ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ

ማኅበረ ቅዱሳን 20ኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ አደረገ

በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

ሰኔ 20 ቀን 2003ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከግንቦት 19 – ሰኔ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ትግራይ አህጉረ ስብከቶች ሃያ ሰባት ልዑካንን በመያዝ ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረጉን በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል መደበኛ መምህርና የሐዋርያዊው ጉዞ አስተባባሪ ቀሲስ ለማ በሱ ፍቃድ አስታወቁ፡፡

ቀሲስ ለማ በሱፍቃድቀሲስ ለማ በሱ ፍቃድ እንዳሉት ሐዋረያዊ ጉዞው ከሁለት አህጉረ ስብከቶች በተመረጡ ሰባት ዋና ዋና ከተሞች ማለትም ከደቡብ ወሎ /መርሳ ወልዲያ፣ ፍላቂትና ቆቦ/ እንዲሁም ከደቡብ ትግራይ /አላማጣ፣ ኮረምና ማይጨው/ ማኅበሩ በእነዚህ ሁለት የተመረጡ አህጉረ ስብከቶች ሐዋርያዊ ጉዞ ያካሄደበትን ዓላማ ቀሲስ ለማ እንዲህ በማለት አብራርተዋል፤ ሕዝቡና ካህኑ እንዳለ ተከባብሮ የሚኖርበት ቦታ በመሆኑ፥ አህጉረ ስብከቶቹ የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ፣ የታላላቅ አድባራትና ገዳማት ባለቤት እንዲሁም ብዙ ቅርሶች ያሉባቸው በመሆናቸውና የሕዝቡ ባህል ሃይማኖታዊ ስለሆነ እነዚህ እንዳሉ ተጠብቀው እንዲቆዩ ሕዝቡን ለማጽናት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዚህ አካባቢ ከወቅታዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ብዙ ፈተናዎች ይበዛሉ፤ ይህንንም በማስገንዘብ ምእመናን ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ ነው ብለዋል፡፡

1600 ኪሎ ሜትር በሸፈነው ሐዋርያዊ ጉዞ የቀረቡት ትምህርቶችና መዝሙሮች በወቅታዊ የቤተ ክርሰቲያን ችግሮች ዙሪያ ያጠነጠኑ፥ ምእመኑ በሚረዳው ቋንቋ የቀረቡና ምእመኑ ለለውጥ የተነሳሳበት፣ ልዑካኑም ከምእመኑ የተማረበት ነበር ያሉት ቀሲስ ለማ በየጉባኤዎቹ መጨረሻ "ሕያው እውነት" መንፈሳዊ ፊልም መታየቱም የራሱ የሆነ ልዩ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን ጉዞው በብዙው ስኬታማ ቢሆንም፥ ምእመናን የሰሟቸውን መዝሙሮች ለመገዛት ቢፈልጉም አለመመቻቸቱ፣ የጋዜጠኛ አብሮ አለመጓዝ፣ የካሜራ ባለሙያ አንድ መሆንና የመሳሰሉት ችግሮችን እንዳአስተዋሉ ቀሲስ አስታውቀው ለወደፊቱ መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዋና ክፍሉ ለሐዋርያዊ ጉዞ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን በፕሮጀክት እየቀረጸ ለባለሀብቶች፣ በጎ አድራጊዎችና ለመንፈሳዊ ማኅበራት ያቀርባል፡፡ በእነዚህ አካላት ድጋፍ ሐዋርያዊ ጉዞ ያደርጋል፡፡ ለዚህኛውም ሐዋርያዊ ጉዞ 33,000 ያህል የወጣ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች መንፈሳዊ ጉባኤ 25,000 ብር ሲለግሱ  ቀሪውን ወጪ ደግሞ ማኅበሩን መሸፈኑ ታውቋል፡፡ 

ምእመናን

ለሐዋርያዊ ጉዞው መሳካት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት አህጉረ ስብከቶቹ ናቸው ያሉት ቀሲስ ለማ የአህጉረ ስብከቶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ከፍተኛ ቅስቀሳና መመሪያ በመስጠት፤ ሥራ አስኪያጆች፣ ልዩ ልዩ የመምሪያ ኃላፊዎችና የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት በጉባኤ በመገኘት፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ፣ ሕዝቡን በመቀስቀስ ከፍተኛ ቦታ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከጠዋቱ 11፡00 እስከ ሥራ ሰዓት መግቢያና ከሥራ መልስ በሰዓቱ በመገኘት ሥራውን ሳይፈታ ከትምህርቱም ሳይለይ የሚማር፣ ካህናቱም ሕዝቡን በመቀስቀስና የራሳቸውን አስተዋጽኦ በወረብና ቅኔ በማበርከት የተሳተፉበት ጉባኤ ነበር ብለዋል፡፡

ቀሲስ ለማ በጉባኤው ወቅት በማይጨው መካነ ሰማዕት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ባለው የሰማዕታት አፅም የሰማዕታት መታሰቢያ በዓል ለማክበር የመጡት ባለሥልጣናት ታዳሚ የሆኑበት፣ እኛም ለጊዜው ጉባኤውን አቁመን የአከበርንበት ሁኔታ ነበር ብለዋል፡፡

የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ የከተማው ከንቲባ፣ የአርበኞች ፕሬዝዳንት በአደረጉት ንግግር፣ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ የምታደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀው ይሄ ዓይነቱ ጉባኤ የከተማውን መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሚያፋጥኑት ነገሮች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሐዋርያዊ ጉዞ ለቤተ ክርስቲያንዋም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋዕኦ የሚያበረክት ምዕመናንን በእምነታቸው እንዲጸኑ፣ ባህላቸውንና ቅርሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርግ መንፈሳዊና ትውፊታዊ የጉዞ ጉባኤ ነው፡፡