የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተካሄደ
ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደቡብ ክ/ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጉባኤውን ሚያዚያ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ፡- በክፍለ ከተማው የሚገኙ 32 ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በጉባኤው ላይ ተገኝተው ትምህርተ ወንጌል የሰጡት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ክቡር ቆሞስ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ናቸው፡፡
የመምሪያ ሓላፊው “ልጄ ሆይ ሰው ሁን” በሚል ርዕስ ባስተማሩት ትምህርት ላይ “ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የአንድነት ጉባኤ በየዓመቱ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ይህንን ጉባኤ ማካሄዳችን በየሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ያሉብንን ችግሮች ለማስወገድና በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የበኩላችንን እገዛ ልናደርግ እድል ይፈጥርልናል፡፡ በየሰንበት ት/ቤቱ የሚገኙ ልጆቻችንም ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከብፁአን አባቶቻችን ቡራኬና ትምህርት የሚቀበሉበት መርሐ ግብር ይሆናል በአጠቃላይም ይህን ጉብኤ ለማዘጋጀት የማደራጃ መምሪያው ድጋፍ አይለየውም” ብለዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምክትል ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ዘሪሁን መኮንን በጉባኤው ላይ ባቀረበው ሪፖርት ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን በየዓመቱ የደመራ በዓልን ለማክበር በአደባባይ ከመሰባሰብ ውጪ መንፈሳዊ አንድነት ፈጥረው እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነት ሊያበረክቱት የሚገባቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ሳይቻላቸው በርካታ ጊዜያት ማለፋቸውን አስታውሶ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን የተጠናከረና ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በእኩል ሊያሳትፍ የሚችል መተዳደሪያ ደንብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረታቸውን በመጠበቅ የጋራ ዕቅዳቸውን ለማሳካት አገልግሎታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጿአል፡፡ ም/ሰብሳቢው በክፍለ ከተማው የተሠሩ ሥራዎችን ሳያብራራ፡- በሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያሬዳዊ ዝማሬን ለማስጠናት የሚችሉ የአሰልጣኞች ሥልጠና ለሦስት ዓመታት ተካሂዷል” ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መምህራንን በማፍራቱና በማሰልጠን ረገድ በ3 ጊዜያት ቁጥራቸው ከ146 በላይ አባላትን ማስተማሩንና በተመሳሳይ መልኩ ከልዩ ልዩ አድባራት የተውጣጡ መምህራን የሰጡትን የአብነት ትምህርት በሚገባ የተከተሉ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ሥልጣነ-ክህነት እንዲቀበሉ ማድረጉን አስረድቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አንድነት ለመመሥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው ክፍለ ከተማው የተሃድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የመከታተል ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ፣ እንዲሁም ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የአስተዳደርና ሒሳብ አያያዝ ሥልጠና መስጠቱን ገልጿል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ “ድንግል ሆይ ብረሳሽ” የተሰኘ መነባንብ፣ እንዲሁም “ሰንበት ት/ቤት” የሚል ግጥም ቀርቧል፡፡
ከጉባኤው በኋላ የክፍለ ከተማው ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ሳሙኤል እሸቴን “የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማኅበር አወቃቀሩ ምን ይመስላል?” ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ ምላሽ ሲጠጥ “….በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ የተዋቀረ ተጠሪነቱም ለአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የሆነ የአገልግሎት ክፍል አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ የአገልግሎት ክፍሎች አሉ፡፡ እነኚህን ለማገዝ በክፍለ ከተማችን የሚገኙ 32 ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በ4 ምድብ በመክፈል እየተናበቡ ተግባራትን እንዲያስፈጽሙ እያደረግን እንገኛለን፡፡ ይህንንም ለማገዝ በማደራጃ መምሪያው መልካም ፈቃድና እገዛ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ቢሮ ተሰጥቶናል” ብሎናል፡፡
ወጣት ሳሙኤል ከዚሁ ጋር አያይዞ ሚያዝያ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ስለተከናወነው መርሐ ግብር በተመለከተ ሲናገር “የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በሚል ርእስ በየዓመቱ የሚከናወነው መርሐ ግብር ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የተከናወነ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት በአንድ ጉባኤ ተሰብስበው የመማራቸው ፋይዳው፡-
የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ለእናት ቤተ ክርስቲያን ሊያበረክቱ የሚገባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፤ በቅርቡም በዝቋላ የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ለማጥፋት እርስ በርስ ተጠራርተው መሄዳቸውና ያንን የመሰለ አስደናቂ ተግባር ፈጽመው መመለሳቸው የመገናኘቱ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል የማደራጃ መምሪያችን ሓላፊ ቆሞስ አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው በጉባኤያችን ላይ ተገኝተው በየክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ትምህርትና ቡራኬን ከብፁዓን አባቶች መቀበል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሰላሳ ሁለቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምን ያህል አባላት አሉ? የሚል ጥያቄ ያቀረብንለት ወጣት ሳሙኤል “በግምት ከ20 እስከ 30ሺ የሚደርሱ አባላት አሉን፡፡ በቅርቡ ግን በእያንዳንዱ ሰንበት ትምህርት ቤት ምን ያህል አባላት እንደሚገኙ በዕድሜአቸው በትምህርታቸው /በሙያቸው/ እንዲሁም በሌላ አስፈላጊ መረጃዎች የተጠናከረ መረጃ /ዳታ/ የማሰባሰብ ሥራ እንጀምራለን፡፡ ይህም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ያልተነካ የሰው ኃይል በሰንበት ትምህርት ቤቶቿ እንዳላት መረጃ ይሰጣልና፡፡”
በስተመጨረሻ የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በመወከል ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ካለህ? ተብሎ የተጠየቀው ወጣት ሳሙኤል፡፡
“የሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን በአብነት ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአብነት ትምህርት ጉዳይ ለነገ የሚባል ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የነገ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድ የሚፈሩባቸው ከመሆናቸው አንፃር በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተናጠል ከመሥራት ወጥተን /የአንዲት ርትዕት ቅድስት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆናችን/ በአንድነት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማፋጠን መሥራት ይኖርብናል፡፡ በመጨረሻ በሰንበት ትምህርት ቤቶች የምንገኝ ወጣቶች ሁላችን ሀገራዊ ራእይ ሃይማኖታዊ አቋምን አጠናክረን ልንይዝ ይገባናል” ብሏል፡፡