የክህነት አገልግሎት
በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ
በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ዋና ክፍል የተዘጋጀ
የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
‹ክህነት›፣ ‹‹ተክህነ – አገለገለ›› ከሚል የግእዝ ቃል የወጣ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹አገልግሎት፣ መላላክ፣ ለሌሎች መኖር፣ መጥዎተ ርእስ (ራስን መስጠት) መላ ሕይወትን ለእግዚአብሔር ማስረከብ›› ማለት ነው፡፡ ክህነት ካለ ካህናት ይኖራሉ፤ ክህነት አገልግሎቱ፣ ሹመቱ፤ ካህናት ደግሞ አገልጋዮቹ፣ ተሿሚዎቹ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ካህናት መላእክት ናቸው፡፡ የመጀመሪያ የእግዚአብሔር እና የሰው ልጆች አገልጋዮች፡፡ ‹‹በዙፋኑ ዙሪያ ሃያ አራት ወንበሮች ነበሩ፡፡ በእነዚያ ወንበሮችም ሃያ አራት አለቆች (ካህናተ ሰማይ) ተቀምጠዋል፡፡ ነጭ ልብስም ለብሰዋል፡፡ በራሶቻቸው ላይ የወርቅ አክሊሎች ደፍተው ነበር … በዂለንተናቸው ዓይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የነበረውና ያለው፣ የሚመጣውም፤ ዂሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ› እያሉ›› ቀንና ሌሊት አያርፉም፡፡ እነዚህ በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለም እስከዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት አውርደው ይሰግዳሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፤ ‹ጌታችን እና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ዂሉን ፈጥረሃልና በፈቃድህም ኾነዋልና ተፈጥረውማልና ክብርና ውዳሴ ኀይልም ለአንተ ይገባል፤››› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ራእ. ፬፥፬)፡፡
ይህ ከላይ የተመለከትነው ኃይለ ቃል ለክህነት እና ለካህናት አገልግሎት መሠረቱ ነው፡፡ ‹‹በመዓልትም በሌሊትም አያርፉም›› ያለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን የዘወትር አገልግሎት በግልጽ ያሳያል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ምስጋናው በሰማይና በምድር የሞላ ነው›› በማለት የምታሰመግነው በክህነት እና በካህናት አማካይነት ነው፡፡ ካህናት፣ ምድራውያን መላእክት ናቸው፡፡ መላእክት እንደሚያመሰግኑ ያመሰግናሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲቆሙ ይቆማሉ፡፡ የክህነት አግልግሎት ከመላእክት ቀጥሎ የተሰጠው ለሰው ልጅ ነው፡፡ ለሰው የተሰጠው ክህነት ፈጣሪውን እንዲያመሰግንበት ብቻ አይደለም፡፡ መሥዋዕት ሊሠዋበት፣ ዕጣን ሊያሳርግበት፣ ሰውን ሊረዳበት የተሰጠ ነው፡፡ ለሰው ክህነት ተሰጠው ስንል ሰው ዂሉ ካህን ነው ማለት አይደለም፡፡ ከሰው ልጆች ወገን ለክህነት የተመረጡ አሉ፡፡ ዂሉም ሰው ተነስቶ ካህን ነኝ ሊል አይችልም፡፡ ይህ ማለት የአካል ክፍል እንደማጥፋት ማለት ነው፡፡ በአካል ውስጥ ዓይን፣ እጅ፣ እግር፣ አፍ፣ አፍንጫ … አሉ፡፡ ዂሉም የአካል ክፍሎች ዓይን መኾን አይችሉም፡፡ እጅ መዳሰስ፣ እግር መሔድ፣ ዓይን ማየት፣ አፍንጫ ማሽተት፣ አፍ መጉረስ ነው የሥራ ድርሻቸው፡፡ እጅ፣ እግር፣ አፍ፣ አፍንጫ፣ ጆሮ ካላየን ቢሉ፣ ዓይን እንኹን ብለው ቢያስቡ ወይም ነን ቢሉ ዓይን መኾን (ማየት) አይችሉም፡፡ ማየት የዓይን ተግባር እንደ ኾነ ዂሉ ሰዎችም ካህን ሳይኾኑ ነን በማለት መዓርገ ክህት አይገኝም፡፡ እግዚአብሔር የመረጣቸው ካህናት ይኾናሉ እንጂ፡፡
ክህነት በብሉይ ኪዳን
እግዚአብሔር ሙሴን ለምስፍና (ለመስፍንነት)፣ አሮንን ለክህነት መርጧቸዋል፡፡ የመረጠበት ግብርም ረቂቅ ነው፡፡ ዂሉም እስራኤል ግን መሳፍንት፣ ገዢዎች፣ መሪዎች አልነበሩም፡፡ የሌዊ ወገን ለክህነት፣ የይሁዳ ወገን ለመንግሥት የተመረጠ ነበር (ዘኍ. ፫፥፮)፡፡ የሌዊ ነገድ ተለይተው የክህነቱን አገልግሎት፣ መሥዋዕት መሠዋት የመሳሰሉትን ይሠሩ ነበር (ዘዳ. ፲፥፰፤ ፳፰፥፩-፵፫)፡፡ ሌሎች ነገደ ፳ኤል ድንኳን በመሸከም ልዩ ልዩ አገልግሎት ይሠጡ ነበር፡፡ ይህን የተላለፈ ፳ኤላዊ መቀሠፍቱ ከባድ ነበር፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ለክህነት መመረጥ፣ መለየት፣ መቀባት፣ መሾም፣ መቀደስ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ማንም ዝም ብሎ ካህን ነኝ፤ ነቢይ ነኝ ማለት አይችልም፡፡ መሥዋዕቱን ምእመናነ እስራኤል ያመጣሉ፤ አሮንና ልጆቹ ደግሞ መሥዋዕቱን ያቀርባሉ፡፡ ሕዝቡ በጉን፣ ርግቡን፣ ዋኖሱን፣ በሬውን ያመጣሉ፤ ካህናቱ እጃቸውን ጭነው ይጸልያሉ፤ ኀጢአትን ያስተሰርያሉ፡፡ ሕዝቡን ያስተምራሉ፤ ይመክራሉ፡፡ ሕዝቡም ይመከራል፤ ይገሠፃል፡፡
በእግዚአብሔር ሳይመረጡና ሳይሾሙ ካህን ነን ቢሉ የሚመጣው ቅጣት ከባድ ነው፡፡ ከሌዊ ወገን የተወለዱ ዳታንና አቤሮን የደረሰባቸው ቅጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል (ዘኍ. ፲፮፥፩-፶፩)፡፡ ያልተሰጣቸውን ሽተው፣ ከህነት ሳይኖራቸው ለማጠን ገብተው የእሳት ራት ሆነዋል፡፡ መሬት ተከፍቶ ውጧቸዋል፡፡ በሕይወት ሳሉ ተቀብረዋል፡፡ ለክህነት የተመረጠው አሮንና ልጆቹ ግን አልጠፉም፡፡ ከዚህ እንዳየነው ለክህነት መመረጥ፣ መቀደስ፣ መለየት፣ መሰጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይኾን ማንም ተነሥቶ ካህን ነኝ፣ ነቢይ ነኝ ቢል ይህ ዕጣ ፋንታ ይገጥመዋል፡፡ እግዚአብሔር አልመረጠውምና፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዕጣን ማሳረግ (ማጠን) ለመቅሠፍት፤ የሳኦል መሥዋዕትም መንግሥትን ለማጣት ዳርጓቸዋል፡፡ ሳኦል፣ ሳሙኤል እስኪመጣ መታገሥ አቅቶት መሥዋዕት በመሠዋቱ ነው መንግሥቱን የተነጠቀው (፩ኛ ሳሙ. ፲፭፥፳፪፤ ፳፰፥፲፯)፡፡
ክህነት በሐዲስ ኪዳን
ክህነት በዓለመ መላእክት፣ በብሉይ ኪዳን ምን እንደሚመስል ተመልክተናል፡፡ በዓለመ መላእክት መሥዋዕቱ ምስጋና፣ ውዳሴ፣ ተልእኮ ነው፡፡ ካህናቱ መላእክት ናቸው፡፡ ቤተ መቅደሱ ዓለመ መላእክት ነው፡፡ በብሉይ ካህናቱ ከሌዋውያን የአሮን ልጆች፣ ቤተ መቅደሱ የመገናኛው ድንኳን፣ መሥዋዕቱ ላም፣ በግ፣ ፍየል፣ ርግብ፣ ዋኖስ የእኽል አይነቶች ናቸው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ክህነቱም፣ መሥዋዕቱም፣ ካህናቱም ከተመለከትነው የተለየ ነው፡፡ ክህነቱና ካህናቱ ልዩ የሚኾንበት ምክንያት መሥዋዕቱ ልዩ በመኾኑ ነው፡፡ መሥዋዕቱ በቀራንዮ ዐደባባይ ዓለም ለማዳን ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍስሶ የሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቀደም ሲል ያየነው የመላእክት መሥዋዕት ዓለምን ማዳን አልተቻለውም፡፡ የሌዋውያንን መሥዋዕትም አንድ ኀጢአተኛ ሰው ያመጣዋል፡፡ ከመርገም ያልተለየ ካህን ይሠዋዋል፡፡ መሥዋዕቱም ሥጋዊ ይቅርታን ብቻ ያሰጥ ነበር፡፡ መሥዋዕቱ፣ በአቀራረቡም ጉድለት ነበረበት፡፡ ስርየቱ የሚያስገኘውም ላመጣው ሰው ብቻ ነበር፡፡
የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ግን መሥዋዕቱ ፍጹም ጉድለት የሌለበት ነው፡፡ መሥዋዕቱም፣ አቅራቢውም፣ ተቀባዩም ኢየሱስ ክርስቶስ በመኾኑ ክህነቱም ፍጹም ነው፡፡ ይህን ፍጹም ክህነት ፍጹም የሆነውን መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ካህናት ሰጠ፡፡ ክህነቱን አገልግሎቱን በትህትና አሳያቸው አስተማራቸው፡፡ ክህነቱንም መሥዋዕቱንም ሰጣቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የሐዲስ ኪዳን ካህናት መላእክት ያልሰዉትን የብሉይ ኪዳን ካህናት ያላቀረቡትን መሥዋዕት የማቅረብ የማገልገል ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው በመሆኑ ክህነቱ ምጡቅ ምስጢሩ ጥልቅ አገልግሎታቸውም ረቂቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹ኢተአምሩኑ ከመ መላእክተ ጥቀ ንኴንን ኅድጉሰ ዘዝ ዓለም፤ የዚህን ዓለም ዳኝነት ተዉትና በመላእክት ስንኳን እንድንፈርድ አታውቁምን?›› ሲል እንደ ጠቀሰው፤ መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ‹‹ዘኢተገብረ ለመላእክት ተገብረ ለካህናት፤ ለመላእክት ያልተደረገ ለካህናት ተደረገ›› በማለት እንደሚያስተምሩን (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፫)፡፡
የብሉይ ኪዳን ካህናት ሰዉን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ አልተቻላቸውም፡፡ የሐዲስ ኪዳን ካህናት ግን የጠብ ግድግዳ ከፈረሰ፣ ልጅነት ከተመለሰ፣ ጸጋ ከተገኘ፣ ሰውና እግዚአብሔር ከተገናኘ በኋላ ስለ ተሾሙ ክህነታቸው ልዩ፣ መሥዋዕታቸው ልዩ፣ ክብራቸው ልዩ ነው፡፡ ምድራውያን ናቸው፤ ነገር ግን ሰማያዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ የተሾሙትም ሰማያዊውን ርስት ለመስበክ፣ ሰውን ከምድራዊ ግብር ለይተው ሰማያዊ ጸጋ አሰጥተው መንግሥተ ሰማያትን ለማውረስ ነው፡፡ አምላክ ይህን ያደረገው በመልእክት አይደለም፤ ሰው ኾኖ መጥቶ ሥርዓቱን ሠርቶ አሳይቶ ሥልጣኑን ሰጥቶ አገልግሎቱን መሥርቶ ነው፡፡ ‹‹ወአልቦ ዘይነስእ ክብረ ለርዕሱ ዳዕሙ ዘጸውዖ እግዚአብሔር በከመ አሮን፤ በቃሁ ነቃሁ ብሎ ክብረ ክህነትን ለራሱ የሚያደርግ የለም፡፡ እግዚአብሔር እንደ አሮን ነው እንጂ (እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብርን ለራሱ የሚወስድ የለም፤››) እንዳለ (ዕብ. ፭፥፬)፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ሥልጣነ ክህነት በጳጳሳት እጅ የሚሰጥ ሥልጣን ነውና ማቃለል አይገባም፡፡ ካህናት የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸውና፡፡ እግዚአብሔር ኀጢአተኛውን የሚያየው፣ የሚጐበኘውና ኀጢአቱን ይቅር የሚለው በእነርሱ በኩል ነው፡፡ ‹‹ሒድ ራስህን ለካህን አሳይ›› (ማቴ. ፰፥፬) ተብሎ እንደ ተጻፈ ካህን አየን ማለት እግዚአብሔር አየን ማለት ነው፡፡ ካህን የእግዚአብሔር ዓይን ነውና፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የምንኾነውም በካህናት ተጠምቀን ነውና (ማቴ. ፳፰፥፲፱)፡፡ በዚህ መሠረት ያለ ካህን እና ያለ መሥዋዕት የሚፈጸም አገልግሎት የለም፡፡ ቢኖርም አገልግሎቱ የውሸት ነው፡፡ ሕሙማን በክህነት አገልግሎት ይድናሉ፡፡ ‹‹ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራና ይጸልዩለት፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት የሃይማኖት ጸሎት ድውዩን ይፈውሰዋል፡፡ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ኾነ ይሰረይለታል፤›› እንዲል (ያዕ. ፭፥፲፫-፲፮)፡፡
ካህናት ይህን ዂሉ የማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ በትረ ክህነት የጨበጡ፣ በእግዚአብሔር የተመረጡ፣ አጋንንትን የሚቀጡ፣ ኀጢአትን እንደ ሰም አቅልጠው የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የእግዚአብሔርን መንጋ ምእመናንን ይጠብቃሉ፡፡ በለመለመ መስክ በጠራ ውኃ ያሠማራሉ፡፡ ማለት ያልተበረዘ ያልተከለሰ ከሐዋርያት የተገኘ ንጹሕ ወንጌልን ያስተምራሉ፡፡ ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ እነሆ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› እያሉ ሰውን ዂሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥትና ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያቀርቡ የድኅነት በር ናቸው (ዮሐ. ፩፥፳፱)፡፡
የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ፤ የሙሴ መንፈስ በኢያሱ እንዳደረ የሐዋርያት መንፈስ ያደረበት እግዚአብሔር የመረጠው የገለጠው ክህነት በአበው ጳጳሳት ቅባትና ጸሎት አማካይነት ይታደላል፡፡ አባቶች ጳጳሳት በአንብሮተ እድ ባርከው በንፍሐት እፍ ብለው በእግዚአብሔር ስም ክህነቱን ካላሳደሩበት በቀር ማንም ካህን መኾን አይችልም፡፡ እግዚአበሔር የሾመው ሐዋርያትን ብቻ አይደለም፤ ጳጳሳትንም የሾመው እርሱ ነውና፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ዂሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡ ጌታችን ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት ዂሉ በሰማይ የታሰረ ይኾናል፡፡ በምድርም የምትፈቱት ዂሉ በሰማይ የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያት የማሰር የመፍታት ሥልጣን እንደ ሰጣቸው በማያሻማ ኹኔታ በቅዱስ ወንጌል ተቀምጧል (ማቴ. ፲፰፥፲፰፤ ሉቃ. ፳፬፥፶፤ ዮሐ. ፳፥፳፪-፳፬፤ ሐዋ. ፱፥፲፯፤ ፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፭)፡፡
ስለዚህ ክህነት በእግዚአብሔር ጥሪ የሚፈጸም በእግዚአብሔር ሰጭነት የሚከናወን መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሥልጣን እግዚአብሔር መጀመሪያ የመረጠው ቅዱሳን ሐዋርያትን ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ካህናት ሐዋርያት ናቸው፡፡ የመረጣቸው፣ የጠራቸው፣ የሾማቸውም እርሱ ራሱ ነው (ማቴ. ፲፥፩)፡፡ ሥልጣኑን ያገኙት ከባለቤቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሥልጣነ ክህነት ሐዋርያት ተቀብለውት የሚቀር ሳይኾን ለተመረጡ ሰዎች ሊሰጡት እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው (ሐዋ. ፩፥፳፬)፡፡ በዚህ መልኩ የሚሾሙ ካህናት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሐዋርያት ተከታዮች ሐዋርያት ናቸው፡፡ ለእነርሱ የተሰጠውን ሥልጣን ማመን፣ መቀበልና መጠቀም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ በየፌርማታው ነቢይ ነኝ ካህን ነኝ ከሚሉት መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ክህነት ዝም ብሎ በየመንገዱ የሚታፈስ አይደለም፡፡ ማንም እየተነሣ የሚዘግነው የእድር ቆሎም አይደለምና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡