ፍኖተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ዐውደ ርዕዩ እሰከ ከነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ይቆያል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍልን የሃያ ዓመታት የአገልግሎት ጉዞ የሚያሳይ ፍኖተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ተከፈተ፡፡

ht
ፍኖጸተ ሐመረ ጽድቅ ዐውደ ርዕይ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቦረና፤ አማሮና ቡርጂ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና አገልጋዮች በተገኙበት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ht 2ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቦረና አማሮና ቡርጂ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ያደረጉትን አስተዋጽኦ፤ እንዲሁም ከአመሠራረታቸው ጀምሮ የተጓዙበትን ሂደት በጥልቀት አብራርተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የማኅበሩ አባላት በተገኙበት ውይይት በማካሔድ ሐመር መጽሔት ተብሎ እንዲሰየም ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው የኅትመት ውጤቶቹ እየሰጡ የሚገኙትን አገልግሎት ሲገልጹም “በሐመር መጽሔትና በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የሚጻፈው፤ የሚነበበው ነገረ ድኅነትን ያመለክታል፡፡ የምንድንበትን መንገድ የሚያስተምሩ፤ ፃድቃን ሰማዕታት አማላጅ መሆናቸውን የሚያውጁ፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የሁሉ ጌታ፤ የሁሉ ፈጠሪ መሆኑን የሚመሰክሩ፤ እምነትንና ምግባርን የሚያስተምሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

ምእመናንን በማነጽ ረገድም “ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው የማያውቁ ወንድሞችና እኅቶች የኅትመት ውጤቶቹን በማንበብ ራሣቸውን በማረም እምነታቸውን እንዲያውቁና እንዲጸኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየተሰራጩ ምእመናንን በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ታላቅ ሐዋርያዊ አገልግሎት ነው” በማለት ወደፊትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ht 3
የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበሩ የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ያላቸውን ፋይዳ በማስመልከት “በሐመር መጽሔትና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የተጀመረው አገልግሎት እድገት በማሳየት ሌሎች የኅትመት ውጤቶችን በመውሰድ ምእመናንን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤቶችንም በመጠቀም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ዘርፍ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በአንድ ጊዜ በመድረስ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ያስችለዋል” ብለዋል፡፡

ዲያቆን ዶክተር መርሻ አለኸኝ የሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ የዐውደ ርዕዩ አስፈላጊነት በሚመለከት “ዐውደ ርዕዩ የሐመር መጽሔትና የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በሃያ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ያሳዩአቸውን ጠንካራና ደካማ ጎን ለይተን እንድናውቅ፤ የኅትመትም ይሁን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው የአገልግሎት ዘርፍ የወደፊት አቅጣጫ እንድንተልም ይረዳናል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሚቀጥለው ወር በመንፈሳዊው ሚዲያ ዘርፍ ልምድ ባላቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች አማካይነት በማኅበሩ የኅትመት ሚዲያ ላይ ዐውደ ጥናት እንደሚካሔድ ገልጸዋል፡፡

ht 4ዐውደ ርዕዩ አራት አበይት ክፍሎች ሲኖሩት ዝክረ ሐመረ ጽድቅ፤ መዛግብትና ቁሳቁስ፤ የፎግራፍና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዘርፍ እንቅስቃሴን ይዳስሳል፡፡ ዐውደ ርዕዩ እሰከ ነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን ምእመናን አራት ኪሎ በሚገኘው በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ከጠዋቱ 4፤00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፤00 ሰዓት ድረስ እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል፡፡