የአዳዲስ ፊዳላት፣ አዳዲስ ቁጥሮች፣ አፈጣጠር ሂደትና አስፈላጊነት

ሚያዚያ 20/2004 ዓ.ም.

ሠዓሊ አምሳሉ ገብረ ኪዳን አርጋው

ኢትዮጵያ ያሏትን መንፈሳዊና ቁሳዊ የታሪክ ዕሴቶች በማበርከት በኩል የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ድርሻ ታላቅ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከእነዚህ ዕሴቶቻችን መካከል ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን የሚያስጠራና እንደ አፍሪካዊነታችን ብቸኛ ባለቤት እንድንሰኝ የሚያደርጉን ፊደላትና ቁጥሮች ናቸው፡፡ ይህን የሊቃውንቱን አርአያነት ያለው ተግባር ተከትለን የበለጠ ማርቀቅና ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በፍልስፍናና በፈጠራ ሥራውም ችግር ፈቺ በመሆን መራመድ እንዳለብን እናስባለን፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ተከትሎ ወንድማችን አምሳሉ ‹‹የኢትዮጵያ ቁጥሮችና ፊደላት በየምክንያቱ ወደጎን እየተተዉ የእኛ ባልሆኑ እኛነታችንንም በሚያስረሱ ሌሎች ፊደላትና ቁጥሮች የመገልገል ዝንባሌ እየታዩ መምጣታቸው ያሳስበኛል በማለት አንድ አስተዋጽኦ ለሀገር ማበርከት አለብኝ ብሏል፡፡ እርሱ እንደሚለው የኢትዮጵያ ፊደላት እና ቁጥሮች በየትኛውም ቋንቋና አሠራር ውስጥ ውጤታማ ናቸው፡፡ አሉ የሚባሉ ውስንነቶችንም መቅረፍ የሚያስችል ዕምቅ አቅም አላቸው ይህንን አቅም እንዲኖራቸው አድርገው ሊቃውንቱ ቀምረው አልፈዋል፡፡ ስለዘህ ጥያቄ ሲነሣባቸው በፈጠራ አዳብረን ለትውልዱ እንዲመጥኑ አድርጎ አቅማቸውን መግለጽ ይቻላል ለዚህም የራሴን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ስለዚህ የፈጠራ ረቂቄን አቅርቤ ሊቃውንትና የማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር አንባብያን የማኅበሩን መካነ ድርና የሐመር መጽሔትን ተጠቅመው እንዲተቹት፤ በዚህ ላይ ተመሥርቶም በዚሁ ረገድ የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና የትውልዱ መነሣሣት እንዲፈጠር እሻለሁ›› ብሏል፡፡ እኛም እርሱ እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነቱ ያሳየውን የፈጠራ ረቂቅ በማቅረብ ሊቃውንቱና አንባብያን ሁሉ አስተያየት በመስጠት እንዲወያዩበት የእርሱን ሐሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡