ደመራ
መስከረም ፲፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
የታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡
ኪራኮስ የሚባለው አረጋዊ ሰው መስቀሉ የተቀበረበትን በሥቃይና በመከራ አስጨንቃ ስትይዘው እንደነገራት ታሪኩ ያስረዳናል፤ ቁፋሮ ልታደርግበት የምትችለውን አካባቢም ሲጠቁማት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ተማፀነች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት፡፡ ንግሥቷም በምልክቱ መሠረት ማስቆፈር ጀመረች፡፡ ለማስቆፈር የወሰደባት ጊዜም ከመስከረም ፲፯ እስከ መጋቢት ፲ ነበር፡፡ በቁፋሮውም መጨረሻ ሦስት መስቀሎችን አገኘች፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ መስቀሎች አንዱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀል እንደሆነ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ፈያታዊው ዘየማንና ፈያታዊው ዘጸጋ ሁለቱ በጌታ ቀኝና ግራ የተሰቀሉት ወንበዴዎች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡
ንግሥት እሌኒ ሦስቱን መስቀሎች ካገኘች የጌታችን መስቀል ለይታ ለማወቅ የሞተ ሰው አስከሬን አምጥታ በላያቸው ላይ አደረገቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ሙቱን አስነሣው፡፡ ይህን ጊዜ ለይታ ያወቀችውን መስቀል በክብር ወስዳ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፤ የደመራ ሥርዓት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከበር ነው፡፡
ደመራ ማለት “መጨመር፣ መሰብሰብ መከመር” ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም የቃሉን ፍቺ “ደመረ” ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን የአስተባበረ መሆኑን ይናገራሉ፤ አያይዘውም የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ (ሰዋሰወ ግእዝ ወግስ መዝገበ ቃላት) በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ቅድስት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡
የበረከት በዓል ያድርግልን፤ አሜን!!!