ጥበብ ዘየዓቢ እምነ ኩሉ ጥበብ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ

ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን እሱባለው

christmas 1

ከሰማይ በታች ባሉት ፍጥረታት ላይ በገዢነት የተሾመው የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ በማለቱ ሞትን ወደ ዓለም አስገብቷል፡፡ በዚህም የተሰጠውን ነጻነት በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ በምትኩም ወደ ሰይጣን ምርኮኝነት እና ጽኑ አገዛዙ ፈጽሞ ሄደ፡፡

 

መፍቀሬ ሰብእ አምላካችንም እንደ ወጣን እንቀር ዘንድ ተቅበዝባዦች እንድንሆንም አልወደደም፤ ባማረ በተወደደ ቸርነቱ ጎበኘን እንጂ፡፡ ወኢኃደጎሙ ውስተ ኃጕል ለዝሉፉ በዕደ ሰይጣን – በሰይጣን እጅ እንደተያዙ ሊቀሩ  በጥፋት ውስጥ አልተዋቸውም እንዲል፡፡ ከነበርንበት ጉስቁልና ያድነን ዘንድ የሰይጣን ምክሩን ያፈረሰው በአምላክነቱ፣ በከሃሊነቱ፣ ከጌትነቱ ወገን በምንም በምን ድል አልነሣውም ወኢሞኦ በኃይሉ መዋኢት ወኢኃየሎ በክሂሎቱ ወኢበምንትኒ እምዕበዩ አላ በትሕትናሁ ወፍትሐ ጽድቁ በትሩፋተ ምሥጢር እንግዳ- እንግዳ በሚሆን ተዋርዶ(ትሕትና) በሠራው ሥራ ድል ነሣው እንጂ፡፡

ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን ለማሳት በእባብ ሥጋ ተሠውሮ የሞት ምክርን በመምከር ምክንያተ ስህተት ቢሆንም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ግን በልዩ ጥበቡ የጠላትን ምክር ያጠፋ ዘንድ አምላክም ሰው ሆነ በዚህም ከነበርንበት ውድቀት አነሣን፣ የጎሰቆለ ባሕሪያችንን አደሰልን አዲስ የሕይወት መንገድን ከፈተልን፡፡ ሰይጣን በእባብ ሥጋ ሲሰወር  ከአዳም ተሰውሮበት እንደ ነበረ ሁሉ የቃል ሥጋ መሆንም ከሰይጣን ዕውቀት በላይ ነበር፡፡ ሊቃውንት ይህንን ሲያብራሩ አምላክ እርሱ ባወቀ ጥበቡ ጽንሰቱንና ልደቱን ከሰይጣን ባይሰውር ኖሮ ጌታን አገኛለሁ በማለት በሄሮድስ አድሮ የገሊላን ሕጻናት እንዳስፈጀው ቀድሞ በርካታ ጽንሶችን ባጨናገፈ ነበር፡፡ የሰውን ነገድ ሊያድን ወድዶ በሰማያዊ ቤቱ ካሉ መላእክት ተሠውሮ በድንግል ማኅጸን ተወሰነ፤ሥልጣኑን የሚቃወሙ አጋንንትን ባለማወቅ ሰወራቸው (እንዳያውቁ አደረገ) እንዲል ትምህርተ ኅቡዓት፡፡

ይህን የአምላክ ሰው መሆን በተመለከተ ሊቃውንት ሲናገሩ “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል(እጅግ ይደንቃል) ይላሉ፡፡ እንደ አምላክነቱ ፍጥረታትን መፍጠር የባሕርይ ገንዘቡ ናት፤ ነገር ግን አምላክ ከብቻዋ ከኃጢአት በስተቀር ሰው ሆኖ የቤዛነት ሥራ መሥራት ከኅሊናት ሁሉ  በላይ የሆነ ነገር በመሆኑ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ ተብሏል፡፡ በዚህ ልዩ የጥበብ ጉዞ ውስጥ ኁልቈ መሣፍርት የሌላቸው ልብን የሚነኩ ምድራውያን ፍጥረታት በምንሆን በእኛ እውቀት የማይመረመሩ የጌትነቱን ሥራ እና ትሕትና ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በቅዱስ በዝርዝር ጽፎት እናገኛለን፡፡/ሉቃ.2/

የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን ገደብ የለውም /Human needs are unlimited/ ሲሉ ይደመጣሉ፤ታዲያ ይህን  ወሰን አልባ መሻቱን እንኳ በገቢር በመሻት እንኳ አያረካውም ፡፡ ዘውትር አንድ የሚጎድለው ነገር እንዳለ ይሰማዋል ይህንንም ለማሟላት ጊዜውና አቅሙ የፈቀደለትን ነገሮች ሁሉ በማድረግ ይጠመዳል፡፡ ከማይገደቡ ፍላጎቶች መካከል ክብርን ዝናን መፈለግ ይገኙበታል፡፡ ክብርና ዝናን የማይሻ ሰው ካለ፥ እርሱ እግዚአብሔር ረድቶት፣ ባሕርያት ተስማምተውለት፥ ራሱን በፈጣሪው ፊት ባዶ ያደረገ ትሁት ሰው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በርካቶች በዚህ ጾር ተወግተው እንደ ወደቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ሕንጻና ልጆች ስምን ያስጠራሉ  በማለት ክብርን ሲሹ ውርደትን የተጎናጸፉ ናምሩዳውያን/ባቢሎናውያንን  ማስታወስ ይችላል ዘፍ፲፩፥፩-፭ ይመለከቷል፡፡

አውግስጦስ ቄሳርም እንዲህ ባለ መሻት ተጠምዶ ስሙ በታሪክ መዝገብ ውስጥ በጉልህ ይጻፍለት ዘንድ  በግዛቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ይቆጠሩ ዘንድ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙም ከሚፈጸሙባቸው የሮማ ግዛት መካከል በገሊላ አውራጃ የምትገኘው የናዝሬት ከተማ አንዷ ነበረች ፡፡በአይሁድ ባሕል እንደ ተለመደው በየነገዳቸው ይቆጠሩ ዘንድ ሁሉም ነገዶች ወደ ዳዊት ከተማ ይተሙ ነበር፡፡ ወደ ከተማዋ ለቆጠራ ከወጡት መካከል ወንጌላዊው ለይቶ ሲናገር …ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበር ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደ ምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ፡፡ ሉቃ ፪፥፬-፮፡፡ ብሏል፡፡

 

እኛን በሕይወት መዝገብ ይጽፈን ዘንድ ወደዚህ ዓለም የመጣው ፍጥረቱ ጋር የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ አውግስጦስ ቄሣር ባዘጋጀው መዝገብ ለመመዝገብ /ለመቆጠር/ ከእናቱ ጋር ወጣ፡፡ሉቃ ፲፥፳፣ ፊሊጵ ፬፥፫ ይመለከቷል፡፡

አዋጁ ለአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ከባድ ነበር በእርግና ዕድሜ ላይ ነበርና መውጣት መውረዱ እንዲህ በቀላል የሚወጣው ተግባር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመውለጃ ጊዜዋ ተቃርቧል፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ ያንን ረጅም ጉዞ በድካም አጠናቅቀው ወደ ከተማዋ ሲገቡ ጠንከር ያሉት ተመዝጋቢዎች ቀድመው በመድረስ ከተማዋን አጣብበዋታል፡፡ የዳዊት ከተማም የዳዊትን ልጅ የምታስተናግድበት ሥፍራ አልነበራትም፡፡ ሉቃ ፪፥፭-፯፡፡

ጌታችን የዳዊት ከተማ በተባለች ቤተልሔም የተወለደው ያለምክንያትና  በአጋጣሚ አልነበረም፡፡ እርሱ ባወቀ አስቀድሞ ምሳሌውን አስመስሎ ትንቢቱን አስነግሮ ቆይቷል እንጂ፡፡ ይህም ሊታወቅ “አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡” የሚለው የነቢዩ ሚኪያስ ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ሚክ 5፥2 ከ4ቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነ ነቢዩ ኢሳይያስም በትንቢቱ 1፥3 በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ በማለት በመንፈሰ እግዚአብሔር እንደተናገረ፣ እረኛና ሰብሳቢ ይሆነው ዘንድ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ  ሥጋን ይዋኻድ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡

 

ይህን የወልድን ትሕትና ስናስብ ፍጻሜ ወደሌለው አግራሞት ይመራናል፡፡ ከግሩማን ፍጥረታት ይልቅ ግሩም የሆነ ገናናነቱ፣ ተቆጥረው የማያልቁ ብዙ የብዙ ብዙ የሚሆኑ ትጉሃን መላእክት የሚያመሰግኑት ፈጣሪ እንደ ምስኪን ድሃ በግርግም መወለዱን ስናስብ ዕፁብ ዕፁብ ብሎ ከማድነቅ የበለጠ ምን ቋንቋ ሊኖረን ይችላል?

መጠንና መመርመር በሌላት ፍቅሩ ስለወደደን በከብቶች ግርግም ተወለደ፣ ጒስቈልናችንን  ያርቅልን ዘንድ ስለ እኛ ጒሰቈለ፤ መርገማችንን አስወገደ ፡፡ ዘፍ ፫፥፲፮፡፡ ሰው መሆን ቢያቅተን ሰው ሆኖ ያድነን ዘንድ ወደደ ተወልደ “በአምሳሊከ ከመ ይለድከ በአምሳሊሁ-በራሱ አምሳል ይወልድህ  አንተን መስሎ ተወለደ” እንዳለው፡፡  አረጋዊ መንፈሳዊ፡፡

ከአበው አንዱ ይህን ሲተረጉም፡- ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ ያደርገን ዘንድ፥ ከሰማያት ወረደ፤ ወደ ምስዋዕ(መሰውያ) ከፍ ከፍ ያደርገን ዘንድ በበረት ተወለደ፤ ለራሱ ከበረት በቀር ሌላ ማደሪያ ሳያዘጋጅ፥ ለእኛ በአባቱ ዘንድ ብዙ ማደሪያን ያዘጋጅ ዘንድ፥ ከልዕልና ወደ ትሕትና ወረደ” ብሏል፡፡ ዮሐ፲፬፥፪፡፡

በሰዎች ዘንድ ማደሪያን ቢፈልግ አላገኘም፤ ግእዛን የሌላቸው እንስሳት ግን ያላቸውን አልነፈጉትም፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንዳለው እስትንፋሳቸውን በመገበር ጌታቸውን እንዳወቁ መሰከሩ፡፡ የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢትም ተፈጸመ፡፡ኢሳ ፩፥፫ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ ማደሪያዎቹ የሆን እኛ ሰውነታችንን ምን ያህል ለእርሱ አዘጋጅተን ይሆን ወይስ እንደ ዳዊት ከተማ በእንግዶች ብዛት ሥፍራ ነሥተነው ይሆን? በመጽሐፍ ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ እንደ ተባለ ልባችንን መስጠት ያስፈልገናል፡፡ ከደጅ ቆሞ ሲያንኳኳ በራችንን የከፈትንለት ስንቶቻችን ነን?

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ  በነገሥታት፣ በሠራዊቱ እና በጻሕፍት ዘንድ ማደሪያን እንዳላገኘ፣  በዚያም እንዳላደረ፥ ዓለምና ፈቃዷ በሚናኝበት ሰው ዘንድም እንዲሁ ሥፍራ ስለማይኖረው በዚያ አያድርም፡፡ ይልቁንም …የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እንደርጋለን፡፡ ዮሐ ፲፬፥፳፫ ፡፡ እንዳለው ልደቱን ስናስብና  በዓሉንም ስናከብር የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን መሠራት ይጠበቅብናል፡፡.. “መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ፡፡” እንዲል ፩ጴጥ ፪፥፭፡፡

ልደቱንም ወዲያው ንጉሡ እና ሠራዊቱ  እንዲሁም ኦሪትንና ነቢያትን ጠንቅቀን እናውቃለን ይሉ የነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሌሎቹም ወገኖች በሙሉ ይህንን ታላቅ የምስራች ለመስማት አልበቁም፡፡ ዓለም እንዲህ ባለ ዝምታ ታላቁን  የነገሥታት ንጉሥ ተቀበለች፡፡ ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክት ግን ዝምታን አልመረጡም፥ በብርሃን ጐርፍ ተጥለቅልቀው፣ በአንክሮ ተውጠው ምስጋናን ጀምሩ፡፡ ዓይናቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው፥ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሐርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ በግርግም በግእዘ ሕፃናት የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን አይተው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት” በማለት አመሰገኑት ዳግመኛ ወደ ምድር ሲመለከቱ በእመቤታችን እቅፍ ሥጋን ተዋኽዶ አገኙት በዚህን ጊዜ እየሰገዱ “ወሰላም በምድር  ለዕጓለ እመሕያው” በማለት አመሰገኑት እንጂ፡፡ መንጋቸውን በትጋት በመጠበቅ ላይ ለነበሩት ኖሎትም ዓለም ያልተረዳውን እውነት አበሠሩ፡፡ ትጉኅ እና እውነተኛ እረኛ መድኀኔዓለም ልደቱን በበረት ገለጠላቸው፡፡

የተመሰገነ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጠውን ይህን የአምላካችንን ጥበብ ለምን እንዲህ ባለ ሁኔታ እንደ ፈጸመው ሲገልጽ ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድኃ ሆነ” ፪ቆሮ፰፥፱ ብሏል፡፡

መላእክት ቀድመው ትስብእቱን በደስታ እንዳበሰሩት አሁን ደግሞ ልደቱን በልዩ ደስታ አወጁ፡፡ ከዚያ በፊት በርካታ ነቢያት፣ካህናት፣ መሳፍንትና ነገሥታት ተወልደው ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተሰማ የምስጋና ቃል አልነበረም፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ግን ልዩ ቃለ ማኅሌት ተሰምቷል፡፡ ምክንያቱም የተወለደው ነቢያትና ካህናት ለሰው ልጆች ይሰጡ ዘንደ ያልተቻላቸውን ድኅነት ይሰጥ ዘንድ የመጣ እግዚአ ነቢያት/የነቢያት ጌታ/፣ ሰያሜ ካህናት/የካህናት ሿሚ/እና የነገሥታት ንጉሥ  በመሆኑ ልዩ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፡፡ መዝ፹፰፥፮-፯ እንዲል፡፡

ጌታ በተወለደባት ሌሊት ታላቁን የደስታ ምስራች ከመላእክት በመስማት መንጋቸውን በትጋት በመጠበቅ ላይ ከነበሩት ኖሎት የቀደመ አልነበረም፡፡ በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡እነሆም የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ፡፡መልአኩም እንዲህ አላቸው እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፥ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ ፡፡እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር  በአርያም ይሁን፥ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡ሉቃ፪፥፰-፲፬፡፡

እነዚህ እረኞች የሌሊቱ ግርማ ያላስፈራቸው ስለ መንጋቸው በትጋት የቆሙ፣የተሰጣቸውን ሓላፊነት ከመወጣት ቸል ያላሉ በመሆናቸው፥ የታማኝ አገልጋዮች ምሳሌ ናቸው፡፡መንጋውን በትጋት የሚጠብቁ እረኞች ሁሌም ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህም ነው መልአኩ ዜና ልደቱን ለማብሠር ወደ ምኵራብ ወይም ወደ ንጉሡ ያልሄደው ይልቁንም ወደ ተጉት እረኞች ሄደ እንጂ፡፡

ሁላችንም ዛሬ እንደ እረኞቹ በቤተ ክርስቲያን የየራሳችን ድርሻ ይኖረናል፡፡ የእረኝነት ሓላፊነት የተሰጠን መንጋውን በመጠበቅ፣ የተቀረነው ደግሞ ከመንጋው አንዱ  እንደመሆናችን ራሳችንን  ለማስጠበቅ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ስንታመን የደስታው ተካፋዮች እንሆናለን፡፡

እረኞቹ ከመላእክት ጋር አመሰገኑ፥ ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን፥ እነሆ በአንድ የምስጋና  ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑ ዘንድ መላእክትና ሰዎች አንድ መንጋ ሆኑ፡፡” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “እነሆ ቤተልሔም ጽርሐ አርያም ሆነች” በማለት ተናግሯል፡፡

ይህቺን ዕለት ያዩ ዘንድ ብዙ ነቢያት ሽተው፣ በትንቢታቸው በርካታ ነገርን ተናግረዋል ክንድህን ላክልን፣ ብርሃንህን ላክልን፣ ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ እያሉ ተማጽነዋል፡፡ ሁሉም ነቢያት በአንድ መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ በትንቢት ቃል ተንብየዋል፡፡ይህ ሁሉ ትንቢት ሲከናወን እያንዳንዱን ነገር ትመለከት የነበረችው  የነቢያት ትንቢታቸው የተባለች፣ በሰው ልጅ የመዳን ሂደት(ነገረ ድኅነት) ውስጥ ምክንያተ ድኂን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከጥበብ ሁሉ  በላይ የሆነውን ይህን የአምላክ ሰው ሆኖ መገለጥ ጥበብ በልቧ ትጠብቀው ነበር፡፡

በጾሙ እንደ ነቢያት የጌታን መወለድ ናፍቀናል፡፡ እኛ ግን ነቢያት ያላገኙትን ዕድል አግኝተናል፡፡ ይኸውም በዐይናችን ዐይተነዋል፣ በጆሮአችንም ሰምተነዋል፡፡ ስለዚህ ካየነው ከሰማነው ዘንዳ ሰውነታችንን ለእርሱ እንዲመች አድርገን ወደ ሕይወታችን እንዲመጣ ልንፈልግ፣ ልንፈቅድ ይገባናል፡፡ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ወደ ሕይወታችን ይገባልና፡፡

የሕይወታችን መሪ እርሱ ነውና፥ በዓለም ማዕበል ተነድተን ከጽድቅ ወደብ ሳንደርስ ወድቀን እንዳንጠፋ በእመቤታችን አማጅነት በቅዱሳን ሁሉ ቃል ኪዳን በልዩ ጥበቡ በጽድቅ ጎዳና እንዲመራን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን