የጽድቅ ብርሃን
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ታኅሣሥ ፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የወንጌላዊው ማርቆስ ብሥራት
የካህኑ ዮሐንስ በረከት
የደጋጎች የዘር ፍሬ
የማርያም ዘመዳ ዝማሬ
በብርሃናት ልብስ ተሸልሞ…
በብዙ ሀብታት ያጌጠ
ሥጋን ከነምኞቱ ሰቅሎ…
ለምትበልጠው ጸጋ ያለመታከት የሮጠ
አሽቀንጥሮ ጥሎ ምድራዊ ድሎት…
በገድል ትሩፋት እጅግ የደመቀ
መንፈስ ቅዱስ ያደረበት…
በምሥጢር ጥበባት የመጠቀ
ወንጌል እየዘራ በሚያንፅ ስብከት
አእላፍ ነፍሳትን ከበረቱ የጨመረ
ከተፈጥሮ ሕግ አይሎ…
በዋጀው ዘመኑ ለመንጋው የኖረ
በትጋት ባፈራው በድንቅ ተአምራቱ…
በምሁር ሰማይ ላይ ፀሐይን ያቆመ ብርቱ
ቃል ኪዳኑን አምነው “አባት ሆይ” ለሚሉ…
ሌት ከቀን ‘ሚማልድ ማርልኝ በማለቱ
ይህ ነው ዜና ማርቆስ ትውልድ የሚያወሳው
የጽድቅ ብርሃን… ጧፍ ሆኖ የሚያበራው!