የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ የልደት በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ተከፈተ
ዲ/ን መርሻ አለኸኝ(ዶ/ር)
የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት በግዮን ሆቴል ሳባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከፈተ፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያዎች ሓላፊዎች፣ በዋና ዋና አብነት ት/ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንና የመንግሥትና ልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንት ተገኝተዋል፡፡
ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ማኅበሩ ቅዱሳት መካናት ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩባቸውን ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ አየሠራ እንደኾነ ከገለጹ በኋላ፤ ሊቁ ለሀገራችን ከሰጠው አበርክቶ አንጻር ማኅበሩ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን የቅዱስ ያሬድን የ1500ኛ ዓመት የልደት በዓል በሰፊ ዝግጅት ለማክበር እንደወሰነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዐውደ ጥናቱን በንግግር ከፍተዋል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ቅዱስ ያሬድ ለሀገራችን ካበረከተው አስተዋጽዖ አንጻር የልደት በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ በእጅጉ ተገቢ እንደኾነ በመጥቀስ፤ ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን ካመሰገኑ በኋላ ማኅበሩ በተለይ ቅዱሳት መካናትንና አድባራትን በመርዳት በኩል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያግዝ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ ወርቅነህ አክሊሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሀብት ከቤተ ክርስቲያኗ አልፎ የሀገር ሀብት በመኾኑ ሁሉም እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲያደርግለት፣ በሕይወት ያሉትን የዜማውን ሊቃውንት ከመንከባከብ ባሻገር መዳከም የሚታይበትን የዜማውን ሽግግር ለማንቃት ተረካቢዎችን ማፍራት እንደሚገባ በመግለጽ የጉባኤውን ታዳሚ ቀልብ የገዛ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከዐውደ ጥናቱ መርሐ ግብር ለመረዳት እንደሚቻለው በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ዜማዎቹ ዙሪያ በዘርፉ ሊቃውንትና ተመራማሪዎች አምስት ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ነገ እሑድ ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ፡ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና ምእመናን በተገኙበት በሰፊው እንደሚዘከር ታውቋል፡፡