ጉባኤ ኒቅያ
መስከረም ፲፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ለዐራት መቶ ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያን በብዙ አቅጣጫ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውባት እጅግ ስትሠቃይ ኖራለች፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ አንዱ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የዶግማ ትምህርት ልዩነት መፈጠሩ ነው፡፡ በወቅቱም ውስጥ እንደነ ጳውሎስ ሳምሳጢ፣ ሰባልዮ የመሳሰሉት የተነሱበት ነበር፡፡ በተለይም አርዮስ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› ብሎ በመነሣቱ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዓመታት እንድትታወክና እንድትበጠበጥ መንሥኤ ሆኗል፡፡
አርዮስ የተወለደው በ፪፻፷ ዓ.ም አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በሊብያ ነው፡፡ የትውልድ ሐረጉ ግን ከግሪክ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አርዮስ መሠረታዊ ትምህርቱን በሊብያ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ እስክንድርያ በመጓዝ በእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ትምህርት አጠናቆ እንደጨረሰ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄዶ በአንጾኪያ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ የትርጓሜ መጻሕፍትና የነገረ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡ በጊዜውም ሉቅያኖስ ከተባለ መናፍቅ ዘንድ ተምሯል፡፡ ሊቃውንት አርዮስ ከእስክንድርያ ትምህርት ቤት ይልቅ የአንጾኪያ ትምህርት ቤት የክህደት ትምህርት ቅርበት እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ አርዮስ አብዛኛውን የኑፋቄ ትምህርት ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾኪያ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በአንጾኪያ ትምህርት ከጨረሰ በኋላ አርዮስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ኑሮውን በዚያው አደረገ፡፡ (የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ)
አርዮስ ብልህና ዐዋቂ አንደበተ ርቱዕና እምቅ የሆነ የግጥም ችሎታ እንደነበረው ይነገራል፡፡ በጊዜው የእስክንድርያ ፓትርያክ ከነበሩት ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ተቀብሎ አገልግሎት ጀመረ፡፡ አርዮስም በእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ‹‹ወልድ ፍጡር›› እያለ ማስተማር ጀመረ፡፡ የዚህ ጊዜ ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አስጠርተው ትምህርት ሁሉ የተሳሳተ መሆኑንና ከስሕተቱ ተመልሶና ተጸጽቶ ከቅዱሳን አበው ሲተላለፍ በመጣው በኦርቶዶክስ እምነት እንዲጸና መከሩት፡፡ እርሱ ግን ምክራቸውን ወደ ጎን ትቶ የክሕደት ትምርቱን በሰፊው ማስተማር ቀጠለ፤ የዚህ ጊዜ አርዮስን አውግዘው ከዲቁና ማዕረጉ ሻሩት፡፡ የግብጽ ቤተክርስቲያን ትውፊት እንደሚለው ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ያወገዙት ጌታችን ኢየሱስ በራዕይ ተገልጦ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሌሊት በራዕይ ጌታ ኢየሱስ በሕፃን ልጅ አምሳል እንደ ፀሐይ የሚያበራ ረጅም ልብስ (ቀሚስ) ለብሶ ነበር፡፡ ልብሱ ግን ለሁለት የተቀደደ ሆኖ ያዩታል ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም ልብስህን ማን ቀደደብህ (መኑ ሰጠጣ ለልብስከ?) ብለው ሲጠይቁ ጌታ ኢየሱስም ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› ይላቸዋል፡፡ በዚያኑ ቀን ሁለቱን ተማሪዎቻቸውን አኪላስንና እለእስክንድሮስን አስጠርተው የተገለጠላቸውን ራዕይ በመግለጥ አርዮስን እንዳይቀበሉት ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዳይኖራቸው አዘው፤ በዲዮቅልጥያኖስ ሰማዕት ሆነው ዐረፉ፡፡
ከተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ሞት በኋላ አኪላስ በ፫፻፫ ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ አርዮስም ወደ አኪላስ ቀርቦ ከውግዘቱ እንዲፈታው በከንቱ ውዳሴ አባበለው፡፡ አኪላስም አደራውን በመዘንጋት ከውግዘቱ ፈታው፤ ይባስ ብሎም የቅስና ማዕረግ ሰጥቶ ሾመው፡፡ ሆኖም አኪላስ በሕይወት ብዙ ጊዜ አልቆየም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ በቀጠል እለእስክንድሮስ ፓትርያክ ሆኖ ተተካ፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮስ ክህደቱን ከማሰራጨት አልታቀበም ነበር፡፡ እንደውም ሕዝቡ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበሉ የክሕደት ትምህርቱን በግጥምና ንባብ እያዘጋጀ ማሰራጨት ቀጠለ፡፡ ያም የግጥም መጣጥፍ ‹‹ታሊያ›› ይባል ነበር፤ ትርጉሙም ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕዝቡ ግጥም ስለሚወድ ትምህርቱን ወደ መቀበል ደርሶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እለእስክንድሮስ እየተዘዋወረ ከአርዮስ ኑፋቄ እንዲጠበቁ በትጋት ያስተምር ነበር፡፡ በ፫፻፳ ዓ.ም አንድ መቶ ሚያህሉ የሊቢያና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳትን እለእስክንድሮስ አሰባስቦ የአርዮስን አስተሳስቦ ገልጾላቸው ጉባኤውም አልመለስ ያለውን አርዮስን በአንድ ልብ አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ለዩት፡፡
አርዮስ ከጓደኞቹ አንዱ ወደ ነበረው ወደ የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ በመገስገስ አንድ በአንድ ዘርዝሮ ነገረው፡፡ አውሳቢዮስም አይዞህ ብሎ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በአርዮስ ጉዳይ ሲኖዶስ አደረገ፡፡ ሲኖዶሱም በግፍ መባረሩን አምኖ ከውግዘቱ ፈቱት፡፡ አርዮስም በ፫፻፳፪ ዓ.ም ወደ እስክንድርያ ተመልሶ እለእስክንድሮስ ቢያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ እያለ የበፊት ትምህርቱን በስፋት ማስተማር ቀጠለ፡፡ የዚህ ጊዜ ቤተክርስቲያን ታመሰች፡፡ በዚህ ምክኒያት ጉዳዩ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ደረሰ የዚህ ጊዜ የእስፓኝ ጳጳስ ሆስዮስን ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ሲመለስ ጉዳዩ የሃይማኖት ችግር እንጂ አስተዳደራዊ ስላልሆነ በጉባኤ መታየት አለበት ብሎ ለንጉሡ አማከረው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ፫፻፳፭ ዓ.ም ጉባኤ እንዲደረግ አዘዘ፤ በዚህም በኒቅያ ፫፻፲፰ አባቶች ተሰበሰቡ፡፡
መሠረታዊ የአርዮስ ክህደቶች
፩ኛ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር አልነበረም
፪ኛ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ ነው
፫ኛ የተፈጠረ እንጂ ከአብ የተወለደ አይደለም
፬ኛ በመጀመሪያ ዓለሙን ይፈጥርበት ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን ፈጠረው፤ እርሱም ዓለምን ፈጠረ፡፡ በአጠቃላይ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ የሚል ነበር፡፡
በአጠቃላይ አርዮስ ያቀረባቸው ጥቅሶች ተመረመሩ፤ ወልድ በባሕርይ ፍጡር ከተባለ በመዳን ላይ ስለሚደርሰው አደጋ ወዘተ በስፋት ተነጋገሩበት፡፡ በተለይም ወጣቱ አትናቴዎስ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኝ ነው፤ ማዳኑን ካመንክ የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብህ፤ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደተቀመጠና በተለይም ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል የጠፋው በግ ምሳሌ የተቀመጠውን ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከመዳናችን በማያያዝ እርሱ አምላክ ካልሆነ እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ ያዳነን እርሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ፍጡር ፍጡርን ማዳን አይችልም በማለት አርዮስን በጉባኤው ረቶታል፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና በባሕርይም ከአብ ጋር አንድ ስለመሆኑ የቀረበውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ከመረመሩ በኋላ በፍልስፍና ገመድ ተጠላልፎ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ ያለውን አርዮስን አውግዘው ከቤተክርስቲያን አንድነት ለዩት፡፡
ጉባኤ ኒቅያ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን የጠበቀችበት፣ አርዮስና አርዮሳውያን የተወገዙበት፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ አዳኝነት፣ ጌትነት፣ መድኃኒትነት የተመሠከረበት፣ ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ትምክህት የሆነበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጉባኤ ትቀበላለች፤ ትልቅም ስፍራ አላት፡፡
ምንጭ፡- ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ መታሰቢያነት የተዘጋጀ ጽሐፍ (በይስሐቅ አበባየሁ)