የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳምን ዳግም ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑ ተገለጸ
ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በደምቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ውስጥ በ1335 ዓ.ም. ተገድማ የነበረችው የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳም ከፈረሰች ከበርካታ ዘመናት በኋላ ዳግም ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገዳሙን መልሶ ለማቋቋም በማስተባበር ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል ገለጹ፡፡
አባ ዘወንጌል ከ23 ዓመታት በፊት በዚሁ ገዳም ውስጥ በጸሎት ከሚተጉ አባቶች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፤ ወደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም በመሄድ በአገልግሎት ሲተጉ ቆይተዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. “የአባቶቼ ርስት እንዴት ቆይታ ይሆን?” በማለት አባቶችን ለመጎብኘት ወደ ቦታው ሲያቀኑ ቤተ ክርስቲያኗ ፈርሳ፤ አባቶችና እናቶች በርካቶቹ አርፈው፤ ገሚሶቹ ተሰደው ሁለት አባቶች ብቻ በእርግና ምክንያት የሚጦራቸው አጥተው በችግር ውስጥ እንዳሉ ይደርሳሉ፡፡
በሁኔታው የተደናገጡት አባ ዘወንጌል ከጣና ሐይቅ ማዶ ያሉትን ነዋሪዎች በመቀስቀስ፤ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ገዳሟን እንደገና ጥንት ወደነበችበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ኮሚቴ በማዋቀር ከበጎ አድራጊ ምእመናን በተገኘ ድጋፍም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗን በማስገንባት ላይ ሲሆኑ፤ በገዳሟ ውስጥም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ መናንያን ተሰባስበውባት በጸሎትና በአገልግሎት በመፋጠን ገዳሟን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ የተጀመረው ግንባታም በመፋጠን ላይ ሲሆን፤ ሠርቶ ለማጠናቀቅም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ የጣሪያ ቆርቆሮ፤ የበር፤ የመስኮት፤ የቤተ መቅደስ፤ የማጠናቀቂያ ሥራዎችና ሌሎችም ስለሚቀሩት በባለሙያዎች ተጠንቶ 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና ይህንን ለማሟላት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በችግር ውስጥ እንደሚገኝ አባ ዘወንጌል ገልጸዋል፡፡ በጎ አድራጊ ምእመናንም ገዳሟ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በ14ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት አባ በረከተ አልፋ በተባሉ አባት ተገድማ እንደ ነበረች የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ የገለጹት አባ ዘወንጌል፤ ገዳሟ በርካታ መናንያንን ስታስተናግድ የኖረች በመሆኗ በገዳማዊ ሕይወታቸውና በትሩፋታቸው ከልዑል እግዚአብሔር በረከትን ያገኙ አባቶችና እናቶች የኖሩባትና ጸሎት ሲያደርሱ የእጆቻቸው ጣቶች እንደ ፋና ያበሩ ስለነበር የአካባበቢው ነዋሪዎች “እጀበራዎች” እያሉ ይጠሯቸው ስለነበር ገዳሟ “ጀበራ” የሚለውን ስያሜ ማግኘቷን ይናገራሉ፡፡
ገዳሟ በድርቡሽ ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የጣና ገዳማት መካከል አንዷ ስትሆን ገዳማውያኑም በመሰደዳቸው እስከ 1956 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ፈርሳ ቆይታለች፡፡ በ1956 ዓ.ም መምህር ካሳ ፈንታ በተባሉ አባት ዳግም ተመሥርታ ብትቆይም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በማረፋቸው ገዳሟን የሚንከባከብ በመጥፋቱ ገዳማውያኑም ወደ ተለያዩ ገዳማት ተበተኑ፡፡ ተሠርታ የነበረቸው መቃኞም በምስጥ ተበልታ ፈረሰች::