የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በድምቀት ተከበረ

ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

img 0442የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል “ሕያው ዜማከ ወሕያው ድርሳንከ” በሚል መሪ ቃል ስድስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል አዳራሽ ግንቦት 11 ቀን 2005 ዓ. ም. በድምቀት ተከብሯል፡፡

ከየአድባራቱና ገዳማት የመጡ ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን የተገኙ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት ዶክተር ውዱ ጣፈጠ በቅዱስ ያሬድ ሕይወት ታሪክና ሥራዎቹ ላይ ያተኮረimg 0335 ጥናት አቅርበዋል፡፡ ከሊቃውንቱ መካከልም በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት የመጻሕፍት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አዲስ የወንጌል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ከሊቃውንቱ መካከል የቤተልሔም፤ የቆሜና የአጫበር ዜማዎችን በየተራ ያቀረቡ ሲሆን የመርሐ ግብሩ ልዩ ድምቀት ነበር፡፡

በራስ ዳሸን ተራራ ላይ በችግር ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ያሬድ ገዳምን ለመርዳት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተደረገ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል እጅግ አስቸጋሪና የአንድ ቀን ሙሉ የእግር ጉዞ በማድረግ የሚደረስበትን በበረዶ የተከበበው ገዳም ድረስ በመሄድ ገዳሙ ያለበትን ችግር ለማጥናት ጥረት ማደረጉ ተገልጻል፡፡

በገዳሙ ከ70 በላይ መነኮሳትና መናንያን የሚገኙ ሲሆን ከቦታው ተራራማነት የተነሳ ምእመናን የማይደርስበት ቦታ በመሆኑ ገዳማውያኑ የሚረዳቸው በማጣት የአልባሳት፤ የምግብና የመጠለያ ችግር እንዳጋጠማቸው ተጠቅሷል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ከገዳሙ አቅራቢያ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ደባርቅ ከተማ ላይ ለገዳሙ አገልግሎት የሚውል የአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ከከተማው አስተዳደር በመረከብ ሕንፃ ለመገንባት ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው ዙርም 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመገለጹ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ተካሂዷል፡፡

በዕለቱ ከተገኙ ምእመናንም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ቃል የተገባ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ለሕንፃጻው ማሠሪያ የሚውል ገንዘብ ለመላክ ቃል ገብቷል፡፡ማኅበረ ቅዱሳን ለአክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም የብር መቋሚያና ጸናጽል በስጦታ ያበረከተ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳimg 0363 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2004 ዓ.ም. የተመረቀውና የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚው ዶክተር አምኃ መሸሻ ለቅዱስ ያሬድ ገዳም ሜዳልያውን አበርክቷል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለምእዳን “ከየገዳማቱና አድባራቱ በዓሉን ለማክበር በመካከላችን የተገኙት ሊቃውንት አባቶቻችን የቅዱስ ያሬድን ፈለግ በመከተል ቤተ ክርስቲያን ያለተተኪ እንዳትቀር አገልጋዮችን በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ፋብሪካዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ ቀዳሚ ዜማ ዘያሬድ የሊቃውንት ማኅበር ያሬዳዊ ዝማሜና ወረብ አቅርበዋል፡፡