የእግዚአብሔር ሠረገላዎች (መጽሐፈ ስንክሳር)
ኅዳር ፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ለቅድስት ሥላሴ ምስጋና ይድረስና እኛ የሰው ልጆች በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ እንዲረዱን ቅዱሳን መላእክትን ፈጥረውልናል፡፡ (ዕብ.፩፥፲፬) በዚህ ዓለም ስንኖር ተስፋ ከሚሆነን፣ ፍርሃትን እንድናስወግድ ከሚረዳን የአምላክ ስጦታ መካከል የነገረ መላእክት ነገር ነው፡፡
ቅዱሳን መላእክት አይደለም እኛን በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርን የሰው ልጆችን ቀርቶ ፀሐይን፣ ከዋክብትን፣ አዝርእትን፣ አትክልትን፣ እንስሳትን፣ አራዊትን፣ ከሰማይ በታች ከምድር በላይ የተፈጠረውን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ መቼም የሚጠብቀን አምላክ እንደማይተኛና በሥራችን ሁሉ፣ በዚህ ዓለም ያለ የነፍስም የሥጋም እንቅፋት እንዳይመታን ይጠብቁን ዘንድ ምድራውያን ያይደሉ ሰማያውያን ጠባቂዎች አገልጋዮቹን ቅዱሳን መላእክትን እንደሚያዝልን ከማወቅ በላይ ምን የሚያስደስትና ፍርሃትን የሚያስወግድ ነገር ይኖራል፡፡ (መዝ.፺፥፲፩)
እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን በዕለተ እሑድ ሲፈጥር በነገድ ፻ (አንድ መቶ) በአለቃ ፲ (ዐሥር) አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ሦስቱ ሰማያት የሚባሉትም ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር ናቸው፡፡ ኢዮር ዐራት፣ ራማ ሦስት፣ ኤረርም እንዲሁ ሦስት ከተሞች አሏቸው፡፡ በአጠቃላይ የመላእክት ከተሞች ዐሥር ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ኪሩቤል ይገኙበታል፤ አለቃቸው ኪሩብ ሲባል ሰማያቸው ኢዮር ከተማቸው ሁለተኛው ነው፡፡
‹‹ከሩቤል›› የሚለው ስም የነገደ መላእክቱ ሁሉ (የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ) እንጂ፣ የአንዱ መልአክ መጠሪያ ‹‹ኪሩብ›› ነው፡፡ ኪሩብ ማለት መልአክ፣ የመልአክ ስም፣ ሥዕሉ ምስሉ ነገዱ አራት አራት ገጽ ካላቸው ከአራቱ ጸወርተ መንበር አንዱ ሲሆን፣ ፍችው መሸከምን፣ መያዝን ይገልጣል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፭፻፵፬)
ነገደ ኪሩቤል የካህናት የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ ሁለተንተናቸው በዓይን የተመላ ነው፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል እንደነገረን ለእያንዳንዳቸው አራት አራት ፊት አላቸው፡፡ (ሕዝ. ፩፥፮) ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከፊት ወደ ኋላ ሳይንቀሳቀሱ አራቱን አቅጣጫ መመልከት ይችላሉ፡፡ ሲሔዱም እንዲሁ እግዚአብሔር ወደ አዘዛቸው ቀጥ ብለው፣ እንደ ሰው አቅጣጫ መቀየር ሳያስፈልጋቸው መንጎድ ይችላሉ፡፡
ኪሩቤል መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው፤ (ወእሉ እሙንቱ ሠረገላሁ ለእግዚአብሔር) እንዲል፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል እንደተመለከታቸው ዙፋኑን ተሸክመው እግዚአብሔር ለወደደው ይገለጻሉ፡፡ እነርሱንም፡- ‹‹ኪሩባውያን አፍራሱ፤ ፈረሶቹ ናቸው›› ሲል መጽሐፍ ይገልጻቸዋል፡፡ ዙፋኑን ተሸከሙ ሲባልም እግዚአብሔርን የመሸከም ኃይል ኑሯቸው ከወዲያ ወዲህ ይዘው መራመድ ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መገለጽ ሲፈቅድ ዙፋኑን እንደፈቀደ (በወደደው) ተሸክመው ስለሚታዩ ነው፡፡
መሐሪና ይቅርባይ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ኪሩቤልን ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ የቅርብ ባለሟሎቹ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ ለእኛ ለሰው ልጆችም ሆኑ ለመላው ፍጥረት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚለምኑልንን ኪሩቤልን በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹላቸው እና በኅዳር ስምንት ቀንም መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘውናል፡፡
የቅዱስ እግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ኪሩቤል በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ከመለያየት ይልቅ ሰውን ሁሉ በፍቅርና በትዕግሥት የምንሸከምበትን ኃይሉን ያድሉን ዘንድ፣ ከአምላካችንም ያስታርቁን ዘንድ በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘላለሙ አሜን!
ምንጭ፡- መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር፣ የአንቀጸ ብርሃን አንድምታ ትርጓሜ /መ/ር ኃይለ ማርያም ዘውዱ / ፣ ምሥጢረ ሰማይ / መ/ር ማዕበል ፈጠነ/