ደራሲዋ መጽሐፋቸውን ለሕንፃ ግንባታ ሥራ አበረከቱ

 

 በደረጀ ትዕዛዙ

 
በማኅበረ ቅዱሳን የሕንፃ ግንባታ ጽ/ቤት አሳታሚነት ለኅትመት የበቃው «እመ ምኔት» የተሰኘው የደራሲ ፀሐይ መላኩ አዲስ ረጅም ልብወለድ መጽሐፍ ተመረቀ፡፡  ጥር 9 ቀን 2002 ዓ.ም አንጋፋና ወጣት ደራሲያን፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሩስያ ባህል ማዕከል /ፑሽኪን አዳራሽ/ የተመረቀው መጽሐፍ፤ በገዳማውያን ሕይወትና በውስብስብ ወንጀል ታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ደራሲዋ የመጽሐፉን ሸያጭ ገቢ ለማኅበሩ ጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ እንዲውል አበርክተዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ተወካይ ዲያቆን ዋስይሁን በላይ በዚሁ ምረቃ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ለበርካታ ዓመታት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሲያበረክት መቆየቱን ጠቅሰው ይህንኑ አገልግሎት     በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን የጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡
በሕንፃ ግንባታው ሂደት በርካታ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን፣ ከአሁን ቀደምም በሦስት ደራስያን ሦስት መጻሕፍት ለሕንፃ ግንባታው ሥራ በድጋፍ መልክ መለገሳቸውን የገለጹት ዲያቆን ዋስይሁን፤ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ለዚሁ ዓላማ ያደረጉት ድጋፍ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ግንባታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ለታቀደው ለዚሁ ሕንፃ ሥራ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በማሳሰብ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው እንዳሉት፤ ከውስብስብስ የወንጀል ታሪክ እና ከዘመናዊ ረጅም ልቦለድ ባሕርያት አንጻር ድርሰቱ የተዋጣ ነው፡፡
«ከመጽሐፉ ውስጥ በገሀዱ ዓለም የሚታዩ እንደ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ቅናት፣ በቀል፣ ምቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ጽናት፣ ወንጀል፣ ተንኮል፣ ትሕትና፣ ደግነት ይንጸባረቁበታል» ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ «ደራሲዋ ይህንን መጽሐፍ ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎችና ለአጥኚዎች በማበርከታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል» ብለዋል፡፡
የደራስያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔና እውቀት ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰው፤ «ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብር አለው» ብለዋል፡፡ «ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን ያህል ታላቅ ሥራ እንደሚሠራ ማኅበሩ ይገነዘባል፡፡» ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች የደራስያን ማኅበር ከጎኑ እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ያበረከቱት አስተዋጽኦም የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ በበኩላ ቸው፤ በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ታሪክ ከሀገራችን የረጅም ታሪክና የበለጸገው ባህላችን የተነቀሰ የጥበብ ሀብት መሆኑን   ጠቅሰው፤ «ይህንኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተንከባለለ የመጣውን ሀብት የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ደራሲዋ ገልጸውታል» ብለዋል፡፡
ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕልም፤ ደራሲዋ ከአሁን ቀደም ለአንባብያን ያበረከቷቸው መጻሕፍት የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ «ይህን አዲስ መጽሐፋቸውን ለማኅበሩ በጎ ሥራ ማበርከታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው» ብለዋል፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ፀሐይ መላኩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ መንፈሳዊ ቅናት ያድርባቸው እንደነበረ    ጠቅሰው፤ እርሳቸውም የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መጽሐፋቸውን ሲለግሱ ከፍተኛ ደስታ እየተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ ተገምግሞ መጽሐፉ ለኅትመት እንደሚበቃ ሲነገረኝ በደስታ አለቀስኩ» ያሉት ደራሲዋ «የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ጥያቄያቸውን በመቀበል ለኅትመት ማብቃቱ ሊያስመሰግነው ይገባዋልም» ብለዋል፡፡
ደራሲዋ እንዳሉት በንስሐ አባቶች፣ በመነኮሳትና ካህናት ላይ የሚሰነዘሩ ገንቢ ያልሆኑ ትችቶች ሲያናድዳቸው ለዚህ ምላሽ ይሆን ዘንድ በመልካም ጎኑ ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ተነሣስተዋል፡፡
መጽሐፍ ከመጻፋቸው በፊት ሐይቅ እስጢፋኖስ አንድ ሱባኤ ከመቀመጣቸው በተጨማሪ ዝቋላ፣ አሰቦት፣ ራማ ኪዳነ ምሕረት፣ ዋሸራ እና ሌሎች ገዳማትን በመጎብኘት በመነኮሳት አኗኗር ላይ ጥናት በማድረግ አሥር ዓመታት ያህል እንደፈጀባቸው ተናግረዋል፡፡ ወደፊት በማንኛውም መልኩ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ለማገዝ አንደሚጥሩም ገልጸዋል፡፡
በአሥራ አምስት ምዕራፍ የተከፈለው ይኸው «እመ ምኔት» መጽሐፍ 2002 ገጽ ያለው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ሺሕ ኮፒ ታትሟል፡፡ መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት በማኅበሩ ማእከላት፣ በሰንበት ት/ቤቶች እና በግቢ ጉባኤያት አማካኝነት እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡ ደራሲዋን ለማበረታታም ከመጀመሪያው እትም ትርፍ አሥራ አምስት በመቶ ፐርሰንት እንደሚከፈላቸውም ተገልጿል፡፡
የሥነ ሥዕል፣ የሥነ ግጥም እና የእደ ጥበብ ሞያተኛ መሆናቸው የሚነገርላቸው ደራሲ ፀሐይ መላኩ ከአሁን ቀደም «አንጉዝ»፣ «ቋሳ» እና «ቢስራሔል» የተሰኙ ረጅም ወጥ ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ደራሲ ፀሐይ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የዜማ ብዕር ኢትዮጵያ ሴቶች የሥነ ጽሑፍ ማኅበር የቦርድ አባል ናቸው፡፡
በምረቃው ወቅት የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን፣ መነባንብ እና የደራሲዋ የተለያዩ ግጥሞች በሌሎች አንባብያን ለታዳሚዎቹ ቀርበዋል፡፡ የምረቃውን ሥርዓት ያዘጋጁት የዜማ ብዕር ኢትዮጵያ ሴቶች የሥነ ጽሑፍ ማኅበር ከማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል፡፡