፲፰ኛው የአሜሪካ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ተካሔደ።

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአሜሪካ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ፲፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሲያትል ዋሺንግተን ቅዳሜ ግንቦት ፳ እና እሑድ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተካሔደ።

በጉባኤው ወደ ፬፻ የሚደርሱ የማእከሉ አባላት፤ የዲሲና የአካባቢው እንዲሁም የካሊፎርንያና ምዕራብ አሜሪካ አህጉረ ስብከት ተወካዮችና የሥራ አስፈጻሚ አባላት፤ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጉባኤው በጸሎተ ኪዳን በተጀመረበት ቅዳሜ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ሕልምነህ ስንሻው የእንኳን ደኅና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ በማእከሉ የተተገበሩ ዋና ዋና የአገልግሎት ሥራዎችን ዘገባ አቅርበዋል። የዲሲ እና የአካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መሥፍን ተገኝም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን መልእክት ለጉባኤው ካስተላለፉ በኋላ በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው “ሥራ የበዛበት ትልቅ በር” /፩ኛቆሮ. ፱፥፲፮/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡

በመቀጠል የማእከሉ የአገልግሎት ክፍሎች ዓመታዊ ጠቅላላ ሪፖርትና የቀጣይ ዓመት ዕድቅ ለጉባኤው ቀርቧል፡፡ በቀረበው ሪፖርትም በንዑሳን ማእከላት በርካታ ትምህርታዊ ጉባኤዎች እንደተካሔዱ፣ በልዩ ልዩ ከተሞች የማኅበረሰብ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደተጀመረ፣ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ኢአማንያንን ለማስተማርና ለማስጠመቅ ለተዘረጋው የስብከተ ወንጌል ፕሮጀክት ከአባላት እና ከምእመናን የተሰበሰበ የእርዳታ ገንዘብ ወደ ዋናው ማእከል እንደተላከ ተገልጿል።

የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ተወካይ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም የዋናውን ማእከል መልእክት እና ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከጉባኤው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠታቸው በተጨማሪ የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በሁለቱ ቀናት ጉባኤ ላይ በሲያትል ንዑስ ማእከል የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ውዳሴ ማርያምና ሰዓታት በንባብና በዜማ፤ የጸሎተ ቅዳሴ ተሰጥኦና ምስባክ፤ እንደዚሁም የአብነት ትምህርትን አሰጣጥና ሒደት የሚያሳይ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ቅኔ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ እና የተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።

በተጨማሪም የሲያትል ንዑስ ማእከል የአገልግሎት ተሞክሮዉን ለጉባኤው ያካፈለ ሲኾን፣ የማእከሉ የአገልግሎት ክፍሎች የበጀት ሪፖርትም ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ከስድስት ወር በኋላ የማእከሉ የዕቅድ ክለሳ እንደሚደረግም በጉባኤው ተገልጿል።

እንዲሁም ዝክረ አበው በሚል መርሐ ግብር የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ በማስመልከት የተዘጋጀ ፊልም ለእይታ በቅቷል።

በዕለቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ማዕከሉን ይመራ የነበረው የሥራ አስፈጻሚ የሥራ ዘመን በመፈጸሙ፣ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማእከሉን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ፲፫ አባላት በጸሎትና በዕጣ ተመርጠዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ በማእከሉ ፲፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የዝግጅቱ ሒደትና በሲያትል ከተማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ያበረከቱት ከፍተኛ አገልግሎት በዝርዝር የቀረበ ሲኾን ይህ አሳታፊነትና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቅንጅት የመሥራት ልምድ ለሌሎች ንዑሳን ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች ያለው አርአያነት የጎላ መኾኑ ተገልጿል።

በመጨረሻም ፲፱ኛው የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በቦስተን፣ ፳ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ በቨርጂንያ እንዲካሔድ ተወስኖ ጠቅላላ ጉባኤው በዝማሬ እና በጸሎት ተጠናቋል።