“ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” (ዮና.፩፥፮)
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ጥር ፳፮፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ይህን ቃል የምናገኘው በትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ውስጥ ነው፤ የተናገሩት ደግሞ እግዚአብሔርን የማያመልኩ ይልቁንም ጣዖት አምላኪ ሰዎች ናቸው። በነነዌ ሀገር ንጉሡ ስልምናሶር በነገሠበት ዘመን የነነዌ ሕዝቦች እግዚአብሔርን በደሉ፣ ከሥርዓቱ ፈቀቅ አሉ፤ ጣዖት አምላኪዎች ሆኑ፤ ጩኸትም አበዙ።
እግዚአብሔርም ተቆጣቸውና ሊገሥጻቸው ዮናስን “ተነሥና ወደ ነነዌ ሀገር ግባ፤ በድለውኛልና ነነዌ በሦስት ቀን ትጠፋለች ብለህ ስበክ” አለው። ዮናስ ግን “የአንተ ምሕረት እጅግ የበዛ ሲሆን ትጠፋለች ብዬ ተናግሬ እሳት ከሰማይ ሳይወርድ ቢቀር ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን?” አለና ከእግዚአብሔር ሊደበቅ መንገድ ጀመረ። (ዮና.፩፥፩-፫)
ነቢዩ ዮናስ እንደ ስሙ ትርጓሜ የዋህ ነበርና ከእግዚአብሔር ሊሠወር ፈለገ፤ ዓለምን በእጁ የያዘ ከዓለም በአፍአ ከአለው እግዚአብሔር ሊሸሽ መሞከሩ በእውነት የዮናስን የዋህነት ያመለክታል። ክቡር ዳዊት “ተነክረ አእምሮትከ በላዕሌየ ጸንዐተኒ ወኢይክል ምስሌሃ አይቴኑ አሐውር እም መንፈስከ ወአይቴ እጎይይ እምቅድመ ገጽከ፤ ዕውቀትህ በእኔ ላይ ተደነቀች፤ በረታችብኝ፤ ወደ እርሷም ለመድረስ አልችልም። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ጥልቁም ብወርድ፤ አንተ በዚያ አለህ” በማለት ተናግሯል። (መዝ.፻፴፰፥፮-፰) ስለዚህ በተርሴስ እግዚአብሔር የለምን?
ዛሬም እንደ ዮናስ ስንት ሞኝ ሰው አለ መሰላችሁ? እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ ፍለጋ የሚንከራተት ብዙ ሰው እግዚአብሔር በመጠጥ ቤት፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በዩንቨርሲቲ፣ በመንግሥት መሥርያ ቤት፣ በሌሊት እግዚአብሔር የለም ብሎ ኃጢአት የሚሠራውን ቤት ይቁጠረው። ክርስቲያን ማለት የክርስቶስን ስም የተሸከመ፣ በስሙ የሚጠራ፣ የክርስቶስን መስቀል ተሸክሞ የሚከተል፣ ዘወትር ቀራንዮን የሚያስታውስ፣ ሆኖ ሳለ ቦታና ሰዓት እየመረጡ እግዚአብሔር የለም ማለት ይገባልን? ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ “እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ? እርሱም እንዲሰቀል አስቀድሞ የተጻፈለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” እንዳለ ዘወትር ቀራንዮን እያስታወስን ከክርስቶስ ጋር እንኑር። (ገላ.፫፥፩)
ወደ ተነሣንበት ታሪክ ስንመለስ ዮናስ በባሕር ላይ መንገዱን ቀጠለ፤ ማዕበሉ መርከቧን እያማታት ነው። ዮናስ ግን ትልቅ እንቅልፍ ላይ ነው። በእውነት ዛሬ ስንት እንቅልፋም አሉ? ቤተ ክርስቲያን የመከራ ዶፍ እየወረደባት ማዕበሉ እያማታት ከቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ተኝተው የሚያንኮራፉ ስንቶች አሉ? የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! እነዚህ የተኙትን ሰዎች ማን ይቀስቅሳቸውና ወደ አምላካቸው ይለምኑ?
ዮናስ ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ነው፤ መርከቢቱ ግን እጅግ እየተናወጸች ነው። በዚህም ተሳፋሪዎች ተጨነቁ፤ መጥፋቸውም እንደሆነ በማሰብ አለቀሱ። ሁሉም ወደ ሚያመልኩት አምላክ ጮሁ፤ ነገር ግን መልስ አላገኙም። የያዙትን ዕቃ ቢቀል ይሻል እንደው እያሉ ወደ ባሕር ወረወሩት፤ ነገር ግን ማዕበሉም ሆነ ወጀቡ እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አልመጣም። በመጨረሻም የተኛውን ዮናስ ቀሰቀሱትና እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ፡፡… ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድን ነው? ….ሀገርህ ከየት ነው?” ድንቅ ጥያቄ ነው ክርስቲያኖች! እኛ ብንጠየቅ ምን ይሆን መልሳችን? በእውነት ሥራችን ምንድን ነው? የምናመልከውስ ማንን ነው? መንገደኛው ዮናስ ግን እንዲህ አለ፤ “እኔ ዕብራዊ ነኝ የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” አለ፤ ሀገሩን ግን አልተናገረም።(ዮና.፩፥፮-፱)
ክርስቲያኖች እስኪ እኛም “እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ ሥራዬም እግዚአብሔርን ማምለክ ለእርሱም መገዛት ነው” ብለን እንመለስ! መከፋፋል የሌለበትን ነገር እንምረጥ። እኛ የተወለድነው ከማይጠፋ ዘር በማዕከለ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ አይደል? ተፈጥሮን ስንመረምር እግዚአብሔር ሰውን ከእንስሳት ይልቅ ከምድር ከፍ አድርጎ በሁለት እግሩ ቁሞ ወደ ላይ፣ ወደ ታች፣ ወደ ኋላ፣ ወደ ፊት፣ እንዲያይ ሲያደርገው፣ በትሕትና ወደ መገናኛው ወደ ምድር ጎንበስ እንዲል፣ ሰማያዊ ተስፋ ያለው፣ ሀገሩ በሰማይ እንደ መሆኑ አውቆ ቀና ብሎ እንዲያስብ አይደል? ቤተ ክርስቲያንም በቅዳሴዋ “አልዕሉ አልባቢክሙ፤ ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ”፣ “በሰማይ የሀሉ ልብክሙ፤ ልቡናችሁ በሰማይ ይኑር” በማለት ከምድራዊ ነገር እንድንወጣ ሰማያዊውን ነገር እንድናስብ ትነግረናለች። እናም ከምድራዊ ሐሳብ ይልቅ ሰማያዊውን ሐሳብ እንምረጥ።
ዮናስ ከእንቅልፉ ተነሥቶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ ዐውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ፀጥ ይልላችኋል፡፡” (ዮና.፩፥፲፪) ከቅድስና መዓርጋት አንዱ ኩነኔ (በራስ ላይ መፍረድ) ነውና ዮናስ በራሱ ላይ ፈረደ። ክርስቲያኖች ከዮናስ ይህን እንማር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ኃጢአትን ማመን፣ ስለሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠት፣ እግዚአብሔርን አምኖ በመከራ ውስጥ ሆኖ ጸሎት ማቅረብን እንማር። እንዲህ ባለማድረጋችንም ዓለማችን ድብልቅልቋ ሲወጣ ስለ ሕዝቡ ክፋት እግዚአብሔር “ጨካኝ ንጉሥ ያነግሣል” የተባለው ሲፈጸም ያጣነው “ለዚህ ተጠያቂ እኔ ነኝ” የሚል ከሚመጣው መከራ ወገኖቹን መታደግ የሚል ሰው ነው።
ማዕበሉ መቆም ስላልቻለ ዮናስ መጣል ግድ ሆነበት፤ አውጥተውም ወረወሩት፤ ያኔ ባሕሯ ድርጎዋን ተቀብላ ፀጥ አለች፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ። ዮናስ ግን መንገድ ቢቀይርም ጉዞውን ቀጠለ፤ ወደ ተርሴስ በመርከብ ተጭኖ ሊሄድ የነበረው ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ተጭኖ ወደ ነነዌ መጓዝ ጀመረ። ዮናስ በታላቅ ዓሣ አንበሪ ተውጦ ወደ ነነዌ ተጓዘ፤ በመከራ ውስጥ መንገድ ያለው እግዚአብሔር በባሕሩ መካከል የሚያሳልፈው የታመነ ስለሆነ መርከቡን አዘጋጀለት። ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ጀመረ፤ ነቢዩ ዳዊት “በመከራ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ” እንዳለ በመከራው ጊዜ ወደ አምላኩ ጮኸ። (መዝ ፵፱፥፲፭)
ክርስቲያኖች መከራ ሲያጋጥማችሁ ያሰባችሁት አልሳካ ሲል ጉዞአችሁ ወዴት ነው? ለማን ነው አቤት የምትሉ? ተስፋ ባጣችሁ ጊዜስ ወደ የት ነው የምትሔዱት? ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ቀርበን ችግራችንን እንነግረው ዘንድ አይገባምን? እግዚአብሔር ዮናስን ሰማው፤ በሰላምም ከሦስት ቀን እና ሌሊት በኋላ ዓሣ አንበሪውን አዘዘው፤ ከነነዌ ከተማ ባሕር ዳርቻም ተፋው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀበለ፤ ልብ በሉ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ ኃጢአት በበዛባቸው ቦታዎች ሒዶ የሚያስተምር ማን ነው? በእውነቱ ሰባኪውስ ያስተውላልን? መጠጥ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ መዝናኛ ቦታዎች፣ በልዩ ልዩ ቦታ የሚያስተምር ይኖር ይሆን? የእኛ ስብከት የምሕረት ዐደባባይ በሆነችው በቤተ ክርስቲያን አልተወሰንምን? ልትጠፋ ላለችው ከተማ ማን ይላክ ይሆን?
ነቢዩ ዮናስ ግን ወደ ነነዌ ገባ፤ አፉንም ከፈተ፤ “ነነዌ ከሦስት ቀን በኋላ ትጠፋለች? በማለት ቃሉን አሰምቶ ተናገረ፤ (ዮና.፪፥፬) እንደ መብረቅ የሚያስደነግጥ ስብከት! ዮናስ የሚያስፈራውን ስብከት ቀጠለ፤ “የነነዌ ከተማ ትጠፋለች” እያለ መጮህን አበዛ። ይህ ቃል ከቤተ መንግሥት ሳይቀር ተሰማ፤ ንጉሡም ዐዋጅ ዐወጀ፤ እንስሳት ሳይቀር ሁሉም እንዲጾሙ አዘዘ፤ እርሱም አመድ ነስንሶ፣ ማቅ ለብሶ፣ ከዙፋኑ ወርዶ አለቀሰ ጸለየ። ዛሬ ግን የእኛ ስብከት ሰሚ ያጣ አይመስላችሁም? እንኳንስ ቤተ መንግሥት ቤተ ክህነት እንኳን መሰማት አልችል ብሎ ከዙፋኑ የሚወርድ፣ ለጸሎት እጁን የሚዘረጋ ጠፋ።
እናም ሁላችንም በአንድ ቃል ሆነን “ነቢዩ ዮናስ ሆይ፤ እባክህ ና እና አስተምረን! ና ዛሬ ለቤተ መንግሥቱ ንገርልን! ጀሮ ያለው መስማትን ይሰማ ዘንድ ና አትዘግይብን!” እያልን እንማፀነው። ዮናስ አሁንም መንገዱን ቀጠለ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ከተማዋ ስትጠፋ ሊመለከት ወደ ተራራ ወጣ፤ በእዚያም ጎጆ ሠራ፤ አምላክ በቸርነቱም አንዲትን ቅል አበቀለ እና ከፀሐይ እንደትጋርደው አደረገ፤ በዚያ ሆኖም የእግዚአብሔርን መዓት ይጠባበቅ ጀመረ። እግዚአብሔር ግን ምሕረቱ እጅግ የበዛ ኃጢአትን ይቅር የሚል ስለሆነ ጾም ጸሎታቸውን ሰምቶ የታዘዘው እሳት የዕፅዋቱን ቅርንጫፍ ለምልክት እያቃጠለ ተመለሰ።
ነቢዩ ዮናስ ግን እጅግ አዘነ፤ ነቢየ ሐሰት ተብሎ መኖርን ቢፈራም እግዚአብሔር ግን ሊያስተምረው ፈልጎ ስለነበር በቅላ ጥላ የሆነችውን ቅል ትል በልቶአት እንድትደርቅ አደረገ። ነቢዩም ፈጽሞ አዘነ፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ በውኑ ስለዚህች ቅል ታዝናለህን? እርሱም “እስክሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ” አለ። “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምክባት፣ ላላሳደግሃትም በአንድ ሌሊት ለቀበለች በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃልና፤ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃይ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ እንዴት አላዝን? አለው። (ዮና.፬፥፱-፲፩) ነቢዩ ዮናስም ተጸጽተ፤ ሰብአ ነነዌም ከመጣው መዓት ዳኑ፤ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶአልና።
አምላካችን እግዚአብሔር ልመናችንን ሰምቶ ከሚመጣው መዓት በቸርነቱ ይታደገን፤ አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።