የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአደረጃጀት መዋቅር እንዲጸድቅ በዕንባ ተጠየቀ
ጥር 6/2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
- ቅዱሰ አባታችን ለልጆቼ ምን ላውርሳቸው? ሙስናን? የምእመናን ተወካይ
- የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር እናስተካክላለን ብለን ከዚህ ደርሰን ወደኋላ እንመለሳለን ማለት ዘበት ነው፡፡ በጭራሽ አይሞከርም!!! ሐቋንም ይዤ እጓዛለሁ!!! ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያስጠናው መዋቅራዊ ለውጥ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ ተሻለ ልማት ያራምዳል፤ ሙስናን ያጠፋል፤ወደ ሌላ በረት የገቡትን በጎች ይመልሳል፤ እኛም የቤተ ክርስቲያን አካል በመሆናችን የተሻለ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚያደርገን በመሆኑ በአስቸኳይ ተግባር ላይ እንዲውልልን በማለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ምእመናን ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በንግግርና በእንባ ጠየቁ፡፡
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ምእመናን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ መሰባበሰባቸውን ቀጥለዋል፡፡ የምእመናኑ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በመገኘት ምእመናን የሚያቀርቡት ጥያቄ እንዳላቸውና ይህንንም ለማቅረብ እንዲችሉ ፈቀዳቸውን ለመጠየቅ ቀርበዋል፡፡ የቅዱስነታቸው ልዩ ጽ/ቤት በርካታ ምእመናንን ማስተናገድ ስለማይችል 60 ምእመናን ብቻ እንዲገቡ ተፈቀደ፡፡ ሆኖም ግን በግቢው ውስጥ ቁጥራቸው ከ500 በላይ ምእመናንና ምእመናት በመገኘታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዲፈቀድ ተደርጎ ምእመናንን ወደ አዳራሹ በመግባት ቦታቸውን ያዙ፡፡
ቅዱስነታቸው ምእመናኑን ለማነጋገር ፈጠን ፈጠን እያሉ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ገብተው በመምጣት በግራም፤ በቀኝም የሚገኙትን ምእመናንን እየባረኩ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ መርሐ ግብሩን በጸሎት ከፍተዋል፡፡
ከጸሎት በኋላ የምእመናን ተወካዮች ለቅዱስነታቸው ጥያቄዎቻቸውን በጽሑፍ ማቅረባቸውን ቀጠሉ፡፡
“በአኩሪ ታሪክና ምግባር የምትታወቀው ቤተክርስቲያናችን የዘመናት ስሟንና ክብሯን የማይመጥን እኩይ ተግባራት የሚፈጸምባት ቦታ፤ ከሃይማኖት ይልቅ ግላዊ ጥቅም በሚያስቀድሙ የውስጥ አርበኞች ብልሹ አሠራር፤ ዘረኝነት፤ ሙስና እና የሥነምግባር ጉድለት ጎልቶ የሚታይባትና ተከታዮቿን የሚያሸማቅቅ ተግባር የሚፈጽሙባት እየሆነች መጥታለች” በማለት በእድሜ ገፋ ያሉ አዛውንት በንባብ ገለጹ፡፡
የውስጥ የቤተክርስቲያን ጠላቶች ያሏቸውንም መለያቸውን ሲገልጹ፡- “ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሥራ ላይ እንዳይውል በጥብቅ ይከላከላሉ፤ ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከት እንዲሁም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በተዘረጋ የሙስና መረብ ከሕጋዊ መዋቅሩ በበለጠ እርስ በእርስ በመደጋገፍ፤ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ይሸፋፈናሉ፤የሥራ ዕድገት በሙያና በትምህርት ብቃት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በዘመድና በጉቦ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፣ ጥፋተኛነቱ የተረጋገጠ የደብር አለቃ ወይም ኃላፊ ላይ ተገቢውን የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ በመውሰድ ፋንታ ወደ ሌላ የተሻለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል” በማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተካሔደ ያለውን ብልሹ አሠራር ተቃውመዋል፡፡
አዛውንቱ ቀጥለውም በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚስተዋለው የሥነ ምግባር ግድፈቶች፣ ጎጣዊ/ዘረኛ አሠራሮችና የሙስና መንሰራፋት ለመምዕመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መጉረፍ ምክንያት ከመሆናቸውም ባሻገር ፤በቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የተጠናና የተደራጀ በሚመስል ሁኔታ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ጉድለቶች በማየት አንዳንድ ምዕመናን ከቤተክርስቲያን እየራቁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
“የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ ጥናቱ ተግባራዊ ሆኖ ቤተክርስቲያኒቱን ሰንገው አላንቀሳቅስ ያሏት ሙስናና ጎጠኝነት ተወግደው፤ ምዕመናን ለቤተክርስቲያን የሚሰጡት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ፤ በጥናቱ ያልተደሰቱ የተወሰኑ ግለሰቦች ባቀረቡት ቅሬታ ጥናቱ ተግባራዊ ከመሆን ታግዶ እንደገና ባዲስ መልክ እንዲታይ መወሰኑን በከፍተኛ ድንጋጤ ነው የሰማነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ተንሠራፍቶ የቆየው ሙስናና ብልሹ አሠራር ጊዜ ሊሠጠው የማይገባ ለነገ ሊባል የማይችል ባስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ያለበት ስለሆነ የቤተክርስቲያቱን ሥር የሰደደና የተከማቸ ችግር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው ጥናት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በአጽንኦት እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
የተቋማዊ ለውጡ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ማግኘቱ በራሱ ከፍተኛ ውጤት ቢሆንም አስፈላጊው የአፈጻጸም ስልትና በቁርጠኝነት ሥራ ላይ ሊያውል የሚችል ቅን ታታሪ ታማኝ ተግዳሮቶችን በከፍተኛ ጽናት መቋቋም የሚችል የሰው ኃይል ካልተመደበለት ብልጣብልጦቹ እጅ ወድቆ የታሰበውን ውጤት ሳያስገኝ ሊከሽፍ እንደሚችል የጠቆመው መግለጫው፤ ተቋማዊ ለውጡን በተሟላና በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋልና ዘለቄታማነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
- በጥናቱ ላይ ጥያቄ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን ቢኖር ጥያቄውን በዝርዝር አቅርቦ በጥናት ቡድኑ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚታመንበት ነገር ካለ አስፈላጊው ማሻሻያ ከሚደረግበት በስተቀር በጉጉት የምንጠብቀው የጥናት ውጤት ቢቻል ለማስቆም ካልተቻለም ለማዘግየት እንደገና በአዲስ መልክ እንዲታይ እየተደረገ ያለው አካሄድ ቆሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ልዕልና ተጠብቆ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዲደረግ፤
- የተጠናውን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥናት የሚገመግም አዲስ ኮሚቴ በተመለከተም ጥናቱን ሊያዳብር በሚችል መልኩ በፍጥነት ሰርተው ያቀርባሉ ብሎ ለማሰብ ከኮሚቴው አባላት መካከል ከአሁን ቀደም በሀገረ ስብከቱም ሆነ በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ በተመሳሳይ ችግር ተጠቃሽ የሚሆኑ ሰዎች መካተታቸው ያሳሰበን በመሆኑ እንደገና እንዲታይልን እንዲደረግ
- ተቋማዊ ለውጡን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዳይፈጸም በሚያውኩና በሚቃወሙ ላይ ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ጥብቅ የሥነ ሥርዓት ርምጃ እንዲወሰድ እንዲደረግ፤
- ከቅን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞች፣ ከሰንበት ት/ቤት እንዲሁም ከምዕመናን የተውጣጣ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጸሚ አካል እንዲቋቋም፤
- ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ የፈጸሙ ሁሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድልን፣
- ስለ ጎጠኝነትና ሙስና አስከፊነት የሥልጠናና ትምህርት መርሃ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ እንዲደረግ፣
- ከሙስና የጸዱትንና የላቀ መልካም ተግባር የሚፈጸሙትን አገልጋዮች በመሸለም እንዲበረታቱ እንዲደረግ፣
- ቤተክርስቲያኒቱ ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር እራሷን እየፈተሸች፣ ችግሮቿን እየለየች መፍትሔ በማስቀመጥ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላት የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም እንዲደረግ፣
- ከመንግሥት አሠራር ልምድ በመቅሰም በስፋት የተንሰራፋውን የሙስና ተግባር መቋቋም ይቻል ዘንድ የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና አካል ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን እንዲቋቋም እንዲደረግ በቅድስት ቤተክርስቲያናቸን ስም አበከረን እንጠይቃለን በማለት በመግለጫቸው አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም በቅዱስነታቸው ፈቃድ የምእመናን ተወካዮች ጥናቱን አስመልከቶ ሀሳባቸውን ከገለጹት መካከል፡-
“ይህ አዲስ መዋቅር ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ብዝበዛን፤ የአስተዳደር ብልሹነትን፤ ግማሹ እያለቀሰ ሌላው እየተደሰተ እንደፈለገ እየሆነ ያለበት አስቸጋሪ ሁኔታን የሚያስተካክል ነው፡፡ የዚህ መዋቅር መውጣት የሚያስደነግጣቸው ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ ብዝበዛን፤ ብልሹ አስተዳደርን ስለሚያስቆም በዚህ ሕይወት ውስጥ የበለጸጉና ከፍተኛ ጥቅማጥቅሞችን ያገኙ የነበሩ ግለሰቦች የለመዱት ሲቋረጥባቸው ሊደነግጡ ይችላሉ፡፡ እንኳን ቤተ ክህነት በቤተ መንግሥት ውስጥ አዳዲስ አሠራሮች ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ሲነሱ ሁሉም እልል ብሎ አይቀበልም፡፡ ይህ የመዋቅር ጥናት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ ታላቅ ምእራፍ የከፈተ ነውና እርስዎ ጀምረውታል፤ ለስምዎ፤ ለታሪክዎና ለቤተ ክርስቲያኗ ሕልውና ሲሉ ያስፈጽሙት፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከብዝበዛ ያድኗት፤ ከፍጻሜም ያድርሱት” በማለት የእድሜ ባለጸጋና ቀድሞ ቃለ ዓዋዲን ካረቀቁ ሊቃውንት መካካል የነበሩ አባት እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡
አንድ እናትም ንግግራቸውን ቀጠሉ “የእግዚአብሔር ዓላማ የጠፉትን ወደ ቤቱ ለመመለስ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ደርሷል ብለን እናምናለን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ችግር በሚገባ አውቀናል፤አዝነናል፤ አልቅሰናል፤ ዋጋችንንም አግኝተናል፤ ተቀጥተናል ይበቃናል፡፡ ልጆቻችን ቤተ ክርስቲያናችንንና እምነታችንን ይረከቡ ዘንድ እኛ ወላጆች ድልድዮች ነን፡፡ቤተ ክርስቲያናችንን ለልጆቻችን ለማስረከብ እንድንችል ይርዱን፡፡ቅዱስ አባታችን ለልጆቼ ምን ላውርሳቸው? ሙስናን??? ቅዱስ አባታችን ቤተ ክርስቲያን አሁን በሌላ በረት ያሉ ልጆቿን የምትሰበስብበት ሰዓት ደርሷል፡፡ይህ ጥናት ተግባራዊ ቢሆን የጠፉ ልጆቿ በሕይወት ይኖራሉ፡፡በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰበሰብነው ምእመናንን እንዳንበተን ይህ መዋቅር በቶሎ ተግባራዊ ይደረግልን” በማለት እያለቀሱ ተማጽነዋል፡፡
ቅዱስነታቸውም ለቀረቡት የምእመናንን ጥያቄዎች በማረጋጋት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ይህንን ጉዳይ ገና ከመግባቴ ያወጅኩት እኔ ነኝ፡፡ሙስና፤ የገንዘብ ብክነት፤ ሓላፊነት የጎደለው አስተዳደር እንዲጠፋና መልካም አስተዳደር፤ ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲሰፍን መሥራት አለብን፡፡ አንድ ጥናት የተወሰኑ ሰዎች ያጠኑታል፡፡ ከዚያም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲያዩት ይደረጋል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያንን ቋንቋ፤ ባሕል ተመርኩዘው ቢያጠኑት ይጠነክራል፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም ቀርቦ ይጸድቃል፡፡ በፍጹም ስጋት አይግባችሁ፤ ጩኸቱ የእኔ ነው፡፡ ተጠናክሮ እንጂ ተዳክሞ አይመጣም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ መስመሯን እንድትይዝ ነው ፍላጎታችን፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር እናጠራለን፤ እናስተካክላለን ብለን ከዚህ ደርሰን ወደኋላ እንመለሳለን ማለት ዘበት ነው፡፡ በጭራሽ አይሞከርም!!! ሐቋን ይዤ እጓዛለሁ!!! እናንተም ደግፋችሁን ቤተ ክርስቲያናችን የቀድሞ ቅድስናዋን መመለስ አለብን፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲኗ ሊቃውንትና የዘመናዊውን የአስተዳደር ትምህርት የተማሩ ምሁራን ተቀናጅተው፤ አይተውት ጠርቶ እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ ችግር ካለበት ያኔ ሀሳብ ልንሰጥበት እንችላለን፡፡አይዟችሁ አትፍሩ” በማለት ምእመናንን በማረጋጋት ባርከው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ምእመናንም እግዚአብሔር ይመስገን ይህችን ቀን ቀድሶ ለሰጠን እያሉ በመዘመር ቅዱስነታቸውን ሸኝተዋል፡፡