የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፱

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲ .

፪. የሩካቤ ሥጋ ሥርዓት

በባልና በሚስት መካከል የሚደረግ የመኝታ ግንኙነት ወይም መተዋወቅ ‹ሩካቤ ሥጋ፣ ግብረ ሥጋ› ይባላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሩካቤ ሥጋ ለአዳም የተሰጠውን ተስፋ ተከትሎ የመጣ ሥርዓት መኾኑን ይናገራሉ፡፡ ጥንተ ታሪኩም እንዲህ ነው፤ አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን ጥሰው ከገነት ከወጡ በኋላ ጥረው ግረው በምድር እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አዳም እግዚአብሔርን “የሥጋዬን ነገርስ ነገርኸኝ፤ የነፍሴ ነገርስ እንደምን ይኾን?” ብሎ ጠየቀው፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ባይና ሰውን ወዳድ አምላክ ነውና ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከልጅ ልጁ፣ (ከድንግል ማርያም) ተወልዶ፣ በፈቃዱ ተገፍፎ፣ ተገርፎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሥጋዉን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ፣ ሞቶ፣ ተነሥቶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡፡

የተስፋው ቃል እስከሚፈጸም ድረስ፣ አዳምና ሔዋን በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈርዶባቸው በማዘንና በመተከዝ እያለቀሱ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አምላካችን አዳምን “አእምራ ለሔዋን፤ ሔዋንን በግብረ ሥጋ ዕወቃት” በማለት እንዲበዙ፣ እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሏት አዘዛቸው (ዘፍ. ፫፥፲፯)፡፡ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለው የተስፋው ቃል ይፈጸም ዘንድ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አስፈላጊ ነበረና አዳም ሔዋንን በግብር አውቋታል፡፡ “አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፤ ቃየንንም ወለደች” እንዲል (ዘፍ. ፬፥፩፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ከዚህ ታሪክ እንደምረዳው ሩካቤ ሥጋ፣ በአንድ በኩል ፈቃደ ሥጋን ለመቋቋም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘር መብዛትና ለትውልድ መቀጠል የሚያስፈልግ፤ በጋብቻ ለሚኖሩ ለሰው ልጆች የተሠራ ሥርዓት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር እግዚአብሔር አምላካችን ወንድና ሴትን ያስተሳሰረበት ማለት እንዲፈላለጉ ያደረገበት የድንቅ ጥበቡ መገለጫም ነው፡፡ ሁለቱን የጋብቻ ዓላማዎች ማለትም መረዳዳትንና ዘርን መተካትን የሚያስተሳስራቸውም ሩካቤ ሥጋ ነው፡፡ ባልና ሚስት በሩካቤ ወቅት የሚያገኙት የደስታ ስሜት እርስበርስ እንዲፈላለጉ የመሳሳቢያ መንገድ ይኾናቸዋል፤ የጋብቻ ሕይወታቸዉንም የጣፈጠ ያደርግላቸዋል፡፡ የሩካቤ ሥጋ ስሜት ባይኖር ኖሮ ሴትና ወንድ ላይፈላለጉ ይችሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ፈቃድን ለመፈጸም ካልተቻለ ልጅ ለመውለድ ብቻ ወይም ለመረዳዳት ብሎ ወደ ጋብቻ ሕይወት የሚገባ ሰው ለማግኘት ይከብዳልና፡፡

ስለዚህም የሰው ልጅ መጋባትን እንዳይጠላ እግዚአብሔር አምላክ ሴትና ወንድ የሚፈላለጉበትን ስሜት (ሩካቤ ሥጋን) ፈጥሯል፡፡ ኾኖም ግንኙነቱ ሥርዓት ባለውና በሕጋዊ መንገድ እንጂ እንደ እንስሳት በዘፈቀደ አይፈጸምም፡፡ አዳምና ሔዋን በሩካቤ ሥጋ የተዋወቁት ከገነት ወጥተው ቆይተው ንስሓ ከገቡ በኋላ መኾኑም ሩካቤ ሥጋ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ግንኙነት መኾኑን ያመለክታል፡፡ ከጋብቻ ውጪ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም እንደማይቻልም ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡ በጋብቻ እስካልተወሰንን ድረስ ካገኘነው ዂሉ ጋር መተኛት ሕገ እግዚአብሔርን መጣስ፣ ሰውነትን ማርከስ ነውና፡፡ ከዚህም ባለፈ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያመጣብን ቅጣትም የከፋ መኾኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡

በመኾኑም ያላገባን እስክናገባ ድረስ ክብራችንን መጠበቅ፤ በጋብቻ የተወሰንን ሰዎችም እስከ መጨረሻው ድረስ ተዋሕዷችንን ማጥበቅ ይገባናል፡፡ ስለ ተጋባን ብቻ ከሥርዓት ውጪ ሩካቤ ሥጋን መፈጸም እንደማይገባም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ቀን የሥራ፣ የጸሎት፣ የጾምና የመመገቢያ (የደስታ) ሰዓት እንዳለው ዂሉ ሩካቤን ለመፈጸምም የተወሰነ ሥርዓት አለው፡፡ በቂ የሕሊና ዝግጅትና ስምምነትም ያስፈልገዋል፡፡ በጋብቻ ግንኙነት የሚወለዱ ሕፃናት የተባረኩና የተቀደሱ ይኾኑ ዘንድ መኝታው ንጹሕ ሊኾን ይገባዋልና፡፡ “ጋብቻ ክቡር፣ መኝታውም ንጹሕ ይኹን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” እንዳለ (ዕብ. ፲፫፥፬)፡፡ ሩካቤ ሥጋን ሥርዓት በሌለው መንገድ መፈጸም የጋብቻን ክቡርነት፣ የመኝታውንም ንጽሕና ማቃለል ነው፡፡

፪.፩ ሩካቤ ሥጋ የማይፈጸምባቸው ጊዜያት

ሩካቤ ሥጋ፣ በምን ዓይነት ሥርዓት ሊፈጸም እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ተደነግጓል፤ “ወሰብሳብሰ ዘሠርዖ እግዚአብሔር ለደቂቀ ዕጓለ እመሕያው አኮ በእንተ ወሊደ ውሉድ ባሕቲቱ አላ በእንተ መፍቅድ ዘኢዕቁብ ወባሕቱ ኢይኩን በርኵስ፤ እግዚአብሔር ሩካቤን ለሰው የሠራው ልጅ ለመውለድ ብቻ አይደለም፤ የማይወሰን የማይገታ የፈቲውን ፆር ለማራቅ ጭምር ነው እንጂ፡፡ አንድ ጊዜ የሚከለከሉበትን፣ አንድ ጊዜ ፈቃዳቸውን የሚፈጽሙበትን ሠራ፡፡ ነገር ግን አንድ ወንድ ለአንድ ሴት፣ አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ብለው ዘወትር ሊያደርጉት አይገባም፡፡ አጽዋማትን፣ በዓላትን፣ ኅርስን፣ ትክትን ለይቶ ሊያደርጉት ይገባል እንጂ፤” (ፍት. ነገ. አን. ፲፭፥፣ ቍ. ፴፰-፵፰)፡፡ ከላይ እንደ ገለጽነው ሩካቤ ሥጋ በሥርዓት የሚፈጸም እንደ መኾኑ የማይፈጽምባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናው፤

ሀ. የእርግዝና እና የንጽሕ ጊዜያት

ሚስት በፀነሰችበት ወይም ባረገዘችበት ወቅት፤ በወር አበባዋና በመውለጃዋ ጊዜ (ወንድ ከወለደች ከዐርባ፣ ሴት ከወለደች ከሰማንያ ቀን በፊት) ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አይገባም (ዘሌ. ፳፥፲፰)፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም “ወበመዋዕለ ትክቶሃ ወኅርሳ ኢትቅረባ ከመ ኢይኩን ተዋስቦትከ ዘእንበለ ሕግ፤ በኅርሷ፣ በደሟ ወራት ሚስትህን አትድረስባት፡፡ ግቢህ ከመጽሐፍ ሥርዓት የወጣ እንዳይኾን” በማለት በፅንስ (እርግዝና) እና በንጽሕ ጊዜያት ማለትም በአራስነትና በወር አበባ ወቅት ግንኙነት መፈጸም እንደማይገባ አዝዟል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፷፬)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሚስት ፅንሷ ከታወቀ በኋላ ለመረዳዳት ካልኾነ በቀር ባሏ ሊቀርባት እንደማይገባ ተደንግጓል (አን. ፳፬፣ ቍ. ፰፻፴፰)፡፡

ለ. ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱባቸው ቀናት

እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ሲነጋገር ከመስማታቸው (ሕጉን ከመቀበላቸው) ከሦስተኛው ቀን በፊት እንዲቀደሱ፣ ልብሳቸውን እንዲያጥቡና ሩካቤ እንዳይፈጽሙ ታዝዘው ነበር፡፡ ዛሬም በሐዲስ ኪዳን ባለ ትዳሮች ትምህርተ ወንጌል ለማዳመጥ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል፣ ጠበል ለመጠመቅና ለመጠጣት፣ ወይም ለሌላ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ ከሩካቤ ሥጋ እንዲከለከሉ ታዝዟል (ዘፀ. ፲፱፥፲-፳፭)፡፡ ከዚህም ሌላ በጥምቀት ክርስትና የሚያነሡ (የክርስትና እናት ወይም አባት የሚኾኑ ምእመናን) ክርስትና ከማንሣታቸው በፊትና በኋላ ለሁለት ቀናት ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ይገባቸዋል፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስን ለማክበር ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት ጸጋን፣ ክብርንና ልጅነትን የሚያሰጥ ምሥጢር ስለ ኾነ፡፡ ካህኑ ዘካርያስ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ከፈጸመ ከሁለት ቀን በኋላ ከኤልሳቤጥ ጋር መገናኘቱም ለዚህ ትምህርት ነው፡፡ “ወእምድኅረ ክልኤ መዋዕል ፀንሰት ኤልሳቤጥ ብእሲቱ፤ ከሁለት ቀን በኋላም ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፬፤ ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፴፰)፡፡

ሐ. በዓላት

ቅዳሜ፣ እሑድና በዓበይት በዓላት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም የተከለከለ ነው፡፡ ይኸውም በመንግሥተ ሰማያት ጋብቻና ፈቃደ ሥጋን መፈጸም አለመኖሩን ለማጠየቅ ነው፡፡ በዓላት፣ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌዎች ናቸውና ፡፡ “በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይኾናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም” እንዲል (ማቴ. ፳፪፥፴)፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ “ንጹሕ የኾነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው … በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” በማለት ቅዱስ ያዕቆብ እንደ ተናገረው (ያዕ. ፩፥፳፯)፣ በእነዚህ ዕለታት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበልና ራስን መጠበቅ ተገቢ ስለ ኾነ ነው፡፡ “ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ ሰንበትንም ደስታ፣ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ‹ክቡር› ብትለው፣ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ፣ ፈቃድህንም ከማግኘት፣ ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፣ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፤ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ” ተብሎ ተጽፏልና (ኢሳ. ፶፰፥፲፫-፲፬)፡፡

መ. አጽዋማት

“ጸዋሚ ሆይ፥ መላው አካልህ ይጹም፤ አፍህ ክፉ ከመናገር፣ አንደበትህ ከሐሜትና ከስድብ፣ ዓይንህ ሴቶችን ከማየት፣ ጆሮህም ዘፈንና ጨዋታ ከመስማት ይጹም” ተብሎ እንደተ ነገረን (ርቱዐ ሃይማኖት) ሩካቤ ሥጋም ሰውነት የሚደሰትበት ፈቃድ ስለ ኾነ በጾም ወቅት መታቀብ ይገባል፡፡ “ወመፍቅደ ሕግሰ በጾም ከመ ትድክም ኃይለ ፍትወት … ወዓዲ ከመ ያምልኮ ለእግዚአብሔር በኵለንታሁ በአሠንዮተ ጾም እመንገለ ተአንስሶ ወበጸሎት እመንገለ ነባብያን፤ ጾምን ያሻው ፈቃድ የፈቲው ፆር ትደክም ዘንድ ነውና … ዳግመኛም ሰው እንስሳትን በሚመስልበት ባሕርዩ በጾም፤ መላእክትን በሚመስልበት ባሕርዩ በጸሎት እግዚአብሔርን በነፍስ በሥጋው ያገለግል ዘንድ ነው” ተብሎ ተጽፏል (ፍት. ነገ. ፲፭)፡፡ ስለዚህም በጾም ጊዜያት ሩካቤ ሥጋ ከመፈጸም መታቀብ ያስፈልጋል፡፡ “ኢታርስሖን ለመዋዕላት ቅዱሳት እንተ ጾም፤ ጾም የሚጾምባቸውን ዕለታት አታሳድፋቸው” እንዳለ ቅዱስ ባስልዮስ፡፡

ይኸውም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛትና የሚወለዱ ልጆችን ከደዌ ለመጠበቅ ሲባል የተሠራ ሕግ ነው፡፡ “በጾም ወቅት ከሩካቤ መከልከል ስለ ጾም የሚኾን ፈቃደ ነፍስ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ይኸውም ነባቢት ነፍስን ለማክበር ደማዊት ነፍስን ከእንስሳዊ ግብር መከልከል ነው፡፡ ሰውነትን (ሥጋ) በሚጐዳ በጾም ወራት ሰውነቱን፣ ልጁን ከደዌ ለመጠበቅ ለሰው ዂሉ እያንዳንዱ ከሩካቤ መከልከል ይገባዋል” እንዲል (ፍት. ነገ. አን. ፳፭፥፣ ቍ. ፶-፶፪)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ባልና ሚስት በንስሓ አባታቸው የተሰጣቸዉን የንስሐ ቀኖና ወይም በራሳቸው ፈቃድ የገቡትን የጾም ሱባዔ እስከሚፈጽሙ ድረስ ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ይገባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ባልና ሚስት በፅንስ፣ በአራስነትና በወር አበባ ወቅት፤ እንደዚሁም በበዓላትና በአጽዋማት ቀን ሩካቤ ሥጋ ማድረግ እንደማይገባቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሰይጣን የሚፈትንበትን ክፍተት እንዳያገኝ ባልና ሚስት ሊለያዩ አይገባም፡፡ “ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልኾነ በቀር እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ኹኑ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፭)፡፡ ይህ የሐዋርያው ትምህርት “ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጋችሁ በምትጾሙበት፣ በምትጸልዩበት ጊዜ ነው እንጂ ሥራችሁን ከፈጸማችሁ በኋላ ግን ወደ ፈቃዳችሁ ተመለሱ፡፡ የምትሹትን ስላጣችሁ ሰይጣን ድል እንዳይነሳችሁ” ተብሎ በፍትሐ ነገሥትም ተጠቅሷል (አን. ፲፭፣ ቍ. ፳፬)፡፡ ይህም ባልና ሚስት፣ የጾም፣ የጸሎት፣ የበዓል ወቅት ካልኾነ በቀር ሳይለያዩ ፈቃዳቸዉን መፈጸም እንደሚገባቸው ያስገነዝባል፡፡

ይቆየን