የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታ በመከበር ላይ ነው
ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.
በ እንዳለ ደምስስ
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደትና የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታ እሑድ ሚያዚያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በድምቀት ተከበረ፡፡ “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት አብረን እንሥራ በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን ህዝብ ግንኙነት ክፍል የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ተጀምሮ በዝማሬ በስብከተ ወንጌል አገልግሎትና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምክር ተካሒዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የምዕራብ ትግራይ ሴቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የአዲስ አበባና የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የምዕራብ ወለጋ ጊምቢና አሶሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል፡፡
በዕለቱ የተጉኙት ሊቃነ ጳጳሳት ማኅበረ ቅዱሳን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፡፡ “የፈተና ጊዜ ነው ፈተናውን የምናልፈው በእግዚአብሔር ረድኤት ነው እግዚአብሔርን በመከተል ነው፡፡ ሌላ ኀይል የለንም፡፡…. እናንተ እግዚአብሔርን መከተል መርጣችኋልና መጨረሻችሁን እግዚመብሔር ያሳመርላችሁ፡፡ በርቱ፡፡” ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡/
“የዚህ ታላቅ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሥርዓታዊ፣ መንፈሳዊና ሰዋዊ ማኅበር አካላት ሁሉ ሥራ እየሠራችሁ ነው እዚህ የደረሳችሁት ምርት እያመረታችሁ ያላችሁባቸው ዓመታት ምርታችሁንም እያያችሁና እየተጠቀማችሁበት የምትገኙበት ዕለት ነውና እንኳን አደረሳችሁ” /ብፁዕ አቡነ ሉቃስ/
ይህ ማኅበር 20 ዓመታት ሲጓዝ እግዚአብሔር ስለረዳው እግዚአብሔር ከማኅበሩ ጋር ስለሆነ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች እግዚአብሔር ስለመራው ነው ዛሬ 20ኛውን ዓመት ለማክበር የበቃው በርቱ፡፡ /ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ/
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ሊሞቱ ሲሉ ካስተማሯቸው ተማሪዎቻቸው /ማኅበረ ቅዱሳንን ከመሠረቱት/ መካከል ሁለቱን፣ አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ አቅፈው፣ ጸሎት አድርገው የሁለቱን ራስ አጋጭተው በመያዝ” በሉ ልጆቼ መቃብሬ ላይ እናንተ ናችሁ የምታለቅሱት እኔ ለኩሼዋለሁ እናንተ አንድዱት አሏቸው ለአትክልተ ጎርጎርዮስ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ምንጭና ግንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም የማኅበረ ቅዱሳን ግንድ ደግሞ አቡነ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚገባውን ምግብ እያበላና እያጠጣ እዚህ ያደረሰው ማኅበር ነው፡፡” /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ/
የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም እንደገለጹት ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ተተኪ ሰባኪያንን ለማፍራት ባደረጉት ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ከግቢ ጉባኤያት 12 ተማሪዎችን በማሠልጠን ጀመረ፡፡ ዛሬ ይህ ጥረት አድጎ በጅማ፣ በአዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባሕርዳርና በማይጨው ሥልጠናው ተጠናክሮ በመቀጠል በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ማፍራት ተችሏል፡፡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በመላው ዓለም በአገር ውስጥና በውጪ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ሲገልጹ ማኅበረ ቅዱሳን 44 ማዕከላት፣ 333 ወረዳ ማዕከላት 181 ግንኙነት ጣቢያዎች 325 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማስተባበርና በመምራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከምዕመናን ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ለተጠየቁ ጥየቄዎች የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከመምህር ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን የማኅበሩ መዝሙር ክፍል አባላት የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርት ማዕከል ሕፃናት ተማሪዎች፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ በየተራ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል፡፡