ጸሎትና ክርስቲያናዊ ሕይወት
በለሜሳ ጉተታ
ጸሎት ክርስቲያኖች ከሚያከናውኗቸው መንፈሳዊ ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ክርስቲያን በጸሎት የሚተጋ ሰው ነው፤ ያለ ምግብ ሰው መኖር እንደማይችል ሁሉ ክርስቲያንም ያለ ጸሎት መኖር አይችልም፡፡ ከውኃ ውስጥ የወጣ ዓሣ ሕይወት እንደማይኖረው ሁሉ ከጾም ከጸሎት እና ከንስሓ ሕይወትም የተለየ ክርስቲያን የሞተ ነው፤ ሕይወት የሌለው በነፋስ ብቻ የሚንቀሳቀስ በድንም ይሆናል፤ መጸለይ ሕይወት ነውና፤ አለመጸለይ ደግሞ የነፍስ ሞት ነው፡፡
ጸሎት የክርስቲያኖች የነፍስ ምግብ ነው፡፡ ያለ ጸሎት መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ያለ ጸሎት በአገልግሎት ላይ መትጋት መንፈሳዊ ፍሬዎችን ማፍራት እና ከሥጋ ፈቃድ ሐሳብና ተግባርም መራቅ አይቻልም፡፡ የማይጸልይ ሰው ሕይወት የተለየው ሰው መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፤ ጸሎት ሰላምና ዕረፍት ነው፡፡ ሰላምና ዕረፍትንም ለማግኘት ከኃጢአት እራሳችንን ለመጠበቅ የጽድቅ ሥራንም ለመሥራት የቅድስና ሕይወትን ለመኖር የቅዱሳን አስረ ፍኖትን ለመከተል ከበረከታቸው ለመካፈል ጸሎት መሠረታዊ ተግባር ነው፡፡
ጸሎት ምስጋናና ልመና ነው፤ እግዚአብሔር ስላደረገልን፣ ስለሚያደርግልንም እንዲሁም ለሚያስብልንም ነገር የምናመሰግንበት መንገድ ጸሎት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ንጹሕ ልቡና እንዲሰጠን ከክፋት፣ ከተንኮልና ከምቀኝነት እንዲጠብቀን ጥበብና ማስተዋሉንም እንዲሰጠን፣ ቅን ልቡና እንዲፈጥርልን ልዩነትንና ክፋትን ከመካከላችን እንዲያጠፋልን እና እውነተኛ ፍቅር እንዲሰጠን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ በአሁን ጊዜ በዓለማችን በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ሰላም ጠፍቷልና እርሱ ሰላምን እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል፤ ጌታችን‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› ብሎ ያስተማረን ለዚህ ነው፡፡ (ማቴ.፳፮፥፵፩)
ጸሎታችን የማይሰማው ለምንድን ነው ?
(የምትለምኑትን አታውቁም.ማቴ.፳፥፳፪)
‹‹የምትለምኑትን አታውቁም›› ብሎ የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህንን ቃል የተናገረውም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ልመናንን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ልጆቿን ለማክበር ፈልጋ ከምድር ከፍ ብዬ እነግሣለሁ ሲል ስለሰማች አንዱን በግራው ለሌኛውን ደግሞ በቀኙ ሹመት እንዲሰጣቸው በማለት ልመናን አቅርባ ነበር፡፡ እርሱ ግን በዕለተ ዐርብ የሚቀበለው ምድራዊ ሥልጣንና ሹመት ሳይሆን መከራን ነበር፡፡ ለዓለም እና ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን ሥጋዊ መከራ፡፡ ይህንንም ጌታችን እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው›› (ማቴ.፳፥፲፰-፲፱)፡፡ እኛም ዛሬ ልመናችንን ልናውቅ ይገባል፤ ከዚህም የተነሳ ልማናና ጸሎቷ ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቷዋል፡፡
የመጀመሪያው ለጸሎታችን ሥምረት (ተቀባይነት) የልብ ንጽሕና ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በልባችን ውስጥ ቂምና በቀልን ይዘን በጥላቻ ተሞልተን የልዩነት ግንብን መሥርተን በተለያዩ ሥጋዊ ነገሮችም እየተከፋፈልን መጸለይ በእውነት ድፍረት ነው፡፡ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በእውነት ልቡ ንጹሕ የሆነ ሰውን ( ክርስቲያን ) ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከክፋትና ከተንኮል የራቀ እምነት ያለው በጎ ምግባር የሚያዘወትርና ዓለምን ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርስን መሪ ማግኘት ከብዶናል፡፡ ሁሉም ሰው በፖለቲካ፣ በዘር፣ በሀገር፣ በድንበር ጉዳይ በመከፋፈል ወደ ግጭትና ጦርነት እያመራ ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ግን ተግባሩ አረማኔያዊ ነው፤ ወገንተኛ ሆነናል፡፡ ጥላቻ፣ ዘረኝነትና የገንዘብ ፍቅር ገዝቶ ባሪያም አድርጎናል፡፡ ይህንን መጥፎ ስሜት ይዞ መጸለይ ድፍረት ከመሆኑ በተጨማሪ ከንቱ ልፋት ነው፤ እግዚአብሔርን ማሳዘንም ነው፡፡ ይህ እምነትን ያሳጣል፤ ወደ ጥርጣሬም ይከታል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ላይም ዝለትን ያመጣል፡፡ ስለዚህ ከመጸለያችን በፊት ልብን ንጹሕ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምን እንዴትና መቼ እንደምንጸልይም ልናውቅ ይገባል፡፡ ክርስትና በየዋህነት ብቻ የሚከተሉት ሳይሆን ዕውቀትና ሕይወትም ይፈልጋልና፤ ቅዱስ ዳዊት አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ያለው ለዚህ ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን የጸሎት መርሐ ግብራት ላይ መሳተፍ፣ ቅዳሴ ማስቀደስ፣ ኪዳን ማድረስ፣ ውዳሴ ማርያምና ዳዊት ማንበብ (መድገም) ክርስቲያናዊ ምግባር ነውና ንጹሕ ልቡና ይዘን ይህን ልንፈጽም ይገባል፡፡
ሁለተኛው ጸሎታችን ተሰሚነት የማያገኘው የእምነትና የምግባር ባዶዎች ስለሆንን ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን ክርስትናን በስምና በልብስ (በበዓላትና በወቅት) እንጂ በእውነትና በሕይወት የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ ክርስትና ተከታይነት ብቻ አይደለም፤ ሕይወትና ኑሮን ይፈልጋል፡፡ የእኛ ሕይወትና እምነታችን ለየቅል ነው፤ ላያችን ጥሩ መሳዮች ነገር ግን ውስጣችን ክፋት የሞላበት ሆኗል፤ ኑሯችን የፉከራና የሽለላ ሆኖብናል፡፡ በዕውቀትና በእምነት ሳይሆን በስሜታችን መመራት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ ጥዋት ቤተ ክርስቲያን ከሰዓት ጣዖት ቤት ሆኖብናል፡፡ በሥጋ ፍሬ ተጋባር፤ ሥጋዊ ሐሳብና ምኞት ማንነታችንን አሳጥቶናል፤ ፍቅርና ርኅራሄ ርቆናል፤ መተዛዘን አቁመናል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆኖ መጸለይ በራሱ ትልቅ ድካም ነው፤ መመለስን ይፈልጋልና፡፡ ፍቅራችን የጥርስና የስም ሆኖብናል፤ እምነትና ምግባርም ርቆናል፤ ጌታችን ‹‹የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ያለን ለዚህ ነው፡፡ (ሉቃ.፲፰፥፰)
እምነት የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ ምግባር ደግሞ ማገር ነው፤ ያለ እምነትና ተግባር የጸሎት ሰው መሆን አይቻልም፤ ስለዚህ እምነት ምንድን ነው ? ምግባርስ? የእምነት ጥቅምና ዓላማው ምንድን ነው፤ የእኔ የእምነት ሕይወት ምን ይመስላል ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ርኅራኄ ርቆን በጭካኔ ሰንሰለት ታስረናል፤ የእምነትና የምግባር ድቀት (ባዶ መሆን) እያንገላታን ነው፤ ዓለምና የገንዘብ ፍቅር ገዝቶናል፡፡ ታዲያ በእንዲህ አይነት ሕይወት ውስጥ ሆኖ መጸለይ እንዴት ይቻላል? ብንጸልይስ ምን አይነት ውጤትን እንጠብቃለን? ከዚህ ችግር ለመውጣት መጸለይ ያስፈልጋል፤ ግን ጸሎታችን በንጹሕ ልቡና መሆን አለበት፤ አረማችንን ነቅሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ እምነትና በጎ ኅሊናም ሊኖረን ይገባል፤ የንስሓ ሕይወትም ያስፈልጋል፤ እንዲህ ከሆነ ጸሎታችን ተቀባይነትን ያገኝልናል፡፡
ሌላው ለጸሎታችን ሥምረት መሠረት የሆነው ነገር የልብ ኃዘን፣ ጸጸት (ልቅሶ) እና ንስሓ ነው፡፡ የተጠናወተን ክፉ መንፈስ ከእኛ የሚርቀው በልብ ንጽሕና፣ በእምነትና በበጎ ምግባር ስንኖር ነው፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ልባቸው ንጹሕ ስለነበረ ፀሐይን አቁመዋል፣ ባሕርን ከሁለት ከፍለዋል፣ የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል፣ በልብስና በጥላቸውም ድውያንን ፈውሰዋል፤ እሳትን አጥፍተዋል፤ ሕይወታቸው በጸሎት እና በትጋት የተሞላ ነበርና፡፡ ሳይናገሩም እግዚአብሔር የልባቸውን ያውቅ፣ ያሰቡትንም ይፈጽምላቸው ነበር፤ እኛስ ከአባቶቻችን ምን እንማራለን? የእኛስ ሕይወት ምን ይመስላል? ብለን ራስን ማየት ያስፈልጋል፡፡
ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ችግር ላይ በመሆናቸው ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ጠፍቷል፤ እርስ በእርስ ተጨካክነናል፡፡ የዘርና የብሔር፣ የመሬት፣ የሥልጣን፣ የገንዘብና የዓለም ፍቅር አይሎብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተቃጥላለች፤ ተዘርፋለች፤ ካህናትና ምእመናን ተሰደዋል፤ ተገድለዋል፡፡ ዘረኝነትና ሙስናው አምላክ ሆኖብናል፡፡ ከዚህ የሚያወጣን የሐና እና የራሔል ዕንባ በእውነት ያስፈልጋል፡፡ ሱባኤ እንገባለን፤ ሰባቱ አጽዋማትን እንጾማለን፤ ቅዳሴና ኪዳን እናደርሳለን፤ መንፈሳዊ ተግባራትን እንፈጽማለን፤ ግን ለምን መልስ አጣን? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡
ጸሎት ለክርስቲያን የአገልግሎትና የነገሮች ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከጸሎት የሚበልጥ አገልግሎት የለም፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ነገር መሠረቱ ጸሎት ነውና፡፡ ከዚህ የተለየ አገልግሎትም ባዶ ልፋት ከንቱ ዕሩጫ ብቻ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ውጤት የሌለው ድካም ብቻ ይሆናልና፡፡ መጸለይ ስንል የጸሎት መጻሕፍትን ማንበብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ነጭ ልብስም ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መመላለስ ማለት ብቻም አይደለም፡፡ መጸለይ በሕይወት፣ በእውነት፣ በፍቅር፣ በምግባር የሚገለጥ መሆን አለበት፡፡ ጸሎታችን ሰላምና ፍቅርን አንድነትን የሚያመጣ ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት የሚጠብቅ፣ ልዩነትን፣ ዘረኝነትን የሚያጠፋ፣ በአገልግሎት እንድንተጋ የሚረዳን ሊሆን ይገባል፡፡ ጸሎት በልማድ ወይም ለታይታ የሚደረግ አይደለም፡፡ ለንስሓ፣ ለጽድቅና ለቅድስና እንዲሁም ለክብርና ለጸጋም የሚያበቃን ሊሆን ይገባል፡፡ የሚያገለግል ሰው ጸሎት ሊያዘወትር ይገባል፡፡ ከማገልገል በፊት ጸሎት ይቀድማል፡፡ በጸሎት ሰዓት ለሥጋ ቅድሚያ መስጠት የመንፈስ ዝለት እና የነፍስ ሞትም ነው ከምግብ ጸሎት ቀዳሚ ነው፡፡
ቅዳሴ ላይ ቆመን ወይም ኪዳን እያደረስን የምናወራው ስለ ዘርና ብሔራችን ሆኗል፤ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቆመን በስልክ እናወራለን፤ ያውም እንዋሻለን፤ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም ገንዘብ ከመውደዳቸው የተነሳ ቅጥር በገንዘብ፤ በዝምድናና በቋንቋ ሆኗል፡፡ እውነት፣ ፍትሕ፣ ርትዕ፣ ምግባር፣ ሃይማኖት፣ መንፈሳዊነት ዋጋ አጥተዋል፤ በብዙ አረሞች ተከበናል፤ አረሞቻችንን ነቅለን ልንጥል ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ጸሎታችንን አምላክ ይሰማናል፤ የልባችን መሻትና ፍላጎትንም ይፈጽምልናል፤ ዕንባችንም ዋጋ ያገኛል፡፡ እርሱም በምሕረቱና በቸርነቱ ይታረቀናል፡፡ ለዚህ ክብርና ጸጋ የሚያበቃን ሕይወት፤ እምነትና ምግባርም ሊኖረን ይገባል፤ ለዚህ ሕይወትና ክብር እርሱ ያብቃን፤ አሜን፡፡