የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተራዳኢነት
ዲያቆን ዳዊት አየለ
ነሐሴ ፲፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ምልጃ ማለት “ልመና (መለመን)፣ አስታራቂነት” ሲሆን አንዱ ስለሌላው የሚያቀርበው ልመናና ጸሎት ነው፤ በቤተ ክርስቲያናችንም ከሚደረጉ የጸሎት ዓይነቶች አንዱ ምልጃ (ጸሎተ አስተብቊዖት) ወይም ስለሌላው የሚቀርብ የጸሎት ዓይነት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፯፻፸፭)
አንድ ሰው ወዳጁን በአንድም በሌላም ካሳዘነው ወይም ካስቀየመው ያንን ወዳጅ ፊት ለፊት ቀርቦ ለማናገር ዕፍረት ወይም ፍርሃት ሊያድርበት ይችላል፤ በዚህም የተነሣ መበደሉን፣ ማስቀየሙን፣ ማሳዘኑን ሲረዳ እና በፈጸመው ስሕተት ሲጸጸት እንዲያስታርቀው አማላጅ ይልካል። አማላጅም የሚልክበት ትልቁ ምክንያት ያስቀየመውን አካል ከማክበሩ የተነሣ በቀጥታ መሄዱን እንደ እፍረት በመቁጠሩ (ስለሚያፍር) ነው፤ ሌላው ደግሞ ያስቀየመውን አካል በመፍራት “እንዴት አድርጌ ዓይኑን አያለው፤ በፊቱስ እንዴት እቆማለው” በማለት የሚልከውን አማላጅ በተበዳዩ ዘንድ መስማት፣ መደመጥ፣ መወደድ ያለው መሆኑን አረጋግጦ መርጦ ይልካል። በዚህም መሠረት እኛ ኃጢአተኞች በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያላቸውን ባለሟሎቹ የሆኑ ቅዱሳንን እንዲያማልዱን፣ እንዲያስታርቁን፣ እንለምናቸዋለን፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ መልዕልተ ፍጡራን ወላዲተ አምላክ ናትና ይበልጥ እንማጸናታለን።
ምልጃ በሚከናወንበት ሂደት ውስጥ ሦስት አካላት ይኖራሉ፤ እነርሱም፦
አማላጅ፦ ማማለድ ለፍጡራን ባሕርይ የሚስማማ የትሕትናና የፍቅር ሥራ ነው፤ በመሆኑም ቅዱሳን ሁል ጊዜ ስለ ኃጥአን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ያማልዳሉ። በእነርሱ ልመናም ጌታችን መድኃኒታችን ይቅርታን ምሕረትን ያደርጋል፤ ዘወትርም ይሰማቸዋል። የሚማልዱትም ራሳቸውን (ሕይወታቸውን) ለኃጥአን አሳልፈው እስከመስጠት ድረስ ነው። “ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ ወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጥአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁን ይህን ኃጥአታቸውን ይቅር በል። ያለበከዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ። ”(ዘፀ.፴፪÷፴፩-፴፪ ) ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም፦ “ሕዝቡ ይቆጠር ዘንድ ያዘዝኩ እኔ አደለሁምን? የበደልኩና ክፉ የሠራው እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፥ ነገር ግን ይቀሠፍ ዘንድ በሕዝብህ ላይ አትሁን” ብሏል። (፩ኛ ዜና ፳፩÷፲፯) በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥ ጭንቀት አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፥ አልዋሽም፥ ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፥ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና።” (ሮሜ ፱÷ ፩ – ፫) የተናገረውን ስንመለከት ቅዱሳን ራሳቸውን በፍቅር ሆነው አሳልፈው በመስጠት ስለ እኛ እንደሚማልዱ (እንደሚለምኑ) እንረዳለን።
ተማላጅ፦ ተማላጅ ማለት “ምልጃ፣ ተቀባይ የሆነ፣ የሚለመን” ማለት ሲሆን ፍጥረታትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የሚመግባቸው የሚገዛቸው የሁሉ ባለቤት “ሁሉ በእርሱ የሆነ” (ዮሐ.፩÷፫) እግዚአ ዓለማት አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። ተማላጁ እግዚአብሔር እንደ አማላጆች ብዙ አይደለም፤ አንድ ነው። አንድ እግዚአብሔር ስንልም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው። ሦስቱ አካላት በአንድ ጌትነት፣ በአንድ ሥልጣን፣ በአንድ ክብር፣ በአንድ መለኮት፣ በአንድ ፈቃድ፣ በሰማይና በምድር የሚገኙ ፍጥረታትን ልመና ተቀብለው የፈቃዳቸውንና የቸርነታቸውን ሥራ ይሠራሉ። ቅዱሳን ያማልዳሉ ሲባል እግዚአብሔር ጨካኝ፥ ቅዱሳን ደግሞ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰዎች የሚያዝኑ ደጋጎችና ርኅሩኅ ሆነው አይደለም። እንደ እግዚአብሔር ያለ ቸርና ርኅሩኅ ማንም የለም፤ የቅዱሳን አማላጅነት ድንቅና ጥልቅ የሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት የሚሠራበት (የሚገለጥበት) ስለሆነ ነው።
የሚማለድለት፦ የሚማለድለት አካል ገና ድኅነታችንን ያልፈጸምን በምድር የምንኖር ኃጢአት የሠራን ሰዎች ስንሆን፣ በደላችንን አምነን፣ ተጸጽተን፣ ንስሓ በመግባት በአማላጅነታቸው የምንማጸን ነን። አንድ ሰው በቅዱሳን ምልጃ ለመጠቀም ንስሓ መግባት እንዳለበት የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እንዲህ ይላል፤ “አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ እጅ ወደ እኛ የላከውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን። የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን” (ኤር. ፵፪ ÷ ፭ – ፮ በማለት እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ ሆነው አማላጃቸውን ኤርምያስን ሲናገሩ ተጽፎ እናገኛለን። ፣ ነገረ ቅዱሳን-፩ በቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው፣ መድሎተ ጽድቅ ቅጽ-፩ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ)
አማላጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፤ ይህም ይታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር አቤሜሌክን ወደ አብርሃም ልኮታል፤ “አብርሃም ነቢይ ነው፥ ስለአንተ ይጸልያል፥ ትድናለህም” የሚለው የመጽሐፍ ክፍል ምስክር ነው፤ (ዘፍ.፳÷፯) ከስጦታዎች ሁሉ ደግሞ ልዩና የፍቅር፣ የመስቀል ሥር ስጦታችን፣ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ምሉአ በኩለሄ የሆነ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠባት፣ እናታችን፣ እመቤታችን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ በሁለት ወገን ድንግል፣ ንጽሕት ወብርህት፣ ወላዲተ አምላክ፣ ሰአሊተ ምሕረት፣ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለዓለም አሳልፎ ከመስጠቱ አስቀድማ እራሷን ለእግዚአብሔር “…እነሆኝ፥ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ…” በማለት የሰጠች፣ በቅዱስ ሐዋርያ ዮሐንስ እጅ የተቀበልናት ንጽሕተ ንጹሓን ማርያም ነች። (ሉቃ.፩÷፴፰)
ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የተተነበየውን ትንቢት የሚያህል ትንቢት የተተነበየላትና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የተጻፈላት ሴት የለችም። ስለ እርስዋ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ብዙ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል፤ ሐመረ ኖኅ፣ ሰላማዊት ርግብ፣ የአብርሃም ድንኳን፣ የሲና ሐመልማል (ዕፀ ጳጦስ)፣ ጽላተ ሙሴ፣ የኢያሱ የምስክርነት ሐውልት፣ የኤልያስ የወርቅ መሶብ፣ በትረ አሮን፣ ፀምር ዘጌዴዎን፣ ደብር ነዋኂት ዘዳንኤል (የዳንኤል ረጅም ተራራ)፣ የኖኅ የቃል ኪዳኑ ምልክት (ቀስተ ደመና)፣ ዕፀ ሳቤቅ፣ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያያት መሰላል፣ የኤልሳዕ ማሰሮ፣ የታጠረች ተክል የታተመች የውኃ ምንጭ እና ሌሎች ምሳሌዎች በሰፊው የተነገሩላት የተጻፉላት የተመሰሉላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። በቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችን መጻሕፍት ውስጥ ክብሯን የሚያጎሉ አገላለጾችና ተመስጦዎች እንደ ምን የበዙ ናቸው! ቤተ ክርስቲያን እርስዋን ለመጥራት የምትጠቀምባቸው ቅጽል ስሞችዋና ውዳሴዎቿ ምንኛ ድንቅ ናቸው! በመጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ገላጭነት በቅዱሳን የተነገሩ ምስጋናዎቿስ እንደምን ድንቅ ናቸው! እርሷ የሁላችንም እናት ናት፤ እርስዋ ከንጉሡ በስተቀኝ የቆመችው ንግሥት ናት፤ እርሷ ዘለዓለማዊ ድንግል ናት፤ እርሷ የእግዚአብሔር ጸጋ የሞላባት ንጽሕት ቅድስት ድንግል ናት፤ እርሷ የሰው ሁሉ ረዳትና ርኅሩኅ እናት ናት፤ እርሷ የብርሃን፣ የምሕረት፣ የድኅነትና የአማናዊው ወይን እናት ናት። (መጽሐፍ ቅዱስ፣ ድንግል ማርያም በአቡነ ሽኖዳ አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው፣ ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት በማኅበረ ቅዱሳን፣ ውዳሴ ማርያም)
እመቤታችን ፍጽምት ንጽሕት እንዲሁም እጅግ ትሑት ነች፤ ከፍጥረት ሁሉ ተለይታ ፈጣሪዋን ለመውለድ ወላዲተ አምላክ ለመሆን የተመረጠችበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ትሕትናዋ ነው። የአምላክ እናት እንደምትሆን ተነግሯት እንኳን እመቤታችን “የባሪያይቱን መዋረድ ተመልክቷልና” በማለት በትሕትና ነበር ምስጋናዋን ያቀረበችው፤ (ሉቃ.፩÷፵፰) ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ “እርሷ በእግዚአብሔር ዓይን በታየ የቅድስና ውበት የተሞላች ነበረችና በእርሷ ንጹሕ ማሕፀን ሊያድር ወደደ፤ እንደ ድንግል ማርያም ራሱን ዝቅ ያደረገ ትሑት ማንም የለም” ይላል።
ቅዱስ ኤፍሬም “በትሕትና የተናገርሽ ተራራ ሆይ…” ብሎ ያመሰገናት ይህች ድንግል እንደ ተራራ ከፍ ያለች ስትሆን ራሷን እንደ ሸለቆ ዝቅ አድርጋ “እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንደምን ይደረግልኛል” ብላ በልብዋ አሰበች፤ በዚህ በእናታችን ትሕትና እጅግ እንደነቃለን፤ ‹‹ድንግል ሆይ እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንምን አይደረግልሽም?›› የተመረጥሽው የሰማይና ምድርን ፈጣሪ ልትወልጂ አይደለም ወይ? እሳተ መለኮትን ተሸክነመሽ፣ ሰማይና ምድር የማይችሉትን ችለሽ እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንደምን አይደረግልሽም? እያልንም እናመሰግናታለን። እመቤታችን ቅድስት ማርያም ጸጋን የተሞላች በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል የሆነች፥ ልጇ አምላኳ አምላኳ ልጇ የሆነላት ባለሞገስ ነችና በምልጃዋ አምነው በንስሓ ሆነው ለሚማጸኗት ከእርሷ የተሻለ አማላጅ ከወዴት ይገኛል። መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሰላምታ ሲሰጣት “ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ” ብሏታል፤ (ሉቃ.፩÷፴) ይህም ማለት ክብር፣ ሞገስ፣ መለመን የማስታረቅ ኃይል አግኝተሻል ሲል ነው። በዚህም መሠረት እመቤታችን ድንግል ማርያም ለማማለድ የታመነች ናት፤ እግዚአብሔር ዓለምን ኃጢአት በወለደው ንፍር ውኃ ሲያጠፋት ሸሽጎ ያስቀራት ንጽሕት የኖኅ ርግብ ነችና ዛሬም በኃጢአት ገመድ ታሥረው ምሕረትን ለሚሹ በምልጃዋ የምሕረትን በር የምታስከፍትልን እናታችን ናት።
(ቃና ዘገሊላ እና የብርሃን እናት በመምህር ሄኖክ ኃይሌ፣ ውዳሴ ማርያም፣ የሉቃስ ወንጌል ትርጓሜ)
ስለ እመቤታችን ምልጃ ምስክር ሆነው በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በግልጽ ከተቀመጡ ክፍሎች ዋነኛው በፍቁረ እግዚእ ወንጌላዊው ዮሐንስ የተጻፈው የዶኪማስ የሠርግ ቤቱ ታሪክ ነው፤ በዚህ ሠርግ ቤት ጌታችን ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቶ ነበር። “የወይን ጠጃቸውም ባለቀ ጊዜ እናቱ ጌታችን ኢየሱስን፥ ‘የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም’”(የሐ.፪÷፫) በማለት ወይኑ እንዳለቀባቸው ማንም ሳነይነግራት የፊትን መጥቆር የልብን ኀዘን የምትረዳ ከዓይን ጥቅሻ ፈጥና የምትደርስ እናታችን እመቤታችን፣ ወሳኝ በሆነ ሰዓት ላይ ነቢዩ ኢሳይያስ “ፈጣን ደመና” ብሎ የጠራት ፈጣኗ ደመና ለቃና ሙሽሮችም ፈጥና ነበር የደረሰችላቸው፣ ከውርደትም ያዳነቻቸው። (ኢሳ.፲፱÷፩) ይህን የእመቤታችንን ፈጣን ምልጃ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፤ “እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሰው ወገን የሰው ችግር ቶሎ የሚገባት ቶሎ የሚታያትና የሚሰማት ርኅርኅት ናት። የሰዎቹ ችግር ገብቷት ለልጇ ነገረችው”። ችግራቸውን ፈጥና የተረዳች እመቤታችን አሁንም ልጇን ፍጹም ትሑት በሆነ መንገድ ነበር የጠየቀችው እንጂ ልጄ ነው ብላም አላዘዘችም፤ “ባለ ውለታህ ነኝ” ብላም ማሳሰቢያ አልሰጠችም፤ ብቻ “ወይን እኮ የላቸውም” ብላ እጅግ በሚጣፍጥ ትሕትና ለመነችው፤ ግሩም ነው! ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልመናዋን ሰምቶ ውኃን ወደ ወይን ለውጦላቸው የመጀመሪያውን የአምላክነት ምልክት በሠርጉ ቤት አድርጓል፤ በዚህም የእመቤታችን ምልጃ በጎላ በተረዳ ነገር ታውቋል። (ቃና ዘገሊላ በመምህር ሄኖክ ኃይሌ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ)
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነቷና ተራዳኢነቷ በብዙ መልኩ ዛሬም ድረስ ያልተለየን የዘለዓለም ቃል ኪዳን የተገባላትና ቃል ኪዳኗም ለዘለዓለም የሚሠራ ነው፤ “ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” ብሎ ለምርጦቹ ቃል ኪዳን የሰጣቸው አምላክ (መዝ.፹፰÷፫) ከሌሎች ቅዱሳን በተለየ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም”…መታሰቢያዋን ለሚያደርግ፣ ስሟን ለሚጠራ፣ ለድሆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ…” (ስንክሳር ዘወርኃ የካቲት) የአማላጅነት የእናትነት ቃል ኪዳን ሰጥቷታል። በተሰጣት ቃልኪዳንም “…በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች…” ብሎ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ዘወትር በቀኙ ቆማ ታማልደናለች። (መዝ.፵፬÷፱)
እኛም ክርስቲያኖች የዐሥራት ልጆቿ ዘወትር “ንጽሕት ድንግል ማርያም የታመነች አምላክን የወለደች ናት። ለሰዎች ልጆችም የምሕረት አማላጅ ናት። ኃጥአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ክርስቶስ ለምኝልን” እያልን የቅዱስ ኤፍሬምን አንደበት አንደበታችን አድርገን እናመሰግናታለን እንለምናታለን። (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋርም እንዲህ እያልን እንማጸናታለን፤ “ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! እታመንሻለው፤ ከተሠወረው መከራ፣ በግልጽ ከሚመጣብኝ ጥፋት ሁሉ በዚህ ዓለም እንድታድኚኝ። በሚመጣውም ዓለም ከገሃነመ እሳት ጥርስ ማፋጨት ጽኑ ለቅሶም ካለበት፣ ከሚያስጨንቅ መቅሠፍትም ትሠውሪኝ ዘንድ፣ እኔም በአንቺ አማላጅነት፣ በልጅሽ ምሕረት የታምንሁ ነኝ። በፈረሰኞች ሰልፍ በሠረገላም መንኮራኩር የምታመን አይደለሁም በአንቺና በልጅሽ እታመናለው እንጂ።” (አርጋኖን ዘእሑድ) እርሷም ዘወትር አትለየንም።
የመስቀል ሥር ልዩ ስጦታችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያምን አክብረን፣ በምልጃዋ ታምነን፣ በንስሓ ታጥበን፣ በጸሎቷ አማልዳን ከልጇ ከወዳጇ አስታርቃን ዘንድ ዘወትር እርስዋን እንለምን፤ የመንግሥቱ ወራሽ የስሙ ቀዳሽ እንድንሆን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን! የእመቤታችን ምልጃ ተራዳኢነቷና በረከቷ ዘወትር አይለየን፤ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!