ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 20
ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.
ስለ ሰማዕታት፤ ስለ አማንያን፤ ስለ ከሃድያን
ቍ.744፡- ብፁዕ ኤጲስ ቆጶስ ያዕቆብና ቅዱስ እስጢፋኖስ በእኛ ዘንድ የከበሩ እንደሆኑ ሰማዕታት በእናንተ ዘንድ የከበሩ ይሁኑ፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ትሩፋታቸውም የማይገኝ ነው፡፡
ቍ.747፡- ሰማዕታትም እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው እነዚህ ናቸው፡፡/ማቴ.10፤32/ በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ አሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡
ቍ.748፡- ሰማዕታትን ከሚረዱዋቸው ወገን አንዱ መከራ ቢያገኘው ብፁዕ ነው፡፡ እርሱ የሰማዕታት ተባባሪያቸው ነውና፡፡ በመከራዎቹም ክርስቶስን መስለው እኛንም ከካህናት ብዙ መከራ አገኘን፡፡ ከእነርሱም ዘንድ ደስ እያለን ወጣን፡፡ ስለመድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ መከራን እንቀበል ዘንድ አድሎናልና፡፡ /የሐዋ. 5፤41/ እናንተም እንደዚህ መከራ በተቀበላችሁ ጊዜ ደስ ይበላችሁ፡፡ እናንተ በፍርድ ቀን ትመሰግናላችሁና፡፡
ቍ.749፡- ስለሃይማኖት የሚያሳድዷቸውን ስለጌታችን ትእዛዝ ከአገር ወደ አገር የሚሸሹትን ተቀበሏቸው፤ አሳርፏቸውም፤ ጥቀሟቸውም፤ እንደ ሰማዕታትም አድርጋችሁ አክብሯቸው፡፡ በተቀበላችኋቸውም ጊዜ እናንተ ደስ ይበላችሁ፡፡ ጌታ ክርስቶስ ስለ እኔ ባሳደዷችሁ ጊዜ እናንተ ብፁዓን ናችሁ፤ ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፡፡ እንደዚሁም ከእናንተ አስቀድመው የነበሩ ነቢያትን አሳደዷቸው፡፡ እኔን ካሳደዱ ግን ዳግመኛ እናንተን ያሳድዷችኋል፡፡ ከዚች አገር ቢያሳድዷችሁ ወደ ሌላይቱ አገር ሂዱ ብሏልና፡፡ /ማቴ. 5፤11-12፣ ማቴ. 10፤23/
ቍ.750፡- ዳግመኛም እንዲህ አለ፤ በዚህ ዓለም መከራና ኀዘን ያገኛችኋል፡፡ ወደ አደባባይ ያገቧችኋል፡፡ ለእናንተ ምስክር ሊሆንላችሁ ስለ እኔ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ያደርሷችኋል፡፡ እስከ መጨረሻው የታገሠ እርሱ ይድናል፡፡ ለክርስቶስ እንዳልሆነ የሚክድ ከእግዚአብሔርም ይልቅ ፈጽሞ ራሱን የወደደ ሰው ግን ይቅርታን አያገኝም፡፡ የእግዚአብሔር ጠላት የሰዎች ወዳጅ ሊሆን ወድዷልና፡፡ ስለተባረከችውም መንግሥት ፈንታ የዘለዓለም እሳትን ወድዷልና፡፡ /ማቴ. 10፤17-23/ ስለእርሱም ጌታችን በሰው ፊት የካደኝን ስሜንም የለወጠውን እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ እለውጠዋለሁም አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤8-9/
ቍ.751፡- እንደዚህም ለእኛ ለደቀ መዛሙርቱ ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን ወይም ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድ እኔን አይመስለኝም፡፡ የሞቱንም መከራ ተሸክሞ ያልተከተለኝ እኔን አይመስለኝም አለ፡፡ ሰውነቱን የሚወድ ይጣላት፤ ሰውነቱን የጣላ ግን በእኔ ዘንድ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል? ሰው ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር፡፡ /ማቴ. 10፤37-39፣ ማቴ. 16፤22-27/ ዳግመኛም ሥጋችሁን የሚገድሉትን ሰዎች አትፍሯቸው፡፡ ነፍሳችሁን ግን መግደል አይቻላቸውም፡፡ ነፍስና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሃነም እሳት መቅጣት የሚቻለውን ፍሩት እንጂ አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤4-5፣ ማቴ. 10፤28/
ቍ.754፡- ብንጨነቅም ኃላፊውን ዘመን ስለመፍራት ሃይማኖታችንን አንለውጥ፡፡ አንዱስ እንኳ አለኝታውን ቢክድ ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለጥቂትም ዘመን ከሚሆነው ሞት የተነሣ ቢፈራ ድኅነት በሌለበት በጸና ደዌ ነገ ቢያዝ ከዚች ሕይወት የተለየ ይሆናል፡፡ የወዲያውንም ዓለም ያጣል፡፡ ልቅሶ፤ ጥርስ ማፋጨት ባለበት በጨለማ ውስጥ ለዘለዓሙ ይኖራል፡፡ /ማቴ. 8፤13/
ቍ.755 እና 756፡- ያልተጠመቀ ሰውም ልቡ አይዘን፡፡ ስለ ክርስቶስ የተቀበለው መከራ የተመረጠ ጥምቀት ይሆንለታልና፡፡ የሞቱን ምሳሌ በተቀበለ ጊዜ በጌታ አምሳል ሞቷልና፡፡ ሁለት ልብ አይሁን፡፡ እነርሱ ቢገድሉት እርሱም ቢገደል ይጸድቃልና፤ በደሙ ብቻ ተጠምቋልና፡፡
ቍ.761፡- በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ደማቸውን ላፈሰሱ ሁሉ ባረፉበት ቀን መታሰቢያቸውን ያድርጉላቸው፡፡
ቍ.765:- በሰማዕታት በዓል የሚሰበሰቡትን ሰዎች የሚንቃቸው ሰው ትዕቢትን የተመላ ነውና የተወገዘ /የተለየ/ ይሁን፡፡
ቍ.766፡- ምእመናን የክርስቶስን ሰማዕታት ትተው ዓላውያን ሰማዕታ ወደሚሏቸው ቦታ መሄድ አይገባቸውም፡፡ ስለ ክርስቶስ ፍቅር መጋደላችን እንዴት መሆን እንደሚገባው እነሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጻፈ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንዲህ አለ፤ የክርስቶስን ፍቅር ማን ያስተወናል? መከራ ነውን፤ እስራት ነውን፤ ስደት ነውን ረሃብ ነውን፤ መራቆት ነውን መጣላት ነውን፤ ሰይፍ ነውን፤ ስለአንተ ዘወትር ይገደላሉና እንደሚታረዱም በጎች ሆን ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ የወደደን በመውደዳችን እኛ ድል እንነሳለን፤ እኔም ሊለየኝ የሚችል እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ሞት ቢሆን፤ ሕይትም ቢሆን፤ መላእክት ቢሆኑ፤ አለቆችም ቢሆኑ፤ አሁን ያለውም ይመጣም ዘንድ ያለው ሥራ ሁሉ ቢሆን ኃይለኞችም ቢሆኑ፤ ላይኛውም ቢሆን፤ ታችኛውም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየኝ አይችልም፡፡ /ሮሜ. 8፤35-39/