ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት
ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዓለ ጰራቅሊጦስን ተከትለው ሁለት ዐበይት አጽዋማት ይጀመራሉ፡፡ እነዚህም ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ) ሲኾኑ፣ ቍጥራቸውም ከሰባቱ አጽዋማት ነው፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማሩ በፊት ጾሟል (ዘፀ.፴፬፥፳፰)፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም የተስፋውን ቃል መፈጸም እየተጠባበቁ እግዚአብሔርን ውረድ፤ ተወለድ እያሉ ይጾሙ፣ ይጸልዩ ነበር፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የምግባር መሠረት መኾኑን ሊያስተምረን ወንጌልን ከመስበኩ አስቀድሞ ጾሟል (ማቴ.፬፥፩-፲፩)፤ ሐዋርያትም በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ሕገ ወንጌልን ለሕዝቡ ከማስተማራቸው አስቀድሞ ጾመዋል፡፡ እኛም እነርሱን ተከትለን፣ በእነርሱ ሥርዓት በመመራት፣ በሐዋርያት ላይ ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብት በእኛም ላይ እንዲያድርብን በየዓመቱ ጾመ ሐዋርያትን እና ጾመ ድኅነትን፣ ሌሎችንም አጽዋማት አክብረን መጾም እንደሚገባን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል (ፍት.ነገ. ፲፭፥፭፻፹፮)፡፡
ጾመ ሐዋርያት ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በመላው ዓለም ተዘዋውረው ወንጌልን ከመስበካቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ድኅነት ደግሞ ስያሜው እንደሚያመለክተው ‹የመዳን ጾም› ማለት ሲኾን፣ ይህም በብሉይ ኪዳኑ አጽዋማት በጾመ አስቴር እና በጾመ ዮዲት የተተካ የሐዲስ ኪዳን ጾም ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በሐማ ምክንያት በእስራኤል ላይ ታውጆ የነበረው ሞት በጾመ አስቴር እንደ ተሻረ ዅሉ፣ በሐዲስ ኪዳንም በዕለተ ረቡዕ በጌታችን ላይ በተፈጸመው ምክር የሰይጣን ሴራ ፈርሷልና በጾመ አስቴር ምትክ ረቡዕን እንጾማለን፡፡
በብሉይ ኪዳን በጾመ ዮዲት ምክንያት ሆሎሆርኒስ ድል እንደ ተደረገበት ዅሉ፣ በሐዲስ ኪዳንም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት ዲያብሎስ ድል ተደርጓልና በጾመ ዮዲት ምትክ ዓርብን እንጾማለን፡፡ ዕለተ ረቡዕ የጌታ ሞት የተመከረበት፤ ዓርብም አምላካችን የተሰቀለበት ዕለት ነውና በመስቀሉ መሥዋዕትነት ያገኘውን ድኅነት ዘወትር ማሰብ ስለሚገባን ዅልጊዜ እንድንጾማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡ የእነዚህ የሁለቱ ቀናት (የረቡዕ እና ዓርብ) ጾም ‹ጾመ ድኅነት› ይባላል፡፡
በአጠቃላይ ጾመ ሐዋርያትና ጾመ ድኅነት እንደ ጾመ ነነዌና ዐቢይ ጾም የበዓላትና የአጽዋማት ማውጫ ቀመርን ተከትለው የሚመጡ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል የሚመደቡ የጾም ጊዜያት ናቸው፡፡ የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ (መፈጸሚያ) የቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በዓለ ዕረፍት (ሐምሌ ፭ ቀን) ሲኾን፣ ጾመ ድኅነት ግን ከበዓለ ኀምሳ በስተቀር ዓመቱን ሙሉ የሚጾም ጾም በመኾኑ ፋሲካው በዓለ ትንሣኤ ነው፡፡
በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ግንቦት ፳፰፤ ጾመ ድኅነት ደግሞ ግንቦት ፴ ቀን ይጀመራሉ፡፡ በመኾኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፤ የምንወቀሰውም በራሳችን መጥፎ ድርጊት መኾኑን ተረድተን ይኼ የቄሶች፤ ይኼ የመነኰሳት ነው የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ዅላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው ጸጋና ሀብት ይበዛልናልና ራሳችንን ለጾም እናዘጋጅ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡