ፅንሰተ ድንግል ወተስእሎተ ቂሣርያ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በነሐሴ ወር በሰባተኛው ቀን ከሚከብሩ በዓላት መካከል በዛሬው ዝግጅታችን የእመቤታችንን ፅንሰት እና ተስእሎተ ቂሣርያን የተመለከተ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ በመጀመሪያም ፅንሰተ ድንግል ማርያምን እናስቀድም፤
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሲል በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ የቈረሰውና ያፈሰሰው፤ እርሱን የበሉና የጠጡ ኹሉ መንግሥቱን የሚወርሱበት፤ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ቅዱስ ሥጋውና የሚቀዳው ክቡር ደሙ ከንጽሕተ ንጹሐን፣ ከቅድስተ ቅዱሳን ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተዋሐደው ሥጋና ደም ነው፡፡ እመቤታችንን እናታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ እያልን የምናከብራት፣ የምናገናት፣ የምንወዳት ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደችልን ነው፡፡ ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል …፤ ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …›› /መዝ.፵፭፥፬/ በማለት እንደተናገረው አምላክን በማኅፀኗ ለመሸከም የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችው ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› እንዲል /ቅዳሴ ማርያም/፡፡
ታሪኩን ለማስታዎስ ያህልም የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጠጎች እና መካኖች ነበሩ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘባቸውንና የንብረታቸውን ብዛት አይቶ ሚስቱ ቴክታን ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ኹሉ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› ባለችው ጊዜ ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ በዚህ ጊዜ ኹለቱም እያዘኑ ሳሉ ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡
ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ቴክታ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ሄኤሜን አለቻት፡፡ ትርጕሙም ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለዓቅመ ሄዋን ስትደርስም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ነበሩ፡፡ በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ቢሔዱ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማ ‹ብዙ ተባዙ› ብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው በመቅረቱ፤ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ በመከልከሉ እያዘኑ ሲመለሱ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና በተመለከተች ጊዜ ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትን አብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡
ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ከተሳሉ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ሐና ለኢያቄም ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ኹሉ ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ነገረችው፡፡ ኢያቄም ደግሞ ለሐና ‹‹ጸዓዳ ረግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ነገራት፡፡ ሕልም ተርጓሚው ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ባላቸው ጊዜም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመልሰዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ ነግሯቸው ሐዲስ ኪዳን ሊበሠር፤ ጌታችን ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን በሐና ማኅፀን ውስጥ ሳለች ከተደረጉ ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል አንድ ዓይና ሴት (አክስቷ) ሐናን ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ ማኅፀኗን በዳሰሰችበት እጇ ብታሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡ ይህንን አብነት አድርገውም ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ ሰላም ላንቺ ይኹን›› ብሎ ሕልም ተርጓሚው ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከሐና እመቤታችን፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛ ፀሐይ የተባለው ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ /ምንጭ፡- ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰/፡፡
በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን የሚዘከረው ሌላኛው በዓል ደግሞ ‹‹ተስእሎተ ቂሣርያ›› የሚባለው የጌታችን በዓል ነው፤ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ ማለት ሲኾን ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያቱን ወክሎ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት አድንቆለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹አንተ አለት ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መታነፅ፣ ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል /ማቴ.፲፮፥፲፫-፲፱/፡፡
ይህም ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኀጢአት ስንሰናከል ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፣ እንደዚሁም እየተባረክን ‹‹ይፍቱኝ›› የምንለው ጌታችን ለእነርሱ የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ ከናዘዙን በኋላ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠር የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ›› ብሎ በመጠየቅ አምላክ ወልደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን ለጴጥሮስ በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡
በዚህ በተስእሎተ ቂሣርያ ጌታችን ሐዋርያቱ ማን እንደሚሉት ስለ ማንነቱ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱም በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› /ዘፍ.፫፥፲/ ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል /ቀሌምንጦስ/፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ያለችበትን ቦታ ካናገረው በኋላ ‹‹ሣራ የዛሬ ዓመት ልጅን ታገኛለች›› የሚል በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያበሥር ቃል መናገሩ ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.፲፰፥፱-፲፭/፡፡
በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› /ዮሐ.፲፩፥፴፯/ ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ ጋርና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው፡፡ ይኼ ኹሉ ቃል እግዚአብሔር ያላወቀ መስሎ በመጠየቅ የሰዎችን ስሜት እንደሚገልጥና የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎ ሥልጣንን፣ በረከትንና ጸጋን እንደሚያድል የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በምድር በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? (ልትድኚ ትወጃለሽን?) እያለ በመጠየቅ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ እምነታቸውን አይቶ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ /ንጽሒ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወስ /ተፈወሺ›› እያለ በአምላካዊ ቃሉ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡
በአጠቃላይ ‹‹እመቤታችን ከእርሷ እንድትወለድ ዐውቆ አዳም ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ይላት ነበር›› እንደ ተባለው የኹላችንም ሕይወት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ቤዛዊተ ዓለም እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው የድኅነታችን ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው፤ ዳግመኛም በቂሣርያ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የመሰከሩት፣ እርሱም ሥልጣነ ክህነትን የሰጣቸው በዚህች ዕለት ነውና በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው፤ የእመቤታችን በረከት አይለየን፡፡