“ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሄዳለሁ” (መጽሐፈ ስንክሳር)
ጥቅምት ፲፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ለመንግሥቱ ፍጻሜ ለባሕርዩ ኅልፈት ውላጤ የሌለበት ወይም የማይኖርበት እግዚአብሔር አብ፣ አዳምን ለማዳን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሥጋዋን ተዋሕዶ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ወልድ፣ በባሕርዩ መጉደል ወይም መጨመር ሳይኖርበት በመንግሥቱ ከአብ ከወልድ ጋር አንድ የሚሆን በኀምሳኛው ቀን በደብረ ጽዮን የወረደ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይድረሳቸውና ለእኛ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ውስጥ ለምንኖር ምእመናን ብንቆጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ የሚበዙ ድንቅ ምስክሮችን ጻድቃንን በአማላጅነታቸው እንድንጠቀም አድለውናል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጥቅምት ፲፬ ቀን በዓላቸውን የምናከብረው ቅዱስ አባታችን አቡነ አረጋዊ እና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ይገኙበታል፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊ አስቀድሞ ራሱ ባለቤቱ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ የመሠረተውን ሥርዓተ ገዳምን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያመጡ ታላቅ መናኝና ጻድቅ አባት ናቸው፡፡ አባታችን ከእንጦንስና ከመቃርስ፣ ከጳኵሚስም የምንኵስና ሐረግ ዐራተኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ከሮም ነገሥታት መካከል ከሆኑት ከአባታቸው ከይስሐቅ ከእናታቸው ከእድና የተወለዱት አባታችን ወላጆቻቸው የታላላቅ ነገሥታት ወገን የምትሆን ሚስት ቢያጩላቸው እምቢ በማለት ከሮም ወደ ፅርዕ (ግሪክ) አገር በመሔድ ታላቁን የመንፈሳዊ ማኅበር ከመሠረተውና የመነኮሳት አባት ከሆነው ከቅዱስ ጳኵሚስ ዘንድ የምንኵስናን ልብስ የተቀበሉና ክርስቶስን ለመከተል ገና በልጅነታቸው የመረጡ አባት ናቸው፡፡ በሥጋዊ መጠነ ቁመታቸው ወይም በዕድሜ ታናሽ የሆኑት አባታችን በጥበብ ፣ በምክርና በዕውቀት ግን የልጅ ዐዋቂ በመሆናቸው ዘሚካኤል ከተባሉበት ስማቸው አረጋዊ ለመባል በቅተዋል፡፡
ጻድቁ አባታችን አምላክን በወለደች በእመቤታችን በድንግል ማርያምና ጌታችን ዐሥራት አድርጎ በሰጣት በኢትዮጵያ ፍቅር ልባቸው በመነደፉ ከሁለት ደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ቅዱስ ሚካኤል እየመራቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ከእርሳቸው ጋር ዘጠኝ ለሆኑት ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት የሆኑ አባት ናቸው፡፡ በጥቅምት ፲፬ ዕለትም እንደነ ሄኖክ ፣ ኤልያስና ዕዝራ ሞትን ሳያዩ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተሰወሩበትን በዓል የምናከብራላቸው ክርስቶስን በእውነት የተከተሉ አባት ናቸው፡፡
የቅዱስ ገብረ ክርስቶስም ሕይወት እንደ ቅዱስ አባታችን አቡነ አረጋዊ ክርስቶስን የመከተል ሕይወት ነው፡፡ የቊስጥንጥንያ ንጉሥ የሆነው አባቱ ቴዎዶስዮስ እና እናቱ መርኬዛ ከሮም ንጉሥ ልጅ ጋር ቢያጋቡትም ክርስቶስን ለመከተል ከሙሽራ ቤት የወጣ ታላቅ የትሕትና እና የትዕግሥት መምህር ነው፡፡ በጥቅምት ፲፬ ቀን የሚነበበው የስንክሳር መጽሐፋችን ስለ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ የሰርግ ምሽት እንዲህ ይላል ፡- “ከሌሊቱ እኩሌታም በሆነ ጊዜ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ተነሥቶ ወደ ሙሽራዪቱ ገባ፤ እጅዋንም ይዞ ከእርስዋ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ከዚያም የሃይማኖት ጸሎት “በአንድ አምላክ እናምናለን” የሚለውን እስከ መጨረሻ ጸለየ፤ የተሞሸረበትንም ልብስ ከላዩ አውልቆ የግምጃ ልብስን ለበሰ፤ ወደ ሙሽሪቱም ሒዶ ራስዋን ሳማት፤ እንዲህም እያለ ተሰናበታት፤ “እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኑር፤ ከሰይጣን ሥራ ሁሉ ያድንሽ፡፡ እርሷም አልቅሳ “ጌታዬ ወዴት ትሔዳለህ? ለማንስ ትተወኛህ?” አለችው፤ እርሱም “በእግዚአብሔር ዘንድ እተውሻለሁ፤ እኔም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሔዳለሁ፤ የአባቴ መንግሥት አላፊ ነውና አንቺም መሐላሽን አስቢ” አላት፤ ያን ጊዜ መሐላዋን አስባ ዝም አለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይህን የቅዱስ ገብረ ክርስቶስን የልዕልና ተግባር “ቦ ዘፈለሰ ኀዲጎ ብእሲቶ ኃዲጎ ብእሲቶ ቦ ዘፈለሰ ወቦ ገዳመ ዘተግሕሠ መኒኖ መንግሥቶ መንግሥቶ ገብረ ክርስቶስ፤ ሚስቱን ትቶ ተሰደደ ገብረ ክርስቶስ ንግሥናውን ንቆ ገዳም ገብቶ ተቀመጠ” በማለት ጠቅሶታል፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአርማንያ አገር በተሠራች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚኖር ሆነ ፡፡ በዚህም ‹‹አብደርኩ እትገደፍ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር፤እምንበር ውስተ ቤተ ኃጥአን፤ በኃጥአን ድንካኖች ከመቀመጥ ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” የሚለውን የቅዱስ ዳዊትን ቃል ፈጸመ፡፡ (መዝ.፹፫፥፲)
ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሔዳለሁ›› በማለት እውነተኛውን ፍቅር በመከተል ለክብር በቅቷል፡፡ እኛስ ምን እንከተል? ምንስ እንተው? ፍቅርን ትተን ጥላቻን በመከተላችን በእያንዳንዳችንም ሆነ በሀገር ደረጃ ትልቅ መከራ እያሳለፍን ነው፡፡ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ በእመቤታችን ስም በታነጸች ቤተክርስቲያን ደጅ መጣልን መርጧል፤ እኛስ ከየትኛው ደጅ ተጥለን እንገኝ? ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት ከምትሰብከው በኅብረት የመኖር ደጅ ወይስ በዘር የመለያየት ደጅ? አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም፣ በአባቶቻችን በአቡነ አረጋዊ እና በቅዱስ ገብረ ክርስቶስ አማላጅነት ጥላቻን ትተን፣ ንቀንና ፍቅርን ተከትለን በቤተ ክርስቲያን ኅብረት በአንድነት እንድንኖር ይርዳን፡፡
ምንጭ ፡- ስንክሳር ዘወርኀ ጥቅምት፣ ገድለ አቡነ አረጋዊ