የጀበራ ማርያም ገዳምን እንደገና ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ ነው
ግንቦት 3ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በበሰሜን ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ደሴቶች ውስጥ ከሚገኙት ገዳማት አንዱ የሆነውና ለረጅም ዘመናት ጠፍ ሆኖ፤ ፈርሶ የቆየው የጀበራ ማርያም ገዳምን መልሶ ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡
የጀበራ ማርያም ገዳም በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተገደመ ሲሆን በደርቡሽ ወረራ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ሙሉ ለሙሉ ፈርሷል፡፡ ነገር ግን አባቶች መልሰው ገዳሙን በመመሥረት አጽንተውት የነበረ ቢሆንም የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወርር በ1956 ዓ.ም. መምህር ካሳ ፈንታ በሚባሉ አባት ቤተ ክርስቲያኑን በማነጽ፤ ገዳሙን መልሶ በመገደም ጥንት ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው ካረፉ በኋላ ከእግራቸው ተተክቶ ገዳሙን አጠናክሮ ለመያዝ የሚችል አባት በመጥፋቱ ገዳሙ ተፈታ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑም እንጨት በምስጥ ተበልቶ በንፋስ ኃይል ስለፈረሰ ታቦቱ ከሐይቁ ማዶ በምትገኘው ቅድስት ሃና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
ገዳሙን መልሶ በማቅናት ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል በገዳሙ ውስጥ ከዚህ ቀደም ለሦስት ዓመታት ቆይተው፤ በችግር ምክንያት በመውጣት ወደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከሔዱ 20 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ “የገዳሙ መፈታት በመስማቴና ህሊናዬ ሊያርፍ ባለመቻሉ አባቶቻችን ያቆዩልንን ገዳም ዳግም ለመመሥረት ወደዚህ መጣሁ፡፡ ከመጣሁም ገና 3 ወራት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት” ይላሉ፡፡
በሦስት ወራት ውስጥ ቤተልሔምና ቤተ እግዚአብሔር /ምግብ ማብሰያ/ ተሰርተው ተጠናቀዋል፡፡ በቀጣይነትም ለመናንያን በዓት፤ የእንግዳ ማረፊያ ቤት፤ ከደሴቱ ማዶ በሚገኘውና የገዳሙ ይዞታ በሆነው አንደ ሄክታር መሬት ላይ የሞፈር ቤት ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች እንደተጠናቀቁም በጅምር ላይ የሚገኘውን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ጥረት እንደሚያደርጉ አባ ዘወንጌል ይገልጻሉ፡፡
ጀበራ ማርያም ገዳም ውስጥ በጾም በጸሎት ተወስነው የሚገኙ አባቶች በጸሎታቸው ወቅት እጆቻቸው እንደ ከዋክብት ያበሩ ስለነበር በአካባቢው የሚገኙ ምእመናን “እጀበራዎች” እያሉ ይጠሯቸው ስለነበር የገዳሙ ስያሜ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ውስጥ ስድስት መናንያን ብቻ ,ይገኛሉ፡፡