የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው? – ክፍል ሁለት
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
፬. የሰው ልጅ እና የክህነት ክብርን፣ እንደዚሁም መንፈሳዊ ባህልን ማቃለል
ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ በታች በተጠቀሰው ትምህርቱ በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ጠባይ ይነግረናል፡፡
‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይኾናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የኾነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይኾናሉ፡፡ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል፡፡ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ፡፡ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን፣ በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን፣ ዅልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው፣ ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ኾነው እውነትን ይቃወማሉ፡፡ ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ኾነ፤ ሞኝነታቸው ለዅሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም፤›› /፪ኛጢሞ. ፫፥፩-፯/፡፡
ይህንን ትምህርት ለማገናዘብ እግዚአብሔርን የማያምነውን ሕዝብ ትተን፣ በመላው ዓለም ዅሉ ካሉ የክርስትና ሃይማኖት አማኞች ተግባር አንጻር ጥቂት ነጥቦችን እንደሚከተለው እንመልት፤
ሀ. መንፈሳዊ ባህልን ማፍረስ
ዅሉም ባይኾኑ አንዳንድ አማኞች ‹‹… ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይኾናሉ፡፡ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል …›› የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደ ኾኑ ቅዱስ ጳውሎስ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ እንደ አማኝ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ክደዋል›› ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመንፈሳዊው ባህል የጠነከሩ ብዙዎች እንዳሉ ዅሉ አንዳንድ ሥራ ፈቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ አሉባልታ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ እኩያን ተግባራትን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይስተዋላል፡፡
እነዚህም አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን ክፉ ሥራ ሲገልጥ፡- ‹‹አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም፣ ከግሪክ ሰዎች ብዙ፣ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ፡፡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፤›› በማለት ቅዱስ ሉቃስ እንደ ተናገረላቸው ሰዎች ያሉ ናቸው /ሐዋ. ፲፯፥፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከላይ እንደ ጠቀስነው ‹‹ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ዅልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና›› ይላቸዋል፡፡
ለ. የክህነትን ክብር ማቃለል
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹… ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ኾነው እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፣ ሞኝነታቸው ለዅሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም …›› እንዳለው ዅሉ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት በአንብሮተ እድ የሰጣቸው፤ በትውፊት ከእኛ ላይ የደረሰው፤ የድኅነት መፈጸሚያ የኾነው ሥልጣነ ክህነት ዛሬ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ባሉ ሰዎች ዘንድ እየተናቀ፣ እየተቃለለ ነው፡፡ ከክህነት ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን ከሚፈጸሙ ስሕተቶች መካከል ጥቂቶቹን ቀጥለን እንጠቅሳለን፤
በቅዱስ ወንጌል፡- ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፤›› እንደዚሁም፡- ‹‹በዚያን ዘመን ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስበርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፡፡ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረው /ማቴ. ፳፬፥፲/፤ ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት እንዲሁ ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በድፍረት የሚከፋፍሉ፤ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ክህነት የሰጠቻቸውን እናታቸውን እስከ ማውገዝ ድረስ የደረሱና በድፍረት ኀጢአት የሚበድሉ አገልጋዮች የሚገኙበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ‹‹ዅሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የኾነ ምንም የለም፡፡ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል፡፡ እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ፣ ለበጎ ሥራም ዅሉ የማይበቁ ስለ ኾኑ በሥራቸው ይክዱታል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ/ቲቶ. ፩፥፲፭/፡፡
ሠለስቱ ምእት በኒቂያ ጉባኤ ‹‹ያለ ኢጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ከክህነቱ ይሻር›› ብለው ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ አገር እየተለመደ የመጣው ጉዳይ የትኛውንም ኤጲስቆጶስ ሳያስፈቅድ አንድ ካህን፣ ከዚያም አልፎ ዲያቆን ወይም ምእመን እንደ ማንኛውም ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ፤ ቦርድ አቋቋምኩ እያለ በድፍረት ምእመናንን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በሚደርግበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ለተቋቋሙ ‹አብያተ ክርስቲያናት› የሚገለገሉበት ሜሮን፣ ታቦት ከየት ተገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም፡፡ ‹‹ብዙዎች ይስታሉ›› እንደ ተባለው በድፈረትና በስሕተት መሠረት ላይ የስሕተትና የድፍረትን ግድግዳ ማቆም፤ የስሕተትና የድፍረት ጣሪያንም ማዋቀር እንደ ሕጋዊ ሥራ ከተቈጠረ ሰነባበተ፡፡
‹‹የጥፋት ርኵሰት በተቀደሰው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ማቴ. ፳፬፥፲፭/፣ በየአጥቢያው የሚሰማውን ክፉ ወሬ ስናስተውል የዚህን ትንቢት ተፈጻሚነት እንረዳለን፡፡ የተሐድሶ ሤራ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠረው ጭቅጭቅ፣ ሐሜት፣ ሙሰኝነት፣ ዘረኝነት፣ ወዘተ. ምን ይነግሩናል? በአንዳንድ የውጭ አገር ክፍሎችም አብያተ ክርስቲያናት በሰበካ ጉባኤ ሳይኾን ለካህናት ክብር በማይጨነቁ የቦርድ አመራሮች መተዳደር ጀምረዋል፡፡ ይህ አሠራር ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከኖረችበት አገልግሎት አንጻር ስናየው እጅግ የራቀና የከፋ ነው፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሥልጣነ ክህነት እንድትተዳደር ሲኾን ይህኛው አሠራር ግን በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመኑን አስተምራ፣ አጥምቃ፣ አሳድጋ እንደገና በተንኮለኞች ሤራ ልጆቹዋን ቀስጠው በእርሷ ላይ እንዲያምጹ ማድረግ የጥፋት ርኵሰት መኾኑን ስንቱ ተረድቶት ይኾን?፡፡ በመወጋገዙ ሒደት ያለው ጉዳትንስ ማን አስተዋለው? እግዚአብሔር ይማረን እንጂ እንደ ሰውኛው ከኾነ መጨረሻው ከባድ ነው፡፡
ከዚህ ዅሉ በደል ለመራቅም ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር፣ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በኾነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢኾን፣ በትዕቢት ተነፍቶአል፤ አንዳችም አያውቅም፡፡ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፡፡ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር፣ ስድብም፣ ክፉ አሳብም፣ እርስበርስ መናደድም ይወጣሉ፡፡ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው፣ እውነትንም በተቀሙ፣ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚኾን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ፤›› ሲል ያስተማረንን ትምህርት በተግባር ላይ ማዋል ይጠቅመናል /፩ኛጢሞ. ፮፥፫-፭/፡፡ በእርግጥ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን ቢቃወሙትም ሙሴ ሥልጣኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠው በመኾኑ የእግዚአብሔር ክብር በእርሱ ላይ፤ ቍጣው ደግሞ በበደለኞቹ ኢያኔስና አንበሬስ ላይ እንደ ተገለጠ ዅሉ፣ ዘለዓለማዊዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ክህነታዊ ክብርዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነውና በአገልጋዮቿ መከፋፈል አትበተንም፤ አትፈርስም፡፡
ሐ. የሰው ልጅ ክብርንና የዕድሜ ደረጃን አለመጠበቅ
ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይኾናሉና፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የኾነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ …›› በማለት የዘረዘረው የሰው ልጅ የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትሥሥርና ክብር እንዲጠፋ ለሚሠሩ ሰዎች ተስማሚና በቂ ማስረጃ ነው /፩ኛጢሞ. ፫፥፩-፫/፡፡
በአጠቃላይ የምጽአት ምልክቶች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከምሁሩ እስካልተማረው፣ ከትልቁ እስከ ትንሹ ድረስ ያገባውም ያላገባውም፤ ካህኑም መነኵሴው ሳይቀር ብዙዎቹ በአንድነት ከቅድስና ርቀው ከጥፋት ርኵሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋደሽ መኾናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- ‹‹ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ኾኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፡፡ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፤ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፤›› ሲል እንደ ተናገረው /መዝ.፵፱፥፪-፫/፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም ተባብረው እንደ መሰከሩት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት ይመጣል፤ አይዘገይም፡፡
ከላይ እንደ ተዘረዘረው ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ ብዙ ሰዎች የተጠመዱበት በዓለማዊ ሥራ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሔዳሉ እንጂ ከጥቂቶቹ በስተቀር ወደ መንፈሳዊው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ሰው (ምእመን) ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመፅ እየበረታ በቤተ መቅደሱ ሳይቀር የድፍረት ኀጢአት የሚሠራው እየበዛ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከዚህ ዅሉ ኀጢአት ለመራቅና ወደ መንፈሳዊው ተጋድሎ ለመምጣት እግዚአብሔርን ደጅ መጽናት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች ነን የምንል ዅሉ የጥፋት ትንቢቱ በእኛ ላይ እንዳይፈጸምብን አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኵሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! ወለወላዲቱ ድንግል! ወለመስቀሉ ክቡር!