“ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ምሳሌ ፳፩÷፴፩)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

የካቲት ፳፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በዓለማችን ላይ አያሌ ጦርነቶች ተደርገዋል፤ እስከ አሁንም ድረስ እየተደረጉ ይገኛል፡፡ ብዙ ጊዜ በግለሰቦችም ይሁን በማኅበረ ሰብእ ደረጃ ጦርነት እንዲቀር ስለተፈለገ ብቻ ጦርነት ሊቀር ወይም ሊወገድ አይችልም፡፡ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንደሚባለው በዓለም ላይ የሁከት ሰዎች እስካሉ ድረስ ጦርነቶች ይኖራሉ፡፡ ጦርነት ጠንሳሾች፣ አቀጣጣዮች በመጨረሻም አስጀማሪዎች ይኖሩታል፡፡

የመጀመሪያ ጦርነት ጠንሳሽ ተብሎ የሚታወቀው ዲያብሎስ መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፡፡ ዘንዶውም ከመላእክት ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም” በማለት ይነግረናል፡፡ (ራእይ ፲፫÷፯) ሰይጣን ያልተሰጠውንና የሌለውን ሽቶ “የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ” በማለቱና ብዙዎችንም በማሳቱ ምክንያት ቅዱሳን መላእክት ዘንዶ የተባለ ዲያብሎስን ውጊያ እንደ ገጠሙትና ድል እንደነሡት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ይነግርናል፡፡ በዚህ ጦርነት የጦርነቱ ጠንሳሽና ምክንያቱ ሰይጣን ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክትም እግዚአብሔር ኃይል ስላስታጣቃቸው፣ እውነትን ስለ ያዙና ሐሰትን ስለ ተቃወሙ እግዚአብሔር ድል የሚነሡበትን ኃይል ሰጥቷቸው ጠላት ሰይጣንን ድል ነሥተውታል፡፡

በማናቸውም ውጊያ እግዚአብሔርን ኃይል ያደረጉና ለእውነት የቆሙ ሁሉ የሚያሸንፋቸው ማንም አይኖርም፡፡ የእግዚአብሔር ወገን የተባሉ እስራኤል ዘሥጋ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከቤተ አሕዛብ ጋር እንደ ተዋጉና የእግዚአብሔርን ሕጉ ጠብቀው፣ ፈቃዱን በመፈጸምና እርሱን በመማጸን ሀገራቸውን፣ ርስታቸውንና እምነታቸውን ለመከላከል ለሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ድል ያደርጉ እንደ ነበር መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናገኘው በአንድም ይሁን በብዙ ምክንያት የእስራኤል ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት የእርስ በእርስና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ውጊያ አካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ወቅቶች ግን አምላካችን እግዚአብሔር ከእነርሱ አልተለየም ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ታቦተ ጽዮንን ይዞ ሽንፈት አልነበረም፡፡ (ዘኅ. ፳፩፣ ፴፩፣ ፴፪) ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው “ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት እንደ ተናገረው እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን፣ ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈባቸውን ጽላት በመያዝ እስራኤላውያን በርካታ ጦርነትን አሸንፈዋል፡፡ (ምሳሌ ፳፩÷፴፩)

በአንጻሩም ከእግዚአብሔር ርቀው፣ ሕጉን አፍርሰው፣ በጉልበታቸው ተመክተው በሚወጡበት ጊዜ ይሸነፉ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ (ኢያሱ ፯÷፮-፲፭፣ ፩ኛ ሳሙ. ፬÷፩-፳፪) ጎልያድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ፣ በጉልበትና በኃይሉ ተመክቶ፣ እስራኤልንም ንቆ፣ በጦር ቀጥቅጦ እንዲገዙለት በተመኘና ሠራዊትም ባሰለፈባቸው ጊዜ እጅግ በናቀው ነገር ግን ደግሞ በእግዚአብሔር ተመክቶ በነበረ በትንሹ ብላቴና በዳዊት በተወረወረ አንድ ጠጠር ተመትቶ ወድቋል፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፲፯፥፩-፶)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን አበው ሲናገር “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ” በማለት የተናገረው በሀገራችን ኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረውን የዐድዋ ጦርነት ያወሳናል፡፡ (ዕብ.፲፩÷፴፫) ታላቁ የዐድዋ ድልም ምሥጢሩ በወቅቱ የነበሩ ጀግኖች አባቶቻችን፣ ለእነርሱም ስንቅና ትጥቅ በማቀበል በተዘዋዋሪ የተሳተፉ እናቶቻችን ከጦርነቱ በፊት ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔር ኃይል እንዲያስታጥቃቸው፣ መንገዳቸውንም እንዲያቀና መማጸናቸው ነው፡፡ በጣሊያኖቹ ዕብሪት፣ ንቀትና ማን አለብኝነት እንዲሁም ማታለል ምክንያት ሊፈነዳ ዘንድ ያለው ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ “ያገሬ የኢትዮጵያ ሰው ሁሉ ስማ! እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፍቶ ሰጠኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ሀገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት፥ ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፤ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘንህ ርዳኝ፤ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም” በማለት ያወጁት ታሪካዊ፣ በታሪክ አጥኚዎችም ዘንድ እጅግ በጣም ግልጽ አጭርና አነሣሽ የጦርነት ዐዋጅ ምስክር ነው፡፡ (Professor Kinfe Abraham :- Adowa and its inspiration on decolonization pan Africanism and the struggle of the black people page 37፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዐድዋ ድል በ፲፱፻፳ዎቹ የተጻፈ ገጽ ፪፻፴፬)

ከዚህ ዐዋጅ በኋላ ቅድመ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአጭር ዐረፍተ ነገር ሲገልጹ “ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስም ከየደብሩ አለቆችና ከድንባሮ ማርያም ካህናት ጋር ባንድ ስፍራ ቆመው ወደ ጦርነቱ የሚገባውን ወታደር “እግዚአብሔር ይፍታህ” እያሉ ይናዝዙ ነበር” በማለት ጽፈዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፪፻፶፮) ከፍቅረ ቢጽ የሚመነጭ፣ ሀገርን፣ ወገንን ለመከላከል በሚደረግ ፍትሐዊ ጦርነት ውስጥ ለሚሳተፉት ክርስቲያኖች የሚደረግ ጸሎተ ፍትሐት እንዳለ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ (ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ድምፀ አሮድዮን ገጽ ፻፷፭)

በዐድዋ ከዚያ በፊት እንኳን ሊደረግ ሊታሰብ የማይችለውን በኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሣሪያና በሠራዊት ብዛት ተደራጅቶ የመጣውን፣ በቆዳ ቀለሙ የጠቆረውን የሰው ዘር እንደ “የነጭ ሰው ሸክም” አድርጎ የሚቆጥርና ራሱን የአምላክ ባለ አደራ አድርጎ የሚቆጥር አደገኛ አስተሳሰብ የተጫነውን የቅኝ ገዢነት አስተሳሰብ ድል የመነሣቱም ምሥጢር ይህ ነው፡፡ በዚያን ወቅት የነበረው የጣሊያን ወረራ ከመነሻው ሰውን ከሰው ያበላለጠ “አንዱ ገዢ ሌላው ተገዢ ነው÷ ወይም መሆን አለበት” የሚል እኩይ አስተሳሰብ የተጫነው የመስፋፋት አባዜ፣ ሁለተኛም ያንኑ አስተሳሰቡን ለማስፈጸም “የውጫሌ ውል” ተብሎ በሚጠራው በዐሥራ ሰባተኛው አንቀጽ ላይ የሰፈረው ቃል አተረጓጎም ነው፡፡ ይህም ጣሊያኖቹ ይህን አንቀጽ ለራሳቸው ለቅኝ ግዛትና በሚመቻቸውና ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ሀገራትን የመበዝበዝ ሕልማቸውን እውን ለማድረግ በሚያስችላቸው መልኩ ለመተርጎም መነሣታቸው ነበር፡፡ ይህ የማታለል ድርጊታቸው የጦርነቱ አንዱ ገፊ ምክንያት መሆኑን ጥናቶችም ታሪክም ያመለክታሉ፡፡ (Professor Kinfe Abraham :- Adowa and its inspiration on decolonization pan Africanism and the struggle of the black people page 33) ይህም ሁኔታና ጣሊያኖቹ የነበራቸው ቅኝ የመግዛት ሕልምና ንቀት ጦርነቱን አይቀሬ ከማድረጉ በተጨማሪ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለጦርነቱ መዘጋጀትና መውጣት ጦርነቱን ፍትሐዊ ያደርገዋል፡፡

ለብዙዎቻችን እንደሚመስለን በዐድዋ ነጮች በጥቁሮች ድል የተነሡበት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ትዕቢት፣ ዕብሪት፣ ግፍ፣ ስግብግብነት፣ አልጠግብ ባይነት፣ ንቀት፣ ሸፍጥና ክፋት በመልካምነት በሀገር ፍቅርና በእግዚአብሔር ኃይል የተሸነፉበት ጦርነት ነው፡፡ ዛሬ ሀገራችን ላለችበት ችግርና ሕዝቦችዋም ለደረሱበት መከፋፈል፣ በዘመናትም ሀገሪቱን ለመከፋፈል በገዛ ልጆችዋ ለተደረጉ ጦርነቶችና ላስከተለውም ዕልቂት ዋና መንሥኤው የእነዚህ ቅኝ ገዢዎች የመስፋፋትና ሀገራትን የመበዝበዝ ትልም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በቅኝ ሊገዙት አሰፍሰው መጥተው በአንድነት ድል የነሣቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋ ከፋፍለው፣ በሐሰት ተረክ አጋጭተው አንዱ በሌላው እንዲነሣሣና ጠላት እንዲሆን በማድረግ ዛሬ በምናየው መልኩ በማጋደል እየተበቀሉት ይገኛሉ፡፡ (Roman Prochazka:- Abyssinia the Powder Barrel A book on the most burning question of the day 1934, John H Spencer, Ethiopia at Bay) እጅግ የሚያሳዝነው ነገር “ምሁራን ነን፣ በእዚህና በዚያ ዩኒቨርሲቲዎች ተምረን እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ይዘናል፤ የጥናት ጽሑፎቻችንን በታወቁ ጆርናሎች ላይ አሳትመናል፤ በታወቁ ሴሚናሪዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎቻችንን አቅርበን ተጨብጭቦልናል” ባልንና እንደ አንዳንድ ታሪክ ጸሐፍያንም አገላለጽ በ አፍሪካ ጠልና ምዕራብ ተኮር አስተሳሰብ ተጠልፈን የተንኮላቸው ሰለባ ሆንን፡፡ (መምህር ግርማ ባቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ገጽ ፸፫)

በመጨረሻም ሕዝብ ሰላምን፣ ልማትንና መበልጸግን እንደሚፈልግ ሕዝብ፣ የፖለቲካ መሪዎችም እንደ አንድ ለሕዝቦች አንድነትና ደኅንነት እንደሚያስብ መሪ፣ ኢትዮጵያ በምትባለው መርከብ ውስጥ በአንድነት ሆነው የተሳፈሩ በጋብቻ፣ በሃይማኖትና በባህል የተሳሰሩ ቀደምት ኢትዮጵያውያውን ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቅሰው የመጣባቸውን ወራሪ ድል እንደነሡ በመረዳት፣ በቋንቋ ማንነት የተከፋፈልንበት፣ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም እርስ በርስ ከመነካከስ ውጭ አንዳችም እንዳላተረፈልን ተገንዝበን ይህን የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓል እንደ አጋጣሚ ብንጠቀምበት የሚኖረው ዋጋ ቀላል አይሆንም፡፡ መጽሐፍ “ “ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” እንዳለው (ፊልጵ.፫፥፲፫) የዚህ ዘመን ትውልድም ካለፈ ታሪካችን መልካም መልካሙን እየመረጥንና ክፉ ክፉውን እየተውን ለጋራ ሰላምና ጥቅማችን ብንኖር መልካም ይሆናል፡፡

እግዚአብሔር ሀገራችንን ወደ ሰላምና አንድነት ይመልስልን!!!