያደረጓቸውን ጭብጦች ማጤን ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ማኅበሩም ለመምሪያው ለመታዘዝ ፈቃደኛ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም አሉ፡፡ እርስዎ እንደ ሰብሳቢ ምን ይላሉ?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ቤተክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱም ደንብና መመሪያዎች እንዲጠበቁ በጸኑ የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ ይህ ዋነኛ አጀንዳ ያለው አካል የማደራጃ መምሪያውን አሠራር ጠብቆ አይንቀሳቀስም ከተባለ ­ራዶክስ /መጣረስ/ ይፈጥራል፡፡ ማኅበሩ በመምሪያው የአሠራር ሥርዓት ላይ ችግር የመፍጠር ፍላጐትም ሥልጣንም የለውም ነገር ግን መምሪያውን ከሚመሩት ግለሰብ ዓላማና አቅም ላይ ግን ጥያቄ አለው፡፡ መከሩ ብዙ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት በሆኑበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት የተሰማሩ ማኅበራት እና ሰንበት ት/ቤቶችን በመምራት ረገድ የሚከተሉት የራሳቸው ፖሊሲ  እንደተመሪ /ባለድርሻ/ ምቹ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ላይ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች በውይይትና በክርስቲያናዊ የምክክር ሥርዓት ከመፈጸም ይልቅ በግልጽና በስውር የማኅበሩን ስም ማጥፋትን ሥራዬ ብለው ይዘዋል፡፡ የተለያዩ አካላትም በማኅበሩ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ያላ ሠለሰ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ማኅበሩ ችግር አለበት፤ ለመምሪያውም አይታዘዝም… ወዘተ የሚለውን የራሳቸውን ሓሳብ መነሻ አድርገው የሚጽፏቸውን ደብዳቤዎች ምስክር እያደረጉ መናፍቃን ደግሞ በመጻሕፍት አሳትመው ሲሰድቡን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እያየን ማኅበረ ቅዱሳንን ከሚጠሉ መናፍቃን ጋር እርሳቸው ተመጋግበው እየሠሩ ነው ላለማለት ዋስትና አይሰጥም፡፡ የማኅበሩ አሠራር ችግር አለበት ብለው ቢያስቡ እንኳን ከሠሯቸው በጐ ተግባራት፣ የወጣት ምሁራን ክርስቲያኖች እንቅስቃሴን አስፈላጊነትና አሁን ቤተክርስቲያን ከአጽራረ ቤተ ክርስተያን በኩል እየደረሰበት ካለው ፈተና አንጻር በስብከተ ወንጌል ረገድ ያለውን ርምጃ በመመልከት ችግሮቹን ከሚመለከታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር ተግባብቶ በመፍታት ግልጽ አሠራር ማስፈን ይገባቸው ነበር፡፡ ያንን አላደረጉም፡፡ ስለዚህ በአንዳንድ ማኅበሩ የአሠራር ችግሮች እንዳሉበት ለመምሪያውም እንደማይታዘዝ አድርጐ በማናፈስ ሺሕዎች የተሰለፉለትን ቤተክርስቲያን የመጠበቅ ተልእኮ ማነቆ እንዲያጋጥመው እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቡ ተልእኮ ላይ ማኅበሩ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ሆኗል፡፡ ማኅበሩ ለ17 ዓመታት ከተለያዩ መምሪያ ሓላፊዎች ጋር በምክክር ሠርቷል፡፡ ውጤትም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እኛ ጥያቄያችን ዛሬ እርሳቸው ያገኙት አዲስ ነገር ምንድነው የሚል ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የመምሪያው ዋነኛ ጥያቄ የማኅበሩን ገንዘብና ንብረት ኦዲት በመደረጉ ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ላይ ያለው አቋም  ምን ስልሆነ ነው ችግሮች የተፈጠሩት?

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ- ማኅበራችን ለአገልግሎት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ገንዘብ በሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ካሉ ከማኅበሩ አባላት የሚያገኘው በማኅበሩ የውስጥ ኦዲተሮች የሚሠሩት ሪፖርት ተአማኒነት ስላለውና የሚታዩ ውጤታማ ክንውኖችን መሠረት አድርጐ ነው፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ የማይታመንና ግልጽነት የጎደለው ከሆነና ሥራችንም በጎና ውጤታማ ባይሆን ለቀጣዩ ተግባሮቻችን የሚሆን የገንዘብ መዋጮን መሰብሰብ ባልቻልን ነበር፡፡ ስለዚህ አባላቱ መዝናናት ሳያምራቸው በመጠን እየኖሩ ለቤተ ክርስቲያን ከሚከፈሉት ዓሥራት በኩራት ተጨማሪ ለማኅበሩ አገልግሎት  የሚሰጡትን ገንዘብ፣ ጊዜና ንብረት በአግባቡ መያዝ የእያንዳንዱ አባል ሓላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህ ዋስትና የሚሰጠው ደግሞ የኦዲት ሥራው ነው፡፡ ስለዚህ የኦዲት ሥራን ለማኅበራችን ደኅንነት እንደ አንድ ግብ የምናስብ ነን፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ «ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፋችሁ ተጠንቀቁ» ያለውን ቃሉን ሁሌ እናስባለን፡፡ ስለዚህ በየጊዜው የኦዲት ሥራዎች የውስጥ ኦዲተሮቻችን ይደረጋሉ፡፡ ያንን አለማድረጋችን ከማደራጃ መምሪያው ይልቅ የሚጐዳው ማኅበሩን ስለሆነ ስለነገሩን ሳይሆን ስለሚያስፈልገን መቼም ቢሆን እናደርገዋለን፡፡ ማኅበሩ በጠቅላላ ጉባኤው የቤተክርስቲያን መምሪያ ሓላፊዎች ባሉበት የሂሳብ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ሆነ የሚመለከተው አካል የሂሳብ ሪፖርቱ አላረካኝም በውጪ ኦዲተር ይቀርብ ብሎን አያውቅም፡፡ ጥያቄው ከቀረበ ምንግዜም ማድረግ ይቻላል፡፡

አሁን ግን የተሻለ አደረጃጀትና ሰፊ አገልግሎት በሀገር ውስጥና በውጪም መስጠት ስንጀምር መምሪያው በማኅበሩ አገልግሎት የማይደሰቱ ግለሰቦች እና አካላት ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የመመሪያ ሓላፊው የእኛን ስም ለማጥፋት በመ ጠመዳቸውና ጊዜያቸውን ለዚያ እየሠው በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰ/ት/ቤቶች ከመምሪያው የሚፈልጉትን ያህል ድጋፍ ለማግኘታቸው ከፍተኛ ጥርጣሬ አለን፡፡ ከሁሉ በላይ ሊያሰጨንቀን የሚገባ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንጂ ሌላ አልነበርም በእኛ በኩል ግን የሚጠበቅብንን በማድረግ መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ሁሌም እንሻለን፡፡ ችግራችንም ከመዋቅሩ /ከመምሪያው/ ጋር ሳይሆን ከመምሪያው ሓላፊ ጋር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ርእሰ ዓውደ ዓመት ዮሐንስ

ክፍል ሁለት

በዓሉ እንዴት ይከበራል?

በማኅበረ ቅዱሳን ዐቢይ ማዕከል መምህር የሆኑት ሊቀጠበብት ሐረገወይን አገዘ «ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ታከብረዋለች» በማለት እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡
 

መንፈሳዊ ክንውኖች

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጽላት ባለባችው አብያተ ክርስቲያናት ከዋዜማው /ጳጉሜን 5/6/ ከሰዓት/ ጀምሮ በሌሎቹ ደግሞ ከምሽት ጀምሮ ማኅሌት ይቆማል፡፡ በዕለቱ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና የአዲስ ዓመትን መግባት በሚያነሱ ያሬዳዊ ዜማዎች ምስጋና ሲቀርብ ያድራል፡፡

በበዓሉ ዕለት ጠዋት /ረቡዕ እና ዓርብ ከሆነ ከሰዓት/ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ካህናትና ምዕመናንም ሥጋ ወደሙ ይቀበላሉ፤ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን የምታከብርበት ዋና ምክንያትም ይኸው ነውና፤ ምዕምናን ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት የዕረፍት ቀን ያገኙ ዘንድ፡፡

አይሁድ የዘመን መለወጫ በዓላቸው የሆነውን ሮስ ሆሻና /በዓለ መጥቅዕ/ በሚያከብሩበት ዕለት ሊቀ ካህናቱ የአገልግሎት አልባሳቱን ለብሶ ቆሞ የዓመቱ በዓላት የሚውሉበትን ቀን ያውጅ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ትውፊት በመከተል ከቅዳሴ በኋላ /ቅዳሴው ከሰዓት ከሆነ ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ሊሆን ይችላል/፡፡ የባሕረ ሀሳብ አዋቂ የሆኑ አባቶች የዓመቱ ተለዋዋጭ በዓላትና አጽዋማት የሚወሉባቸውን ቀናት በባሕረ ሃሳብ ቀመር እያሰሉ ያውጃሉ፡፡ 

በዚህም መሠረት መስከረም አንድ ቀን 2002 . የሚከተለው ይታወጃል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ነው፡፡

 

በዓላት /አጽዋማት

የሚውሉበት ቀን

ጾመ ነነዌ

ጥር 17

ዐቢይ ጾም

የካቲት 1

ደብረ ዘይት

የካቲት 28

ሆሣዕና

መጋቢት 19

ስቅለት

መጋቢት 24

ትንሣኤ

መጋቢት 26

ርክበ ካህናት

ሚያዝያ 20

ዕርገት

ግንቦት 5

ጰራቅሊጦስ

ግንቦት 15

ጾመ ሐዋርያት

ግንቦት 16

ጾመ ድኅነት

ግንቦት 18

 

ከዚህ በኋላ በዓመቱ የሚቀርቡ መስዋዕቶችን ሁሉ ወክለው ስንዴ /መገበሪያ/ ወይን /ዘቢብ/ ዕጣን፤ ጧፍ፣ወዘተ ይቀርቡና ይባረካሉ፡፡ በመጨረሻም ሠርዎተ ሕዝብ ይደረጋል፤ ሕዝቡ ይሰናበታል፡፡

ማኅበራዊ ክንውኖች

«ከዚህ በኋላ ማኅበራዊ ክንውኑ ይቀጥላል» ይላሉ ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን፡፡ በዓሉን ምክንያት አድርገው ሰዎች ወዳጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም የተቸገሩትና የሚበሉት የሚጠጡት ያጡ ወገኖችን በመጥራት ይጋብዛሉ፡፡ እነርሱም ይጋበዛሉ፡፡

«ይህ በበዓላት ላይ በእምነት ከማይመስሉን ጋር ሳይቀር የሚደረገው መተሳሰብና የፍቅር ግንኙነት ማኅበረሰቡን አንድ አድርጎ ይዞ የኖረ ገመድ ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል፡፡» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ «በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ፣ የሚበሉትና የሚጠጡት ያጡ ነዲያን ወገኖቻችንን ልናስብና «ብራብ አብልታችሁኛል» የሚለውን አምላካዊ ምሥጋና ለመስማት የሚያበቃ ሥራ ለመሥራት ልንተጋ ይገባናል» በማለት ያሳስባሉ፡፡

የበዓሉ መንፈሳዊ ትርጉም /ፋይዳ

የአዲስ ዓመት በዓል ለእኛ ለመንፈሳዊያን ሁለት ዋና ዋና መንፈሳዊ ትርጉሞች /ፋይዳዎች/ አሉት፡፡

  1. የምስጋና ዕለት ነው

በእርግጥ እግዚአብሔርን ማመስገን የዘወትር ተግባራችን መሆን አለበት፡፡ እርሱ ኅልፈት የሌለበት ዘመናትን ግን የሚያሳልፍና የሚለዋውጥ እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት አሳልፎ ለአዲስ ዓመት ሲያደርሰን ደግሞ ቢያንስ ለሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ልናመሰግነው ይገባል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ የምህረትህነ ዓመት ትባርካለህ» /መዝ.64.11/ እንዳለው ያለፈውን ዓመት ሙሉ በመግቦቱ ከምንተነፍሰው አየር ጀምሮ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ስላዘጋጀልንና በጠብቆቱም እኛ ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው ነገሮች ጠብቆ ወደ አዲሱ ዓመት ስላደረሰን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «አንተ ኃጢአትን ብታስብ፤ አቤቱ በፊትህ ማን ይቆማል» እንዳለው እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ቢያስብብን እና እንደ ኃጢአታችን ቢፈርድብን አንዲት ደቂቃ እንኳን መኖር አንችልም ነበር፡፡ እርሱ ግን ኃጢአታችንን እየታገሰ፤ አይቶ እንዳላየ እየሆነ በንስሃ እንድንመለስ ዕድሜ ይጨምርልናል፡፡ ሰዎች ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔደው ጲላጦስ ስለገደላቸውና ደማቸውን በመስዋዕታቸው ጋር ስለቀላቀለው ሰዎች የነገሩት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው «ይህች መከራ ስላገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ይልቅ ተለያይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? አይደለም፡፡ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ፡፡» አላቸውና የሚከተለውን ምሳሌ ነገራቸው፡፡

«አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሔዶ አላገኘም፡፡ የወይኑን ጠባቂም፡– «የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ ሦስት ዓመት ሆነኝ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት» አለው፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አለው «አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስካስታቅፋት ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን ተዋት፡፡ ምናልባት ለክረምት ታፈራ እንደሆነ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን» /ሉቃ.131-9/

ስለዚህ የዘመን መለወጫን በዓል የምናከብረው እግዚአብሔር በዕድሜያችን ላይ ሌላ ዓመት የጨመረልን በቸርነቱ ኃጢአታችንን ታግሶ የንስሐ ጊዜ ሊሰጠን መሆኑን በማስተዋልና ለዚህም ምስጋና በማቅረብ፤ እንዲሁም ቀጥለን እንደምንመለከተው የተጨመረልንን ዓመት ተጠቅመን ለከርሞ አፍርተን እንድንገኝ ለንስሐ እና ለለውጥ በመነሣት መሆን አለበት፡፡

2. ንስሐ እና ለውጥ

ንስሐ ማለት በኃጢአት መጸጸት፤ ኃጢአትን ለመተውና አዲስ ሕይወት ለመጀመር መወሰን ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፤ «የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁት ያለፈው ዘመን ይበቃል» /1ጴጥ. 4.3/

መንፈሳዊ ሕይወትና የክርስትና ጉዞ ሁል ጊዜ ራስን መመርመርና የቆሙበትን ማወቅ፤ ከዚያም የተሻለ ነገር ለማድረግ መወሰንን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁል ጊዜ መደረግ ያለት ቢሆንም የዘመን መለወጫ ወቅት ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የተሻለ የሥነ ልቡና ዝግጅት ያለበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

ስለዚህ የዘመን መለወጫ በዓልን ስናከብር ከበዓሉ አስቀድሞ ወይም በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ይህንን ለማድረግ ጊዜ መመደብና ቁጭ ብለን በዕርጋታና በጥሙና ያለፈውን ዓመት መገመግም፣ የነበሩትን ደካማ ጎኖች /ችግሮች/ እና ጠንካራ /መልካም/ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት ከነበሩት ችግሮች ውስጥ በአዲሱ ዓመት ልንፈታቸው የሚገቡ ችግሮችን ለይተን ማስቀመጥ ይገባናል፡፡ ከዚያም ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ «እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል» /ያዕ.4.15/ እንዳለው፡፡ እያንዳንዳቸውንም እንዴት አድርገን እንደምንቀርፋቸው አስበን ስልት መቀየስና ዕቅድ ማውጣት ዕቅዳችንን ለመፈጸምም መወሰን ይገባናል፡፡

ሊቀጠበብት ሐረገወይን «የምንቀበለው ዓመትአዲስሊባል የሚችለው እኛ መታደስ ከቻልን ብቻ ነው» ይላሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዲስ ኪዳንን ሲመሠርት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነገሮችን አድሷቸዋል፡፡ ደካማ የነበሩትንም ነገሮች አጠንክሯቸዋል አበርትቷቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ክህነት፣ መስዋዕት፣ ሕግ፣ በኃጢአት የተበላሸውን የሰው ልጅ ባሕርይ እና ሌሎቹንም ሁሉ መቅረት ያለባቸውን አስቀርቶ፣ መስተካከል ያለባቸውን አስተካክሎ፣ ሐዲስ ኪዳንን ሠርቷል፡፡ ጌታችን ይህንን ካደረገ በኋላ ያለውን ዘመን «ዘመነ ሐዲስ» ያስባለው የእነዚህ ነገሮች መስተካከል ነው፡፡

«ይህ በእያንዳንዳችን ሕይወት መደረግ አለበት፡፡ መጪው ዓመት አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዘመን የሚሆንልን ዓመቱ ችግሮቻችንን ቀርፈን፣ ጥንካሬዎቻችንን አጎልብተን የተሻለ ሕይወት የተሻለ አመለካከት የተሻለ ሥራ የምንጀምርበት ከሆነ ነው፡፡ ይህ ካልሆነና አምና የነበረውን ችግር ሁሉ መልሶ መድገም ካለ ግን ዓመቱ ለእኛ አዲስ ዓመት አይደለም» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ይህ ነገር በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም በአገልግሎታችንም ሁሉ መደረግ አለበት፤ ያን ጊዜ እውነትም ወደ አዲሱ ዓመት እንሸጋገራለን፡፡

«የዘመን መለወጫ በዓል የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ እንዲሆንልን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት፣ የቅዱሳን ሁሉ አማላጅነትና ተራዳኢነት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የመጥምቀ መለኮተ ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወትና አገልግሎት ክፍል ሁለት

                                 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እና ነቢዩ ኤልያስ

 ቅዱስ ዮሐንስ በበርካታ መንገዶች ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተያይዟል፡፡ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣትና መንገድ ጠራጊነት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

የመጥምቀ መለኮተ ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወትና አገልግሎት ክፍል አንድ

በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም 1 እስከ 7 ያለው ጊዜ  ዘመነ ዮሐንስ ይባላል፤ ሳምንቱ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕይወቱ፣ትምህርቱና ምስክርነቱ የሚታሰቡበት ነው ፡፡

test page

adye abeba 2006

ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ

ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” /1ኛ.ጴጥ.4.3/

adye abeba 2006መስከረም 1 ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ይህንን ምክንያት አድርገን በዚህ ጽሑፍ የዘመን አቆጣጠርን ምንነትና ታሪክ፣ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር እንዲሁም የዘመን መለወጫ በዓልና አዲስ ዓመት ሊኖራቸው የሚገባውን መንፈሳዊ ትርጉምና ፋይዳ አስመልክተን አንዳንድ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን፤

የዘመን አቆጣጠርን መጀመር አስፈላጊ ያደረጉ ሁለት ዋና ዋናምክንያቶች ነበሩ፡-

1. አዳም በበደሉ ምክንያት ከገነት ተባሮ ወደዚች ምድር ሲመጣ በመጸሐፈ ቀሌምጦስ እንደተጠቀሰው እግዚአብሔር «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን አንድ ሺሕ ዓመት መሆኑንና ይህ አምስት ቀንተኩል የተባለው ጊዜ 5500 ዓመት መሆኑን አዳምም ፣ ቀደምት አበውም ያውቁ ነበር እግዚአብሔር ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዳምን ሲያዘው «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞትለህ» ብሎት ነበር /ዘፍ.2.17፡፡ ይሁን እንጂ አዳም የሞተው በሰው አቆጣጠር 970 ዓመት ኖሮ ነው፡፡ይህ እግዚአብሔር ቀን ብሎ የገለጸው ምን ያህል እንደሆነ ለአዳም የሚያሳውቅ ነበር፡፡

 

ክቡር ዳዊትም “ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ሰዓት ነውና” /መዝ.89.4/ በማለት መናገሩ ደግሞ ቀደምት አበው ስሌቱን እንደሚያውቁት የሚጠቁም ነው፡፡እንግዲህ አበውና ነቢያት ይህንን በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን የሚቆጥሩት የዘመን አቆጣጠር አስፈለጋቸው፡፡

2. የሰው ልጆች ወደ ምድረ ፋይድ ከወረዱ በኃላ “በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ.. ወደ መጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ » /ዘፍ.2 .16-17/ በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት የሚበሉትን ለማግኘት የግብርና እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡በዚህ ጊዜ አየሩ የሚሞቅበትንና የሚቀዘቅዝበትን፣ ዝናም የሚኖርበትንና የማይኖርበትን፣ ቀኑ የሚረዝምበትንና የሚያጥርበትን ጊዜ ለማወቅና ሥራን ከዚህ አንጻር ለማቀድና ለመተግበር የዘመን መቁጠሪያና የጊዜ መስፈሪያ አስፈልጓቸዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የሰው ልጆች የተለያዩ መስፊሪያዎችን /መለኪያዎችን/ በመጠቀም ጊዜን / ዘመንን ሰፍረዋል፡፡ በሁሉም ቦታ የነበሩትና ዐበይት የሚባሉት የዘመን መስፈሪያዎች እግዚአብሔር «ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ፣ ለዕለታት፣ ለዘመናትና ለዓመታት ምልክት ይሆኑ ዘንድ» / ዘፍ.1. 14- 15/ የፈጠራቸውን የፀሐይንና የጨረቃን እንቅስቃሴ መሠረትያደረጉት መስፈሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም፡-

ሀ. ዕለት- አንድ ዕለት አንድ ቀንን /የብርሃን ክፍለ ጊዜን / እና አንድ ሌሊትን /የጨለማ ክፍለ ጊዜን/ ያካተተ ፀሐይ አንድ ጊዜ ከወጣች በኋላ ተመልሳ እስክትወጣ ድረስ ያለውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን አንድ ዕለት ምድር በራሷ ዛቢያ አንድ ጊዜ የምትሸከረከርበት ጊዜ ነው፡፡

ለ. ውርኅ- ወርኅ ማለት በግእዝ ጨረቃ ማለት ነው፡፡ አንድ ወርኅ የሚባለው ጊዜ ሙሉ ጨረቃ ከወጣች በኋላ ድጋሚ እስከምትወጣ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን / በጥንቱም ጨምሮ/ ይህ ጨረቃ መሬትን አንድ ጊዜ ዙራ ለመጨረስ የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወር ሃያ ዘጠኝ ተኩል ዕለታትን ይፈጃል፡፡

ሐ. ዓመት- አንድ ዓመት ማለት መሬት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ ይህም 365 ከ1/4 / ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከሩብ/ ዕለታት ይፈጃል፡፡ይህ ከመታወቁ በፊትም ግን የዓመት ጽንሰ ሓሳብ ነበር፡፡

 

ፕሮፊሰር ጌታቸው ኃይሌ የፅንሰ ሐሳቡን አመጣጥ እንዲህ ያስረዳሉ፡-

ሰዎች ርዝመታቸው እኩል የሆኑ ሁለት ሻማዎችን ሠሩና ልክ ፀሐይ ስትወጣ /ቀኑ ሲያልቅና ሌሊቱ ሲጀምር/ አንዱን ሻማ አበሩት፡፡ ልክ ፀሐይ ስትወጣ እሱን አጠፋናሌላውን / ሁለተኛውን/ ሻማ አበሩት፤ ጧት ፀሐይ እንደገና ስትወጣ / ሌሊቱ አልቆ ሌላ ቀን ሲጀምር/ ሻማውን አጠፉት፡፡ አሁን እንግዲህ ከየሻማዎቹ /ከሁለቱ ሻማዎች/ ምን ያህል እንደተቃጠለላቸው ሲያስተያዩት ከሁለቱ ሻማዎች የተቃጠለው እኩል አለመሆኑን ተመለከቱ በዚህም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል አለመሆኑን ተረዱ፡፡ ቀደም ብለውም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ መሆኑን ልብ ብለው ነበርና ይህንን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ በቀኑና በሌሊቱ ርዘማኔ /በሚቃጠለው የሻማዎቹ መጠን/ መካከል ያለው ልዩነት ከወቅት ወቅት የተለያየ እንደሆነ ተመለከቱ፡፡ ይህን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ ግን በየ182 /ተኩል/ ዕለቱ ቀኑና ሌሊቱ እኩል የሚሆኑባቸው ሁለት ዕለታት በዓመት ውስጥ እንዳሉ ተገነዘቡ፡፡ እነዚህ ዕለታት አንዱ የሙቀት ወራት ከመጀመሩ በፊት የሌላው ደግሞ የቅዝቃዜው ወራት ከመጀመሩ በፊት የሚመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት አንድ ጊዜ እኩል ሁኖ ደግሞበዚያው ወቅት እኩል እስከሚሆን ድረስ ያለውን ጊዜ ማለትም /182 ተኩል +182=365/ ዕለት አንድ ዓመት አሉት፡፡ አሁን ባለን ግንዛቤ ምድር በራሷ ዛቢያ እንደተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች፡፡ ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምትዞረው ወደ ጎን 23 ተኩል ዲግሪ ያህልአጋድላ ነው፡፡ ይህ የቀንና የሌሊት ርዝመት መለያየትም የሚከሰተው በዚህ ማጋደል ምክንያት ነው፡፡

 

እንግዲህ በአጠቃላይ ዋናዎቹ የጊዜ / የዘመን/ መስፊሪያዎች ዕለት፣ ወር እና ዓመት ናቸው፡፡ ሦስትቱም ተመላላሽ ክስተቶችን / ለምሳሌ የፀሐይን መውጣት/ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚሀ ተመላላሽ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪከሰቱ የሚፈጁት ዘመንnወይም ጊዜ ዓውድ ይባላል፡፡ ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ እንደ ቀለበት ዙሮ የሚገጥም ማለት ነው፡፡ ስለዚህዓውድ ማለት ክስተቶቹ አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪመጡ ድረስ ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከላይ ያየናቸው ሦስት መስፈሪያዎች/ ዕለት፣ ወርኀ፣ ዓመት/ ዓዕዋዳት / ዓውዶች/ የሚወጡበት ጊዜ ዓውደ ዕለት፣ ዓውደ ወርኀ፣ ዓውደ ዓመት ይባላሉ፡፡

መጀመሪያ ላይ ሰዎች እነዚህን ሦስቱን መስፈሪያዎች /ዓዕዋዳት/ /በተለይም ቀንና እና ወርን/ለየብቻቸው ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ከዚህን ያህል ቀን፣ከዚህን ያህል ወር በኋላ /በፊት/ እያሉ ጊዜን ይለኩ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስቱን በቅንብር/በቅንጅት/ ለመጠቀም ሲፈለግ ግን የዘመን አቆጣጠር ስሌት ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም አንድ ወር 29 ከግማሽ ቀን ነው፡፡ እንዲሁ እንዳለ ለመቁጠር ቢፈለግ የመጀመሪያው ወር ጠዋት ላይ ቢጀመር ሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ይጀምራል፣ ሦስተኛው ደግሞ ድጋሚ ጠዋት ላይ ይጀምራል፤ ይህን ለመቅረፍ ወሩን ሙሉ ሰላሳ ቀን ቢያደርጉት ከትክክለኛው ወር /የጨረቃ ዐውድ/ ግማሽ ቀን ይተርፋል፤ 29 ቀን ብቻ ቢያደርጉት ደግሞ ግማሸ ቀን ይጎድላል፡፡

አንድ ዓመት 365 ከሩብ ዕለታት አሉት፡፡ ዓመትን በወራት ለመቁጠር ቢፈለግ፤ዓመቱን 12 ወር ቢያደርጉት የዓመቱ /የዕለታት ቁጥር /29.5X12=354/ ብቻ ይሆናል፡፡ይህም ከትክክለኛው ዓመት /365-354=11/ ዕለታት ያህል ያንሳል፡፡13 ወር ቢያደርጉት ዓመቱ /365X13=385.5/ ቀናት ይሆናል ይህም ከትክክለኛው ዓመት /383.5-365=19/ ቀናት ያህል ይበልጣል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መስፈሪያዎች በቅንጅት ለመጠቀምይህንን አለመጣጣም የሚፈታ ቀመር /የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት/ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአይሁድን፣የሮማውያንን እና የሀገራችንን አቆጣጠሮች በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 29 እና 30 ዕለታት ያሏቸው 12 ወራት አሏቸው፤

 

 

.

የአይሁድ ወራት

የዕለታት ብዛት

ወራቱ በእኛ

1

ኒሳን

30

መጋቢት/ ሚያዝያ

2

ኢያር

29

ሚያዝያ/ ግንቦት

3

ሲዋን

30

ግንቦት/ ሰኔ

4

ታሙዝ

29

ሰኔ/ ሐምሌ

5

አቭ

30

ሐምሌ/ ነሐሴ

6

አሉል

29

ነሐሴ/ መስከረም

7

ኤታኒም

30

መስከረም/ ጥቅምት

8

ቡል

29/30

ጥቀምት/ ኅዳር

9

ከሴሉ

30/29

ኅዳር/ ታህሳስ

10

ጤቤት

29

ታህሳስ/ ጥር

11

ሳባጥ

30

ጥር/ የካቲት

12

አዳር 1

29

የካቲት/ መጋቢት

 

 

እነዚህ የዓመቱ 12 ወራት በአጠቃላይ 354 ያህል ብቻ ዕለታት ይኖሯቸዋል፡፡ ይህም በትክክለኛው ዓመት በ11 ዕለታትያህል ቢያንስም አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ልዩነቱ በሁለት ዓመታት 22 ዕለታት፣ በሦስት ዓመት ደግሞ 33 ዕለታት ያህል ይሆናል፡፡ስለዚህ በየሦስት ዓመቱ ከአስራ ሁለተኛው ወር ጳጉሜን በፊት አንድ ሌላ ወር ይጨምሩና የዓመቱን የወራት ቁጥር ዐሥራ ሦስትያደርጉና ልዩነቱንያስተካክሉታል፡፡

የኢትዮጵያውያንና የግብጻውያን ዘመን አቆጣጠር

የሀገራችን ኢትዮጵያ እና የጥንት ግብጻውያን /ዛሬም ድረስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን Yየምትጠቀምበት/ የዘመን አቆጣጠር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለታችንም እኩል ሰላሳ ቀናት ያሏቸው12 ወራት አሉን፡፡ እነዚህ 12 ወራት / 12X30=360/ ቀናት አሏቸው፡፡ እነዚህ ቀናት በትክክለኛው ዓመት በ/365.25-360=5.25/ ቀናት ያንሳሉ፡፡ይህንንም 5 ቀናት/ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት/ ያሏትን 13ኛ ወር በመጨመር ያስተካክሉታል፡፡የኢትዮጵያውያን እና የግብጻውያን ወሮች ስም እንደሚከተለው ነው፡፡

 

 

ተ.ቁ

የግብጽ ወሮች

የኢትዮጵያ ወሮች

1

ቱት/ዩት

መስከረም

2

ባባ/ፓከር

ጥቅምት

3

ሀቱር

ኅዳር

4

ኪሃክ/ከያክ

ታኅሣሥ

5

ጡባ/ቶቢር

ጥር

6

አምሺር/ሜሺር

የካቲት

7

በረምሃት

መጋቢት

8

በርሙዳ

ሚያዝያ

9

በሸንስ

ግንቦት

10

ቦኩሩ

ሰኔ

11

አቢብ

ሐምሌ

12

መስሪ

ነሐሴ

13

ኒሳ/አፓጎሜኔ

ጳጉሜን

/ባሕረ ሐሳብ፣ፕ/ ጌታቸው ኃይሌ ፣ገጽ.65/

የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር

የጥንት ሮማውያን የመጀመሪያው የዘመን መቁጠሪያ 30 እና 31 ቀናት ያሏቸው 10 ወራት ብቻ ነበሩት፡፡ በአንድ ዓመት ያሉት ቀናት ቁጥር 304 ብቻ ነበር፡፡ሮማውያን ይህን ያዘጋጀው የሮማ ከተማን የመሠረተው ሮሙለስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በ713 ዓመት ቅ.ል.ክ ኑማ ፓምፒለስ /Noma Pompilos/ የተባለ የሮማ ንጉሥ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ወራት ጨመረበት፡፡

ጁሊያን የዘመን አቆጣጠር /Julian Calander/ የሮማው ንጉሥ ጁልየስ ቄሳር ለሲጃነስ የተባለ እስክንድርያዊ ሥነ ከዋክብት ተመራማሪን አማክሮ ጥንታዊውን የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር አሻሽለው 30 እና 31 ቀናት ያላቸው11 ወራትና 28 ቀናት የአራት ዓመቱ 29 ቀናት ያሉት አንድ ወር ያለው የዘመን አቆጣጠር አዘጋጀ፡፡

አሁን ምዕራባውያን የሚጠቀሙበት የጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከተደረጉበት የቀናት ማስተካከያ በስተቀር ይኸው የጁልያን አቆጣጠር ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ልዩ ልዩ አቆጣጠሮች መኖራቸው እንደ እውነቱ ከሆነ የሚያስከፋ አይደለም፤ ሁሉምዓላማቸው አንድ ነውና፤ ሦስቱን የጊዜ መስፈሪያዎች ማጣጣም፡፡ ጥያቄ ሊሆኑ የሚገባቸው የሚከተሉት ሁለት ነጥቦች ናቸው፡፡

1. የዘመን ቁጥር ልዩነት

ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ የዘመን አቆጣጠር መለያየትን መነሻ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ «ክብ የሆነ ነገር ሲከብ ከየትኛውም ቦታ መጀመር ይቻላል፤ የዘመን አቆጣጠር /ዓውደ ዓመትም/ ይኸው ነው፡፡ ዋናው ነገር አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ አንድ ታላቅታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው፤ የዘመን አቆጣጠሮቹም ልዩነት መንስኤው ይኸው ነው» ይላሉ፡፡

ባሕረ ሐሳብ፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ ገጽ.65/ ለምሳሌነትም ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን/ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደ ነበር ይጠቅሳሉ፡፡ መሐመድና ተከታዮች ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ የአይሁድን አቆጣጠር ትተን ከላይ ያየናቸው ሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች /የምዕራባውያኑ የጁልስ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርና የኢትዮጵያና የግብጽ አቆጣጠር/ ሁለቱም ዘመንን የሚቆጥሩት ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው፡፡ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ 2002 ዓ.ም ነው ስንል እነርሱ ደግሞ 2009 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡

በመካከሉ የ7/8 ዓመታት ልዩነት አለ፡፡እንግዲህ ጥያቄው ትክክለኛው የትኛው ነው? የሚለው ነው። ጉዳዩ መጻሕፍትን ሊያጽፍ የሚችልና በእርግጥም የተጻፉበት ቢሆንም ለማሳያ ያክል ሁለት ነገሮች እንመልከት፡-

 

  1. አሁን ባለው የምዕራባውያን አቆጣጠር ሄሮድስ የሞተው 4 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው። ሄሮድስ የሞተው ጌታ ተወልዶ በስደት ሦስት ዓመት ያህል በግብጽ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ይህ ማለት በእርሱ አቆጣጠር ጌታ የተወለደው በ7 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው ማለት ነው።እንግዲህ ጌታ በትክክል በተወለደበት በአንድ ዓ.ም እነርሱ ጌታ ሰባት ዓመት ሆኖታል ይላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት አሁን ካላቸው ቁጥር ላይ ሰባት ዓመት መቀነስ አለባቸው፡፡

  2. ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የአይሁድን ታሪክ የጻፈው ሊቅ እንደ መሰከረው ጌታ የተወለደበት ዓመት ነው ተብሎ በወንጌል ላይ የተጻፈው የቆጠራ ዓመት /ሕዝቡ ሁሉ የተቆጠረበትን ዘመን /ሉቃ.2.1/ በጎርጎሪያን ዘመን አቆጣጠር «7 ዓመተ እግዚአ /A.D/ ላይ ነው፡፡» በማለት መረጃ ትቶልናል ይህ ማለት ደግሞ ከምዕራባውያኑ ዘመን አቆጣጠር ላይ 7 ዓመቶች የግድ መቀነስአለበት ማለት ነው፡፡ ያ ሲደረግ ደግሞ የኛን ዘመን አቆጣጠር ያመጣል፡፡

 

2. የዘመን መለወጫ ቀን ልዩነት

ሁለተኛው ጉዳይ የዘመን መለወጫ ወርና ዕለት ልዩነት ነው፡፡ እኛ መስከረም 1 አዲስ ዓመት ስንጀምር እነርሱ በ January 1 / በእኛ ታኅሣሥ 23/ አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ከየት የመጣ ልዩነት ነው? የእኛ እና የግብጻውያን አቆጣጠር እዚህ ጉዳይ ላይ ከአይሁድ አቆጣጠር ጋር ይስማማል፡፡በአይሁድ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር ኒሳን የሚባለው /በእኛ መጋቢት/ ሚያዝያ/ ነው፡፡«ይህ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፣ በዚህም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የአንድ ዓመት ተባዕት ላይ ወስደው ይረዱ፡፡ /ዘፀ.12.1-14/ ተብሎ የተሰጣቸውን የፋሲካ በዓል የሚያከብሩት በዚህ ወር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ የዓመት በዓል አድርገው የሚያከብሩት «የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁናችሁ፡፡ በዚሁ በመለከት ድምጽ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ መስዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት» /ዘሌ.13.23-25/ ተብሎ የተሰጣቸው የሮሽ ሆሻና፣/የመለከት በዓል ወይም በዓለ መጥቅዕ/ ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው፡፡ ይህም ማለት አዲስ ዓመት የሚያከብሩት በሰባተኛው ወር በኢታኒም ወር /በእኛ መስከረም ጥቅምት/ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችንም ትምህርት ዓለም የተፈጠረው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ መስከረም ደግሞ ከመጋቢትጀምሮ ሲቆጠር ሰባተኛው ወር ነው ይህም ከአይሁድ ዘመን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አይሁድስ ቢሆኑ የመጀመሪያው ወር እያለ አዲስ ዓመትን ለምን በሰባተኛው ወርያከብራሉ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ዓይነት ምላሾች /ምክንያቶች/ ይሰጣሉ፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት «ሰባተኛው ወር ኖኅ ከመርከብ የወጣበት ወር በመሆኑ ይህ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ መከበር በመጀመሩ ነው» የሚል ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዕለት ልጃገረዶች አበባ እና ለምለም ሣር መያዛቸው ርግቢቱ ለኖኅ ካመጣችው ለምለም ወይራ /ቄጠማ/ ጋር ተያይዞ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛው ደግሞ መስከረም የቀንና የዕለቱ ርዝመት እኩል የሚሆኑበት ወር በመሆኑ ነው የሚል ነው፡፡ የመስከረም1 ቀን ስንክሳር «የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርእስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው» ይላል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባው ሌላው ጉዳይ በቤተክርስቲያናችን ትምህርት እመቤታችን ጌታን የጸነሰችው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ይህም ቅዱስ ጳዉሎስ ፣የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ» /ገላ.4.4/ እንዳለው የ5500 ዘመኑ ፍጻሜ /ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ/ ነው፡፡ ጽንሰትን መጋቢት 29 ካልን በኋላ ልደትን ታህሣሥ 29 ቀን እናከብራለን፡፡ ከመጋቢት 29 እስከ ታህሣሥ 29 ድረስ 9 ወር ከ5 ቀን ነው፡፡ /ጳጉሜን ጨምሮ/፡፡ ጳጉሜ 6 በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ታህሣሥ 28 ቀን ልደት ስለሚከበር አሁንም በመሐሉ ያለው ጊዜ 9 ወር ከአምስት ቀን ይሆናል፡፡

የዘመን ቆጠራ ለቤተ ክርስቲያን

የዘመን ቆጠራ ከጌታችን ልደት በፊት የነበረው ሃይማኖታዊ ፋይዳ የሰው ልጆች ሁሉ /በተለይ አበውና ነቢያት/ በተስፋ ይጠብቁት የነበረውን የጌታችንን መምጣት የቀረውን ጊዜ ለማወቅ ነበር፡፡ተስፋው ከተፈፀመ በኋላ ደግሞ የዘመን ቆጠራ ዋና አገልግሎቱ በዓላትና አጽዋማት በዓመቱ የሚወሉበትን ዕለት ለማወቅ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ድንቅ ነገሮችና ውለታዎች የሚታሰቡባቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ በዓላት ሁሉ መጀመሪያ በተደረጉባቸው ቀናት ይከበሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ስቅለት መጋቢት 27፣ ትንሳኤ መጋቢት 29፣ ልደት ታኅሣስ 29፣ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ኅዳር 12፣ ወዘተ. . . ማለት ነው፡፡ አጽዋማቱም እንዲሁ፡፡

የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ዲሜጥሮስ ግን አንዳንድ በዓላትና አጽዋማት መጀመሪያ በተፈጸሙባቸው ዕለታት እንዲውሉ ይመኝ ነበር፡፡ በተለይም ነነዌ የዐቢይ ጾም መጀመሪያ፣ እና የጾመ ሐዋርያት መጀመሪያ ሁል ጊዜ ሰኞ እንዲውሉ፤ ደብረ ዘይት፤ ሆሳዕና፤ ትንሳኤ ጰራቅሊጦስ ከእሁድ እንዳይወጡ፣ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት፣ ከረቡዕ፤ ዕርገት ከኀሙስ ስቅለት ከዓርብ እንዳይወጡ ይመኝ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ «ዲሜጥሮስ ሆይ ይህ ሁሉ በሐሳብ አይፈጸምም፤በተግባር ቢያደርጉት ካልሆነ» ብሎ ሱባኤ እንዲገባ ነገረው፡፡

 

ዲሜጥሮስም ሱባዔ ገባና የተመኘውን ሊያደርግበት የሚችል ቀመር ተገለጠለት፡፡ ቀመሩን በመጠቀምም ግብጻውያን እነዚህ በዓላት የሚውሉቸውን ቀናት በየዓመቱ እየወሰኑ ማክበር ጀመሩ፡፡በ325 የተደረገው የኒቅያ ጉባኤም ትንሳኤ ሁል ጊዜ እሁድ እንዲከበርና በዓሉ የሚከበርበትን ዕለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንድታስታውቅ በመወሰኑ ይህ ቀመር ተስፋፍቷል፡፡ቀመሩ ወደ ሃገራቸንም መጥቷል፡፡ ስሙም ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡

ቀመሩን እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘነው ትምህርቱን በድጋሚ ካስፋፋው 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ከነበረው ከግብጻዊው ዲያቆን ከዮሐንስ አቡሻክር በመሆኑ የአቡሻክር ትምህርትም ተብሎ ይጠራል፡፡ /ባሕረ ሐሳብ፣ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ፣ገጽ 19/ የእኛ ሀገር ሊቃውንትም አስፋፍተውታል፤አራቀውታልም፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ቀመር በመጠቀም በየዓመቱ የሚውሉትን ተለዋዋጭ በዓላት እና አጽዋማት መቼ እንደሚውሉ ትወስናለች፡፡

ስለ ዘመን አቆጣጠር ይህንን ያህል ካልን ቀጥለን ደግሞ ዐቢይ ትኩረታችን ስለሆነው ስለ ዘመን መለወጫ በዓል እንነጋገር፡፡

 

የዘመን መለወጫ በዓል የበዓሉ ስያሜዎች

 

ይህ በዓል “የዘመን መለወጫ”፤ “አዲስ ዓመት” ከሚሉት በተጨማሪ ሌሎች ስሞችም አሉት፡፡

 

ሀ. ቅዱስ ዮሐንስ-

a st.john 2006ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተብሎ ከጌታችን ስብከት አስቀድሞ እንደሚመጣና ጥርጊያውን እንደሚያዘጋጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ተነግሮለት ነበር /ኢሳ.40.3/፡፡ በዚህም መሠረት በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ተነስቶ «መንግሥት ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» «እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» በማለት ስለ ጌታችን አዳኝነት መስክሯል፤ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው እየገሰፁ ንስሐ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ጌታችንንም በዮርዳኖስ ወንዝ አጥምቋል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት/ምትረት ርእስ/ የሚታሰበው መስከረም ሁለት ቀን ቢሆንም እንኳን ተግባሩ በዘመነ ወንጌልና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረ መሸጋገሪያ በመሆኑ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መታሰቢያ በዓል የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ከሚሆነው ካለፈው ዓመት የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ወደሚሆነው አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ በሆነው በመስከረም አንድ ቀን እንዲከበር፤ በዓሉም በእርሱ ስም እንዲሰየም አባቶ ወስነዋል፡፡

ለ. ርእሰ ዓውደ ዐመት

ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው የሚመጡበት ጊዜ ማለት መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ዓውደ ዓመት ማለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ከተጀመረ በኋላ ሁለተኛ ዓመት እስኪጀመር ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ዓመትን መቁጠር ከየትኛውም ወር እና ቀን መጀመር ይቻላል፡፡ኅዳር 13 ብንጀምር አንድ ዓውደ ዓመት ማለት እስከሚቀጥለው ኅዳር 12 ቀን ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መደበኛው ዓውደ ዓመት የሚጀምረው መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ርእሰ ዓውደ ዓመት የተባለውም «የሁሉም ዓውደ ዓመት መጀመሪያዎች ቁንጮ ነው» ለማለት ነው፡፡

ሐ. ዕንቁጣጣሽ

ሐጎስ ዘማርያም ለምለም በቀለን ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ያቀረበችውን ጽሑፍና ሌሎች የቃል ማስረጃዎችን ጠቅሶ በሐመር መጽሔት የ1997 ዓ.ም መስከረም/ ጥቅምት ዕትም ላይ በቀረበው ጽሑፍ «ዕንቁጣጣሽ» ለሚለው የዚህ ስያሜ ሁለት ዋና ዋና መነሻዎችን እንዳሉት ገልጿል፡፡

 

  1. ዕንቁጣጣሽ የሚለው ቃል ሁለት ቃላት ካሉት ጥምር ቃል የተገኘ ነው፡፡ ዕንቁ እና ጣጣሽ ከሚሉ ዕንቁ የከበረ ዋናው ውድ የሆነ አብረቅራቂ ድንጋይ ነው፡፡ ጣጣሽ የሚለው ቃል ፃዕ ፃዕ ከሚለው የግእዙ ቃል የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙ ግብር፣ ጣጣ፣ ገጸ በረከት፣ ማለት ነው፡፡ለምሳሌ በሸዋ አካባቢ ግብር አለብኝ ሲል «ጣጣ አለብኝ» ይላል፡፡ይህ ስያሜ ለበዓሉ የተሰጠው ከንግሥተ ሳበ /ንግሥት ማክዳ/ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጎብኘት ሔዳ ሳለ የጸነሰችውንቀዳማዊ ምኒልክን በወለደች ጊዜ ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ ብሎ እልል እያሉ «አበባ እንቁ ጣጣሽ» እያለ ገጸ በረከት ለንግሥቲቱ አበረከቱ፡፡ያ የዘመን መለወጫ በዓልም ልጃገረዶች የአበባ ገጸ በረከት የሚያቀርቡበት ስለሆነ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

  2. ዕንቁጣጣሽ ግጫ ማለት ነው፤ ግጫ ደግሞ የሣር ዓይነት ነው፡፡የአበባ፣ የእርጥብ ስጦታ መስጠት የተጀመረው በኖኅ ዘመን ነው፡፡ ኖኅ የጥፋት ውኃ በጎደለ ጊዜ መጉደሉን ለማረጋገጥ ርግብን ልኳት የወይራ ቅጠል አምጥታለች ይህ የሆነበት ወቅት የመስከረም ወር በመሆኑ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዘመን መለወጫ ሆነ፡፡በርግቧ አምሳልም ልጃገረዶች የተለያየ ዓይነት ሣርና አበባ በመያዝና በማደል በዓሉን ያከብራሉ፡፡ በሣሩ ስምም በዓሉ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

ስብከት

ቅድስት ቤተክርስቲያን አምልኮቷን የምትፈጽምበት እጅግ የተደራጀ ሥርዐተ አምልኮ አላት፡፡ ከዚህ ሥርዓተ አምልኮ አንዱ ክፍል ዓመታዊ የምስጋና መርሐ ግብር እና የሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ የተደራጀ ነው፡፡

ሀ. ቀናትን መሠረት በማድረግ

በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ጥልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጊቶች እና ክንውኖች በዓመቱ ውስጥ ቀናት ተመድበውላቸው በበዓላትና በአጽዋማት መልክ ይታሰባሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እነዚህን በዓላትና አጽዋማት የምታከብርበት ዓመታዊ መርሐ ግብር እና በበዓላቱና በአጽዋማቱ የሚታሰበውን ነገር አስመልክቶ አባላቶችን የምታስተምርበት ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡

እንደዚህ ባለ መርሐ ግብር ከሚታሰቡት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮችና ያስተማራቸው ትምህርቶች /ፅንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሳኤ፣ ዕርገት፣ ደብረ ታቦር፣ምጽአት/፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት  /ልደቷ፣ ዕረፍቷ፣ ቤተመቅደስ መግባቷ፣ ድንቅ ተአምራት ያደረገችባቸው ዕለታት/፤፣ የቅዱሳን በዓላት /ልደታቸው፣ ዕረፍታቸው፣ ተአምራት ያደረጉባቸው. . / ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ለ. እሁዶችን /ሳምንታትን/ መሠረት በማድረግ

በዓመቱ ውስጥ ያሉት ቀናት/ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜን 5/ ብቻ ሳይሆኑ እሁዶቹም /ሳምንታቱም/ የተለያዩ ነገሮች ይታሰቡባቸዋል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሁዶች /ሳምንታት/ በእያንዳንዳቸው የሚቀርበው ምስጋና እና የሚሰጠው ትምህርት ምን እንደሆነ የሚገልጽ መርሐ ግብር እና ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡ ለምሳሌ ከመስከረም 1 እስከ 7 ድረስ ያለው እሁድ /ወይም በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ዮሐንስ አኅድአ»፣«ዮሐንስ መሰከረ ይባላል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕይወት እና ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡

መስከረም 8 ቀን እሁድ ቀን ቢውል ያ እሁድ «ዘካርያስ» ተብሎ ይጠራና የመጥመቁ ዮሐንስ አባት የካህኑ የዘካርያስ ነገር ይታሰብበታል፡፡

ከመስከረም 9 እስከ 17 ያለው እሁድ /እና በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ፍሬ» ይባላል፡፡ በዚህ እሁድ እግዚአብሔር ለምድር ፍሬን እንደሚሰጥ ይታሰባል፡፡
በዚህ መልኩ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሑዶች በሙሉ ምን እንደሚታሰብ የሚገልጽ መርሐ ግብርና ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ ይህም በተለያዩ ወቅቶች ያለውን የአየር ጠባይ እና የግብርና እንቅስቃሴ ያገናዘበ ነው፡፡

 

በእነዚህ ዕለታት ምስጋና የሚቀርብበት እና ትምህርት የሚሰጥበትን ጉዳይ /ርእስ/ መወሰን ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ነገሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡

«ስንክሳር» የሚባለው መጽሐፍ ከመስከረም አንድ እስከ ጳጉሜን 5/6 ድረስ የሚታሰቡ ቅዱሳንን እና ክንውኖችን ዝርዝር ታሪክ ይዟል፡፡

«ግጻዌ» የሚባለው መጽሐፍ በየዕለቱ /በየእሁዱ/ ከሚታሰበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት /ከመልእከታተ ጳዉሎስ፣ ከሰባቱ መልእክታተ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከወንጌል/ መርጦ ያቀርባል፡፡

የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትም /ድጓ፣ ዝማሬ፣ምዕሪፍ፣ ዝማሬ መዋስዕት/ በዚህ መርሐ ግብር መሠረት የተዘጋጁ ሲሆኑ በየዕለቱ ስለሚታሰቡት ነገር ዝርዝር እና ጥልቅ የሆኑ ትምህርቶችን እና ምስጋናዎችን የያዙ ናቸው፡፡

በዚህ «ስብከት» በሚለው ዓምድ ሥር ይህንን መርሐ ግብር፣ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት አድርገን ትምህርቶችን እናቀርባለን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓምድ ስር የሚቀርቡት ትምህርቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
1. ሳምንታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር በእያንዳንዱ እሁድ/ሳምንት/ የሚታሰቡትን ጉዳዮች አስመልክቶ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
2. ወቅታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር ቀናትን መሠረት አድርገው ከሚከበሩት በዓላት መካከል ዋና ዋናዎቹን በተመለከተ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
3. ሌሎች– ይህ ንዑስ ዓምድ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ስብከቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡

አዘጋጆቹን በጸሎት በማሰብ፣ በሚቀርቡ ስብከቶች ላይ አስተያየት በመስጠትና ስብከቶችን በመላክ ለዚህ ዓምድ መጠናከር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡ እግዚአብሔር ሐሳባችንን እንድንፈጽም ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ

በዳዊት ደስታ

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጅ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ» ተብሎ በኢሳይያስ እንደ ተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነሥቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ለኃጢአት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ በዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ገልጾታል፡፡ /ማር.1.40፤ኢሳ.40.3-4/፡፡

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡

ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡

ዘመን መለወጫ

አስቀድመን ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ማንነትና የዘመን መለወጫ መግቢያው ላይ በስሙ ስለመጠራቱ ተመልክተናል፡፡ ዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት 364 ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /ሔኖክ.21.49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/ኩፋ.7.1/
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡

እንቁጣጣሽ

ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ፣ እንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይመ ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡
በዚህ በአዲሱ ዓመት የሁለተኛው ሺሕ ማብቂያና የሦስተኛው ሺሕ መግቢያ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሁለት ሺሕ ዓመተ ምሕረት ያሳለፈቻቸውን መልካም ሥራዎችና የደረሰባትን መጥፎ ሥራዎችን አልፋ አሁን ላለው ትውልድ ደርሳለች፡፡ ይሕ ትውልድ ደግሞ በሦስተኛው ሺሕ ዓመት እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷን አውቆ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት፡፡
                           
ለዚህም የሚረዳውን ገዳማትና አድባራትን በማጠናከር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዘመናዊ አስተዳደር በመዘርጋት ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ጥሩ ግንኙነት በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል፡፡
ሺሕ ዓመቱ ሲለወጥ በዋዜማው ላይ በምንገኘኝበት ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ተቀራርቦ በመሥራት የሰው ዘር በሙሉ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡

                                             

                                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር