ፅንሰታ ለማርያም
ነሐሴ ፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናት ቅድስት ሐና የተወለደችው በቤተ ልሔም ይሁዳ ውስጥ ነው፡፡ ኢያቄም የሚባል ሰው አግብታ ትኖር ነበር፡፡ ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ሐና መካን ስለነበረች ልጅ መውለድ አልቻሉም፡፡ በዚህም ለበርካታ ዓመት ሲያዝኑና አምላካቸውን ሲማጸኑ ኖሩ፡፡ በዚህም መካከል ስዕለትን ተሳሉ፤ ፈጣሪ ልጅ ቢሰጣቸው ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደሚሰጡም ቃል ገቡ፡፡
አንድ ቀን ሁለቱም የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ተገልጦ የተባረከ ልጅ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው፡፡ እጅግም ደስ ተሰኙ፤ በነሐሴ ሰባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች፤ ሁለቱ ጻድቃን የእግዚአብሔር ሰዎቸም በግንቦት አንድ ቀን እንደ ፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅን ወለዱ፡፡ እስከ ሦሰት ዓመት ድረስም በቤት ካሳደጓት በኋላ ስዕለታቸውን አስበው ለቤተ ከርስቲያን ሰጧት፡፡
እመቤታችንም በቤተ መቅድስ ለዘጠኝ ዓመት ኖራለች፤ ከዚያም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመወለድ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንዳበሠራትና ለጻድቁ ዮሴፍ እንዲጠብቃት እንደሰጠች ቅዱሳት መጻሕፈት ይነግሩናል፡፡
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተራዳኢነት ከሁላችንም ጋር ይኑር፤ አሜን!