hawassakidusgebriel.jpg

የሐዋሳ ጉዳይ 1

hawassakidusgebriel.jpgባለፉት ጥቂት ወራት በሐዋሳ ከተማ፥ በተለይም ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ ቆይተዋል። ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ወደ ሐዋሳ የተጓዘው ሪፖርተራችን ተሥፋሥላሴ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ፥ የዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪንና ምእመናንን አናግሮ ዘገባ አጠናቅሯል።
በመጀመሪያ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገ/ጻድቅ ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ በሁለት ክፍል እናቀርባለን። በቀጣይነት በቦታው ያለውን ዝርዝር ሁኔታ የሚመለከት ሐተታዊ ጽሑፍ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለማስነበብ እንሞክራለን።
  • ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም ሆነ እርስዎ ከመጣችሁ ጥቂት ጊዜያት ቢሆንም፥ በሀገረ ስብከቱ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ በጎ ነገሮችና ፈተናዎች ካሉ ቢገልጹልን?

እኔም ሆንኩ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተመድበን ከመጣን ወደ 3 ወር የሚጠጋ ጊዜ ብቻ አስቆጥረናል፡፡ እኛ ከመምጣታችን በፊት በቦታው ላይ አንዳንድ አለመግባባቶችና ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ነው እኛ የመጣነው፡፡ ቢሆንም ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን የማረጋጋት፣ የመምከር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ደንብ፣ መመሪያ፣ ሥርዓትና ሕጉን የማሳወቅ፣ ሰዎች ሁሉ ወደ በጎና ወደ ቀና አስተሳሰብ እንዲመጡ የመመለስ፣ ያልተረዱት ነገር ካለ እንዲረዱ ያላወቁት ካለ እንዲያውቁ፤ አጠቃላይ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ሕግ በተከተለ መልኩ መንገዶችን የማሳየት፣ የማስተካከል፣ ይሄኛው ያስኬዳል፣ ይሄኛው አያስኬድም በማለት  እየነገርንና እያስተካከልን ነው የቆየነው። ችግሮቹ ምን እንደሆኑ፥ አነሣሣቸው ምን አንደሆነ በውል ባናውቀውም ከኛ በፊት አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ሽማግሌዎችን ካህናትን፣ ማኅበረ ምዕመናንንና፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶችንና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር በተቻለ መልኩ ችግሮች በሰላም፥ በውይይትና በመግባባት የሚፈቱበትን የተቻለውን ያህል ብዙ ጥረት አድርገናል። ከዚህም በኋላ የሀገር ሽማግሌዎችም እንዲሁ ሃሳቡን እንዲያግዙንና ድጋፍ እንዲያደርጉልን አድርገን፤ እነርሱም የሚቻላቸውን በትብብር መልክ ሰርተዋል፡፡ የመንግሥት አካላትም ጭምር በእውነት ለቤተ ክርስቲያናችን በሚያስፈልገው በማንኛውም መልኩ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ በተለያዩ በፀጥታ፣ በፖሊስ፣ በደህንነት በቀበሌም በማንኛውም ሕዝባውያንና መንግስታውያን ድርጅቶች የሚገኙ፥ ቤተክርስቲያኒቷ ሕጓ፣ ሥርዓቷ፣ ደንቧ ተጠብቆ በአግባቡ ሥራዋን እንድታከናውን፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ በሚተላለፈው መመሪያና ውሳኔ መሠረት፥ ማንኛውም ሥራ መመሪያና ደምቡ ተጠብቆ እንዲሠራ፣ ሁሉም የሚቻላቸውን ከፍተኛ ድጋፍን እገዛ እያደረጉልን ይገኛሉ፡፡ በዚህ አይነት ነው ሥራዎችን እየሠራንም እያስተካከልን የቆየነው፡፡ እንግዲህ ከቆየታው ማነስ የተነሣ /ከመጣን አጭር ጊዜ ቢሆንም/ በተቻለ መልኩ ችግሩን ከማስወገድ አንፃር ሥራዎችን በተዋረድ እያከናወንን ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ወደየ ወረዳዎቹ እንቅስቄሴ በማድረግ ለየወረዳዎቹ ሊቃነ ካህናትና ለየወረዳዎቹ ቤተክህነት ኃላፊዎች እንደሁም ለርዕሰ ከተማዋ /ሐዋሳ/ አድባራት አስተዳዳሪዎች ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት እንዲሁም ጸሐፊዎች በሁለቱም የብፁዕነታችን ሀገረ ስብከቶች ለሚገኙት፣ ሰበካ ጉባኤን ለማጠናከር፤ ሰንበት ትምህርት ቤትን ለማደራጀት፣ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ የአሥራት በኩራትና የሰበካ ጉባኤ ክፍያዎችን ለማጠናከር በብፁዕነታቸው መሪነት የ3 ቀናት ሴሚናር አካሂደናል፡፡

  • ከመጣችሁ በኋላ ችግሮችን በመፍታት እንዳሳለፋችሁ ገልጸዋል፡፡ የችግሮቹ አካሄድ አፈጣጠር ምን እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉ?
በሀገረ ስብከታችን ከርዕሰ ከተማው በስተቀር ቢያንስ ከ125 በላይ አብያተ liquehiruyan.jpgክርስትያናትና 13 የወረዳ ቤተ ክህነቶች ይገኛሉ፡፡ በሌሎቹ አብያት ክርስቲያናት ምንም ዓይነት የተለየ ችግር አላጋጠመንም አልፎ አልፎ አንዳንድ ቦታዎች ቢታዩም ይሄን ያህል አይደሉም፡፡ ትልቁና ከፍተኛው ችግር አልፎ አልፎ እየተነሣ ያለው በመንበረ ጵጵስናው ርዕሰ ከተማ በሚገኘው ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ነው፡፡ ውሳኔዎች፣ መመሪያዎች፣ ሰርኩላሮች ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ወደ ሃገረ ስብከቱ በተዋረድ ይመጣሉ፤ ተወረዱንም ጠብቆ ወደ አድባራትና ገዳማት ይወርዳሉ፡፡ በደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪና ሰበካ ጉባኤ በኩል ግን መመሪያን የመፈጸምና የማስፈጸም፥ የቃለ አዋዲውን ሕግ የመጠበቅና የማስጠበቅ፤ በአጠቃላይ ግቢውን ከሁከትና አላስፈላጊ ከሆነ ነገሮች ሁሉ የመጠበቅና የማስጠበቅ ጉዳይ የሰበካ ጉባኤ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አባላቱና የደብሩ አስተዳዳሪ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት ነው ይሄ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ያለው። ይሄንንም ችግር እንዲፈቱ ለአስተዳዳሪው በብጹዕነታቸው ከአንድም ሁለት ሦስቴ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡ የሰበካ ጉባኤውንም በጋራ አሰባስበን የአቅማቸውን ቃለ ዐዋዲውን ጠብቀው እንዲሠሩ፥ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲገኝ ደግሞ ለሃገረ ስብከቱና ለመንግሥት አካላት አቅርበው እንዲያስከብሩ፣ ግቢውን እንዲያስጠብቁ፤ ተደጋጋሚ ውይይቶች የጽሑፍም ሆነ የቃል መመሪያዎች ተሰጥተዋል፤ ነገር ግን ተፈጻሚነት ሳያገኙ እየቀሩ፥ በቸልታ እየታለፈ ችግሩ ወደ አለመወገድና መድረኩ በተለያየ ጊዜ የጭቅጭቅ መድረክ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ከፍተኛው ይሄ ችግር የሚታየው የገዳሙ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ነን በሚሉት በኩል ነው፡፡ በካህናቱም፣ በማኅበረ ምዕመናኑንም በመላው ሐዋሳ ከተማ በሚገኙ ምዕመናን በእውነት ለቤተ ክርስቲያናቸው የሚያስፈለገውን የሚያደርጉ፣ የሚታዘዙትን የሚፈጽሙ፣ ቅንነት የዋህነት ያላቸው፣ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ይዘው ለቤተ ክርስቲያናቸው አስፈላጊውን ሁሉ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ እንደ ቃለ ዓዋዲው በሰንበት ትምህርት ቤት የሚታቀፉት ከ4 ዓመት እስከ 3ዐ ዓመት ያሉ ናቸው። ነገር ግን በቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ የ4ዐ ዓመት የ5ዐ ዓመት ትልልቅ ሰዎች ሁሉ አሉ የእድሜ ገደቡም የሚመለከታቸው አይደለም። ይሄ የሚያሳየው ድርሻቸውን ለይተው አለማወቃቸው ነው ከ3ዐ ዓመት በኋላ ወደ ማኅበረ ምዕመናን ነው መቀላቀል ያለባቸው፡፡ ይህን ማድረግም የሰበካ ጉባኤው የሥራ ድርሻ ነበር፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት በቤተ ክርስቲያን ሊቋቋሙ ከሚገባቸው ከ13 ንዑሳን ክፍሎች ውስጥ አንድ ነው ይሄንን መፈጸም የሰበካ ጉባኤው ድርሻ ነው እኛ ከመምጣታችን በፊት እኛ ከመጣንም በኋላ ተቀላቅለው አንድ ዓይነት ትምህርት ነበር የሚሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ድርሻዎችን የመለየት፣ መመሪያዎችን የማወቅና ነገሮችን በቅንነት የመመልከት ሁኔታው የለም፡፡

በሌላ በኩል በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደሪጃ መምሪያ በኩል የሚፈጸም መመሪያ አለ፡፡ ያንን ተከትሎ መሄድ ቢቻል ምንም ዓይነት ችግር አይኖርም፡፡ ነገር ግን ሰንበት ትምህርት ቤት ነን ይላሉ ዕድሜአቸው ከጣሪያ በላይ የሆኑ በውስጣቸው አሉ፡፡ እነዚያው ክፍሎች ደግሞ የገዳሙን አውደ ምህረት ይዘን እኛ ነን መስበክ ያለብን ይላሉ፡፡ ለመስበክ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ዶግማ ሥርዓት ቀኖና መማር ከሊቃውንት እግር ሥር ቁጭ ብሎ መጻሕፍትን መመርመር ይገባል፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እናስተምራለን እንሰብካለን ማለቱ ደግሞ ወደ ስህተት ትምህርት ይወስዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሰባክያነ ወንጌል ነን፣ ዘማርያን ነን፣ ባሕታውያን ነን፣ እናጠምቃለን እንዲህ እናደርጋለን የሚሉትንና የመሳሰሉትን በሚመለከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በ2001ዓ.ም የካቲት ወር ያሳለፈውና ለመላው ስብከት ያስተላለፈው ሰርኩላር አለ፡፡ በዚያ ሰርኩላር ላይ ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ወይም ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ያልተሰጠው ማንም ሰው መስበክ አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ የምትመራና ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የራሷ የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር ያላት በመሆኗ፥ በዚያው በመዋቅር ውስጥ ተካቶ ሕጋዊ እውቅና ኖሮት፥ በየሃገረ ስብከቱ ያለውም የየሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የሃገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አሊያም ጠቅላይ ቤተ ክህነትም የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያው አውቆት በዚህ አይነት ነው መስበክ ያለበት ይላል መመሪያው። ይሄ መመሪያ የተላለፈው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ክቡር ፊርማ ተፈርሞ ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስና ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የሚሰጠውን መመሪያ የመፈፀም የማስፈጸም ኃላፊነት፣ የቤተክርስቲያን ልጅነትና አደራ አለብን፡፡

እንደ ሀገረ ስብከት ግን እገሌ ይስበክ እገሌ አይሰበክ የሚል አመለካከት የለንም፡፡ በአንዳንድ አካላት ግን እንደዚህ አይነት ሰባክያን ካልመጡልን እንደዚህ ዓይነት መምህራን ካልመጡልን የሚል የግል ጥያቃቄዎች ይነሳሉ፤ ሃሳቦቹ ለምን ኖሩ አንልም፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚያሰማራቸው፣ የሚቆጣጠራቸው፣ አንድ ጥፋት  ቢያጠፉ ሊጠይቃቸው የሚችል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደርን የሥራ መዋቅር ውስጥ የተካተቱ ሊሆን ይገባል፡፡ ደግሞም በርካታ ሠራተኞችና ሊቃውንት አሏት፡፡

እናስተምራለን ለሚሉ ግን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ወይም ለሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መጠየቂያ ቀርቦ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ጉዳዩን መርምሮና አጣርቶ፥ ይህ ሰው ብቁ ነው ብቁ አይደለም፥ ለማስተማር አስፈላጊውን የትምህርት ሆኔታ ይዟል አልያዘም፥ የሚለውን ሁሉ አይቶ ሲያሰማራ /ሲፈቀድ/ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በራሱ ተነሳሽነት ተነስቶ ወይ ባሕታዊ ነኝ ወይም ሰባኪ ነኝ ብሎ አንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ላይ እሰብካለሁ ቢል፡-
1.    የደብሩ አስተዳዳሪ ወይም ሰበካ ጉባኤ አያውቁም፣ የወረዳው ቤተ ክህነት፣ ሀገረ ስብከትና ጠቅላይ ቤተክህነቱም አያውቁም
2.    እዚያ ቦታ በአጋጣሚ ሆኖ /እግዚአብሔር አያድርስና/ ችግር ቢፈጠር፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነቱም ሀገረ ስብከቱን መጠየቁ አይቀርም ሀገረ ስብከቱም የደብሩን ተጠሪ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እንደኃላፊነት ሀገረ ስብከቱ እያወቀው መሆን አለበት፡፡ ምዕመናንም ምን አልባት የስሕተት ትምህርት እየተላለፈ እንደሆነ፣ ቃለ ዐዋዲውም እየተከበረ እንደሆነ፣ አበው ያቆዩት ሥርዓት እየተጠበቀ እንደሆነ ሊከታተሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡

ስለዚህ በአጠቃላይ ችግሮቹ የተፈጠሩት በመጀመሪያ ያለ እድሜያቸው በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ተካተው ድርሻቸውን ሳያውቁ የሚኖሩ ስላሉ፣ ቀጥሎም በተናጠልም ሆነ በቡድን ተሰባስበው እኛ መስበክ አለብን ወይም እገሌ ካልሰበከ አይሆንም በማለት እንደግል አመለካከት በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ስላሉ ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ ሰበካ ጉባኤው ባለው ሥልጣን ማስተካከል ይችላል፡፡

•    በአለመግባባቱ ውስጥ ሁለት ዋና ቡድኖች እንደተፈጠሩ ይነገራል፤ የቅዱስ ገብርኤል ወርሃዊ በዓል ማግስትም ግጭቶች እንደተፈጠሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ምንድን ነው አካሄዳቸው? ወይም ምክንያታቸው?

ሰዎች በራሳቸው እይታ ሁለት ቡድን አለ ሊሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ሀገረ ስብከት ግን እኛ ሁለት ቡድን አለ የምንለው ነገር የለም፡፡ በመሠረቱ ቤተክርስቲያን ዓላማዋ ሰውና እግዚአብሔርን ማገናኘት ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ደግሞ ወንጌልን፣ ፍቅርን ትህትናን እርስ በእርስ መከባበርን መተሳሰብን እንዲይዙ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትም የቡድን አካሄድ የመከፋፈል አካሄድ፣ የመለያየት አካሄድ አነ ዘአጵሎስ ወአነ ዘኬፋ የሚለው አነጋገር በቅዱስ ወንጌልም የተደገፈ አይደለም፡፡ እኛ ከመጣን ጀምሮ የምናየው ቅድም እንዳልኩት ነው፡፡ ከችግሮቹ ምንጮች እንደገለጽኩት ከሰንበት ትምህርት ቤት የተውጣጡ የተወሰኑ የእድሜ ገደብ ያለፋባቸውና እኛ ብቻ ነን መስበክ ማስተማር ያለብን የሚሉና ወጣቶችንም ወደ ስሜት ወደ መገፋፋት የሚያመጡና፣ የቤተክርስቲያኗ ደንብ ሥርዓትና መመሪያ ያለመቀበል ሁኔታ የሚያሳዩና እንደ ራሳቸው ሃሳብ የመሄድ ጉዳይ ይታያል በሌላ በኩል መላው ምዕመናን ማለት ይቻላል፤ ሕጉ ሥርዓቱ የሲኖዶሱ መመሪያ ተከብሮ ቤተክርስቲያን ሥራዋን በአግባቡ ታከናውን የሚል ብቻ ነው ያለው፡፡ እንግዲህ አሁን የመለያየትና የቡድን ስሜት የለውም፡፡ ሕጉና መመሪያው ሲነገር ሁሉም ይሰማል፣ ሁሉም ያከብራል እዚህ ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት ያሉ ጥቂት ወጣቶች ግን የልጅነትም ሊሆን ይችላል ከረር የማለትና መድረኩን እኛ ካልያዝነው፣ ስብከቱንም እኛ ካልሰበክነው የሚል የግል አካሄድ ያሳያሉ እንጂ ከሁለት የተከፈለ ቡድን የለም፡፡

የአገር ሽማግሌዎችን አባቶች፣ እባካችሁ ይሄንን መመሪያ እንዲያከብሩ አድርጓቸው፣ ትንሽ እኛን አልሰማ አሉ የሚቻለውን ነግረናል ብለን ስናስረዳ፤ እግዚአብሔር ይስጣችሁ፥ ሸክሙን እንድናግዛችሁ ወደ እኛ ማምጣታችሁ ጥሩ ነው ብለው ብዙ ደክመዋል በዚህ ጉዳይ፡፡ የተቀበሉ አሉ፥ ልክ ነው ያሉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን የለም አይሆንም ያሉ አሉ፡፡ እንደዚህ እንደዚህ አይነት አካሄዶች ናቸው እንጂ እንደ ሰው አባባል ሁለት ቡድን የለም፡፡

•    በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደዚህ አይነት አለመግባባቶች ምንጫቸው ምንድን ነው? እንዲያው ዝም ብሎ ቃለ ዐዋዲን ብቻ ባለ ማክበር የሚፈጠሩ ናቸው ብለው ያስባሉ?

ሰው ምን ጊዜም ችግር የሚገጥመው ከሕግ፣ ከሥርዓትና ከመመሪያ ሲወጣ መሆኑ ግለፅ ነው። ያለን ቆይታ አጭር በመሆኑ እስከ አሁን ያየነው ሁኔታ ከላይ የገለፅኩትን ነው የሚመስለው። ከበስተኋላው ምንድን ነው ይሄ ነገር? ምንስ አይነት እንቅስቄሴ አለው? ወይስ የተለየ ዓላማ አለው? ወይስ ሕጉን ያለማወቅ ብቻ ነው? ወይስ ደግሞ ቃለ ዐዋዲውን ያለመቀበል ነው? እስከ አሁን እንደምናየው መመሪያው እየተነገረ እያዩ እየሰሙ ያለመቀበል ነው ያለው? ግን ከበስተኋላ ምን አለው? ተጨማሪ ነገር አለው ወይ? የሚለው ግን ትንሽ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ሲነገራቸው ተስተካክለው በመስመር መጓዝ የጀመሩና የሄዱ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የለም እንዲህ ነው እያሉ ክርር የሚሉ አሉ፡፡ ሰው ሕሊናው እያየ አእምሮው ያስባል፡፡ ማንኛውም በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው ሲነገረው ይሰማል፤ ሲያይ ያነባል፥ ግን አንብቦ፣ ተነግሮት ሰምቶ፣ ተረድቶ፣ እውነቱን አውቆ ግን ይሄ ነው ማለት መቻል አለበት፡፡ ይሄንን ካልቻለ ችግሩ ምን እንደሆነ የሰውየው ሁኔታ ነው አላማውን የሚያውቀው፡፡

የቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት የራሱ የሆነ መምህር የለውም፡፡ ከዚህም የተነሳ ከብፁዕ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ጋር ጉዳዩን በመመካከርና በመነጋገር፣ እንደብፁዕነታቸውም መመሪያ በመቀበል አሁን የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በሂደት ሰንበት ትምህርት ቤቱ በአግባቡ መምህር እንዲኖረው፣ ልጆች ተኮትኩተው የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ደንብ ጠንቅቀው አውቀው እየተገበሩ እንዲያድጉ ለማድረግ፣ ይሄ በእቅድ ደረጃ ተይዟል፡፡ ትምህርትም ሲሰጥ እንደ እድሜ ደረጃቸው ነው። ወጣቶች አሉ፣ ህፃናት አሉ፣ አዋቂዎች አሉ፣ እንደወንጌሉም ግልገሎች፤ ጠቦቶች በጎች፣ ብሎ ይለየዋልና። እዚያ ሰንበት ትምህርት ቤት ደግሞ ተቀላቅለው ነው የሚማሩት ይህ ችግር ይፈጥራል፡፡

የትምህርት አሰጣጡ ይስተካከል ሲባል ደግሞ በአንዳንድ ሰዎች ይሄ የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ ግን ልማድ ሲጋነን ባሕል ይሆናል ይባላልና ልማድን ትተው ሊስተካከሉና መስመር ይዘው ሊጓዙ ቃለ ዐዋዲውንም ሊያከብሩ ይገባል ማለት ነው፡፡

ሌላው ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ምንም አይነት የሥራ ድርሻ የሌላቸው ያልተቀጠሩ፣ የሥራ ውል የሌላቸው ወይ ዲያቆን፣ ቄስ፣ መነኩሴ፣ መሪጌታ፣ አወዳሽ ቀዳሽ ያልሆኑ፣ እንደ አንድ ምዕመን ጸልየው ወይም ትምህርት ሰምተው መሄድ ብቻ የሚገባቸው ሆነው ሳለ በማይገባቸው አንዳንድ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣለቃ የመግባት ነገር ይታያል፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤትም፣ በስብከተ ወንጌልም፣ በአውደ ምህረትም ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ናቸው ነገሩንም እንዲባባስ እያደረጉት የሚገኙት፡፡

•    የቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ ችግሮቹን ለመፍታት ከእናንተ ጋር ያላቸው ተግባቦት ምን ይመስላል?
 

በእርግጥ አሁን ያለው ሰበካ ጉባኤ እኛ ከመምጣታችን በፊት ጊዜያዊ ተብሎ የተመረጠ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ብዙ ጊዜ፥ አንዳንድ ሥራዎችን ለመሥራት ሲቸገሩ እናያለን፡፡ ጠርተን በጋራ አወያይተናል፥ ተመካክረናል ጊዜያዊ ሆነው እንዴት እንደተመረጡ ለእኛም ግለፅ አይደለም፤ ምክንያቱም ባልነበርንበት ጊዜ ስለነበር፤ አንዳንድ ምዕመናንም አልመረጥንም፤ ጊዜያዊ ናቸው፤ የማለት ያለመተባበር ችግር ይታያል፡፡

እኛ ከመጣን ግን የገዳሙን አስተዳዳሪና ሰበካ ጉባኤውንም በጋራ ቁጭ አድርገን አወያይተናል፥ ማደሪያ ጉዳዩንም አገላብጠን ተመልክተን ጊዜአዊ ሰበካ ጉባኤ መሆናቸውን እነርሱም አውቀውት፥ እነርሱም ባሉበት ሆነው፣ ከወጣቱም፣ ከአገር ሽማግሌዎችም፣ ከልማት ኮሚቴም፣ ከሚመለከታቸው አካላት የተወሰኑ ይዘን የመንግሥት አካላትም በታዛቢነት እንዲገኙልን አድርገን የቃለ ዐዋዲውን ሕግና መመሪያ በጠበቀ መልኩ ተገቢውን ቅስቀሳና ትምህርት ተሰጥቶ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ሥራ በአግባቡ ሊመራና ግቢውን ሊያስከብር ሊጠብቅ የሚችል ሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሄድ የሚል ውሳኔም ስምምነት አድርገናል፡፡
 
አሁንም ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንገኛለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን አሁን ያለው ሰበካ ጉባኤ ያለውን ኃላፊነት እንዲወጣና ለአንድ ቀንም ቢሆን ኃላፊነት ስላለው ግቢውን እንዲያስከብር፣ እንዲጠብቅ በተደጋጋሚ ጊዜ ተወያይተናል መመሪያ ተሰጥቷል ብፁዕ አባታችንም በሰፊው ደክመውበታል፡፡ ተፈፃሚነቱ ግን እምብዛም አይታይም፡፡ የአቅም ማደስም፣ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ሊሆን ይችላል እንግዲህ ምክንያቱ፡፡

በግቢው ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ሰበካ ጉባኤውንም አስተዳዳሪውን በመጀመሪያ ደረጃ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ አዛው አጥቢያው ላይ እንደ ቃለ ዐዋዲው የማስኬድ ፣ መመሪያውን የመጠበቅና የማስጠበቅ፣ መስመሮችን እንዳይለቁ የመከታተልና ቁርጥ ያለ ውሳኔና ፍትሕ የመስጠት አስተዳደራዊ ሥራ ቢሠራ ምንም አይነት ችግር አይኖርም፡፡

                                                                                    ይቆየን