የዛፉ ፍሬ

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ጥቅምት ፲፯፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ወይ! አፈር . . . .
አፈር ተለወሠ
አፈር ተቀደሠ
በአፈር ላይ ነገሠ

ንጉሥ በግዛቱ ረዳት ማጣቱ
ደግ አይደለምና አገኘ ከአጥንቱ
ከእንግዲህ ቀርተዋል እናትና አባቱ
ከጐኑ የማትለይ . . .አለች አጥንቱ
የራስ ጌጥ ዘውዱ ናት ዕውቀት ብልሀቱ

በራሱ ላይ ሆና ሴቱቱ እያየችው
እያየ ባያያት . . . . ዓይኖቹን ሳይገልጠው
ዓመታት ተቆጥረው . . . . ቀናት ቢሠለፋ
መቼ ይተያያሉ . . . ተጋርደው በዛፋ

አቤት ዛፋ! . . . አቤት ዛፋ አራራቁ!
በሴቴቱ ጥበብ ፍሬው ላይ ቢወድቁ
አዳምና ሔዋን . . . በደንብ ተሳለቁ

ኦ! ሔዋን . . .
ሔዋን የደስታ ምንጭ . . . የሐሴት መፍለቂያ
የወርቅ ቀለም ነሽ ፍቅርን መጻፊያ
እንኳንም ቆረጥሽው እንኳንስ ቀጠፍሽው
አዳምን አግባብተሽ ቀምሰሽ ባታቀምሽው
የፍቅር ብርሃን መቅረዙ እንደጠፋ
ተገልጦ ሳይታይ ሳይወጣ በይፋ

አዳም ያየ መስሎት ዓይኑ እንደተዘጋ
ይኖር ነበር ገነት ብቻውን ሲተጋ

ሔዋን ባትቀጥፈው የበለሱን ፍሬ
መቼ ይሰማ ነበር የአምላክ ልጅ ወሬ

አዳም የተከለው የፍቅር አበባ አድሮ እየጐመራ
አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን አብቦ ቢያፈራ
ከላይ ከሰማያት መንበረ ጸባኦት
የአምላክን አንድ ልጅ መዓዛው ጐትቶት

ረቂቁ ገዝፎ . . . በምድር ላይ ወርዶ
ፍቅርን አገኘነው፤ በላነው፤ ጠጣነው፤ ሥጋን ተዋሕዶ
ተዋሕዶ . . . ተዋሕዶ . . . ተዋሕዶ
ንጽሕት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ!