‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› (መዝ.፴፫፥፯)
ቀሲስ ሀብታሙ ተሾመ
ሰኔ፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ልበ አምልክ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ጠባቂ መልአካቸው በዙሪያቸው ሰፍሮ የሚጠብቃቸው መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ሰዎች ከአራቱ ባሕሪያተ ሥጋ የተፈጠሩ በመሆናቸው ሥጋዊ አካል የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ እንዲሁም የሚጨበጡ ሲሆኑ ቅዱሳን መልአክ በሰዎች ዙሪያ ይሰፍራሉ ሲባል ግን ረቂቀ በሆነ አካል እንጂ እንደ ሰው በሚጭበጥ ሚዳሰስ ሥጋዊ አካል አይደለም፡፡ ሰዎች የሚጠበቁት በሦስት በኩል ነው፤ አንደኛው በእግዚአብሔር መለኮት ሁለተኛው በቅዱሳን መላእክት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ በሰው ነው፡፡ የሰው ጥበቃ በሚታይ አካለዊ መልኩ ነው፤ የመለኮት እና የመላእክት ጥበቃ ግን በረቂቅ አካል እንጂ እንደ ሰው በሚታይ ሥጋዊ አካል አይደለም፡፡
በየዓመቱ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል የሚታሰበው በዓል የመልአከትን ጥበቃ መሠረት ያደረገ ነው፤ የመታሰቢያ በዓሉም በደመቀ ሁኔታ ይከበራል፤ በአንደኛነትም የሚከበርበት ምክንያት እስክንድርያ በምትባል ከተማ አክላወ ባጥራ የተባለች ንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ባሠራችው ታላቅ ምኵራብ በየዓመቱ ሰኔ በባተ በዐሥራ ሁለት ቀን በምኵራቡ ሕዝቡ ተሰብስቦ ታላቅ ክብረ በዓል ይደረግ ነበር፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እና ቅዱሳን ባለሟሎቹ በሚዘከሩበት ዕለት በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል ለሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣዖት ብዙ ፍሪዳዎችን አርደው ያከብሩት ነበር፤ ይህ የሚደረገው በዓሉ በሚከበርበት በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን ነበር፡፡
አባ እለእስክንድሮስ እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣዖት ሲገብሩ ኖረዋል፡፡ ይኸውም ሦስት መቶ ዓመተ ምሕረት ተፈጽሞ በአራተኛው ምዕት ዓመት አባ እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ፣ ጻድቅ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት አስፋፍተው ጣዖቱን እንዲሰበር በአዘዙ ጊዜ ሌሎቹ ሰዎች ‹‹እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል፤ እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል፤ ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም›› አሉት፡፡ አባ እለእስክንድሮስም ‹‹ይህ ጣዖት የማይጠቅም ነው፤ እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል፡፡ ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ፤ ይኸውም ጣዖቱን እንድንሰብረው፣ ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ በመላእክት አለቃ በሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው፡፡ እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን፡፡ የሚታረዱትም ላሞችና በጎች፣ ለድኆችና ለጦም አዳራዎች፣ ለችግረኞችም በከበረው መልአክ ስም ምግብ ይሁኑ፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለሆነ ስለ እኛ ይማልዳልና›› በማለት ገሥፆና አስተምሮ እንዲሁም ከስሕተታቸው መልሶ ትእዛዙን እንዲቀበሉ አደረጋቸው፡፡ ያንንን ምኩራብ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አደርገው ሰይመው በዚያ ዕለት ክብረ በዓል አድረጉ፤ እስላሞችም እስከ ነጉሡበት ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ ቢያፈርሱትም ያ በዓል ተሠራ፤ እስከ ዛሬም ጸንቶ ይኖራል፡፡
የከበረ የመልአክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው የከበረ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን በተለይም በሰኔ እና በኅዳር ወር በይበልጥ ያከብር ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለ ጸጋ ሰው ነበረ፡፡ ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያዘክርበት ጊዜ ያቃልለውና ለድኆች በመራራቱም ይዘባበትበት ነበረ፡፡ የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክቡር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ምጽዋት ታቀርብ ዘንድ ሚስቱን ከአዘዛት በኋላ ዐረፈ፤ ገንዘው ቀበሩት፡፡
ሚስቱም ፀንሳ ስለነበር የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ በያዛት ጊዜም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሆና ‹‹የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ፤ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ›› ብላ ጸለየች፤ ይህንንም ጸሎት በአቀረበች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው፤ ‹‹ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለ ጠጋ፣ ገንዘብና ሀብት፣ ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዟል›› አለው፡፡
ባለ ጸጋውም በቤቱ በአልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ፡፡ ይህንን በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ውስጥ ተዋጠ፡፡ በዚህም ምክንያት ያ ባለጸጋ ሕፃኑን የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ በቅዱስ ሚካኤል ይጠብቀውና ያስጠብቀው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ያ ባለጸጋ ‹‹የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ፤ እኔም እየመገብሁና እያለበስሁ አሳድገዋለሁ፤ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ ልጁን ስጭኝ›› አላት፡፡ ሴትዮዋም ይህንን ጉዳይ ከባለጠጋው በሰማች ጊዜ ችግሯ መፍትሔ ስላገኘ እጅግ ደስ ብሏት ልጅዋንም ሰጠችው፡፡ እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት፡፡ ያ ባለጸጋ ሰውም ልጅዋንም ወሰደው የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው፡፡
ከዚያም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አድርጎ ዘጋበት፤ እስከ ባሕርም ተሸክሞ ወስዶ በባሕር ጣለው፡፡ በአምላክ ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ወደ ወደቧ እስከ ሚደርስ በባሕሩ ላይ ለሃያ ቀን መንገድ ያህል ተንሳፎ ቆየ፡፡ በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቀው ሰው ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ ባየ ጊዜ ሣጥኑን ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው፡፡ ያንን ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ሲያስብ ቆይቶ ሰውየው ወደ ባሕሩ ይሔድ ዘንድ አማላካችን አግዚአበሔር በልቡናው ስለአሳሰበው ወደ ባሕሩ ሔደ፤ አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰውም አገኘ፤ ዓሣ አጥማጁንም ‹‹መረብህን በኔ ስም ጣል፤ ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡
አጥማጁም በታዘዘው መሠረት መረቡን ሲጥል ታላቅ ዓሣ ከመረቡ ገባ፤ ለዚያም ዓሣ ዋጋውን ሰጥቶ ዓሣውን ይዞ ወደ ቤት ሔደ፤ ለራትም ይሆን ዘንድ አረደው፤ በሆዱም ውስጥ የበር መክፈቻ ቁልፍ አገኘ፡፡ በልቡም ‹‹ይህ መክፍቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን?›› ሲል እራሱን ጠየቀ፡፡ በዚያ ቁልፍ ሣጥኑን ሲከፍተው በውስጡም ታናሽ ብላቴና አገኘ፡፡ ያ ሰው ልጅ የሌለው ስለነበር በታላቅ ደስታ ተዋጦ አምላኩን አመሰገነ፤ ሕፃኑንም በእንክብካቤ በመልካም አስተዳደግ ሁኔታ አሳደገው፤ ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ፡፡
ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጠጋ ተነሥቶ ልጁ በሣጥን ወደተገኘበት ሀገር ሲሔድ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ፡፡ ያ ባለጸጋ በግ ጠባቂውን ‹‹እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን? ኪራዩንም እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ በግ አርቢውም ‹‹እንዳልክ ይሁንና እደር›› አለው፡፡ ባለ ጠጋውም በዚያ በአደረበት ጊዜ ራት በሚቀርብም ጊዜ በግ ጠባቂው ሕፃኑን ‹ባሕራን› ብሎ ጠራው፡፡ ባለ ጠጋውም ሰምቶ ‹‹ልጅህ ነውን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ በግ ጠባቂውም ‹‹አዎን፤ ታናሽ ሕፃን ሆኖ ሳለ ከባሕር ስለአገኘሁት እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው›› አለው፤ ባለ ጠጋውም ‹‹በምን ዘመን አገኘኸው?›› አለው፤ እርሱም ‹‹ከሃያ ዓመት በፊት›› ብሎ መለሰለት፤ ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን ዐውቆ እጅግ አዘነ፡፡
በማግሥቱም ያ ባለጸጋ ሰው በሰይጣናዊ እሳቤ በግ አርቢውን ‹‹ከምኖርበት ሀገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስላለ እንድልከው ልጅህን ይታዘዘኝ ዘንድ የአንተን መልካም ፍቃድ እሻለሁ፤ የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው፡፡ በግ አርቢውም ያንን ሕፃን ‹‹ልጄ ባሕራን ሆይ፥ ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ይፈልጋል፤ ወደ ቤቱም ደረሰህ በሰላም ትመለሳለህና ሒድ›› አለው፡፡ ያን ጊዜም ባለ ጸጋው ‹‹ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፤ ማንም ዐይወቅ›› በማለት በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎና አሽጎ ለባሕራንም ሰጠው፤ ለመንገዱም የሚሆነውንም ስንቅ ሰጠው፡፡ ባሕራንም ሲጓዝ ሰንብቶ አንዲት ቀን ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው?›› አለው፡፡ ‹‹ከአንድ ባለ ጸጋ የተጻፈችውን ደብዳቤ ወደ ባለጻጋው ቤት ለማድረስ ነው›› አለው፤ እርሱም ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፤ ባሕራንም ስለ ፈራው ሰጠው፡፡
በዚያን ጊዜም መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደምስሶ በንፍሐት ለውጦ ‹‹ይቺን ደብዳቤ ይዞ የመጣውን ባሕራንን ደብዳቤዋን ካነበብክ በኋላ ልጄን አጋቡት፡፡ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን፣ ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና፤ የፈለገውንም እንዲያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁ፤ እኔ ብዙ እዘገያለሁ አትጠብቁኝ፡፡›› መልአኩ ደብዳቤዋን አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ‹‹ወደ ባለ ጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፤ በጉዞህም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፤ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ›› አለው፡፡
ባሕራንም ‹‹እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ›› አለ፡፡ ባሕራንም ወደ ባለ ጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፡፡ በአነበባት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት ስለአገኘና ስለ ዐወቀ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለ ጸጋውን ልጅ አጋቡት፤ ዐርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ባለ ጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሆኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ‹‹ይህ የምሰማው ምንድነው›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹‹ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህን ስለአጋቡት እነሆ ለዐርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ አንተ እንዳዘዝከው ሰጥተውታል›› አሉት፤ ይህንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ ሞተ፡፡
ባሕራንም የተገለጠለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እንደ ሆነና ሊገድለው የሚሻውን የባለ ጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ሆነ ተረዳ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ፤ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው፡፡ ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያገለገለ ኖረ፡፡ በጎ ሥራዎችን እየሠራ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል አዳኝነት ከመገደል ተጠብቆ የዘለዓለም ሕይወትን ወረሰ፡፡
መድኃኒታችን በተነሣባትም ቀን ይህ ክቡር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከውስጠኛው መጋረጃ ውስጥ ገብቶ በክብር ባለቤት ፊት ‹‹እውነት ስለ ሆነ ቃል ኪዳንህ በምድር መታሰቢያዬን የሚያደርጉትን ትምርልኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ሆይ! እኔ አገልጋይህና መልእክተኛህ ከቸርነትህ እለምናለሁ፤ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና›› እያለ ጸለየ፤ የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹የመንፈሳውያን ሰማያውያን መላእክት አለቃቸው ሚካኤል ሆይ! መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ መሸከም እንደምትችል ከሲዖል ሦስት ጊዜ በክንፎችህ ተሸክመህ እንድታወጣ እነሆ እኔ አዝዤሃለሁ፡፡›› ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት የበዓሉን መታሰቢያ ከሚያደርጉት በክንፎቹ ተሸክሞ የእሳቱን ባሕር አሳለፋቸው፡፡
ስለዚህም የዚህን የታላቁን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የበዓሉን መታሰቢያ በማድረግ በተራዳኢነቱና በአዳኝነቱ እንድንኖር፣ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ሁሉም ይጠብቀን ዘንድ፣ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይ ዘንድ፣ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፣ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፣ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፣ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍት ይሰጥ ዘንድ፣ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላምና በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፣ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፣ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፣ የክርስቶስ ወገኖች የሆኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ እንለምነው፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚለምንልን ቅዱስ ሚካኤል ለዘላለሙ ይጠብቀናል፡፡
ዳግመኛም በሰኔ ፲፪ እግዚአብሔርን የሚፈራ አስተራኒቆስ የሚስቱ የቅድስት አፎምያ የዕረፍቷ መታሰቢያ በሆነበት ቀን የቅዱስ ሚካኤል በዓል ይደረጋል፡፡ እርሷም የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባሏን የለመነችው ናት፡፡ እርሱም አሠርቶ ሰጣትና በቤቷ ውስጥ በክብር አኖረችው፡፡ ባሏም ከዐረፈ በኋላ ያዘዛትን መሥራት ጀመረች፡፡ ሰይጣን ግን ቀናባት፡፡ በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋር ተነጋገረ፡፡ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ አዝንልሻለሁ፤ እራራልሻለሁም፡፡ ገንዘብሽ ሳያልቅ፣ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ፡፡ ባልሽም መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል፡፡ ምጽዋትም አይሻም፡፡›› አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ ‹‹እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገናኝ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ፡፡ ርግቦችና መንጢጦች እንኳን ሌላ ባል አያውቁም፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህ ሊሆን እንዴት ይገባል?››
ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርአያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት፡፡ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ፤›› እርሷም የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰኔ ፲፪ ቀን የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት እያደረገች ባለችብት ጊዜ ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ ‹‹አፎምያ ሆይ! ሰላም ላንቺ ይሁን! እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፡፡ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምእመን ሚስት ትሆኚ ዘንድ አዞሻል፡፡›› ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ፤ እንደ አብርሃምና ያዕቆብ እንደ ዳዊትም እንደነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገባ፤ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ይጠቃቅስላት ጀመረ፡፡
ቅድስት አፎምያም መልሳ ‹‹አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋር ወዴት አለ? የንጉሥ ጭፍራ የሆነ ሁሉ የንጉሡን ማኅተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድም›› አለችው፡፡ ሰይጣኑም ይህንን በሰማ ጊዜ መልኩ ተለወጠና አነቃት፡፡ እርሷም ወደ ከበረው መልአክ ወደ ሚካኤል ጮኸች፡፡ ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት፡፡ ያንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ፤ ሰይጣኑም ጮኸ፤ ‹‹ማረኝ፤ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ፤ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና›› እያለ ለመነው፤ ከዚያም ተወውና አባረረው፡፡
የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልም ‹‹ብፅዕት አፎምያ ሆይ! ሒደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ፡፡ አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለያለሸ፤ እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል፡፡›› ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት፤ ወደ ሰማያትም ዐረገ፤ የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋለ ወደ ኤጲስ ቆጶሱና ወደ ካህናቱ ሁሉ ላከች፡፡ ወደ እርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ሁሉ አስረከበቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች፤ የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንሥታ ታቅፋ ሳመችው፤ ያን ጊዜም በሰላም ዐረፈች፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንን የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ይጠብቀን፤ ለዘለዓለሙ አሜን!
ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፪ ቀን እና መጽሐፍ ቅዱስ