ጸበል ጸዲቅ (ክፍል አንድ)

ሚያዚያ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ቡድንን የያዘና ሰባት አባላትን ያቀፈው ልዑክ በምዕራብ ጎጃም፤ ደቡብ ጎንደርና ሰሜን ጎንደር የተመረጡ ቅዱሳት መካናትና አድባራትን ለመዘገብ ሃያ ሁለት ቀናት ቆይታ ለማድረግ ከሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሰናል፡፡ በተጓዝንባቸው ቦታዎች ያጋጠሙንና እያከናወንናቸው ያሉትን ሥራዎች ለአንባቢያኑ እናቀርባለን፡፡ ሂደቱን በተመጠነና በቅምሻ መልክ የምናቀርብ በመሆኑ ከዚህም ከዚያም የምናገኛቸውን መረጃዎች ለአንባቢያን እናደርሳለን፡፡ በዚህም ምክንያት የጉዞ ማስታወሻችንን ጸበል ጸዲቅ በሚል ሰይመነዋል፡፡

መነሻ :-
መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፤ በእርሱም ታመን፤ እርሱም ያደርግልሃል /መዝ.36፥5/ እንዲል ቅዱስ ዳዊት መንገድ ከመጀመራችን በፊት በማኅበሩ ጽ/ቤት አሸኛኘት ተደርጎልናል፡፡ እስካሁን ማኅበሩ ካደረጋቸው የጋዜጠኞች የሕብረት ተልእኮ አንጻር ይህ ልዑክ በብዛት ሆኖ መጓዙና ብዛት ያላቸው ቅዱሳት መካናትን በማካለል ረገድ ለየት እንደሚያደርገው የተገለጸለት ሲሆን በጉዞው የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሙት እንኳን በትዕግሥትና በጥበብ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ተልእኮውን አሳክተን እንድንመለስ  አደራውን ተቀብለን በአባቶች ምክር፤ ጸሎትና ቡራኬ ተደርጎልን ተንቀሳቅሰናል፡፡

ከረፋዱ 4፤05 ሰዓት መነሻንን ብናደርግም ከመኪና ጥገና ጋር በተያያዘ ለተወሰኑ ሰዓታት በመቆየት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጥገናውን በማጠናቀቅ ጉዞውን ጀመርን፡፡ ጫንጮ፤ ደብረ ጽጌ፤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሊባኖስ ገዳም መገንጠያ፤ ፍቼ፤ ገደብ፤ ገብረ ጉራቻ፤ ኩዩን አልፈን  ጎሐ ጽዮን ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ደረስን፡፡ ከጎሐ ጽዮን እስከ ዐባይ ድልድይ ያለውን የ20 ኪሎ ሜትር አስፈሪውን መንገድ የመኪናችን ሾፌር ነብያት መኪናውን እየተቆጣጠረ ጠመዝማዛና ቁልቁለታማውን መንገድ ካለ ስጋት እንድንጓዝ አስችሎናል፡፡ ፍርሃትና ጭንቀት ከእኛ እንዲርቁም የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ቶማስ በየነ ፈገግታ አዘል ጨዋታዎች አግዘውናል፡፡ ቪዲዮ ቀራጩ ሙሉጌታም አልፎ አልፎ ለቴሌቪዥን ፕሮግራም ግብአት የሚሆኑ ምስሎችን ለመውሰድ መኪናውን እያስቆመ ወርዶ ይቀርጻል፡፡ ሌሎቻችን ለራሳችን በሚመቸን መልኩ ውስጣችን የተፈጠረውን ስሜት በራሳችን አገላለጽ በማስታወሻ ደብተራችን እንከትባለን፡፡

ሃያ ኪሎ ሜትሩን አገባደን አባይ ድልድይ ደረስን፡፡ የኦሮሚያንና የአማራን ክልል የሚለየውን የአባይ ድልድይ ላይ ሁላችንም ወርደን ለማስታወሻና ለዘገባችን የሚረዳንን ፎቶ ግራፍ በመነሳትና በማንሳት ተመልሰን የአባይን ድልድይ ተሻግረን ቀሪውን እስከ ደጀን ያለውን 20 ኪሎ ሜትር ተያያዝነው፡፡

የአባይን ድልድይ እንደተሻገርን በሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ የተተከለውን የአባይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ተሳልመን አለፍን፡፡ የአባይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጳጉሜን ሦስት ቀን በድምቀት እንደሚከበርና በእለቱም የአባይ ውኃ ወደ ጸበልነት እንደሚቀየር የቪዲዮ ባለሙያው ሙሉጌታ የሚያውቀውን ነገረን፡፡ ተራራውን እየወጣንም የኪዳነ ምሕረት፤ የቅዱስ ገብርኤል፤የአቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ እንዲሁም የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያናትን እየተሳለምን አጠናቀን ደጀን ደረስን፡፡  

ከደጀን የትመን፤ ሉማሜ፤ አምበር፤ ራባ ጫካዎች፤ ደብረ ማርቆስን አልፈን ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ሲሆን ከአዲስ አበባ ደምበጫ ከተማ 350 ኪሎ ሜትር አጠናቀን የደምበጫ ወረዳ ማእከል አባላት ወንድሞቻችን በአክብሮት ተቀበሉን፡፡ ወዳዘጋጁልን ማረፊያም በማምራት በእንግድነት ተቀብለውናልና እግራችንን አጥበው እረፍት አደረግን፡፡ ከእራት በኋላም ውሏችንን በመገምገም እንዲሁም አርብ ስለምንሰራው ሥራ ውይይት በማድረግና ሌሊት የምንነሳበትን ሰዓት በመወሰን በአንድነት ጸሎት አድርሰን ተኛን፡፡
ሚያዚያ ሦስት ውሏችን ይህንን ይመስል ነበር፡፡ እንዲህም አለፈ፡፡

ይቆየን