ጎሐ፤ ጽባሕ
ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ
ጎሐ ፤ ጽባሕ ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያሉት ቀናት የሚጠሩበት ነው፤ ጎሐ ማለት ነግህ ሲሆን ጽባሕ ደግሞ ብርሃን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው «ዘመናትን የምታፈራርቅ፤ የብርሃንን ወገግታ የምታመጣ አንተ ነህ» እያለ በመግለጽ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው፣ ከመኖርም ወደ አለመኖር የሚያሳልፍ፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን ያደረገ እርሱ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ብርሃን እና ቀን የልደት፣ ሌሊትና ጨለማን የሞት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡
ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያለው ወቅት የክረምቱ ጨለማ የሚወገድበት፣ የፀሐይ ብርሃን ወለል ብሎ የሚወጣበት፣ ጉምና ደመና በየቦታቸው ተሰብስበው፣ ሰማይ በከዋክብት አሸብርቆ የሚታይበት ነው፡፡
በክረምቱ ውኃ ሙላት ምክንያት ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ ወገኖች ሁሉ በዚህ ክፍለ ጊዜ ብርሃን ስለሚያዩ፤ መገናኛ መንገዶችም ስለሚያገኙ፣ ክረምቱን እንደ ሌሊት በመመልከት ይህን ወቅት እንደ ንጋት መታየቱን ለመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ጎሐ፤ ጽባሕ›› በሚለው ስያሜ ትጠራዋለች፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩ መዝሙራት ‹‹አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለውና በማለዳ ድምፄን ስማ›› (መዝ.፭፥፪)፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ብርሃንን አየ፣ በሞት ጥላ ሥር ለተቀመጡት ብርሃን ወጣላቸው (ማቴ.፬፥፲፮) የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡