ሐዘን ሲገጥመን ምን እናድርግ? / 2ቆሮ 5÷1-5 /

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
 
የምንወደው ሰው በሞት ከእኛ ሲለይ በእጅጉ እናዝናለን፤ እናለቅሳለንም፡፡ በርግጥም ማልቀስ በአግባቡ ከሆነ ጠቃሚና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በመሪር ሐዘን የተቆጣውን ሰውነታችንን የሚያስተነፍስ መፍትሔ፤ዕንባ፡፡ የውስጥ ሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ቋጥሮበት ወይም በእግርና በእጁ ላይ መግል የቋጠረ የቁስል ጥዝጣዜ ዕረፍት የነሣው ሰው የቋጠረውን ፈሳሽ ወይም የሚጠዘጥዘውን መግል ሲያፈሱለት ደስ እንደሚለውና ዕረፍት እንደሚሰማው በሐዘን ውስጡ የተጎዳ ሰውነትም ዕንባ ሲያፈስ ዕረፍት ማግኘቱ አይቀሬ ነው፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ዕንባ እንዲኖረው አድርጎ የፈጠረውም ዕንባ ጠቃሚና አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ እስከ አሁን በምናውቀው እንኳ ሦስት ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

የመጀመሪያው ጠቀሜታው ዕንባ በሰው ልጅ ታሪክ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ያለው ነው፡፡ ዕንባ የተጀመረው በአዳምና በሔዋን ነው፡፡ ያለቀሱትም አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በልተው እግዚአብሔርን በመበደላቸው   ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ የተጀመረው በንስሐ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ከዚያ በፊት በሰውነታቸው ያልነበረ ነገር ተፈጠረ ማለት አይደለም፡፡ በሩካቤ መተዋወቃቸውን /የተዋወቁበትን ጊዜ/ ይዘን በዚያ ጊዜ የመራቢያ ብልታቸው ተገኘ እንደማንለው ዕንባውም እንዲሁ ነው፡፡ በቀሌምንጦስ «አልቦቱ ካልዕ ሕሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ፤ ለአዳም ስለ ኃጢአቱ ከማልቀስ /ኃጢአቱን እያሰበ ከማልቀስ/ በቀር ሌላ አሳብ /ግዳጅ/ አልነበረውም» ተብሎ እንደተጻፈ ዕንባ የተጀመረው በዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የዕንባ ቀዳሚ ጠቀሜታ ሰውን በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ተመዝግቧል፡፡ «ወበአንብዕየ አርሐስኩ ምስካብዬ፤ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ» የሚለው ቅዱስ ዳዊት የንስሐ ዕንባውን፣ የጸሎት ዕንባውን ነው፡፡ /መዝ 6÷6/ ጌታችንም በወንጌል «ብፁዓን እለ ይላህው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌስሑ፤ ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4/ ሲል ያስተማረው የሚገባው ለቅሶ ወይም ዕንባና ሐዘን የንስሐ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በሌላም ቦታ «እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፣ ታዘናላችሁና፣ ታለቅሱማላችሁ» /ሉቃ 6÷25/ ሲል ያስጠነቀቀን ጠቃሚውን ዕንባና ሐዘን ለማስተማር ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም «ከሳቅ ሐዘን ይሻላል፣ ከፊት ኀዘን የተነሣ ደስ ይሰኛልና፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት [በንስሐ] ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት [ኃጢአት በሚፈጸምበት ቦታ] ነው» በማለት የንስሐ ዕንባን መፈለግ ጠቢብነት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ከዚህም በላይ በቅድስና ሕይወት የሚኖሩ ቅዱሳን በዐሥሩ መዓርጋት ሲሸጋገሩ አራተኛው መዓርግ አንብዕ ይባላል፡፡ ይህም ፊታቸው ሳይከፋውና ሰውነታቸው ሳይሰቀቅ ዕንባን ከዓይናቸው ማፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ ይህን የመሰለ ጠቀሜታ ያለው በመንፈሳዊነትም የብቃት ደረጃ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ጠቀሜታው ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በዓይኑ ላይ ሁልጊዜም ስስ የሆነች የዕንባ ሽፋን አለችው፡፡ ሳይንስም ጭምር እንደ ተረጋገጠው ዓይንን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠብቁት ነገሮች አንዷና ዋናዋ ይህች ዕንባ ናት፡፡ ስለዚህ በነፋስ፣ በፀሐይ፣ ጨረርና በመሳሰለው ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስበት ይህች ዕንባ ትከላከልለታለች፡፡ በነፋስና በሙቀት ደርቃ እንዳታልቅም እግዚአብሔር በጥበብ እንድንጠቀምባት አድርጓል፡፡ ማንኛውም ሰው ዓይኑን ጭፍን አድርጎ ሲከፍተው በዓይኑ ላይ የነበረችውን ስስ የዕንባ ሽፋን ገፍቶ ወደ አፍንጫ በሚያወርደው ቀዳዳ ያስወግድና አዲስ ዕንባ ይተካል፡፡ በዚህ መንገድ በየደቂቃው ወይም ዓይናችንን ጭፍን ግልጥ ባደረግን ቁጥር ይህችን የዕንባ ሽፋን በአዲስ መልክ     ስለምንቀይር ዓይናችንን በረቂቅ መንገድ እንጠብቃለን፡፡ የሀገራችን ሰው «የዓይን አምላክ» የሚለው ለዓይን ይህን የመሰለ ሰፊ የጥበቃ መንገዶችን እግዚአብሔር ስለፈጠረልን ነው፡፡ በመጽሐፍም «ዕቀበኒ እግዚኦ   ከመ ብንተ ዓይን፤ አቤቱ እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ» የሚል ቃል ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ዕንባ ዓይንን እንዲህ አድርጎ ለመጠበቅ ጠቃሚ ነው ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው ጠቀሜታው ደግሞ ሐዘንን ማስወገጃ ማስተንፈሻ የሐዘን ማቅለያ መሆኑ ነው፡፡ ከዛሬው የጽሑፋችን ዓላማ ጋር የሚገናኘውም ይኽኛው ነው፡፡ የመጀመሪያው  አባታችን አዳም የመጀመሪያ ልጁ አቤል በሞተ ጊዜ እጅግ ተጨንቆ ሰውነቱ ሁሉ አባብጦ ተነፋፍቶም እንደነበር ትውፊቱን የመዘገቡ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በመጀመሪያ ሞት ከዚያ በፊት አይታወቅምና ምን ማድረግ እንደነበረባቸው እንኳን አዳምና ሔዋን አያውቁም ነበር፡፡ ዳግመኛም በዚያ ጊዜ     የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በምድር ላይ እነርሱ ብቻ ናቸውና የሚያጽናናቸውም ሆነ የሚመክራቸው ሰው ማንም አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት አዳም ሰውነቱ በሐዘን ተዋጠ፤ ተጨነቀ፤ ሰውነቱም ተቆጣ፤ ታመመም፡፡ በዚህ ጊዜ መላእክት ወደ አዳም መጥተው እንዲያለቅስ አሳዩት፤ አስተማሩት፡፡ እርሱም ሲያለቅስ ውጥረቱ በረደ፤ የተቆጣ አካሉ ተመለሰ፤ ሰውነቱም ዕረፍት አገኘ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሐዘን የሚገጥመንን የሰውነት መታመምና ከባድ ጭንቀት በዕንባ መገላገሉን ይዘን ይኸው እስከ አሁን ዘልቀናል፤ ወደፊትም እንቀጥላለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አልዓዛርን ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከሞት ሊያስነሣው ሲሔድ በእኅቶቹ ቤት እንደደረሰ መጀመሪያ አልቅሶለታል፡፡ /ዮሐ 11/፡፡ ይህም በሞት ለተለየን ሰው በሐዘን ጊዜ ማልቀስ ተገቢ መሆኑን ይህንም በማድረጋችን ኃጢአት እንደማንሠራ ያስረዳናል፡፡ ጌታ ቸር አምላክ፣ ሰውንም ወዳጅ ነውና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከሞት እንደሚያስነሣው እያወቀ እኅቶቹን ሲያገኛቸው መጀመሪያ ሐዘናቸውን በልቅሶ ተካፈለ፡፡ ከዚያም እነርሱን አጽናንቶ ሞቶ የተቀበረውን ከሞት አሥነሥቶ ከመቃብር አውጥቶታል፡፡ በዚህም እጅግ ብዙና ሰፊ ትምህርቶችን አስተምሮናል፡፡

ለክርስቲያኖች በሐዘን ጊዜ ማድረግ ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው ነገሮች መሠረታዊ የሆኑት የትምህርት መነሻዎች ከላይ የጠቀስናቸው እነዚህን የመሰሉት በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጡት ታሪኮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በሞት ለተለየን ቤተሰባችን የተሰማንን ሐዘን በለቅሶና በዕንባ መገላገል ተገቢ ቢሆንም ለእነዚህም ጊዜና መጠን አላቸው፡፡

በጊዜ ያልተወሰነ በመጠን ያልተገደበ ከሆነ እንኳን ሐዘን፣ ለቅሶና ዕንባ ቀርቶ ደስታና ጨዋታም በእጅጉ ጎጂ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ሐዘንን በዕንባ መገላገል ጠቃሚና እግዚአብሔር የፈቀደው ቢሆንም   ከመጠኑ ሲያልፍ ደግሞ ከጥቅሙ በተቃራኒ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ በበጋ የደረቀች መሬትን ለማርጠብ፣ ለማለስለስና እህሉንና ሣሩን ለማብቀል የክረምት ዝናም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመጠን በላይ ከወረደ ግን እርሻውን አጣጥቦ በመውሰድ፣ የበቀለውን አዝመራ በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ለቅሶና ዕንባም እንዲሁ ነው፡፡ ዓይንን ለመጠበቅና ሰውነታችን በሐዘን እንዳይጎዳ ለመከለካል የተፈጠረውን ዕንባ ስናበዛው ዓይናችንን ለማጥፋት፣ ሰውነታችንም ጎርፍ እንደበላው መሬት ሸርሸሮ ለማይድን በሽታ    ያበቃዋል፡፡ ስለዚህ ልክና መጠኑን ጠብቆ በጊዜ ተወስኖ የሚፈጸም ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፡፡ የዓለም ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል፡፡» /2ቆሮ 7÷10/ የሚለን ለዚህ ነው፡፡

አንድ ሰው ከቤተሰብ አንዱ በተለየው ጊዜ የሚያደርገው ነገር በመጠንና በሥርዓት ካልሆነ እንኳን ሥጋውን ነፍሱንም ጨምሮ ይጎዳዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዘናቸው ምክንያት እግዚአብሔርን ያሳዘኑ እርሱም   ያዘነባቸው ሰዎች አሉ፤ እንዲሁም ደግሞ በሐዘናቸው እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ ሰዎች አሉ፡፡ በወንጌል እንደተጻፈው የሰማዩን ቤት የማያስቡ፤ በጎ የሠሩ ሰዎች በሰማይ ከእግዚአብሔር የሚቀበሉትን በጎ ዋጋ ረስተው የሰውን ሞት ተስፋ እንደሌለው እንደ እንስሳ እና እንደ አራዊት ሞት ወይም ተቆርጦ እሳት በልቶት አመድ እንደሚሆን ካለበለዚያም ወድቆ በስብሶ አፈር ሆኖ እንደሚቀር እንደ ዛፍ እንደ ቅጠል ቆጥረው መሪር ሐዘን የሚያዝኑ ሰዎች ሰነፎች ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያሳዝናሉ፤ እግዚአብሔርም ያዝንባቸዋል፡፡ «ሙታናቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸው» ብሎ ጌታ በወንጌል የተናገረላቸው ሰዎች የሰውን ክብር እና የእግዚአብሔርን ኃይል ለማያውቁ ሰዎች ነው፡፡ እንደዚህ ያሉት ሰዎች «ሙታን» የተባሉት በምድር ላይ በሕይወት እየኖሩ ነው፡፡ ሙታን የተባሉት የሞተ ሰው ሥጋው ምንም ሊያውቅ እንደማይችል እነዚህም እየኖሩ የማያውቁና የማያስታውሱ ስለሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ትንሣኤ  እንደሌለን በሰማይ በአባታችን ቤትም ክብርና ጸጋ እንደማይጠብቀን አድርጎ የሚያዝንና የሚያለቅስ ከሆነ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን እንደተጻፈውም ቆሞ የሚሔድ ነገር ግን የሞተ ይሆናል፡፡

በተጠቀሰው መንገድ እግዚአብሔርን ያሣዘኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ እግዚአብሔርን ያስደሰቱትም ደግሞ አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱና ዋናው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው ዳዊት ልጁ በታመመ ጊዜ በእጅጉ አዝኖ ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ ግን ያደረገው ብዙዎችን አስገርሟል፤ አርአያነቱም ታላቅ ነው፡፡ ታሪኩን የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡ «እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሰፈ፣ እጅግም ታምሞ ነበር፡፡ ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፣ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ፡፡ የቤቱም ሸማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፣ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም፡፡ በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ፡፡ የዳዊትም ባሪያዎች ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን ?» በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ፡፡ ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደሞተ አወቀ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹን ሕፃኑ ሞቶአልን? አላቸው፡፡ እነርሱም፡- ሞቶአል አሉት፡፡ ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፣ ተቀባም፣ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ፡፡ ወደ ቤቱም መጣ፣ እንጀራ አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም አቀረቡለት፣ በላም፡፡ ባሪያዎቹም፡- ይኽ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት፡፡ እርሱም፡- ሕፃኑ ሕያው ሳለ እግዚአብሔርም ይምረኝ፣ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁም፡፡ አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለምንድር ነው? በውኑ  እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን?  እኔ ወደ እርሱ እሔዳለሁ እንጂ  እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ፡፡» /2ሳሙ 12÷15-23/፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ንጉሡ ዳዊት ልጁን ምን ያህል ይወደው እንደነበር፤ ከዙፋኑ ወርዶ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ፤ ማቅ ለብሶ አመድ ነስነሶ በጾምና በጸሎት እንደ ተጋደለ እንመለከታለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሞተ በኋላ በሰማይ የሚደረገውን ስለሚያውቅ «እኔ ወደ እርሱ እሔዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመጣም» በማለት በሰማይ ቤት ያለውን ጽኑ እምነት፤ ሞተ ማለትም ወደ እግዚአብሔር ሔደ ማለት እንጂ ሌላ ማለት ስላልሆነ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሔዶ ሰግዶ፤ እግዚአብሔርንም አመስግኖ እንደተመለሰ ይነግረናል፡፡

በመጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈውን ስንመለከት ደግሞ በሐዘን ጊዜ እግዚአብሔርን እንዴት ማስደሰት እንደሚቻል እንረዳለን፡፡ ኢዮብ በአንድ ቀን ዐሥር ልጆቹ ሞተውበታል፤ በዚያው ቀንም ሊቆጠር የማይችል ሀብትና ንብረቱን አጥቷል፤ እርሱ ግን «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ» አለ እንጂ አላማረረም፤ ሐዘኑንም በቅጡና በሥርዓቱ ተወጥቶታል፡፡ በዚህ ምድር ያለን ሰዎች ለሰው የማይቀረው ሞት አንዱ ቤተሰባችን ሲጠራው ከእኛ መካከልም በሞት ሲወሰድ ተመልክተን ይሆናል፡፡ እንደ ኢዮብ ግን ዐሥር ልጆቹ በአንድ ቅጽበት ያጣ ሰው የለም፡፡ በዚህም ከእግዚአብሔር እጥፍ ድርብ ዋጋ አገኘበት እንጂ አልተጎዳበትም፡፡ እንዲያውም ከቀደሙት የበለጡ ልጆች፣ ከቀድሞው ዕጥፍ ድርብ የሆነ ሀብት ተሰጥቶት፤ እንደተረገመ የቆጠሩት ሰዎች ሁሉ አፈሩ፤ እርሱ ግን በማጣቱም በማግኘቱም ጊዜ፤ በሐዘኑም በደስታውም ጊዜ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ ተባረከበትም፡፡ ታዲያ የሕይወታችን እውነታ እንዲህ ሆኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ያለ መጠን የምናዝነው፣ የምንፈተነው እና የምንጨነቀው ለምንድን ነው ? እንደ ኢዮብ እንደ ዳዊት ለመሆንስ ለምን ተሳነን ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፤ ተገቢም ነው፡፡

የዚህን መልስ በአግባቡ ከተረዳን እኛም እንደ ሌሎቹ ብርቱዎች የማንሆንበት ምክንያት አይኖረንም፡፡ ለጥያቄያችን መልስ የሚሆነውንም ቅዱስ መጽሐፍ ስለመዘገበልን ከዚህ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

«ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈረስ፣ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፣ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን፡፡ ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፣ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን፡፡» /2ቆሮ 5÷1-5/ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ እምቅ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን አስቀምጦልናል፡፡እነዚህን በአግባቡ ከተረዳን ብዙ ጥያቄዎቻችን በአግባቡ ይመለሳሉ፡፡ ስለዚህ ፍሬ አሳቦችን በቅደም ተከተል እንመለከታቸዋለን፡፡ ለዚህ ጽሑፍ በሦስት ብቻ ከፍለን እንመለከታቸዋለን፡፡

ይቆየን
ምንጭ፡ሐመር ኅዳር 2003 ዓ.ም