የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የ2004 ዓ.ም. እቅዶቹን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር በ2004 ዓ.ም. ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው የአገልግሎት ዘፍፎች በአብዛኛው እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ፡፡

 

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ክፍል ሓላፊ የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ 2004 ዓ.ም. የክፍሉ የአገልግሎት አፈጻጸም አስመልክቶ እንደገለጹት “በታቀደው መሠረት በመላው ሀገሪቱ 200 የሕዝብ ጉባኤያትን 15 ሐዋርያዊ ጉዞዎችን ለማድረግ ታስቦ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ እንዲሁም በ10 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ ካህናት የትምህርተ ኖሎትና የአስተዳደር የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ታስቦ በ8ቱ ሀገረ ስብከቶች ተተግብረዋል፡፡ በ10 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተተኪ መምህራን ሥልጠና በታሰበው መንገድ ተሰጥቷል፡፡ ሰልጣኞቹም በየሀገረ ስብከታቸው በመንቀሳቀስ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ሠላሳ ሠላሳ ሌሎች ሰልጣኞችን እንዲያሰለጥኑ በመደረግ ላይ ሲሆን ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

 

የሰለጠኑት ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወደታች ወርደው ሥልጠናውን ሲሰጡ ለመገምገም መቻሉን የገለጹት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ “ሥልጠናው የካህናትና የተተኪ መምህራን ብቃት የሚያጎለብት እንደሆነ ጨምረው የገለጹ ሲሆን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያልተቋቋመባቸው ቦታዎች ላይ በማቋቋም የማጠናከሪያ አገልግሎት በመስጠት ወደተግባር መሸጋገራቸውን በተደረገወ ግምገማ ለማረጋገጥ መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በ2005 ዓ.ም. ይህ አገልግሎት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የክፍሉ ሓላፊ ሊቀ ብርሃናትት ሃይማኖት ተስፋዬ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ያሰለጠናቸው አቅም ያላቸው ተማሪዎችና ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙና የተመረቁ መምህራን ወደየመጡበት ሀገረ ስብከት በክረምቱ ስለሚሄዱ ሥልጠናዎችንና የስብከት አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

 

ስላጋጠማቸው ችግር ሲገልጹም “ከፍተኛ ችግራችን የገንዘብና የመገልገያ ቁሳቁስ እጥረት ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. 10 የስብከት 10 የመዝሙር ካሴቶችንና በ4 የተለያዩ ቋንቋዎች መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ በኦሮምኛና በሲዳምኛ መዝሙር በኦሮምኛና በአማርኛ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህን ለምእመናን ለማዳረስ መታተም አለባቸው፡፡ ነገር ግን ዝግጅቶቹ ቢጠናቀቁም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሊሳካልን ባለመቻሉ በእጃችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎችም የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት እንድንችል ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ከበጎ አድራጊ ምእመናን እንጠብቃለን፡፡ በተጨማሪም የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ የተጠቀሙበትና የቀየሩት ኮምፒውተር፣ ፕሪንተርና ሌሎችም ድጋፍ ያደረጉ የገጠር ቤተ ክርስቲያናትን፣ የወረዳና ሀገረ ስብከቶችን ለማጠናከር ጠቀሜታ ስላላቸው ከምእመናን ብዙ ይጠበቃል በማለት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡