የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ክፍል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።
ከማኅበረ ቅዱሳን ሕዝብ ግንኙነት ክፍል
በማኅበረ ቅዱሳን የሀገር ውስጥ ማዕከላትና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥር እያስተማራቸው የሚገኙ ተማሪዎችን የክትትል እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።
አቶ እንዳለ ደጀኔ፥ የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያና ማጠናከሪያ ክፍል አስተባባሪ እንደተናገሩት፥ ማኅበሩ ተማሪዎችን ለማስተማር ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ 21 የመማሪያ መጻሕፍትን ያዘጋጀ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ሥርዓተ ትምህርቱን ሙሉ በሙሉ በመከለስ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱን በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች ከግቢ ከወጡ በኋላ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ለማድረግ የክትትል መስመር ዘርግቶ እየተንቀሳቀስ ይገኛል። ተማሪዎች በሥራ ዓለም ላይ እያሉ በታማኝነት ሀገርን ማገልገል፣ ሕዝብና ሀገር የሚፈልጉባቸውን ግዴታዎች በጥሩ ሥነ ምግባር መወጣት፣ ቤተ ክርስቲያንን በሰንበት ትምህርት ቤትና በሰበካ ጉባኤ ተሣትፎ ማገልገል፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በገንዘብ፣ በዕውቀትና በጉልበት በማገልገል፤ ለሕዝብና ለወገን ጠቃሚ ዜጋ መሆን ከተማሪዎቹ የሚጠበቅባቸው ውጤት እንደሆነ አስተባባሪው ጨምረው ገልጸዋል።
አስተባባሪው አክለውም፥ አባላት በተለያየ ሙያ ላይ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ማገልገል እንችላለን ለሚሉ ተማሪዎችም፥ በማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል።
ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ ዕውቅና ያገኙ 171፥ በክትትል ላይ የሚገኙ 140፥ በድምሩ 311 ግቢ ጉባኤያትና በሥራቸው የሚገኙ ከ120,000 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል ።