ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅታችን ጾም ምንድን ነው? እንዴትና ለምን እንጾማለን? መጾም ምን ጥቅም ያስገኛል? ባንጾምስ ምን ጉዳት አለው? የሚሉ ጥያቄዎች በቤተ ክርስቲያን መምህራን ምላሽ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው የፍልሰታ ጾም በደመቀና በተለየ ኹኔታ የሚጾምበት ምክንያት ምን እንደ ኾነና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ከምላሾቹ በኋላም ጾመ ፍልሰታን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ መልካም ንባብ!

የጾም ትርጕም

‹‹ጾም›› ማለት ‹‹ጾመ –  ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ፤›› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲኾን የቃሉ ትርጕም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው ሲሉ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ባዘጋጁት ‹‹ጾምና ምጽዋት›› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ ፰ ላይ ገልጸውታል፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትም የሚያትተውም ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡ ጾም ጥሉላትን፣ መባልዕትን ፈጽሞ መተው፣ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንደዚሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ዅሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቈጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ማለት ነው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተ የሚሰጡት ማብራርያም ይህንኑ ትርጕም የሚያጠናክር ነው፡፡

የጾም ሥርዓቱና ጥቅሙ 

‹‹መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ› ነው፡፡ ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለ ኾነ ሳይኾን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ስንጾምከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከርወዘተ. መቆጠብ አለብን›› ሲሉ ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የጾም መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡ በሃይማኖት የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከልበት ኹኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጾም ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዓይነት መስመር አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽዋማት ወቅት ከምግበ ሥጋና ከኃጢአት ትከለክላለች፡፡ ከኃጢአት ዅልጊዜም እንከላከላለን፡፡ ከምግብ የምንከለከለው ምግብ ኃጢአት ስለኾነ ሳይኾን ከሃይማኖት የተነሣ ነው፡፡ ምግብ በልተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን ጎስመን ያለ ምግብና ያለ መጠጥ እግዚአብሔርን እያመሰገንን የምንኖርበትን ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ሕይወት የምናስብብት መንገድ ነው›› የሚሉት ደግሞ ቀሲስ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡

የጾም ዓይነቶች

ጾም የግል እና የዐዋጅ (የሕግ) ጾም በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ የግል ጾም ደግሞ የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የዐዋጅ (የሕግ) አጽዋማት ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም)፣ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ስለኾነ፡፡

የፍልሰታ ጾም 

ከዚህ በመቀጠል ጾመ ፍልሰታን ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምን እንደ ኾነ እንመለከታለን፡፡ የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ሳይቀር በልዩ ሥነ ሥርዓትና በደመቀ ኹኔታ ይጾማል፡፡ አብዛኞቹ ምእመናን የዕረፍት ጊዜ በመውሰድ በገዳማትና በየአብያተ ክርስቲያናት ሱባዔ በመግባት ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ አሥራ አምስት ቀን ድረስ ጾም፣ ጸሎት በማድረግ ይቆያሉ፡፡ ጾም ጸሎት ሲያደርጉ ደግሞ በድሎት ሳይኾን በየዋሻው፣ በየመቃብር ቤቱና አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እንጨት ረብርበውና ሳር ጎዝጉዘው ጥሬ እየበሉ ነው፡፡

ፍልሰታ ምን ማለት ነው?

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ለዚህ ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፤ ‹‹ፍልሰታ ማለትፈለሰ – ተሰደደ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ፍልሰትማለት ደግሞ የተለያየ ትርጕም ቢሰጠውምፍልሰታ ለማርያም› ተብሎ ሲገለጽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት (የተነሣችበት) ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ማለት ነው፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ አባተም በተመሳሳይ መልኩ ስለ ፍልሰታ እንዲህ በማለት ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹‹ፍልሰታ ለማርያም› የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾንፍልሰታ› ማለት ደግሞፈለሰ› ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ፍልሰት› ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን (መፍለስን) ያመለክታል፡፡ እመቤታችን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደ ተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር የእመቤታችንን ሥጋ እንዲገልጥላቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን በማየት በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለኾነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቍረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡›› 

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ‹‹የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ‹‹እመቤታችንማ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ናት››  ብሎ ነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሣሣት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባዔ ያዙ፡፡ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋ ነሐሴ ፲፬ ቀን ተቀብራለች፡፡

ይኹንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያየው ሲቀብሯት ያላየው ሐዋርያው ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ አገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችን ስታርግ ሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ ምእመናን ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚዘከርበት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነ ጾም ነው፡፡ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ጾሙን ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቈርባሉ፡፡

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ደጉ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር በመኾኗ እና ሕዝበ ክርስቲያኑ ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው መሬት ላይ እየተኙ፣ ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡ ምእመናን ፍልሰታን ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስለሳባቸው ነው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡

ይቆየን