በክለሳ ላይ ያለው የግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት ትግበራው በ2004 ዓ.ም ይጀመራል ተባለ፡፡

 ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
 
ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ያለውን የግቢ ጉባኤያት የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ በተመለከተ ከማዕከላትና ግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ጋር ውይይት ተደረገ፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋረያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስታወቀ፡፡

ከግንቦት 26 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገው የውይይትና የምክክር መርሐ ግብር ከ11 ማዕከላት የመጡ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ኃላፊዎችና ከ15 ግቢ ጉባኤያት የተወከሉ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ተወካዮቹ ከዚህ በፊት ይነሡ የነበሩ ችግሮች በክለሳውና በዳሰሳ ጥናቱ መታየቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ለተግባራዊነቱ መፋጠን ይኖርብናል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የክፍሉ አስተባባሪ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን እንደገለጡት ክለሳው የተሠራው በ2000 ዓ.ም የተካሄደውን የዳሰሳ ጥናት መሠረት በማድረግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የዳሰሣ ጥናት ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች፣ ለመምህራን ለክፍሉ አባላት መጠይቆችን በመበተን፣ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፣ በአካል ቅኝት በማድረግና በመሳሰሉት እንደተከናወነ አስታውቀዋል፡፡
እስከ አሁን ሲተገበር የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ለማኅበሩ የመጀመሪያ በመሆኑ ወጥነትና አንዳንድ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሳይሟሉ ተግባራዊ እንደሆነ የገለጹት አስተባባሪው አሁን እየተከለሰ ባለው ግን አንድ ሥርዓተ ትምህርት ሊያሟላ የሚገባውን አሟልቷል ብለን እናምናለን፡፡ ማኅበሩም ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ምን ዓይነት ፍልስፍና መከተል አለበት የሚለው ግንዛቤ ውስጥ ገብቷል፡፡ በተለይም ወደ ግቢ ጉባኤያት እየገባ ካለው ትውልድ አንጻር ሥርዓተ ትምህርቱ ሰፊ ፍተሻ እንደተደረገበትና ለሙከራም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደሚተገበር አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚያስተምራቸው የገቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ 20 መማሪያ መጻሕፍትን በማዘጋጀት እያስተማረ እንደሚገኝ ቀሲስ ታደሰ አስታውሰው በሚሰጡ ትምህርቶች ድግግሞሽና መሳሳብ እንደሚስተዋል፣ ለትምህርቶቹ የተመደበላቸው ሰዓቶች ከሚሰጡት ትምህርቶች አንጻር የማይመጣጠኑ እንደነበር በዳሰሳ ጥናቱ ወቅት እንደችግር ጎልተው እንደታዩ ጠቅሰዋል፡፡ ከክለሳው በኋላ የነበሩት 20 ትምህርቶችም ወደ 8 ዝቅ ማለታቸውን ያወሱት ቀሲስ ታደሰ በተጨማሪም ሦስት አዳዲስ ትምህርቶች ታክለዋል፡፡ እነዚህም ትምህርተ ክርስትና መግቢያ፣ ትምህርተ አበውና ልሳነ ግዕዝ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችም ተማሪዎቹ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቆይታ ጊዜያቸው የሚወሰን ሲሆን ለእያንዳንዱ ትምህርት ተመጣጣኝ ሰዓት፣ መለያ ቁጥር፣ ቅደም ተከተል እንዲሁም የትኛው የትምህርት ዓይነት ለማን ይሰጥ የሚሉ ጉዳዮች በቀጣይ የሚወሰኑ ናቸው፡፡
በሥርዓተ ትምህርቱ ክለሳ ፕሮጀክት መሠረት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በዚህ ዓመት ተግባራዊ መሆን አልነበረበትም ወይ? ተብለው የተጠየቁት ቀሲስ ታደሰ ሲመልሱ ፕሮጀክቱ ከተጠበቀው በላይ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑንና በክለሳው የተሳተፉት ባለሙያዎች በሥራ መደራረብ ምክንያት ወደ ትግበራ መግባት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ቢሆንም ግን በ2004 ዓ.ም በተመረጡ ግቢ ጉባኤያት የሙከራ ትግበራ እንደሚጀመር አሳውቀዋል፡፡
ይህንን ሥርዓተ ትምህርት ከግብ ለማድረስ የግቢ ጉባኤያትና የማዕከላት ሥራ አስፈጻሚ አካላትን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም በቂ መምህራንን ለማፍራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት ከሥርዓተ ትምህርት ጋር ተዛማጅ ሙያ ያላቸው አባላት ክለሳውን አጠናቆ ትግበራ ለመጀመር እንዲያስችል በትምህርትና ሐዋረያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በመገኘት በሙያቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ ተግባራዊ ካደረገ 7 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ሥርዓተ ትምህርት ከተተገበረ ከ4 ዓመት በኋላ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ 7 አባላት ያሉት ኃይለ ግብር አቋቁሞ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የክለሳ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡