የደብረ ሊባኖስ ገዳም የልማት ፕሮጀክት ትግበራ በመፋጠን ላይ ይገኛል
ሰኔ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
- ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ይካሔዳል፡፡
በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በ2004 ዓ.ም. በገዳሙና በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበው የገዳሙ ሁለንተናዊ የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሚገኝ የገዳሙ የልማት ኮሚቴ ገለጸ፡፡
የጥናት ቡድኑ በገዳሙ የሚታዩትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየትና ጥናት በማካሔድ፤ የፕሮጀክት ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመሸጋገር በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡
በጥናቱ ተለይተው የተያዙትን ችግሮች ለመቅረፍ በሦስት ዙር የተከፈሉ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር የብዝኀ ሕይወት ጥበቃ፤ የአፈርና የውኃ ጥበቃ፤ የመነኮሳት መኖሪያ ግንባታ፤ የመጸዳጃ ቤትና የአካባቢ ጽዳት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ በሁለተኛው ዙር የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ (የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ፤ የመምህራን መኖሪያ፤ ቤተ መጻሕፍትና የምርምር ማእከል) የያዘ ነው፡፡ በሦስተኛ ዙር የጤና ጣቢያ፤ የሁለገብ ሕንፃ፤ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ የሚደረጉበት መሆኑ የፕሮጀክት ሰነዱ ያመለክታል፡፡
የጎርፍና የመሬት መንሸራተት፤ የቀብር ቦታና የቀብር ሐውልት መስፋፋት፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የአውቶቡስ መናኸሪያ መስፋፋት በጥናቱ የተካተቱና እንደችግር የታዩ በመሆናቸው በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ትግበራም በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ የመጸዳጃና የገላ መታጠቢያ ቤቶች ግንባታቸው 60% መድረሱን የገዳሙ የልማት ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በሦስት ዙር የሚጠናቀቀው የልማት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት በተጠናው ጥናት መሠረት 65,925,976 ብር (ስልሳ አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስድስት ብር) ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የገዳሙንና የምእመናን መንደር፤ የአባቶችና የእናቶች መኖሪያ ይለያሉ፤ መናንያን ለጸሎትና ለአገልግሎት የሚመች በዓት ይኖራቸዋል፡፡ ሱባኤ ለመያዝ በሚመጡ ምእመናንና በገዳሙ አባቶች መካከል ያለው ግንኙነት ሥርዓቱን የጠበቀ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጥናቱ የተካተቱትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የልማት ኮሚቴው የተለያየ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በመንደፍና በማዘጋጀት ፕሮጅክቱን በታቀደለት ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ሰኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡ ምእመናን በሥፍራው ተገኝተው ድጋፍ እንዲያደርጉ የገዳሙ ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ከ2500 በላይ የአብነት ተማሪዎችና ከ800 በላይ ማኅበረ መነኮሳት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡