የአዳዲስ አማንያኑ ቍጥር ወደ ሰማንያ አምስት ሺሕ አደገ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ታኅሣሥ ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

img_0090

በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በተከናወነው የጥምቀት መርሐ ግብር ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ወር ፳፻፱ ዓ.ም ባለው የአገልግሎት ዘመን በመተከል ሀገረ ስብከት በአምስት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ዐሥር የጥምቀት ቦታዎች ስድስት ሺሕ ስምንት መቶ ሃያ አንድ፤ በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዐርባ ምንጭ አካባቢ ሁለት ሺሕ አንድ መቶ ሠላሳ ሰባት፤ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በጂንካ አካባቢ አንድ ሺሕ ስልሳ አንድ፤ በሸካ ቤንች ማጂ ሀገረ ስብከት በማጂ ወረዳ ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ ሰማንያ ስድስት፤ በድምሩ ዐሥራ ሦስት ሺሕ ሰባት መቶ አምስት በልዩ ልዩ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡

ይህም ከአሁን በፊት ማኅበሩ ካስጠመቃቸው ሰባ ሁለት ሺሕ አማንያን ጋር ሲደመር የአዳዲስ አማንያኑን ቍጥር ወደ ሰማንያ አምስት ሺሕ ሰባት መቶ አምስት እንደሚያደርሰው በማኅበሩ የስብከተ ወንጌል ትግበራ ባለሙያ ቀሲስ ይግዛው መኮንን ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡ ከዐሥራ ሦስት ሺሕ ሰባት መቶ አምስቱ አዳዲስ አማንያን መካከልም ከፊሎቹ ታኅሣሥ ፱፣ ፲፮ እና ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የተጠመቁ ናቸው፡፡

metekel-2

የመተከል ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ብርሃን ዓለም ጥምቀቱ በተፈጸመበት ዕለት በድባጤ ወረዳ ቤተ ክህነት አልባሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ትምህርተ ወንጌል ሲሰጡ ‹‹ዛሬ ወላጆች ከልጆቻችሁ ጋር ተጠምቃችኋል፡፡ ከዚህ በኋላ ልጆችን ስትወልዱ ወንዶችን በዐርባ፤ ሴቶችን ደግሞ በሰማንያ ቀናቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን በማምጣት ማስጠመቅ አለባችሁ፤›› በማለት ተጠማቂዎቹን አስተምረዋል፡፡ በማያያዝም ተጠማቂዎቹ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው መኖር እንደሚገባቸው፤ ከዚህም ባሻገር ያልተጠመቁ ዘመዶቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን አስተምረው ወደ ክርስትና ሃይማኖት መመለስ፤ የተጠመቁትንም በሃይማኖትና በምግባር እንዲጸኑ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሥራ አስኪያጁ ተጠማቂዎቹን መክረዋል፡፡

በመተከል ሀገረ ስብከት በተካሔደው የጥምቀት መርሐ ግብር ከልዑካኑ ጋር አብረው የተሳተፉት የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ንጉሤ መብራቱ አዳዲስ አማንያንን ማስጠመቅ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ ዐቢዩና ዋነኛው ተግባር መኾኑን አስታውሰው ለአገልግሎቱ ውጤታማነትና ለተጠማቂዎቹ ቍጥር መጨመርም የማኅበሩ አባላትና የበጎ አድራጊ ምእመናን ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

metekel-3

የማኅበረ ቅዱሳን የግልገል በለስ ማእከል ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ደሳለኝ እና ጸሐፊው አቶ ደግ አረገ አለነ በበኩላቸው ማእከሉ ከመተከል ሀገረ ስብከት ጋር ኾኖ ሰባክያንን በመመደብ፣ ቅኝት በማድረግና በመሳሰሉት ተግባራት አገልግሎቱን በማስተባበር የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣቱን ጠቅሰው ማእከሉ ያለበት የሰው ኃይል፣ የመምህራንና የገንዘብ እጥረት፣ እንደዚሁም የጥምቀት መርሐ ግብሩ የሚፈጽምባቸው ቦታዎች ርቀትና ለአገልግሎት ምቹ አለመኾን አዳዲስ አማንያንን የማስጠመቁን ተልእኮ ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል ዋነኞቹ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ ሰባክያነ ወንጌል መካከል ዲያቆን ቶማስ ጐሹ እና ወንድም ፈጠነ ገብሬ ተጠማቅያኑ ቀደምት አባቶቻቸው ለዚህ ክብር ሳይበቁ በማለፋቸው እንደሚቈጩና የክርስትና ጥምቀትን ለማግኘት ሲሉም ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምረው በእግራቸው እንደ ተጓዙ ገልጸው የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት የቃለ እግዚአብሔር ጥማት እንዳለባቸውና ‹‹ልጆቻችንን የቄስ ትምህርት አስተምሩልን?›› እያሉ እንደሚጠይቋቸውም አስረድተዋል፡፡

ወደ ፊትም ሰንበት ት/ቤቶችን በየቦታው በማቋቋም ተጠማቅያኑ በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ለማድረግ ዕቅድ ቢኖራቸውም ነገር ግን ሰባክያነ ወንጌል በብዛት አለመመደባቸው፣ ቢመደቡም የሚከፈላቸው የድጎማ ገንዘብ አነስተኛ መኾኑ፣ ሞተሮቻቸው ሲበላሹባቸው የሚያስጠግኑበት በጀት አለመኖሩ፣ እንደዚሁም የአካባቢው መናፍቃን ተጽዕኖ መበራከቱ ‹‹አገልግሎታችንን በአግባቡ እንዳንወጣ አድርጎናልና መፍትሔ እንፈልጋለን›› ሲሉ የድጋፍ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

metekel-2

ከተጠማቅያን የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት መካከል አንደኛው ለዚህ ታላቅ ክብር ስላበቃቸው እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ‹‹አጥምቃችሁን መመለስ ብቻ ሳይኾን ለወደ ፊትም አስተማሪ፣ መካሪ ካህን አጥተን ወደ ሌላ ቤተ እምነት እንዳንወሰድ እየመጣችሁ በመምከር፣ በማስተማርና በማበረታታት በሃይማኖታችን እንድንጸና ድጋፍ አድርጉልን፤›› ሲሉ የድረሱል ድምፃቸውን ያሰማሉ፡፡ ሌላኛው ተጠማቂ ወንድምም እንደዚሁ ራሳቸውን ጨምሮ ዐሥራ አራት የቤተሰቡ አባላት በሙሉ በአንድ ቀን መጠመቃቸውን አውስተው ‹‹ያልተጠመቁ ዘመዶቼና ወዳጆቼንም ተምረው የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ አደርጋለሁ›› ብለዋል፡፡

የማኅበሩ ጋዜጠኞችም በመተከል ሀገረ ስብከት ልዩ ልዩ ቦታዎች ታኅሣሥ ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በተካሔደው የጥምቀት መርሐ ግብር በተሳተፍንበት ወቅት በድባጤ ወረዳ ቤተ ክህነት በአልባሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአዊ ብሔረሰብ ተወላጆች ተጠማቂ የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጆችን ክርስትና በማንሣት በሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳይ ዅሉ ከጎናቸው እንደማይለዩ ቃል በመግባት ዝምድናቸውን ሲያጠናክሩና አንድነታቸውን ሲያጸኑ ተመልክተናል፡፡

img_0143በግል መኪኖቻቸው ልዑካኑን በመያዝ በጉዞው የተሳተፉ ወንድሞችም ከአሁን በፊት ብዙ ቦታዎችን እንደሚያውቁ፤ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ መንገድ እንዳላጋጠማቸውና መንገዱም ከጠበቁት በላይ ለመኪናዎቻቸው አስቸጋሪ እንደ ነበረ ገልጸው ማኅበሩ የሚሰጠውን አገልግሎት በመመልከት በመንፈሳዊ ቅናት ተነሳሥተው ብዙ ውጣ ውረዶችን በመቋቋም ተልእኳቸውን ተወጥተው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለ መኪኖቹ ‹‹መንፈሳዊ ጉዞው ወደ ፊት የሚጠበቅብንን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ለመወጣት እንድንዘጋጅ አድርጎናል›› ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

የጥምቀት መርሐ ግብሩን ለማስተባበር በየጠራፋማ አካባቢዎች ተሰማርተው ለነበሩ የማኅበረ ቅዱሳን ልዑካንም የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የልዩ ልዩ ዋና ክፍሎች አገልጋዮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በማኅበሩ ሕንጻ ፮ኛ ፎቅ አዳራሽ የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በዕለቱ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በምቹ ኹኔታዎች የሚፈጸም ተግባር ሳይኾን ፈተና የበዛበት ተልእኮ መኾኑን ገልጸው ልዩ ልዩ ፈተናዎችም ማኅበሩ መንፈሳዊ ተልእኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ስላደረጉት በሺሕ የሚቈጠሩ ኢአማንያን የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ለማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

metekel

‹‹በጠረፋማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ቋንቋ ወንጌልን የሚሰብኩ መምህራን የሕይወት መጻሕፍት ናቸውና ዅላችንም ልንማርባቸው ይገባል፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው በጸሎት፣ በስብከት፣ በማስተባበር፣ በገንዘብ ድጋፍ፣ በጉልበት ሥራና በመሳሰሉት ተግባራት በመሳተፍ ለአማንያኑ መጠመቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን፣ መምህራንና ካህናትን፣ እንደዚሁም በጎ አድራጊ ምእመናንን በማኅበሩ ስም አመስግነዋል፡፡

ከሥራ አመራር አባላት መካከል አንደኛው ከፈጸምነው ተልእኮ ይልቅ ገና ያልሠራነው ብዙ ተግባር እንደሚበልጥ በመገንዘብና ምእመናንን ከቤታቸው ለማስወጣት ተግተው የሚሠሩ አካላት በየቦታው እንደሚገኙ በመረዳት ወደ ፊት ለሚጠበቅብን ዘርፈ ብዙ ሥራ መዘጋጀት ተገቢ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም በጥምቀት መርሐ ግብሩ የተሳተፉ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ የካሜራ ባለሙያዎች፣ ሹፌሮችና ሌሎችም የልዑካኑ አባላት በአገልግሎቱ መሳተፋቸው ምስጋና ለማግኘት ሳይኾን እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ለማገልገል እና ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መኾኑን ሊረዱት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

metekel

ተጠማቂዎቹ እንዳይበተኑና በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ለማድረግ በጠረፋማ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነጽ፣ በየቋንቋው የሚሰብኩ መምህራንና ካህናትን ቍጥር ማሳደግ፣ የትምህርተ ሃይማኖት መማሪያ መጻሕፍትን በየቋንቋው ማዘጋጀት፣ አዳሪ ት/ቤቶችንና ሰንበት ት/ቤቶችን በየቦታው ማቋቋም፣ የስብከት ኬላዎችን ማስፋፋትና ለተጠማቅያኑ አስፈላጊውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ማድረግ ለወደፊቱ በማኅበሩ ሊሠሩ የታቀዱ ተግባራት መኾናቸውን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ምክትል ሓላፊ አቶ ሰይፈ አበበ ጠቅሰው ይህንን ዕቅድ ከግብ ለማድረስም የበጎ አድራጊ ምእመናን ተሳትፎ እንዳይለያቸው በማኅበሩ ስም መንፈሳዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰማንያ አምስት ሺሕ ኢአማንያንን የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲኾኑ ማድረግ ታላቅ ተልእኮ ቢኾንም ከዚህ የበለጠ መትጋት ከኹላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ መላው ሕዝበ ክርስቲያን በአንድነት ኾነን ተባብረን ከሠራን ከዚህ በላይ ቍጥር ያላቸው ኢአማንያንን ለማስጠመቅና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚቻል ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ስለዚህም በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም (መርሐ ግብር) ለሚሠሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች መሳካት የበጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ እንዳይለየን ሲል ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡