የአዳማ ማእከል ለአባቶች የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ
ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በአዳማ ማእከል
በማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማእከል ከምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ከሙያ አገልግሎትና ዓቅም ማጐልበቻ ዋና ክፍል ጋር በመተባበር ለሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ ለወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በአጠቃላይ ፵ ለሚኾኑ አባቶች ከነሐሴ ፳፩-፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሁለት ቀናት በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ፡፡
በሥልጠናውም የሥራ አመራር ጥበብ፤ የውሳኔ አሰጣጥና የግጭት አፈታት ዘዴ፤ ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዓዋዲ ከሥራ አመራር አንጻር፤ እንደዚሁም የፋይናንስ አስተዳደርና ሒሳብ አያያዝ የሚሉ አርእስት የተካተቱ ሲኾን በተጨማሪም የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ለሠልጣኞቹ ተደርጎላቸዋል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት ሥልጠናው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች መሰጠቱን አድንቀው ሥልጠናውን ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን ካመሰገኑ በኋላ ‹‹ያገኛችሁትን ዕውቀት በተግባር ላይ በማዋል ብቁና ዘመናዊ አሠራርን የተላበሰ የሓላፊነት ሥራችሁን እንድትወጡ›› ሲሉ ለሠልጣኞቹ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ‹‹የወሰድነው ሥልጠና መንፈሳዊውን አስተዳደር ከዘመናዊ የሥራ አመራር ጥበብ ጋር በማጣጣም ቤተ ክርስቲያናችንን በአግባቡ ማገልገል እንደምንችል የተረዳንበት ሥልጠና ነው፡፡ በተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ዙሪያ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻም ቤተ ክርስቲያናችንን ነቅተን እንድንጠብቅና የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በስፋት ለማዳረስ እንድንፋጠን አድርጎናል›› ብለዋል፡፡
የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት በአንድነት ማገልገል የሚኖረውን ጠቀሜታ በመጥቀስ ማኅበሩ የራሳቸው መኾኑን ተገንዝበው በሚያስፈልገው ኹሉ ከማኅበሩ ጎን እንዲቆሙ፤ በምክርና በዐሳብም ድጋፍ እንዲያደርጉ አባቶችን አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽዖና ድጋፍ ላደረጉት ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነትና የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ ለወረዳ ቤተ ክህነት፣ ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ እንደዚሁም ለአሠልጣኞችና ለበጎ አድራጊ ምእመናን መ/ር ጌትነት መንፈሳዊ ምስጋናቸውን በማኅበሩ ስም አቅርበዋል፡፡