“መላእክት ሁሉ ረቂቃን አይደሉምን የዘላለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው ለአገልግሎት ይላኩ የለምን” ዕብ.1፡14

 ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም.

kedus kerkos eyeleta

መላእክት እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን የሰማይንም ሠራዊት ፈጠረ በሚለው አንቀጽ እንደተጠቀሰው፤በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሑድ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረዋል፡፡ እግዚአብሔር አፈጣጠሩ ድንቅ ነውና መላእክትን እንደ እሳትና ነፋስ የማይዳሰሱ የማይታዩ አድርጎ ፈጥሯቸው ያመሰግኑታል፡፡ ዘፍ.1፡1 መዝ.108፡4፣ ዕብ.1፡12

እግዚአብሔር የፈጠራቸው 20 ዓለማት ሲኖሩ ሦስቱ፤ ኢዮር፣ ራማ፣ ኤረር የመላእክት ከተሞች ናቸው፡፡

 

መላእክት በ30 ነገድ በ10 አለቃ ተከፋፍለው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረትን የሚለምኑ ናቸው፡፡ 10ሩ ነገድ መኳንንት ይባላሉ፡፡ እነዚህ መላእክት ዓለትን ተራራን ሠንጥቀው የሚሄዱ፣ ቀስት መሳይ ምልክት ያላቸው፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ጊዜ ነፍስና ሥጋን የሚያዋሕዱ መላእክት ሲሆኑ አለቃቸው ሰዳክያል ይባላል፡፡

10ሩ ነገድ ሊቃናት ሲባሉ የእሳት ሠረገላ ያላቸው፣ ኤልያስን በሰረገላ የወሰዱት መላእክት ሲሆኑ አለቃቸው ሰላትያል ይባላል፡፡ 10ሩ ነገድ መላእክት ይባላሉ፡፡ ሕይወት የሌለውን ነገር ሁሉ በሥርዓት እንዲቆዩ የሚጠብቁ ሲሆኑ አለቃቸው አናንያል ይባላል፡፡ የኃይላት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን የአርባብ አለቃቸው ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

መላእክት ብርሃናዊ መልአክ ስለሆኑ የሚያግዳቸው የለም፡፡ አለት ተራራን ሰንጥቀው የመግባት አንዱ በአንዱ የማለፍ ችሎታ አላቸው፡፡ እንደ መብረቅ እንደ እሳት የመሆን ባሕርይ አላቸው፡፡

መላእክት ትጉኃን ናቸው፡፡

“መላእክት ሁሉ ረቂቃን አይደሉምን የዘላለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው ለአገልግሎት ይላኩ የለምን” ዕብ.1፡14 እንዳለ እረፍታቸው ምስጋና ምስጋናቸው እረፍት ሆኖ ሌት ተቀን ይተጋሉ፡፡

መላእክት በእግዚአብሐር ፊት ይቆማሉ፡፡

መላእክት ለምሕረት በእግዚአብሐር ፊት ይቆማሉ፡፡ “በእግዚአብሔር ፊት የቆሙ ሰባት መላእክት አየሁ፡፡” ራዕ.8፡2፡፡እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሉቃ.1፡19፣ ዘካ.1፡12 ፡፡
መላእክት ተራዳኢ ናቸው፡፡

ቅዱስ ዳዊት “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራሉ ያድናቸውማል” መዝ.33፡7፡፡ ሲል በዘፍ.48፡16 “ከክፉ ነገር የዳነን የእግዚአብሔር መልአክ እርሱ እኒህን ሕፃናት ይባርክ” በማለት ተራዳኢነታቸውንና በረከትን የሚያሳድሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ “ያን ጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመልከትና እግዚአብሔር በዕውነት መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና ከአይሁድ ሕዝብ ምኞት ሁሉ እንዳዳነኝ አወቅሁ አለ ሐዋ.12፡16፡፡ እነሆ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ ዳን.10፡13 ማቴ.18፡10 የመላእክትን ተራዳኢነት ያስረዳል፡፡

ጠባቂዎቻቸው ዘወትር የአባቴን ፊት ያያሉ፡፡

መላእክት ይጠብቁናል

በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ መላእክቱን ስላንተ ያዛቸዋልና እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡናል” መዝ.90፡11-12፡፡ “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። ማቴ18፡10

“በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀ ቤት ሥፍራ ያገንህ ዘንድ እነሆ አኔ መልአኩን በፊትህ እሰዳለሁ በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት አትሥሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት ዘፀ.23፡20-22 መላእክት ዕጣንን ያሳርጋሉ፣ ራዕይ.5፡8፣ 8፣3 ፡፡ መላእክት የጸጋ ስግደት ይሰገድላቸዋል ዳን.5፡፡ኢያ.5፡13፣ ነገ.19፡6 15፣ ዘፍ.22፡3 መላእክት የምንመገበውን ይሰጡናል/ይመሩናል/ ት.ዳ.3 መላእክት ከእስር ያስፈታሉ ሐዋ.12፡6፡፡ መላእክት ይፈውሳሉ “እግዚአብሔር የበለዓምን ዐይን ከፈተ ዘሁ.22፡31

የመላእክትን አፈጣጠራቸውን፣አገልግሎታቸውን በመጠኑ ከተረዳን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ሐምሌ 19 ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣን ያዳነበት፣የጸናናበት ለክብር ያበቃበትን ቀን በድርሳነ ገብርኤል የተገለጸውን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ድርሳነ ገብርኤል ዘሐምሌ

በአገዛዝና በቅድምና ትክክል የሆነ፣ ከመታሰቡ አስቀድሞ ሁሉን መርምሮ የሚያውቅ፣ ክረምትን በየዓመቱ የሚያመጣ፣ ሰማይን በደመና የሚጋርድ፣ ምድርን በልምላሜ የሚሸፍናት፣ የባሕርን ውኃ በእፍኙ የሚለካ፣ ምድርን በስንዝሩ የሚመጥናት ከኛ ዘንድ ለሱ ምስጋና የሚገባው፣ ለኛ ሕይወትን የሚሰጠን አንድ አምላክ በሚሆን በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን በሐምሌ 19 ቀን የሚነበብ የሚጸለይ የሰማያውያን አለቃ የሚሆን የቅዱስ ገብርኤል ድርሳን ይህ ነው፡፡

እለ እስክንድሮስ የተባለ መኰንን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑትን ክርስቲኖች ለመቀጣትና ሌሎችም ፈርተው ክርስትናን እንዳይፈልጉ ለማድረግ አስቦ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ፣ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል አንድ ላይ ተቀላቅሎ በብረት ጋን እንዲፈላ አዝዞ ነበር፡፡ ጭፍሮቹም እለስክንድሮስ እንዳዘዛቸው ከአደረጉ በኋላ ያዘዝኸንን ሁሉ ፈጽመን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፤ ድምፁ እንደነጐድጓድ ይጮሃል፤ ወላፈኑም እንደ ፀሐይ ነፀብራቅ በሩቅ ይጋረፋል፤ የፍላቱም ኀይል አሥራ ዐራት ክንድ ያህል ከፍታ ወደላይ ይዘላል፤ እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት፡፡

በዚህ ጊዜ ሕፃን ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በክርስቶስ ስም ስለሚያምኑ አሥረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ሊጨምሯቸው ከእሥር ቤት አወጧቸው፡፡ ፍላቱ ወደ ላይ በሚዘል ብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው የእነዚህን ቅዱሳን አሟሟት ያዩ ዘንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ ታዘዘ፡፡

በዚህ ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማችና ባየች ጊዜ ተሸበረች፤ ተዘጋጅቶላት ከነበረውም ክብር ልታፈገፍግ ሞከረች፡፡

ልጅዋ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናት ሆይ ከዚህ የብረት ጋር ግርማ የተነሣ አትፍሪ፤ ድንጋፄም አይደርብሽ፤ አናንያንና አዛርያን፣ ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከዕቶነ አሳት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ ፡፡ እናት ሆይ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለማዳን ስትይ በማያልፈው በዘለዓለም እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሸን? ይህስ አይሆንም፤ ይቅርብሽ፤ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናቴ ሆይ ሶስናን ከእደ ረበናት፣ /መምህራነ አይሁድ/ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ እሱ እኛንም ከዚህ የጋን ፍላት ያወጣናል፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን፣ ልጆቹንና ሚስቱን፣ በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባጣ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ /ወሰደ/ እግዚአብሔርም እንደ ወደደ አደረገ፤ ከማለት በስተቀር ምንም የተናገረው ክፉ ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም የሱን ዓላማ በመከተል ይህን መከራ ልንታገሥ ይገባናል፤ አላት፡፡

ነገር ግን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በዚህ ምክር ልትጽናና ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ አምላኬ ሆይ ይህችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለህ ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን ይህን እንዳታደርግ ግን ቸርነትህ ትከለክልሃለች፡፡

አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ አንድዱት፤ ቅጠሉን ግን ጠብቁት፤ ብለህ ልታዝ መለኮታዊ ባሕርይህ አይደለም፤ ነገር ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም ባንድ ጠብቁት፤ ብለህ ታዝዛለህ እንጂ፤ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይህን ያየ ሁሉ ማዳን የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከዚህ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡

አቤቱ ዲያብሎስም ከባለሥልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ፤ ቅዱሳኖቹንም ድል ነሣኋቸው፤ ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማሁ፤ በማለት እንዳይደነፋ ለናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ስጣት፤ ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከኢየሉጣ አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡

ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ በሰማያዊ መንግሥት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታህ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ፤ እነሆ በብረት ጋኑ ውስጥ የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም /በምንጭ/ ላይ እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቼዋለሁና አለችው፡፡

እኒህም ቅዱሳን ይህን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን የሚቆለምም፣ ልብን የሚያቀልጥ፣ ሆድን የሚሠነጥቅ፣ ሥርን የሚበጣጥስ መሣሪያ ካለበት የብረት ጋን ውስጥ ጨመሯቸው፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፤ ከቅዱሳኑም አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱ ጋን ማቃጠሉና መፍላቱም ፀጥ አለ፡፡

ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ በጭንቃቸው ጊዜ ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ይህ መልአክ ከሰማዕታትና ከጻድቃን ጎን እንደማይለይ እወቁ፡፡ ለኃጥአንም ኃጢአታቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላቸዋል፡፡ እኛም የዚህን የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓሉን በየወሩ እያከበርን አማላጅና ወዳጅ እናድርገው፤ በዚህም በሚመጣውም ዓለም ሊረዳን ይችላልና፡፡

ዳግመኛም እለ እስክንድሮስ ሀሳቡ ሳይሳካለት ስለቀረ አሥራ አራት የሾሉና የጋሉ የብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ በኢየሉጣ አካል፣ ሰባቱን በቂርቆስ አካል ይቸነክሯቸው ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡

ዳግመኛም የሕፃንን የእራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ፡፡ አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህን መከራ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው በገመድ እንዲጎትቱት አዘዘ፤ በዚህም ጊዜ መልአኩ አዳነው፡፡ ሕዝቡም ይህን ሁሉ ተአምር በአዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ ቅዱስ ገብርኤልንም አከበሩት፡፡ እነዚህን ቅዱሳን ረድቶ ለክብር ያበቃ ቅዱስ ገብርኤል እኛንም በሃይማኖት ጸንተን ለክብር እንድንበቃ ይርዳን፡፡

የቅዱስ ገብርኤል፣የቅድስት ኢየሉጣና የቅዱስ ቂርቆስ በረከት አማላጅነት አይለየን፡፡