የደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተገለጸ
ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የምትገኘው ታሪካዊቷና ተአምረኛዋ የደብረ ምጥማቅ የጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እሰከ 25 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ እየተገነባ መሆኑን በአዲስ አበባ የተቋቋመው የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ደብረ ምጥማቅ የጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በዘመናዊ መልክ ለመገንባት እንዲቻል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ደሳለኝ ሆቴል ታኅሣሥ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የገቢ ማሰባበሰቢያና የምክክር መርሐ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የማእከላዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው መርሐ ግብሩን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የዚህ ታላቅና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ ላይ መሣተፍ ባለ ታሪክ ከማድረጉም ባሻገር የቀደሙ ነገሥታትን አርዓያ መከተል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያኑን ተባብረን እንድንሠራውና የታሪኩ ተካፋይ እንድንሆን ከእኛ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና የጻድቃኔ ቅድስት ማርያም መካነ ቅዱሳን አንድነት ገዳም አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ፊሊጶስ አባተ “ምእመናን ወደ ገዳማችን እየመጡ ጸበሉን እየተጠመቁና እየጠጡ፤ እምነት እየተቀቡ፤ በጸሎት እየተጉ ድኅነትን ያገኛሉ፡፡ ገዳሙ ታላቅ የበረከት ቦታ ነው፡፡ ይህንን የቤተ ክርስቲያን ሥራ ምእመናን አቅማቸውን የፈቀደላቸው ያህል በገንዘብ፤ በጥሬ እቃ አቅርቦት፤ በጉልበትም ሆነ በእውቀታቸው እንዲራዱንና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንጠይቃለን“ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር አማረ አበበ ባቀረቡት ሪፖርትም ቤተ ክርስቲያኑ ከተሠራ ረጅም ዘመናትን ማስቆጠሩ፤ ጣሪያው ማፍሰሱ፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት በነበረው ጦርነት አደጋ ስለደርሰበት፤ እንዲሁም ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚመጡ ምእመናን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑና ቤተ ክርስቲያኑ በመጥበቡ ምክንያት በአዲስ መልክ ለመገንባት ታስቦ ወደ ሥራ ለመግባት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የቤተ ክርስቲያኑ የመሠረት ሥራ ተጠናቆ ወደ ዋናው ግንባታ የተገባና ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን እንዲቻል የምክክር መርሐ ግብር እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከሦስት መቶ በላይ ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን የተገኙ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ላይ ያተኮረ ዶክመንተሪ ፊልም ቀርቧል፡፡ ጥሪ ለተደረገላቸው ምእመናንም የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ በመጨረሻም ምእመናን የቃል ኪዳን ሰነድ ሞልተው ከ1ሚሊዮን በላይ በጥሬ ብር፤ እንዲሁም በጥሬ እቃዎች አቅርቦት ቃል ኪዳን እንደተገባ ሰነድ ለማሰባበሰብ መቻሉን ከኮሚቴው አባላት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ የሚገኘው የደብረ ምጥማቅ ማርያምና የጻድቃኔ ቅድስት ማርያም መካነ ቅዱሳን አንድነት ገዳም በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት እንደተመሠረተ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ቤተ ክርስቲያኑን ሊያሠሩ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያትም፤ በግብፅ ሀገር ሃይማኖት፤ ዘር፤ ቀለም ሳትለይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትገለጽ የነበረችበት ቤተ ክርስቲያን እሰላሞች በማቃጠላቸው እጅግ አዝነው ስለነበር በኢትዮጵያ ውስጥ ሰሜን ሸዋ ላይ ቤተ ክርስቲያኑን እንዳሠሩ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
በንጉሥ ዘርዐ ያዕቀብ የተመሠረተው ይህ ገዳም አሁንም ባለንበት ዘመን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሕልም፤ በራዕይና በተከስቶ እየተገለጸች ምእመናንን እየተራዳች፤ በስሟ ከፈለቀው ጸበል እየጠጡና እየተጠመቁ ከተለያዩ ደዌያት በመፈወስ ላይ ናቸው፡፡
የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ ሥራ መርዳት ለሚፈልጉ ሁሉ በስልክ ቁጥር 0911243678፤ 0911207804፤ 0911616880፤ ደውለው ማነጋገር የሚችሉ ሲሆን በተጨማሪም ለሕንፃው ሥራ መፋጠን በባንክ መርዳት ለሚፈልጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ የደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ በባንክ ቁጥር 1000033548625 መላክ እንደሚቻል ኮሚቴው አሳስቧል፡፡