ጸበል ጸዲቅ /ክፍል ሁለት/

ሚያዚያ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳም
ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

tsebele tsedeke 3ከንጋቱ 12፡30 ደምበጫ ከተማ ላይ ካረፍንበት የማኅበረ ቅዱሳን ከራድዮን ምግብ ቤት ተነስተን ከወረዳ ማእከሉ ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ወደ ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በማምራት ጸሎት አደረስን፡፡ በያዝነው እቅድ መሠረት ዲያቆን ቴዎድሮስ ኃይሉና ዲያቆን ዮሴፍ ይኩኖ አምላክ የጽርሐ አርያምን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲሰሩ እዚያው ትተናቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ቶማስ በየነ፤ የቪዲዮ ካሜራ ባለሙያው ሙሉጌታ፤ ዲያቆን ታደለ ሲሳይና እኔ ሆነን የደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳምን ለመዘገብ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን እግዚአብሔርን ተስፋ አድረገን በሾፌራችን ነብያት መንግስቴ እየተመራን የ47 ኪሎ ሜትሩን መንገድ ተያያዝነው፡፡

ዋድ የገጠር ከተማን፤ ዋድ ኢየሱስ፤ ዋድ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያናትን አልፈን፤ ደግን ወንዝን ተሻግረን፤ ዘለቃን የገጠር ከተማን አልፈን ወደ ገዳሙ መግቢያ ደረስን፡፡ ከተራራው አናት ላይ ሆነው ወደ ገዳሙ ሲመለከቱ እልም ባለ በረሃ ውስጥ ለብቻው ለምልሞ የተገኘ የምድር ገነት ያስመስለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት በጸሎትና በልማት አገልግሎት ላይ የተጠመዱት መነኮሳትና መነኮሳይያት ማረፊያ ቤቶች፤ የመድኀኔዓለምንና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያናትን በመክበብ እጅብ ብለው ደምቀው ይታያሉ፡፡  

አርባ ሰባት ኪሎ ሜትሩን ለማገባደድ 2፡30 ሰዓት ፈጅቶብን የደረስነው ከጠዋቱ 3፡00 ላይ ነው፡፡ ከመኪናችን ወርደን በእድሜ ጠገብ ዛፎች፤ ጥላ ተጋርደን የሙዝ፤ የፓፓያ፤ የብርቱካን፤ የአቦካዶ፤ . . . ዘርዝረን በማንጨርሳቸው የፍራፍሬዎችና የሸንኮራ አገዳ ተክሎችን እያለፍን ጸበል መጠመቂያ ሥፍራ ላይ ደረስን፡፡ ከተለያዩ የገዳሙ አቅራቢያ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በመጡ ተጠማቂዎች ሕጻናትን ጨምሮ ተሞልቷል፡፡

ከተራራው ሥር የሚፈልቁ ምንጮች መውረጃ ቦይ ተዘጋጅቶላቸው አትክልቶቹን ያለመሰልቸት ያጠጣሉ፡፡ ጸበሉም ተጠማቂዎች ከተጠመቁ በኋላ ወደ አትክልልቶቹ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ በግዮን፤ ኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች የተከበበ እስኪመስል ድረስ የንጹህ ውኃ ጅረቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በልምላሜ በተሞላው ገዳም ተውጠው ይቀራሉ፡፡ የሚባክን ውሃ የለም፡፡ ድካማችን ሁሉ ከላያችን ላይ ተገፍፎ በብርታት፤ በእርካታና በተመስጦ ተሞልተናል፡፡ የምናያቸው፤ የምንሰማቸው ድምጾች ሁሉ አዳምና ሔዋን የኖሩባንት ገነትን tsebele tsedeke 5በዓይነ ሕሊናችን እንድናስብ አስገድዶናል፡፡ ደብረ ገነት ሽረት መድኀኔዓለም በምድር ላይ ያለች የገነት ተምሳሌት ሆና ታየችን፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ስንገባ በገዳሙ ውስጥ በምናኔና ገዳሙ በሚያከናውናቸው የልማትና የአስተዳደር ሥራዎች አበምኔቱን በማገዝ ላይ የሚገኙት አባ ዳዊትን ከሌሎች መነኮሳት ጋር በመሆን የእለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ አገኘናቸው፡፡ ቡራኬ ተቀብለን በገዳሙ ሥርዓት መሠረት አባቶች አደግድገው እግራችንን አጠቡን፡፡

የገዳሙ መሥራችና አበምኔት አባ ገ/ኢየሱስ አካሉ ወደ ገዳሙ የሚያስገባውን ጥርጊያ መንገድ ለማሰራት ዘለቃ ወደሚባለው ከተማ በመሔዳቸው የምንፈልገውን መረጃ አባ ዳዊት ሊሰጡን እንደሚችሉ ተስማማን፡፡

አጭር መረጃ ስለ ገዳሙ፡- tsebele tsedeke 4
የደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳም በአባ ገ/ኢየሱስ አካሉ በ1969 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1973 ዓ.ም. በሣር ክዳን ተተከለች፡፡ ሥፍራው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ የነበረ ሲሆን አንበሳ፤ ነብርና ዘንዶ በብዛት ይገኙ እንደነበር አባ ዳዊት ይገልጻሉ፡፡ ቀስ በቀስ ገዳማውያን እየተበራከቱ የልማት ሥራው እየሰፋ ሲሔድ የገዳሙ ይዞታም ሊሰፋ ችሏል፡፡ የክልሉ መንግስት በገዳሙ ውስጥ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰፊ የእርሻ መሬት ለገዳሙ ተሰጥቷል፡፡ ዳጉሳና በቆሎ እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ በስፋት ይመረትበታል፡፡  

በሁለት ቦታዎች ላይ ሞፈር ቤቶች፤ ተራራው ላይ በስተደቡብ አቅጣጫ የአቡነ አረጋዊ ገዳም ቋርፍ ቤት ይገኛል፡፡ በገዳሙ ውስጥ 600 መናንያን ሲኖሩ 320ዎቹ መነኮሳት፤ 280ዎቹ ደግሞ መነኮሳይያት ናቸው፡፡ መነኮሳቱ በወንድ ሊቀ ረድእ፤ መነኮሳይቱ በሴት ለቀ ረድእ ይመራሉ፡፡ የእለት ተእለት ሥራቸውንም በሊቀ ረድኦቻቸው አማካይነት እየተመደቡ ያከናውናሉ፡፡ አረጋውያኑ ደግሞ በጸሎት፤ ቤተ ክርስቲያኑን በመጠበቅ፤ አትክልቶቹን ከአውሬ በመከላከል ገዳሙን ይረዳሉ፡፡ የገዳማውያኑ የጸሎት፤ የሥራና የምግብ ሰዓታትም የተወሰኑ ናቸው፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ የቅዱስ ሚካኤል፤ የአቡነ አረጋዊና የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ታቦት በዚሁ ገዳም ይገኛሉ፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጣሪያው በሣር ክዳን የተሸፈነ ሲሆን ሳይፈርስ በቅርስነት እንዲያዝ በመወሰኑ ከመድኀኔዓለም ክርስቲያን በስተምእራብ አቅጣጫ ከተራራው ሥር ከሚገኘው ቋጥኝ ድንጋይ እየተጠረበ ቤተ ክርስቲያኑ በመገንባት ላይ ነው፡፡

የዮርዳኖስ ጸበል፤ የአቡነ አረጋዊ፤ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የቅዱስ ሚካኤል ጸበል በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሕሙማን እየተጠመቁ ፈውስ በማግኘት ላይ ናቸው፡፡  የዮርዳኖስ ጸበል አፈሩን ከኢየሩሳሌtsebele tsedeke 6ምና ከዋልድባ ገዳማት እንደመጣም አባ ዳዊት ገዳሙን እያስጎበኙን ነግረውናል፡፡

የአብነት ትምህርት ገዳሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከ1975 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. በጉባኤ ቤቱ ቅዳሴን ከአባ ገብረ ማርያም ተምረው በማጠናቀቅ አባ ገብረ ማርያም ሌላ ገዳም ለማቅናት በመሄዳቸው ጉባኤውን የተረከቡት መምህር ገብረ ሥላሴ ፈንታ ለ28 ዓመታት የቅዳሴ ትምህርት በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ ከሁለት መቶ በላይ ደቀመዛሙርትም እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ታላላቅ ሊቃውንትንም አፍርተዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በአባ ገብረ ማርያም ከተማሩት አባቶች መካከልም ብፁዕ አቡነ አብርሐም አንዱ ናቸው፡፡

ይቆየን