የከርቤ ኮረብታ

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

መስከረም ፳፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ከሕያው የመዐዘኑ ራስ ድንጋይ

ታንፆ በጽኑዕ ዐለት ላይ

ተዋጅታ በበጉ ደም ቤዛ

ሺህ ዓመታት ሺህ አቀበት ተጉዛ

እልፍ መንጋ እልፍ ደም ጓዟ

በቅዱሳኖቿ ሕይወት የሚያበራው ወዟ

በጻድቃኖቿ ሞት የምትሸት የከርቤ መዓዛ

ምጽአት ከሚያስረሳ ከዚህ ዓለም ግርዶሽ

                       ከምኞት… አምሮት … አሳድዶሽ

    ልጆቿን ሰብስባ በፍቅረ ቢጽ ጸጋ

      ከጨለማው ራስ በጽድቅ ‘ምታወጋ

በእንባ ጎርፍ በስደት ላባቸው

በጻማ ገድል በደም እሳታቸው

በሥጋ ኮረብታ በአጥንት ቅጥራቸው

ሞት የገደላቸው… ሞት የማይዛቸው

የሚነዱ መብራት መቅረዝ ሰንደቃቸው

ሞታቸው ክብራቸው… ክብራቸው ጌታቸው

 መዐዛ ቅዱሳን…ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

   ለቃል… በቃል የምትቀረጽ ምርጥ ዕቃ

   ከአማናዊው ብርሃን ብርሃኗን ፈንጥቃ

በንስሐ ከርቤ አጣብቃ

በመዐዛ

ወዟ

ለሙሽራዋ…

ጌታዋ

ታቀርባለች… በአኮቴት

ሃሌ ሉያ! በእልልታ!

                       መዐዛ ቤተ ክርስቲያን የከርቤ ኮረብታ!