01desie

የደሴ ማእከል የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ሊያካሂድ ነው

ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም

ከደሴ ማእከል

01desieበማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል የአካባቢውን ማኅበረ ምእመናን በማሳተፍ ወደ ታሪካዊው ደብር ቦሩ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ያካሂዳል፡፡

መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዓላማ ምእመናን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ለማነጽ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መንፈሳዊ ጉዞ ምን መምሰል እንዳለበት ግንዛቤ ለመፍጠር፤ እንዲሁም ወደ ገዳማትና አድባራት በመሄድ በረከት እንዲያገኙ እንደሆነ የማእከሉ ጸሐፊ ዲ/ን ሰሎሞን ወልዴ ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩም የአባቶች ቡራኬ፣ ትምህርተ ወንጌል፣ ያሬዳዊ መዝሙር፣ ምክረ አበው፣ ቅኔ፣ ጉብኝት፣ የፕሮጀክት ምረቃ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡

የጉዞው መነሻ ቦታ የደሴ ማእከል ጽ/ቤት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከጠዋቱ 12፡00 ስዓት ሲሆን፤ የጉዞው ሙሉ ወጪ (ቁርስና ምሳን ጨምሮ) 60 ብር እንደሆነ ዲ/ን ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡

ምእመናን የጉዞ ትኬቱን በማእከሉ ጽ/ቤት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ በማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ቤት፣ በደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ቤት (ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር)፣ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ቤትና ተድባበ መዝሙር ቤት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ማግኘት እንደሚችሉ የደሴ ማእከል ጸሐፊ አስታውቀዋል፡፡